ገመቹ ከድር
አዲስ አበባ፡- በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የቡኖ በደሌ ዞን ምርጫ ክልል 11 የምርጫ ጣቢያዎች በተመደበላቸው ኮታ መሰረት የመራጮች ምዝገባ ማጠናቀቃቸውን ገለጹ ።
የዞኑ የኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ ሀብታሙ ፍቃዱ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት ፤ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በአስቀመጠው መርሃ ግብር መሰረት የመራጮች ምዝገባ በሰላማዊ መንገድ እየተካሄደ ነው።
በዚህም መሰረት እስከ መርሃ ግብሩ መጨረሻ ድረስ 305 ሺህ 314 መራጮችን ለመመዝገብ ታቅዶ እስከ ሚያዝያ 13 ድረስ 310 ሺህ 340 መራጮች ተመዝግበዋል። አሃዙ በመቶኛ ሲሰላ 101.7 በመቶ መሆኑን አስታውቀዋል።
ማህበረሰቡ ዴሞክራሲያዊ መብቱን እንዲጠቀም የተለያዩ የግንዛቤ መስጨበጫ መንገዶችን በመጠቀም ሰፊ ቅስቀሳ መደረጉን ያመለከቱት አቶ ሀብታሙ ፣ ለዚህም ማህበራዊ ሚዲያ ፣ ፌስ ቡክ ፣ ቴሌግራም እንዲሁም ከዞን እስከ ወረዳ ቀበሌ ድረስ ያሉ የማህበረሰቡን አደረጃጀቶችን መጠቀማቸውን አመልክተዋል።
የዞኑ አመራር ጠንካራ የክትትል እና የድጋፍ ሥርዓቶችን ከዞን አስከ ቀበሌ ድረስ በመዘርጋት ከምርጫ አስፈፀሚዎች ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ፈጣን ግብረ መልስ በመስጠት እስከ አሁን የተመዘገቡትን መራጮች መመዝገብ መቻሉን ጠቁመዋል።
በተለይ በበደሌና በጨዋቃ ጣቢያ የተመዝጋቢ ቁጥር በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከተሰጠው ኮታ 1ሺ 500 በላይ መሆኑ በተወሰነ መልኩ ተግዳሮት መፍጠሩን ያስታወቁት አቶ ሀብታሙ ፣ ችግሩን ለምርጫ ቦርድ አሳውቀን ምላሽ እየተጠባበቅን ነው ብለዋል።
በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቡኖ በደሌ ዞን ምርጫ ክልል ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብዮት ማሞ በበኩላቸው፣ የምርጫ መርሃ ግብሩ ይፋ ከተደረገበት ቀን ጀምሮ በዞኑ በሚገኙ 5 የምርጫ ክልል በ491 ምርጫ ጣቢያ በመርሃ ግብሩ መሰረት ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እየተካሄደ መሆኑን ገልፀዋል።
እስከ ሚያዝያ 13 ድረስ በተደረገው አፈፃፀም መሰረት ከ491 የምርጫ ጣቢያዎች በ11 ጣቢያዎች በተመደበላቸው ኮታ መሰረት የመራጮች ምዝገባ ሙሉ በሙሉ ማጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል። ምዝገባ የተጠናቀቀባቸው ጣቢያዎች እስከ ድምፅ መስጫ ቀን ድረስ ተዘግቶ በፀጥታ አካላት ተገቢውን ጥበቃ እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቁመዋል።
ኮታ ሞልቶ ህዝቡ ሳይመዘገብ የቀረባቸው ቦታዎች እንዳሉ የጠቆሙት አቶ አብዮት ፣ ችግሩን ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አሳውቀው ምላሽ እየተጠባበቁ መሆኑን አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 15/2013