ዘላለም ግዛው
አዲስ አበባ:- ‹‹ጥላቻ፣ በቀል፣ ማፈናቀልና መግደል አደገኛ ነገሮች በመሆናቸው ድርጊቱን እናወግዛለን፤ አንዳችን ለሌላችን ጋሻና መከታ፣ መድሃኒትና ፈውስ ሆነን መኖር አለብን ›› ሲሉ የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያን ህብረት ፕሬዚዳንት ፓስተር ጻዲቁ አብዶ ገለጹ።
ፓስተር ጻዲቁ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ አሁን በተለያዩ ቦታዎች የምናየውና የምንሰማው፣ እርስ በእርስ እየሆነ ያለውም ነገር ያጠፋናል እንጂ አያለማንም ድርጊቱ መቆም አለበት፣ ሁሉም ወደ ህሊናው መመለስ ይኖርበታል ።
የመጠፋፋት፣ የመለያየት፣ የመገዳደልና አንዱ ሌላውን የማፈናቀል መንገድ ይወገዛል፣ የእግዚአብሄር ቃልም እያንዳንዱ የዘራውን ያጭዳል ስለሚል አሁን አንዳንዶች ከያዙት መንገድ ተመልሰው የምህረትና የይቅርታ መንገድ መከተል ይገባቸዋል። ድርጊቱ በቀልን ስለሚወልድ መቆም እንዳለበት አሳስበዋል።
‹‹እየተሄደበት ያለው መንገድ በጣም አደገኛ እና ዋጋ የሚያስከፍል ነው። ለእንዲህ አይነቱ መንገድ ሰው ፍርድ መስጠት ባይችል እንኳን በሰማይ ያለ አምላክ ይፈርዳል፣ የእርሱ ፍርድም ከባድ ነው፣ እርሱ ከመፍረዱ በፊት ራሳችን ፈርደን ወደ ልቦናችን እንመለስ›› ብለዋል።
ከክፉ መንገድ መመለስ፣ ምህረትንና ይቅርታን መስጠትና መቀበል ከቻልን የሌሎች እጆች ጣልቃ ሳይገቡ ተግባብተን መቀጠል እንችላለን ያሉት ፓስተር ጻዲቁ ፣ ከጎረቤቶቻችንና ከታሪክ እንድንማር እግዚአብሄር ብዙ ዕድል እንደሰጠንም አመልክተዋል።
ፓስተር ጻዲቁ፤ በአንዱ ላይ የሚደርሰው ጥቃት በሁላችን ላይ የተሰነዘረ ነው፣ በአንዱ ላይ የሚደርሰው በደል በሁላችን ላይ የሚደርስ በደል ነው በሚል ህመሙ ሊሰማን ይገባል ብለዋል ። ከዚህም ባለፈ ጉዳዩ ሁላችንም በሰላም መኖር እንችላለን ብሎ ማመንንም እንደሚጠይቅ አስታውቀዋል።
‹‹እንደ ሃይማኖት አባት ችግሩ እንዲያከትም፣ በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን ወደ እግዚአብሄር እንጮሃለን፣ እንጸልያለን፣ አምላካችንንም እንለምናለን›› ያሉት ፓስተር ጻዲቁ ፣ ችግሮቹ የቆዩ፣ የተወሳቡና ተከምረው የመጡ ናቸው። ከሃይል እርምጃ በመለስ እንዲፈቱ እንደሃይማኖት አባት ጥረት ብናደርግም አልሆነም። ቢሆንም በእግዚአብሄር ተስፋ አይቆረጥም ሁላችንም ወደ ልቦናችን እንመለስ ብለዋል።
እግዚአብሔር ማንም ሰው ሌላውን መግደል እንደሌለበት አዝዟል፣ በህይወት የመኖር መብት በኢትዮጵያ ህገ መንግስትና በዓለም አቀፍ ህጎችም ተደንግጓል። ዛሬ የሚፈስሰው የህጻናት፣ የአዛውንቶች፣ የአረጋውያንና የእናቶች ደም ነገ መከፈሉ እንደማይቀር ጠቁመዋል።
ችግር ሲደርስ ሮጠው ማምለጥ የማይችሉ የህብረተሰብ ክፍሎች በአደጋ እየተጠቁ ባሉበት፣ ምድሪቱ ችግር ላይ በወደቀችበት ወቅት ምህረት ሰጥተንና ተቀብለን ሰላም ለማስፈን ጥረት ማድረግ ይገባናል ብለዋል ።
በቀዳሚነት በሁለንተናዊ መልኩ አምላክን ይቅርታ መጠየቅ ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች አነስተኛ ሆነ ብዛት ያላቸው ቢሆኑም ከዳር ዳር ያለ ስጋት በሰላም መኖር እንዳለባቸው አመልክተዋል።
መንግስት ሰላምና ጸጥታ የማስከበር ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል። ህዝብም ለተግባሩ ካልተባበረ በጣም አስቸጋሪ ይሆናል። መንግስት፣ ተፎካከሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች መሳሪያ ይዞ ያለ ሃይል በአጠቃላይ መላው ህዝብ ኢትዮጵያ በተባለችው ምድር ተግባብተው ለመኖር የሰለጠነ መንገድ መከተል እንዳለባቸው አሳስበዋል ።
የ40 እና የ50 ዓመት ታሪክ ያላቸው አንዳንድ አገሮች በሰላም ይኖራሉ። እኛ የብዙ ዓመት ታሪክ እየቆጠርን ሰላማችንን የምናጣበት ምክንያት ሊኖር አይችልም። ሁላችንም በመጀመሪያ ከእግዚአብሄር ጋር መታረቅ በመቀጠልም እርስ በርስ መታረቅ እንደሚኖርብን አመልክተዋል።
ሁሉም ሰው ከእልህ፣ ከቂመኝነት፣ ከጥላቻና ከቁጣ መውጣት አለበት። ምንም ነገር በሃይል ሊፈታ አይችልም። ሁሉም ነገር በሰይፍ፣ በጉልበት፣ በመሳሪያ ሃይል ሊሆን አይችልም። ከእዚህ አዙሪት ውስጥ መውጣት ይገባናል። ሁላችንም ሃላፊነት ስላለብን ወደ ትክክለኛው መንገድ ፈጥነን መመለስ አለብን ብለዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 15/2013