
አዲስ አበባ፦ በሕገወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ሊገባ የነበረ 186,240 ገጀራ መያዙን የገቢዎች ሚንስቴር አስታወቀ። በአንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች አስመጪው ሕጋዊ እንደሆነ ተደርጎ የሚሰራጨው መረጃ ሐሰተኛ መሆኑን ገለፀ፡፡
ሚኒስቴሩ በድረ ገጹ ትናንት እንዳስታወቀው፣ በሕገወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ሊገባ የነበረ 186,240 ገጀራ ይዟል። የዕቃው ባለቤት እና አስተላላፊው / ትራንዚተሩ/ ተይዘው ጉዳዩ በምርመራ ላይ ይገኛል።
ከ15 ቀን በፊት በአስመጪ ዳዊት የማነ ስም ብዛቱ 186,240 የሆነ የእጅ ገጀራ በአራት ባለ 20 ጫማ ኮንቴይነሮች ከቻይና ተጭኖ ሞጆ ጉምሩክ ተጓጉዞ መድረሱን አመልክቷል።
ዕቃው በዲክላራሲዮን ቁጥር 4-1919/21 ተመዝግቦ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ ከፌዴራል ፖሊስ የተፈቀደለት በማስመሰል እና ሐሰተኛ ሰነድ አዘጋጅቶ ለገቢ ዕቃ አወጣጥ የሰነድ መርማሪው አቅርቦ ሰነዱ ተመርምሮ ከ7.7ሚሊዮን ብር በላይ ቀረጥና ታክስ ተከፍሎበት ተለቆ እንደነበር አስታውቋል።
እቃው ከተለቀቀ በኋላ በጉምሩክ ኮሚሽን እና በሞጆ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኢንተለጀንስ በኩል ክትትል ተደርጎ የቀረበው ሰነድ ሲጣራ ሐሰተኛ እና እቃውም ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ ከፌዴራል ፖሊስ ፈቃድ ያልተሰጠው መሆኑ መረጋገጡንም ጠቁሟል::
ጉዳዩ ከ15 ቀን በፊት የተፈፀመ ቢሆንም፤ አስመጪው ያቀረብኩት ሰነድ ህጋዊ ነው በማለት ቅሬታ ስላቀረበ ከፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጋር በጋራ ሲጣራ ቆይቶ በተደረገው ማጣራት ሰነዱ ሐሰተኛ እና ከፌደራል ፖሊስ ፍቃድ ያልተሰጠው መሆኑ መረጋገጡን አመልክቷል፡፡
በተጨማሪም በጉምሩክ ኮምሽን ሠራተኛ የእጅ ገጀራው ተገቢውን የጉምሩክ ሥነ-ሥርዓት የፈፀመ በማስመሰል ሐሰተኛ ተዘጋጅቶ እቃውን ለማውጣት መሞከሩንን ሚኒስትሩ ገልጿል፡፡
ይህን መነሻ በማድረግም በፌዴራል ፖሊስ ለሞጆ የወንጀል ምርመራ ማስተባባሪያ ጽ/ቤት መረጃውን በመስጠት በተደረገው እልህ አስጨራሽ ክትትል የእቃው ባለቤት እና አስተላላፊው /ትራንዚተሩ/ ተይዘው ጉዳዩ በምርመራ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል::
ገጀራ ክልከላ ከተደረገባቸው እቃዎች አንዱ መሆኑን ያመለከተው ሚኒስትሩ፣ ከፌደራል ፖሊስ ሕጋዊ ፈቃድ ሳያገኙ ማስገባት የተከለከለ መሆኑንም ጠቁሟል ፡፡
በአንዳንድ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በጉምሩክ ኮምሽን ባለሙያ እቃው እንዲወጣ የተፈቀደበት ደብዳቤ በማስመሰልና ሐሰተኛ የደብዳቤ ፎቶ በመጠቀም አስመጪው ሕጋዊ እንደሆነ ተደርጎ የሚሰራጨው መረጃ ሐሰተኛ መሆኑንም አስታውቋል ፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 19/2013