. አራተኛው ዙር መርሃ ግብር ተጀምሯል
ሙሳ ሙሀመድ
አዲስ አበባ፡- በሶስተኛው ዙር የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ገቢ የማሰባሰብ ሂደት ከደንበኞች የተሰበሰበ 122 ነጥብ 47 ሚሊዮን ብር ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል መስሪያ ቤት ገቢ ማድረጉን ኢትዮ ቴሌኮም ገለጸ። አራተኛው ዙር መርሃ ግብር መጀመሩም ተገልጿል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ በአንድ ዓመት ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ደንበኞቹ በ8100 ኤ አጭር መልእክት የተሰበሰበውን 122 ነጥብ 47 ሚሊዮን ብር ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አሸብር ባልቻ ትናንት አስረክበዋል።
በርክክቡ ወቅት ወ/ሪት ፍሬሕይወት እንደተናገሩት፤ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በ8100 ኤ አጭር መልእክት አራተኛው ዙር ገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ይቀጥላል። ከሶስቱ ዙሮች በድምሩ 252 ሚሊዮን ብር ተሰብስቦ ገቢ ተደርጓል።
‹‹የህዳሴ ግድቡ ተጠናቅቆ ለእኛው ብልፅግና እንዲውል ለማስቻል ትናንት በተጀመረው አራተኛው ዙር ድጋፍ ማሰባሰቢያ 8100 ኤ አጭር መልዕክት ተሳትፏችሁን ቀጥሉ›› ሲሉም ወ/ሪት ፍሬሕይወት ጥሪ አቅረበዋል። በሶስቱም ዙሮች ኢትዮ ቴሌኮም ከሰራተኞች 111 ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር ማሰባሰቡንና ተግባሩ ለሌሎች ተቋማት አርአያ መሆን እንደሚችልም ተናግረዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ጽ/ ቤት ሃላፊ ዶ/ር አረጋዊ በርሄ በበኩላቸው፤ ‹‹ግድቡ ለኢትዮጵያውያን የሉዓላዊነታችን ተምሳሌት፣ የአንድነ ታችንና የፍትሃዊነት አመልካች ነው›› ብለዋል። ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በ8100 ኤ አጭር መልእክት ህብረተሰቡ ተሳትፎውን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ መክረዋል።
እስካሁን ድረስ አፍሪካውያን በሃያላን መንግስታትና የገንዘብ ተቋማት፣ በእርዳታና ብድር በተመፅዋችነት በመያዛችን እድገታችን ፈንጥቆ ሊወጣ አልቻለም ሲሉ አስታውሰዋል። ግድቡን በራስ አቅም የመገንባት አካሄድ በዓለም ኢኮኖሚ እይታ ከጥገኝነት ነፃ የሚያወጣ አቅጣጫን የተከተለ መሆኑንም ዶ/ር አረጋዊ አመልክተዋል።
አሁን እራሳችን ለራሳችን አሻጋሪ የሆነውን ፕሮጀክት ጀምረን በውስጥ አቅማችን በመገንባት የግንባታውን ሂደት 79 በመቶ ማድረስ ችለናል፣ የሉዓላዊነታችን ተምሳሌት የሆነውን ግድባችን ይጠናቀቃል ብለዋል።
በመጀመሪያው ዙር ከተሳተፉ 851 ሺህ ደንበኞች 80 ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ብር፣ በሁለተኛው ዙር ከተሳተፉ 525 ሺህ ደንበኞች 49ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ብርና በሶስተኛው ዙር ደግሞ ተሳትፎ ካደረጉ አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን የህብረተሰብ ክፍሎች 122 ነጥብ 47 ሚሊዮን ብር ገቢ መደረጉን አብራርተዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 15/2013