ዳንኤል ዘነበ
እንግሊዛዊቷ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ገጣሚና ሐያሲ ጆርጅ ኢሊዮት በ1860 በጻፉትና ስለ አውሮፓ ትምህርት በሚያወራው ‹The Mill in the Floss› በተሠኘው ልብ-ወለድ ነክ መጽሀፋቸው፤ «ሀገራት አዋቂና ተመራማሪ ትውልድን የመፍጠር ሕልማቸውን የሚያሣኩትም ሆነ የትምህርትን ጥራት ማስጠበቅ የሚችሉት ለመምህራን ተገቢውን ክብርና እውቅና መስጠት ሲችሉ” እንደሆነ ነበር የገለጹት። ከታላቋ ሐያሲ ገለጻ፤ ሀገራት በትምህርት እድገትን፣ ብልጽግናን ማምጣት እንደሚቻል በማመን ለሚያደርጉት ጉዞ ከስኬት ለመድረስ ለመምህራን የሚሰጡት ትኩረትና እውቅና ምን ያህል ጠንካራ መሆን እንዳለበት ያመላክተናል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ለትምህርት ትኩረትና በጥራት አንቱ የተባሉ ሀገራትን የኋላ ታሪክ ሲመረመር የሚገኘው የእውቋን ሐያሲ ገለጻ መሠረት በማድረግ የተጓዙበት መንገድ ስለመኖሩ ያመላክተናል።
በኢትዮጵያም ያለውን ሁኔታ ስንመለከት ለመምህራን ሆነ ለመምህርነት ሙያ የሚሰጠው ክብርና ትኩረት በእጅጉ ዝቅ ያለ እንደሆነ ብዙዎች የሚስማሙበት ሀሳብ ነው። በሀገራችን በተለያዩ መንግስታት ሙያውም የነበረበት ከፍታ ሆነ ስለ ሙያው የነበረው አተያይ የተለያየ ገጽታ የተላበሰ ስለመሆኑ የተለያዩ ሊቃውንት ይመሰክራሉ።
የማይክሮሊንክ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኮሌጅ መሥራች እና የኢትዮጵያ ነጻ-ፕሬስ አለኝታ በሚል የሚታወቁት አቶ ዳኛቸው ይልማ ከሁለት ዓመት በፊት ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ «ይድረስ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ» ሲሉ የጻፉት ደብዳቤ ተጠቃሽ ይሆናል። አቶ ዳኛቸው ፤«በሀገራችን ቀደም ባሉት ጊዜያት ሙያው የተከበረ እንደነበር ሲሆን፤ ከ1966 ዓ.ም በፊት መምህር ለመሆን የምርጦች ምርጥ መሆንን (cream of the cream) ይጠይቅ ነበር። በዚህም መሠረት ወደ መምህራን ማሠልጠኛ ይገቡ የነበሩት ከየትምህርት ቤቶቻቸው የላቀ ውጤት ያመጡት ነበሩ። መምህራኑም ከተማሪዎቻቸው አልፈው ለአካባቢው ኅብረተሰብ ጭምር አርአያ (role models) ነበሩ።
በኋላኛው ዘመን ግን ‹‹መምህሩ መኩሪያን ሣይሆን ማፈሪያ እስከመሆን ደረሠ» ሲሉ ነበር ለሙያው ክብር የሚሰጥበት ዘመንን መኖሩን ያስመለከቱን። የአቶ ዳኛቸውን ሐሳብ ይዘን ወደ ኋላ መለስ ካልን፤ በሀገራችን መምህርነት የተከበረ ሙያ በመንግስት ደረጃም ብቻ ሳይሆን በማህበረሰቡ ዘንድ ሣይቀር የነበረውን ቦታ ያስታውሰናል። በኢትዮጵያ በማህበረሰቡ ዘንድ ለጋብቻ ሣይቀር መምህር መሆን ተፈላጊ የነበረው ሙያ ዛሬ ላይማ ገና መምህር መሆኑ ሲታወቅ ሰው እስከ መሸሽ ሲደርስ ለመታዘብ ችለናል።
የመምህርነት ሙያ ተገቢውን ክብር አለማግኘቱም፣ ማህበረሰቡ ለመምህራን ቦታ ማጣቱን ብዙዎች ሲናገሩ ነበር፤ እየተናገሩም ይገኛሉ። በሀገራችን ትልቅ ክብር ይሰጠው የነበረው ሙያ፤ ከክብር እንዲሆን ያደረገው ምክንያት ምንድን ነበር? የሚል ሞጋች ጥያቄን በማንሳት፤ ምላሹን ለማግኘት አቶ ዳኛቸው ደብዳቤን ደግመን እንመልከት።
«… የመምህርነት ሙያ የነበረው ክብር በጊዜ ሂደት እየተሸረሸረ መጥቷል። በተለይ ላለፉት 27 ዓመታትም የመምህሩ ጉዞ ከድጡ ወደ ማጡ የመጣ ሲሆን፤ የመምህርነት ሙያ መኩሪያ ሣይሆን ማፈሪያ እስከመሆን ደርሷል» ሲሉ ይናገራሉ። አቶ ዳኛቸው የቀደመው መንግስት መምህራንን ማሕበራዊ ዋጋ እንዲያሽቆለቁል፣ ሙያዊ ከፍታው እንዲወድቅ የተለያዩ መንገዶችን መጠቀሙን ይገልጻሉ።
የመጀመሪያው የመምህራን ደመወዝ ማነሱ ያስከተለው መዘዝ፤ በሥራ ዘርፉ ብቃታቸው ከፍ ያሉ ባለሙያዎች ወደ ዘርፉ እንዳይገቡ አድርጓል። ሌላው ወደ ሙያው መግቢያ ነጥብ ዝቅተኛ በማድረግ ሲሆን፤ ወደ መምህራን ማሠልጠኛ የሚገቡት አመልካቾች በማንኛውም መመዘኛ ወደቀ/ች የሚያሠኝ ውጤት ያመጡ ተፈታኞች ሲሆኑ፤ ይህም ትልቅ ተጽእኖ ፈጥሯል።
የመምህራን ማህበራትን የመንግስት ድምጽ እንዲሆኑ ያደረገበት ሁኔታ ሌላው ተጠቃሽ ጉዳይ ነው። ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ መምህራንን ከማንኛውም ለውጥ ለማግለል ማህበሩን አቅም እንዲያጣ የተደረገ መሆኑንም በዝርዝር ያቀርባሉ።
አቶ ዳኛቸው እንደገለጹት፤ ብዙዎች እንደሚስማሙት መንግስት ሆን ብሎ መምህራን ጫንቃቸው ጎብጦ ነገን በደበዘዘ ተስፋ የሚጠባበቁ ‹ምሥኪኖች› ወደ መሆን እንዲሻገሩ አድርጓቸዋል። በኢትዮጵያ መምህራን ላይ በተለይ የቀደመው መንግሥት በሙያው ላይ ያሣረፈውን ሀገር ገዳይ አካሄድ፤ ከባለፉት ሦስት ዓመታት በኋላ እየተስተካከለ እንደሚገኝ ለመታዘብ ተችሏል።
በመንግስት በኩል የተደረጉ ማሻሻያዎችንና ጅምር ተግባራት ደግሞ በተጨባጭ ከክብሩ የወረደውን የመምህርነት ሙያ ወደ ክብሩ የመመለስ ትግል እያደረገ ስለመሆኑ ያመላክታሉ። ከሰሞኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ 183 ምስጉን መምህራን ሽልማት እና እውቅና መሰጠቱ ከእነዚህ ሂደቶች መካከል አንዱና ትልቅ ትርጉም የሚሰጥ ተግባር እንደሆነ በርካታ ሙያተኞች ሳይቀር ነው አድናቆታቸውን የቸሩት። ትምህርት ሚነስቴር ከመምህራን ማህበር ጋር በጋራ በመሆን ሀገር አቀፍን የመምህራን ቀንን ባከበረበት ወቅት ለምስጉን መምህራን ሽልማት እና እውቅና በመስጠት እለቱን ልዩ ትርጉም እንዲሰጠው አድርጓል።
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በእለቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ «መምህራኖች የነገ ትውልድ ተረካቢዎችን የሚያፈሩ የሙያ አባቶችና እናቶች ናቸው። ስለዚህ መምህራኑና ሙያው ሊከበሩ እና ሊመሰገኑ ይገባል» ሲሉ ነበር ያመላከቱት። እንዲህ አይነት እውቅና ሙያውን ወደሚገባው ከፍታ ቦታ የሚያስቀምጠው ስለመሆኑ ነው ያስታወቁት።
«የመምህርነት ሙያ ክቡር ሙያ፤ የሁሉም ሙያዎች አባት በመሆኑ ለመምህራን ላቅ ያለ ምስጋና እና ክብር ልንሰጣቸው ይገባል» ያሉት ደግሞ የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ ነበሩ። መምህራኖችን የማመስገን እና እውቅና የመስጠት መርሀ ግብርም ቀጣይነት ያለው መሆኑን እንዲሁም የመምህርነት ሙያን ሳቢ ለማድረግ ትምህርት ሚኒስቴር ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ መሆኑንም ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቁት።
መንግስት ለምስጉን መምህራን ሽልማት እና እውቅና መስጠቱን ተከትሎ እንዲህ አይነቱ ተግባር በሙያውና ሙያተኞቹ ላይ መነቃቃት እንደሚፈጥር የተለያዩ ወገኖች በአድናቆት ሲናገሩ ተሰምቷል። በእርግጥም ተግባሩ ለውጡን ተከትሎ በመምህርነት ሙያ ላይ የነበረው አተያይ አዲስ መንገድ የያዘ ስለመሆኑ ያመላክታል። ለዚህ ደግሞ ከባለፉት ሦስት ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ መምህራን ላይ በቀደመው መንግሥት በሙያው ላይ ያሣረፈውን ሀገር ገዳይ አካሄድ ለማረቅ የተደረጉ ጥረቶችን ይሄንኑ ይናገራሉ።
በመንግስት በኩል ከነበሩ ጥረቶች መካከል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በግፍ የተባረሩትን መምህራን ጉዳይ ይገኙበታል። በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ቀጭን ትዕዛዝ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተባረሩትን መምህራን፤ በመመለስ የዶክተር አብይ አህመድ መንግሥት የወሰደውን ርምጃ በሙያተኛው ላይ የነበረውን አሉታዊ አተያይ መቀየሩ አስረጂ ይሆናል። በሌላ በኩል መንግሥት አዲስ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት ሌላው ርምጃ ነው። በተመሣሣይ የመምህራን ቀን በየዓመቱ እንዲከበር ተደርጓል።
በቀደመው መንግስት ለመምህራን የሚከፈለውን ዝቅተኛ የደመወዝ እርከንን በማሻሻል የኑሮ ደረጃቸውን ከፍ ለማድረግ ከተሰሩት ስራዎች ጋር፤ ከሰሞኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ 183 ምስጉን መምህራን ሽልማት እና እውቅና መሰጠቱ ሌላው ማሳያ ይሆናል። በተጨማሪ በእውቅና አሰጣጥ መርሀ ግብሩ ላይ ትምህርት ሚኒስቴር የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር እየሰራ ያለውን ስራ ለማመስገን እና ማህበሩን ለማጠናከር የሁለት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል። ይህም ማህበሩን እንዳይጠናከር ከሚደረገው ጥረት በመውጣት ወደ ማጠናከሩ መሸጋገሩን ያመላክታል። እኛም የተጀመሩ ለውጦችን አጠንክሮ ዛሬም ያልተነኩ ጉድለቶችን ቆፍሮ አውጥቶ በመሙላት በሀገራችን የመምህርነት ሙያም ሆነ መምህራን ወደ ነበሩበት የከፍታ ጥግ የሚደርሱበት ጊዜ እንዲመጣ ምኞታችን ነው።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 18/2013