6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ለሀገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ እንደሚያገለግል ተጠቆመ
በኃይሉ አበራ
አዲስአበባ፦ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ለሀገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ እንደሚያገለግል ተጠቆመ። ዜጎች የምርጫ ካርዳቸውን በመውሰድ የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ።
የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር “የጋራ መግባባት በተሻለ የሀሳብ ነጻነት” በሚል ርዕስ ከሲቪክ ማህበራትና ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው ውይይት የማህበሩ ፕሬዚደንት ወጣት ገህሕበበሀዛኸኝ ገብረማሪያም እንዳስታወቀው ፣ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ለሀገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ የሚያገለግል ነው።
ምርጫው ነጻ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ማህበሩ ጽኑ ፍላጎት እንዳለው ያስታወቀው ወጣት ገዛህሕበበሀኸኝ ፣ ለተግባራዊነቱም ማህበሩ በተደራጀ መንገድ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው ብለዋል።
ምርጫ የተለያዩ አማራጮች ቀርበው የሃሳብ ፍጭት ከተደረገ በኋላ ተቀባይነት ያገኘውና በአብላጫ የተመረጠ ሃሳብ ብቻ በሕግ ለተገደበ ጊዜ ገዢ የሚሆንበት ሂደት መሆኑን በመረዳት የከተማዋ ወጣቶች በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቧል።
የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ዋና ጸሐፊ ወጣት ይሁነኝ መሀመድ በበኩሉ ፤ የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ከተመሰረተ 23 ዓመት መሆኑን አስታውሶ፣ ከሁለት ዓመታት ወዲህ የመጣው የማህበሩ አመራር በመግባባት እና በሃሳብ ነጻነት የሚንቀሳቀስ እንጂ ቀድሞ የነበረውን ገጽታ የያዘ አይደለም ብለዋል።
የየትኛውም የፖለቲካ አባል የሆነ ወጣት ከማህበሩ ጋር መስራት እንደሚችል የጠቆመው ወጣት ይሁነኝ፣ አሁን ባለንበት ነባራዊ ሁኔታ ሀገራችን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ውስጥ ትገኛለች። ሁላችንም እድገት፣ ነጻነትና ሰላም መፈለጋችን በጋራ እንድንቀሳቀስ የሚያግባባን ተጨባጭ እውነታ ነው ብሏል።
የምርጫ ካርድ ኢትዮጵያዊ በመሆናችን የምናገኘው፤ ያለንበትን ተረድተን፣ የመጣንበትን አገናዝበን፣ የምንፈልግበትን ተልመን ለመወሰን እድል የሚሰጠን እንደሆነም አስገንዝቧል። ማህበሩ ነጻ ማህበር እንደመሆኑ ዜጎች የምርጫ ካርዳቸውን እንዲወስዱ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ መሆኑን አስታውቋል። ከመንግስት ከምርጫ ቦርድ እና ከተፎካካሪ ፓርቲዎች በኩል ያሉ ችግሮች እንዲታረሙ በቅርበት እየሰራ እንደሆነም አመልክቷል።
የኢትዮጵያ በጎ ፈቃደኛ ጋዜጠኞች እና የኪነጥበብ ባለሙያዎች ህብረት ስራ አመራር ጋዜጠኛ በፍቃዱ አባይ፣ በበኩሉ በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ግንቦት 28 ስንገናኝ የጋራ የሆነ አንድ ነገር ያስፈልገናል፤ የጋራ ነገር ካለን ደግሞ መግባባት ይኖረናል ብሏል።
በምርጫ 97 ወቅት ምርጫ ካርድ ባለማውጣታቸው የተነሳ የተቆጩ እንደነበሩ ያስታወሰው ጋዜጠኛ በፍቃዱ ፣ የምርጫ ካርድ ማውጣት የአምስት ዓመት ዋስትና በእጅ መያዝ ነው። ይህንን እውን በማድረግ ሂደት ውስጥም የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ትልቅ ሃላፊነት እንዳለበት አስታውቋል።
ሁሉም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደጋፊዎቻቸው የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ ቅስቀሳ ማድረግ እንደሚገባቸውም አመልክቷል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 15/2013