
አዲስ አበባ፡- የጎርጎራና አካባቢው ያለውን የኢኮ ቱሪዝም ሀብት ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ ቱሪዝም ኢትዮጵያ አስታወቀ።
የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሽ ግርማ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ ጎርጎራና አካባቢው የውሃ ተኮር ቱሪዝምና የባህልና ታሪክ ተኮር ቱሪዝም ብቻ ሳይሆን ሁለቱንም ያጣመረ የተፈጥሮ ሀብቱን የጠበቀ የቱሪዝም ባለቤት ነው።
” ጎርጎራ በልዩ ሁኔታ ለኢኮ ቱሪዝም ትልቅ አበርክቶት ያላት ስፍራ ናት። ይህ አይነቱ የቱሪዝም ዘርፍ የአካባቢን ምርት በመጠቀም ቱሪስቶችና ማህበረሰቡን የእርስ በርስ ግንኙነት በማጠናከር ትልቅ ገቢ ያስገኛል፤ የሥራ ዕድል በስፋት ይፈጥራልም ” ብለዋል።
እንደ አቶ ስለሽ ገለፃ፤ ባህር ዳር አካባቢ ውሃ ተኮር የቱሪዝም ሀብት በስፋት አለ። ጎንደር አካባቢ ደግሞ ታሪካዊና ባህላዊው የሆነ የቱሪዝም መስህብ አለ። ጎርጎራ ከሁለቱም በተለየ መንገድ የኢኮ ቱሪዝም ሀብት በስፋት ያለው ነው።
በተለይ በውሰጡ ዓሣና ጉማሬ ያለው ሐይቅ መኖሩ ሌላ የቱሪስት መስህብ ነው። በአካባቢው እራሱን የቻለ የቱሪስት መስህብ መሆን የሚችል ብዛት ያለው የወፍ ዝርያ ይገኛል። በተጨማሪም በሃይቁ አካባቢ ፍራፍሬ፣ ልዩ ልዩ የግብርና ምርቶች ይገኙበታል ብለዋል።
የኢኮ ቱሪዝም መስህብ ተፈጥሮ ተኮር ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ተፈጥሮን እየጠበቅን በሚገኘው አገልግሎት ገቢ ማግኘት ይቻላል ያሉት አቶ ስለሽ፣ ኢኮ ቱሪዝም የሃይቁን ሀብት በመጠበቅና የአካባቢው አርሶ አደሮች ፍራፍሬ ሽጠው እንዲጠቀሙ ዕድል እንደሚፈጥር አስታውቀዋል።
ፍራፍሬን ወደ ጁስ ቀይረው በመሸጥና የተለያዩ ግብአቶችን ለሆቴል በማቅረብ ገቢያቸውን ከማሳደጉም ባሻገር ቱሪስቶች በሚዝናኑበት ወቅት ሀይቁን በማይጋፋ መልኩ የተፈጥሮ ሀብቱን በማየትና የአካባቢውን ምርት በመጠቀም የገቢ ምንጭ ይሆናል። ቱሪስቶች ገንዘብ ከፍለው አገልሎቱን በሚያገኙ ጊዜ ለአካባቢው ነዋሪ የሥራ ዕድል በመፍጠር የውጭ ምንዛሬም ያስገኛሉ ብለዋል።
ከመንግሥት በተገኘ ድጋፍ ባለሀብቶች የቱሪስት መዳረሻዎችን ሲሰሩ ቆይተዋል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በተቃራኒው ደግሞ በኢትዮጵያ በጥብቅ ስፍራዎችና መገንባት በሌለባቸው ቦታዎች ላይ የአካባቢውን ባህል በሚበርዝ ሁኔታ ልዩ ልዩ ግንባታዎች ሲሰሩ ቆይተዋል። ይህ ደግሞ በቅርሶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያደርስ እንደነበር አመልክተዋል።
አሁን በጎርጎራ ከተማ ላይ የሚሰራው ፕሮጀክት ለአካባቢው ነዋሪዎች ምን አይነት ጥቅም ይሰጣል? ከአካባቢው ማህበረሰብ የአኗኗር ዘይቤ ጋር ይጣጣማል ወይ የሚለውን በለየ መልኩ መሆን አለበት። የሚሠሩ ሥራዎች በአካባቢው ያሉ በርካታ መንፈሳዊና ታሪካዊ ቦታዎችን ታሳቢ ያደረጉ፣ ለአካባቢው ማህበረሰብ ጥቅም እየሰጠ የሀይቁን ከባቢ ልዩ የመዝናኛ ቦታ በመፍጠር እንዲለማ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
ጎርጎራ የሃይቁ ገጽታ የከበባት፣ ልዩ የሆነ ታሪካዊ ቦታ ያላት እና ከጣሊያንና ከፖርቹጋሎች ጋር ተያይዞ በአካባቢው የተለያዩ እሴቶች ያሉባት የመስህብ ቦታ ናት። በዚህ ቦታ ላይ የሚሠራው ልማት በትክክል ታስቦበት፣ ለአካባቢው ህብረተሰብ ጥቅም በሚሰጥ መልኩ እንዲሆን መንግሥት ኃላፊነቱን መውሰድ እንዳለበት አመልክተዋል።
ሞገስ ጸጋዬ
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 19/2013