ጽጌረዳ ጫንያለው
ከልጅ እስከ አዋቂ፤ ፊደል ከቆጠረው እስከ ምሁር፤ የሚያውቃቸው ሁሉ በአንድ ልብ የሚመርጣቸው አይነት ሰው ናቸው:: የሰዎችን የውስጥ ስሜት ማዳመጥ የሚችሉና ለችግር መፍትሄ ሰጪነታቸውም ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል:: ‹‹አንዳንዴ እርሱ ጋር ስሄድ ምንም ምርመራ ሳይደረግልኝ በተናገርኩት ብቻ ተፈውሼ እመለሳለሁ›› የሚሉላቸው አይነት ሀኪምም ናቸው:: በተለይ ለየት የሚያደርጋቸው ለገንዘብ የማይስገበገቡ አይነት ባለሀብት መሆናቸው ነው:: ምክንያቱም በእርሳቸው ክሊኒክ ያለውም የሌለውም እኩል ይታከማል:: ቶሎ ቶሎ አይቶ ወይም የላብራቶሪ ትዕዛዝ ደርድሮ የሚሸኙ አይነትም አይደሉም:: ታካሚዎች እስከሚበቃቸው ሁኔታቸውን እንዲናገሩ ይፈቅዳሉ:: ከዚያም አልፈው በጣም እርግጠኛ ካልሆኑ በስተቀር ላብራቶሪ ምርመራ አያዙም::
የሚያክሙትም ቢሆን በርካታ ሰው እርሳቸውን ፈልጎ ቢመጣም ችግርን አስፍቶ ከማየታቸው አንጻር በቀን ከ30 በላይ አይሆንም:: እናም የብዙ ሰዎች ምርጫ የሚሆኑትም ለዚህ ነው:: ለእርሳቸው ሰው እንጂ ገንዘብ ምርጫ እንዳልሆነም ያምናሉ:: በዚህም እምነታቸው ነው እየሰሩ የሚገኙት:: ለመሆኑ ይህ ባህሪ እንዴት ዳበረ፤ የወቅቱ ህክምና ተቋም አፋጥኖ ገንዘብ መሰብሰብ እንጂ ሙያዊ ግዴታን መወጣት አይደለም:: የእርሶ ትኩረት ለምን እንዲህ ሆነና መሰል ጥያቄዎችን በመጠየቅ የህይወት ተሞክሯቸውን እንዲያወጉን ጠየቅናቸው::
ይሁንና እርሳቸው ይህንን አደረኩ ባህሪያቸው አይደለምና ትህትናቸው በለጠብን:: ‹‹የተለየ የሚያስተምር ነገር ምንም የለኝም›› ቢሉም በአስፈላጊነቱ ተማምነን ተሞክሯቸውን አካፈሉን:: እኛም ከህይወት ልማዳቸው አባይን በጭልፋ ቢሆንብንም የተወሰኑትን ጨልፈን በ‹‹ ህይወት ገጽታ›› አምዳችን እንካችሁ አልን:: መልካም ቃርሚያ ተመኘን::
የእኔ መሳይ
አባታቸው መሳፍንት ብለዋቸው አያውቁም:: በጣም ስለሚወዷቸው ‹‹ የእኔ መሳይ›› እያሉ ነው የሚጠሯቸው:: በእርግጥ መሳፍንት የሚለውንም ስም እርሳቸው ናቸው ያወጡላቸው:: ነገር ግን ይህንን ስም ብዙም አይጠቀሙበትም:: ሆኖም ስሙን ያወጡበት ግን ምክንያት አለው:: እንደተነገራቸውም በስለት ከብዙ ዓመታት ቆይታ በኋላ ነው ያገኙዋቸው:: ለቤተሰቡም የመጀመሪያ ልጅ ናቸው:: እናም መሳፍንት የተባሉትም ንጉሴ፣ መኳንንቴ፣ መከታዬ ፣ክብሬ ለማለት ስለፈለጉ ነው::
እንግዳችን የቤተሰቡ የመጀመሪያ ልጅ በመሆናቸው ከእናታቸው እኩል የቤት ውስጥ ሥራን ያከናወናሉ:: በተለይ ልብስ አጠባ ላይ ብዙ ጫናን ይቀንሱላቸው ነበር:: ምክንያቱም አባት ወታደር በመሆናቸው ቤት ውስጥ ብዙም አይገኙም:: ስለዚህም የቤተሰቡን ችግር ሳይቀር በቅርበት ይሰሙታል፤ ከቻሉም ይፈታሉ:: በአቅማቸው የሚሆነውን ነገር ከማድረግም ወደኋላ አይሉም::
ዶክተር መሳፍንት በአባታቸው ከመወደዳቸው አንጻርና እርሳቸውን መስለው ከመጓዛቸው አኳያ ‹‹ የእኔ መሳይ›› ይባላሉ:: ከዚህም በላይ ይህን ስም ያወጡላቸው በስነምግባር፣ በትምህርታቸውና መሰል ተግባራቸው የእርሳቸው ምትክ ሆነው እንዲያድጉ ከመፈለጋቸው አንጻርም የእኔ መሳይ እንዳሏቸው ይናገራሉ:: ይህንን ስም ደግሞ ከሚጠሩበት ዋና ስማቸው በላይ ይወዱታል:: በዚህም በስህተት ፈተና ሳይቀር በስሙ ተፈትነው እንደሚያውቁም ያስታውሳሉ:: ይህ ስም የአካባቢ ሰዎች ጭምር የሚጠቀሙበት በመሆኑ ሁለት ስም እንዳላቸውም ይሰማቸዋል::
ባለታሪካችን ትውልዳቸው እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ በተለምዶ ኮርያ ዘማቾች አካባቢ ነው:: በዚህም ለጃንሜዳ ቅርብ ስለሆኑ የልጅነት ጊዜያቸውን ጃንሜዳ ላይ የተለያዩ ጨዋታዎችን በመጫወት ነው ያሳለፉት:: ጃንሜዳ ለእርሳቸው የተለየ ትርጉም ያላት ቦታ ነች:: ብዙ ነገር ቀስመውባታል፤ ጓደኛና ዘመድ ያፈሩባትም ነች:: እንደውም እስከ አራተኛ ክፍል ባለ የልጅነት ጊዜያቸው ከትምህርት ቤት በላይ መዋያቸው እንደነበረችም አይረሱትም:: ምክንያቱም ከትምህርት በላይ ጨዋታ ወዳድ በመሆናቸው በቦታው በስፋት ይገኛሉ::
እንግዳችን በባህሪያቸው መጫወት የሚወዱ፣ አትንኩኝ ባይና ለቤተሰብ ታዛዥ ናቸው:: በዚህም የሰፈር ሰው ሳይቀር የሚወዳቸውና ሊያዛቸው የሚመርጣቸው አይነት ልጅ እንደነበሩ ያስታውሳሉ:: እንደውም የከተማ ደቦ በእኛ አካባቢ ይታያልም ነው የሚሉት:: ለዚህ ደግሞ በምክንያትነት የሚያነሱት በእያንዳንዱ ቤት ያለ ስራ በሰፈሩ ልጆች እገዛ የሚከናወን መሆኑን ነው:: የእናት ገደብ፣ የአባት ልዩነትና የሥራ የእኔ ብቻ በሰፈራቸው ውስጥ አይታወቅም:: ይህ ደግሞ የሰፈሩ ሰው በሙሉ የሁሉም አባት፣ የሁሉም እናት አሊያም ልጅ ሆኖ እንዲኖር አድርጓል:: ስለዚህም በእያንዳንዱ ቤት ያለ ሥራ የሁሉም ልጅ ሀላፊነት ነው:: የአንዱን ቤት ሲጨርስ የሌላውን ቤት ሥራ ወደመስራቱ የሚገባበት ነው::
በእነርሱ ሰፈር “እንትና” የጎረቤት ልጅ ነው የሚባል ነገር አይታወቅም:: ወንድሜ፣ እህቴ፣ ተለቅ ያሉት ደግሞ አጎቴ አክስቴ ነው የሚባሉት:: አዛውንቱን ደግሞ አባቴ እናቴ ከማለት ውጪ ማንንም በስሙ አለያም የሩቅ ሰው አድርገው ጠርተው አያውቁም፤ አይፈቀድላቸውምም:: ስለዚህም እርሳቸው የሌላው ሌላው የእርሳቸው ቤተሰብ ሆነው ነው ያደጉት:: ይህ የሰፈር ትስስር ደግሞ ዛሬ ድረስ በህይወታቸው ላይ ትልቅ አሻራን ስላሳረፈባቸው ኑሮውን ለመኖር እየጣሩ ይገኛሉ:: ቤተሰባዊነት ለእርሳቸው ልዩ ቦታ እንዲኖረውም አድርጓቸዋል:: በሥራቸው ጭምር ቤተሰብ የማያደርጉት ሰው እንዳይኖር ረድቷቸዋል::
ስንፍና በአባት ሲታከም
ከአንደኛ ክፍል እስከ አራተኛ ክፍል በጣም ሰነፍ ተማሪ ነበሩ:: እንደውም አራተኛ ክፍል ላይ እያሉ ከክፍሉ መጨረሻ ወጥተዋል:: ይህ ደግሞ ወላጅ ጭምር አስመጥቶ ያስወቀሳቸው እንደነበር አይረሱትም:: ይህንን ጊዜ ሲያስቡትም እንዲህ ነበር ያሉን‹‹ አባቴ በሥራ ምክንያት ስላልተመቸው እናቴን ነበር ይዤ የሄድኩት:: እናም ወላጅ አምጣ ያለኝ መምህሩ ቢሮ ገብታ የመሳፍንት እናት ነኝ ገና ስትል መምህሩ ቀና ሳይል ‹እ—እ የዚያ የደደቡ እናት ነሽ፣ ለሽልማት አይደለም የጠራንሽ፤ በጣም ደደብና የማይገባው ልጅ እንዳለሽ ልንነግርሽ ነው:: ከቻልሽ እንድትለውጪው ልናስረዳሽ ነው” አላት::
በጊዜው እናቴን ሳያት እንባዋ በአራቱም ማዕዘን እየፈሰሰ ነው:: በጣሙን ተናዳብኛለች:: ምን ብዬ እንደማጽናናትም እንደምናገርም ግራ ገብቶኝ ነበር:: ቁጣዋ ገንፍሎም በቅጽበት ‹አመሰግናለሁ› ብላ እጄን ጎትታ ወጣች:: ከዚያ “ቦጫጨቀችኝ” የሚለው ቃል አይገልጻትም:: ግን ምንም ስላልረካች ይዛኝ ወደቤት ሄደች:: ነገር ግን ቤት አልገባም አልኳት፤ የሚጠብቀኝን አውቃለሁና::
አባቴ እስኪመጣም ምሳ ጭምር ሳልበላ ዋልኩ:: እርሱ ሲመጣ አብሬው ገባሁ:: ጥፋቴ ተነገረው:: ግን ምንም አላለም:: እንደውም በህይወቴ ለውጥ የሚያመጣ ንግግር ተናገረ:: የማልረሳውን ትዝታና ወኔ ሰጠኝም:: ይህም ‹ደደቡ እርሱ ሳይሆን አሳዳጊዎቹ እኛ ነን› በማለት ከዚያ ቀን ጀምሮ አብሮኝ እያጠና እንዳጠና አገዘኝ:: ሁለተኛ ሴሚስቴር ላይም ሁለተኛ ደረጃን ያዝኩ:: ከዚያ በኋላም የትምህርት ቤቱ የደረጃ ተማሪ ብቻ ሳይሆን አንደኝነትን ተቀምቼ አላውቅም:: አንደኛና ሁለተኛ የሚወጣው በተአምር ሳይሆን በማጥናት እንደሆነም ከዚያን ቀን በኋላም ገባኝ›› ይላሉ::
ባለታሪካችን በትምህርት ጉዟቸው አስገራሚ ነገራቸው ይህ ብቻ አልነበረም:: አባታቸው ችግር ገድቧቸው ውትድርናውን ተቀላቀሉ እንጂ በጣም ጎበዝና የት ይደርሳል የተባሉ ነበሩ:: እናም የእኔን ቁጭት የምወጣው በልጄ ነው ሲሉ አምስተኛ ክፍል በማታ ተመዘገቡ:: ልጃቸው ቀን የተማረውን እርሳቸው ማታ እየተማሩ አብረው እያጠኑ ውጤታማ ለማድረግ:: አሳክተውታልም ይላሉ:: ምክንያቱም አንዳንዴ ሳይመቻቸው ሲቀር ‹‹አንተ ገብተህ ተማርና ማታ ታስተምረኛለህ›› እያሉም በማታ ጭምር የሚማሩበትን እድል ሰጥተዋቸዋል::
እንደውም ይህ አጋጣሚ በመምህሮቻቸው ጭምር እንዲጨበጨብላቸውና እንዲታወቁ ያደረገ ክስተትን ፈጥሮላቸዋል:: ነገሩ እንዲህ ነው:: ማታ ገብተው የተማሩት ትምህርት በቀን ትምህርታቸው ላይ መምህሩ ሳያስተምራቸው የመለማመጃ ጥያቄ አድርጎ ሰጣቸው:: እናም በጣም ጎበዝ የተባሉት ሁሉ ያገኙት ከአስሩ አራት ነበር:: እርሳቸው ግን ደፍነውታል:: ይህ ያስገረመው መምህርም መምህራን መሰብሰቢያ አዳራሽ ያስጠራቸዋል:: ምክንያቱም በአስተማረባቸው ጊዜያት ተማሪ መሳፍንት የሚባል ጎበዝ አያውቁም፣ አልሰሙም:: እናም በዚያ አዳራሽ ውስጥ ጠመኔ ቀርቦላቸው ጥቁር ሰሌዳው ላይ ሒሳቡን እንዴት እንደሰሩት እንዲያሳዩ ታዘዙ:: በደንብ እያስረዱም ሰርተው አሳዩ:: መምህራኑም ተገረሙ:: ያ ሳይበቃም ወደ ውጪ ሲወጡ ተማሪዎች እየተመለከቷቸው ነበርና አጨበጨቡላቸው:: ከዚያች ቀን በኋላ በትምህርት ቤቱ ስንት አመጣ የሚባሉት እርሳቸው ሆኑ:: መስፈርትና መለኪያም ከእርሳቸው ውጪ አልነበረም:: እነዚህ የትምህርት ጊዜያት ያለፉት መጀመሪያ በህብረት ፍሬ ትምህርት ቤት፤ ማለትም ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ በተማሩበት ነው:: ከዚያ ደግሞ ሁለተኛ ደረጃን በዳግማዊ ምኒልክ ነው::
ወደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲዛወሩም ቢሆን ስፔሻል ክላስ የሚባል ስለነበር እርሳቸውም በዚህ ክፍል ውስጥ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል:: ይህ ደግሞ ዘጠነኛ ክፍልን ጠዋት አስርን ደግሞ ከሰዓት ተምረው በዓመት ውስጥ አስራ አንደኛ ክፍልን መቀላቀል አስችሏቸዋል:: ስለዚህም በሦስት ዓመት ቆይታ ከሌላው ተማሪ ተለይተው 12ኛ ክፍልን አጠናቀዋል:: ይህ ብቻ ሳይሆን የትምህርት ቤቱ ሰቃይ ሆነው ፎቶ ግራፋቸው ከተለጠፈ የመጀመሪያ ተማሪ መሆን ችለዋልም::
ቀጣዩ የትምህርት ጉዟቸው የሚወስደን ጅማ ላይ ሲሆን፤ ጅማ ጤና ሳይንስ ኮሌጅን በሜዲስን ትምህርት መስክ ነው የተቀላቀሉት:: በእርግጥ የእርሳቸው ፍላጎት ይህ አልነበረም:: ምክንያቱም ሜዲስን የድሀ ልጆች የሚማሩት አይነት መስክ ተደርጎ አይወሰድም:: ስለዚህም ቤተሰቦቼን ቶሎ ከችግር ለማላቀቅ የሚበጀኝ ኢንጅነሪንግ ነው ብለው ስላመኑ እርሱን ለመማር ወስነው ሞልተው ነበር:: ሆኖም ወጋየሁ የተሰኘው መምህራቸው የእርሳቸውን ብቃት ያውቅ ነበርና የሞሉትን ፎርም ቀድዶ ሜዲስን በራሱ ውሳኔ ሞላላቸው:: እናም የመምህራቸው ምርጫ የሆነውን ለመማር ወስነው ወደ ጅማ አቀኑ:: ሰባት ዓመታትንም በዚያ አሳለፉ:: የማዕረግ ተመራቂም በመሆን ትምህርታቸውን አጠናቀቁ::
ህክምና ሁል ጊዜ መማር ነው ብለው የሚያምኑት ባለታሪካችን፤ ሜዲካል ዶክትሬታቸውን ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በጠቅላላ አገልግሎት ህክምና ዘርፍ ተመርቀዋል:: ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ወይም ስፔሻላይዜሽን ከለንደን ሪሀምተን ዩኒቨርሲቲ በማህበረሰብ ጤና የትምህርት መስክ ሰርተዋል:: ከዚያም በተጨማሪ ከአምስት ያላነሱ አለምአቀፍ የህክምና ሰርተፍኬቶችም ያገኙ ናቸው::
በእነርሱ ጊዜ ያለ ተማሪ በማንበብ የሚረካ፣ ያለውን መጽሐፍ አበድሮ ከሌሎች ጭምር እየወሰደ የሚያነብ በመሆኑ እርሳቸውም ከወሰዷቸው ስልጠናዎችና ከስራቸው ከሚያገኙት የየቀን ልምድ በተጨማሪ በማንበብ እውቀታቸውን እንደሚያዳብሩ አጫውተውናል:: እንደውም በየሳምንቱ ሁለት መጽሐፍ የመግዛት ልምድ እንዳላቸው ይናገራሉ:: በተለይም የታሪክ ከሙያቸው ጋር የሚገናኙ መጽሐፍትን መግዛትም ማንበብም ምርጫቸው እንደሆነ አውግተውናል::
ከመቱ እስከ ደቡብ አፍሪካ በሥራ
ስለ ሥራ ሲያስቡ ከአባታቸው የተረከቡትን ነገር ከግብ ማድረስ ህልማቸው ነው:: ምክንያቱም አባታቸው ገና እንደተመረቁ ነው በህይወት የተለዩዋቸው:: እናም ስድስት ልጆችን አባት ሆነው ማስተማር የእርሳቸው ግዴታ ነው:: ስለዚህም የሥራ ጅማሮአቸውን መቱ ሆስፒታል ውስጥ ሲያደርጉ ጎን ለጎን እህትና ወንድሞቻቸውን እያስተማሩ ነው:: ሁሉንም በሚባል ደረጃም እድለኛ ሆነው ዛሬ ላይ ሁለትና ሶስት ዲግሪ እንዲኖራቸው አድርገዋል:: በቅርቡም እንደእርሳቸው ዶክተር የምትሆን እህት አለቻቸው
በመሆኑም ሥራ ለእርሳቸው ቤተሰብን ቁም ነገር ላይ ማድረሻ፤ ሰዎችን ወደ ተሻለ ህይወት ማስገቢያ ነው::
ሥራ ከዚያም ልቆ ቤተሰብ ማግኛም እንደሆነ ይናገራሉ:: ለዚህም መቱ ላይ ባገለገሉበት ሁለት ዓመታት ውስጥ እንደ እናት አባት፣ ወንድም እህት የሚወዷቸው ሰዎችን አፍርተዋል:: ታካሚያቸው ሳይሆኑ ቤተሰባቸው እንደሆኑ የሚሰማቸው ብዙ ሰዎች አሏቸው:: አሁን ያሉበት ላይ ሆነው እንኳን የማይረሷቸው እየሄዱ የሚጠይቋቸው እነርሱም እየመጡ የሚያበረቷቸው ብዙ ናቸው:: ስለዚህም ይህ ሙያ በሥጋ የማይዛመድ ጭምር ዘመድ የሚያደርግበት ነውም ይላሉ::
ከመቱ እንደመጡ ወደ ውጪ ሄደው መስራት ቢፈልጉም ስላልተሳካ አዲስ አበባ ላይ ከትመው በዋናነት በወቅቱ አንቱታን ያተረፈው ሐያት ሆስፒታል ውስጥ በዋናነት እየሰሩ በተጓዳኝ ጥቂት ሆነው እውቅና በነበራቸው ዶጋሊ እና ኢትዮጵያ ክሊኒኮች ውስጥ ይሰሩ ነበር:: ከሁለት ዓመታት ቆይታ በኋላም ያሰቡት ነገር ተሳክቶ ወደ ዚምባብዌ አቀኑ:: በጠቅላላ ሐኪምነት በዚምባብዌ በሐራሬ ሴንትራል ሆስፒታል አሳለፉ:: ዓመት ከመንፈቅ ቆይታ በኋላ የአሜሪካ ዶላሩን በራሳቸው በዚምባብዌ ዶላር መንዝረው መክፈል ሲጀምሩ ብዙም ስላልተመቻቸው ለቀቁ:: ሆኖም ሌላ ቦታ ላይ ማፈላለግ ጀመሩ:: በዚህም ከደቡብ አፍሪካውያን ጋር ተገናኝተው ሁለት ዓመት ያህል እየተመላለሱ እንዲሰሩ አደረጓቸው:: አቅማቸውን ከአዩ በኋላ ደግሞ በሁለት ደቡብ አፍሪካውያን በተከፈተ አፍሪሰንርግ የሚባል ኩባያ እና ፒ ላይፍ ሄልዝ ኬር ግሩብስ ውስጥ የኢትዮጵያ ወኪል ሆነው እንዲሰሩም እድሉ ተሰጣቸው:: በዚህም አገሬን ባገለግል ከዚህ በላይ አተርፋለሁ በሚል የውጪውን ሥራ ትተው ተመለሱ:: ቀደም ብለው ይሰሩበት በነበሩ ክሊኒኮችና ሆስፒታሉ ውስጥ መስራቱን ተያያዙት:: በተጓዳኝ የሆስፒታሎቹን ውክልናም ይሰራሉ::
አንደኛው ክሊኒክ ውስጥ 50 በመቶውን የአክሲዮን ድርሻ ገዝተው በራስ ስሜት እየሰሩ ቆይተዋል:: ሆኖም እድገቱ ሲመጣ ገንዘቡ አሳሳቸውና የ50 በመቶ ተጋሪያቸው ባልሸጥኩ ኖሮ አሰኛቸው:: ከዚያም በላይ ቅይይም የሚያመጣ ነገር ውስጥ ሊያስገባቸው የሚችል ነገር ተከሰተ:: እንግዳችን ግን ይህንን አይፈልጉትምና በእድገት የመጣውን ንብረት ምንም ነገር ሳይካፈሉ ሰው ይበልጣል ብለው ሥራውን አቆሙ::
መልካምነት ይከፍላልና ራሳቸውን ከዚህ መንፈስ ለማራቅና ለማደስ ለዕረፍት ከሄዱበት ቦታ ሲመለሱ ወንድሜ የሚሏቸው የአምባሳደር ልብስ ስፌት ባለቤት አቶ ሰይድ እና አቶ ፋንቱ ቀደም ሲሉም በራሳቸው ክሊኒክ ከፍተው እንዲሰሩ ያበረታቱዋቸው ነበርና ይህ መሆኑን ሲረዱ ቤት ተከራይተው ኪሊኒኩን ሙሉ አመቻችተው ጠበቋቸው:: ‹‹በል ሥራ›› ሲሉም ገጸ በረከታቸውን አቀረቡላቸው:: ከዚያ በኋላም በዚህ ቦታ ላይ ብዙዎችን በህክምናቸው መፈወሱን ተያያዙት፤ የሥራ ቅጥርም ቀረ:: በዚህም ዛሬ ላይ ከላይፍ አዲስ ክሊንክ በተጨማሪ ኢንተርናሽናል አርሾ በሚባለው ስታንዳርድ ልክ ላይፍ አዲስ ብለው የሰየሙትን ላብራቶሪ ከፍተው ሜዲካል ዳይሬክተርም ባለቤትም ሆነው በመስራት ላይ ይገኛሉ::
ከዚያ ሻገር ሲባልም በማህበራዊ ተሳትፎ ብዙ ቦታላይ የቦርድ ሀላፊ፤ አመራር እየሆኑም ይሰራሉ:: ከእነዚህ መካከልም ‹‹አገርህን እወቅ›› የተባለ የጓደኛሞች ማህበር ውስጥ የቦርድ ሰብሳቢ ናቸው:: በዚህም ቤተሰብ ጭምር አገሩን እንዲያውቅ የሚያደርግ ሥራ ይሰራሉ:: አገር ወዳድ ትውልድን እየፈጠሩም ናቸው:: በመኖሪያ አካባቢያቸው ቅጥር ግቢንም 100 አባዎራዎችን በሰብሳቢነት የሚመሩም ናቸው:: በቀጣይም ቢሆን ከአገራቸው መውጣትን ስለማይመኙ ይህንኑ ተግባራቸውን እንደሚያከናውኑ አጫውተውናል::
ምክንያታቸው በሥራም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች ያላዩት አገር የለም:: ግን እንደ አገራቸው የሚመቻቸው እንደሌለ ማረጋገጣቸው ነው:: እናም ሁል ጊዜ ምርጫቸው አገራቸው ነች:: ብዙ የተሻለ እድል የምትሰጥ፣ ሁሉ ነገሮቿን አምላክ አሟልቶ የሰጣት ማን እንደ እርሷ ይላሉም:: ነገር ግን ‹‹በእጅ ያለ›› ሆነና ውጪ እናማትራለን:: እናም ካላቸው ልምድ ሲመክሩ የምንጠቅመውም የምንጠቀመውም ከአገራችን ነው ይላሉ::
ህክምና
‹‹እግዚአብሔር እኔን መርጦ ለዚህ ክብር አብቅቶኝ የታመሙ ብዙ ሰዎችን ከህመማቸው እንዲፈወሱ ስረዳቸውና ተስፋቸውን ሳይ እግዚአብሔር ይመስገን እላለሁ:: ህክምናም ይህ መሆን አለበት›› ይላሉ:: ቀጥለውም ጥቂት ያደረኩት በሙያዬ ሰውን አክብሬ በመስራቴ ነው ባይ ናቸው:: ምክንያታቸውም ህክምና መልካም አድራጊዎቻችንን እያሰቡ የበለጠ መልካም ነገር ለማድረግ መታተር መሆኑን ስለሚያምኑ ነው::
ህክምና የራሱ የሆኑ ህግጋት አሉት:: ከአምላክ ቀጥሎ ውስጡን አምኖ የሚነገርበት ሙያም ነው:: እኛም አምኖ ለሚመጣ እንዴት መጥፎ ነገር ይሰጣል? መሆን የለበትም:: ከዚያ ይልቅ ህክምና ማለት መሰጠት መመረጥ ነውና የተሰጠንን መስጠት ያስፈልገናል:: የእኛ ሽልማት የምናግበሰብሰው ገንዘብ ሊሆንም አይገባም:: ሰው ለስማችን የሚሰጠው እምነት መሆን አለበት:: ምክንያቱም ከአምላክ ቀጥሎ ተስፋ የሚያደርገን እኛን ነው:: ምስጢሩን የሚነግረን ለእኛው ነው:: እናም እኛ የማንታመንለት ከሆነ ብዙ ነገርን ያጣል:: ህይወቱንም ሊሰዋ ይችላል:: እኛም ብንሆን ሁልጊዜ ተጠያቂ ነው የምንሆነው:: ስለዚህም “መርፌ ሲለግም—“ አይነት ሰዎች አንሁን ይላሉ::
ሌላው ስለ ህክምና ያነሱት መታመንን መሰረት አድርገው ነው:: መታመንን ራስን በየጊዜው ማከም ነው ይሉታል:: ለራስ ነጻነት እየሰጡና ለነገ ቅርስ እያስቀመጡ መሄድ፣ መልካም ሰዎችን መፍጠር፣ ሰዎችን መውደድ ነው ባይም ናቸው:: እናም ይህንን መሆን እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ:: እኔን አምኖ የመጣን ሰው ማክበሬን የማሳየው የእውነት ከልቤ ጊዜ ሰጥቼ ስሰማውና ህመሙን አግኝቼ ፈውስን ስሰጠው ነውና ሁላችንም ይህንን መርሀችን እናድርግም መልዕክታቸው ነው::
ህክምና መማር ብቻ ሙሉ አያደርገውም:: ማዳመጥ፣ የእግዚአብሔርንም ሆነ የህክምናውን ህግ ማክበር ካልተጨመረበት ፈውስ አይሰጥም:: ይህ ካልሆነ ደግሞ ሙያው አሳሳች፣ ገንዘብ ብቻ ማግበስበስ የሚቻልበት ስለሆነ አቅጣጫችንን ይዘውረዋል:: በሰው ስቃይ የምንደሰትም ያደርገናል:: ምክንያቱም አላማችን ሰው ሳይሆን ገንዘብ ይሆናል:: እናም ገንዘቡ የትም ሊያደርሰን አይችልምና ለእምነታችን ሥንል የምንሰራበት ሊሆን ይገባል እምነታቸው ነው::
ለሚያምነን ከታመንን ሥራችንን በእውነታው አለም እየተገበርነው እንደሆነ ማሰብ አለብን የሚሉት ዶክተር መሳፍንት፤ ሰውን ምንም መስፈርት ሳያደርጉ ማገልገል ነጻነት፣ ረፍት፣ ደስታና ፍቅርን ያስገኛል:: ቤትንም በበረከት ይሞላል:: ስለዚህም ከእኔ ቢወሰድ የምለው በህክምና ሰዎች ክፍያቸውን ሳይሆን ፈውሳቸውን እንዲያስቡ ማድረግን ነው:: ክሊኒኩ ልሂድና ይጥረጉኝ እንዲባልበት ማድረግ አያስፈልግም:: መጠነኛ ክፍያ ለሚመጥነው ሥራ መሆን አለበት:: ምክንያቱም እኛ አገልጋዮች ነን:: እነርሱ ከሌሉ እኛም አንኖርም:: ስለሆነም ይህንን እያሰቡ ቢሰሩ ይላሉ::
አስበው የሚመጡት እንደሚፈወሱ ሳይሆን ስንት እንደሚከፍሉ ስለሆነ እኛ የተሰጠንን ሀላፊነት በመጠቀም ይህንን ችግራቸውን ልንጋራቸው ይገባል:: አመስጋኝና የከፈለውን የማያስታውስ እንጂ አማራሪ ታካሚ መፍጠርም የለብንም:: ይህንን ስናደርግም ነው አክመናል፣ ዶክተሮች ነን ማለት ያለብንም ባይም ናቸው:: ቀጥለውም አንድ ሰው በአለው ልክ ከፍሎ ማከም ብዙ ህክምና ሳያስፈልጋቸው ሙሉ ምርመራ ለማድረግ የሚመጡ ሀብታሞችን ያገናኛል:: በአንዱ ያጣነውን በሌላው አምላክ ይከፍላል:: እናም ይህንን አምኖ መስራት ለሙያው ክብር መስጠት ነውና ሰዎች ይህንን ቢያደርጉ ሃሳባቸው ነው::
አበርክቶ
ቅድስተማሪያም አካባቢ ላሉና በመረዳጃ እድር እገዛ የሚደረግላቸውን ህጻናት፣ አረጋውያንና አቅመ ደካሞች የህክምና ሙሉ ወጪ ይሸፍናሉ:: በአካባቢያቸው በቀበሌ ደረጃ የተሰጣቸውን ልጆችም ሙሉ ወጪ ሸፍነው ያስተምራሉም:: በክሊካቸው ስም ላይፍ አዲስ የስፖርት ቡድን አቋቁመው ይሰራሉም:: በተጨማሪ ክሊኒካቸውም ቢሆን ለካርድ ብቻ ከፍሎ የሚታከም አይጠፋም:: ከሁሉ በላይ ከደቡብ አፍሪካውያን ጋር በጥምረት የሚሰሯቸው በርካታ ስራዎች በመኖራቸው ነጻ ህክምና ኢትዮጵያን እንዲያገኙ ከጤና ጥበቃ ጋር በመሆን በርከት ያሉ ሥራዎችን ሰርተዋል:: አሁንም እየሰሩ ይገኛሉ::
የህይወት ፍልስፍና
በምድር ላይ ተወለደ፣ አደገ ፣ ሞተ መባልን በፍጹም አይፈልጉም:: ልዩ የሚያደርጋቸውን መትከል ህልማቸውም ሥራቸውም እንዲሆን ይፈልጋሉ:: ለዚህ ደግሞ የተፈጠርኩት ኢትዮጵያ ላይ በመሆኑ ምክንያት አለኝ ብለው ያስባሉ:: በዚህም ለኢትዮጵያ መሆንና ማድረግ ግዴታ እንጂ ውዴታቸው እንዳልሆነ ያምናሉ:: ሌላው ለህክምና የተሰጡ እንደሆኑ ያስባሉ:: ስለዚህም ለዚህ ክብር ያበቃቸው የአገራቸው ህዝብ በመሆኑ እርሱን ማገልገል፣ መኖርን ያስባሉ:: በዚህም ሲሰሩም ቤተሰቤ ቢሆን ብለው ነው::
ቀጣይ እቅድ
ህክምና ከተማ ላይ ተሰርቶ ለውጥ የሚመጣበት ሥራ አይደለም:: ምክንያቱም ታች ያለው ማህበረሰብ ካልተፈወሰ አገልግሎታችንን ውስን ያደርገዋል:: የበሽታዎች ደረጃም ቢሆን የማይፈታና አደገኛ ሊያደርገው ይችላል:: ይህ ደግሞ መንግስትን ጭምር በገንዘብ የማይመልሰው አዘቅት ውስጥ ሊከተው ይችላል:: እናም እንደ ግለሰብ ብቻ ሳይሆን እንደመንግስትም ገጠሩን ክፍል ማየት ያስፈልጋል ይላሉ:: በዚህም እርሳቸውም በክሊኒክ ብቻ ሳይሆን በላብራቶሪ ጭምር ገጠራማው ክፍል ለመድረስ የመስራት እቅድ እንዳላቸው አጫውተውናል::
መንግስት አሰራሩን ከከፈተው ራሳቸውም ቢሆኑ ወርደው መስራትን እንደሚሹ አውግተውናል:: ይህንን ለማድረግ ብዙ የተዘጋጁ አካላት መኖራቸውንም በመጠቆም:: ሌላው ሊሰሩ ያሰቡት አሳዳጊ አልባ ልጆች ላይ ሲሆን፤ እነርሱን ማሳደግና ለቁምነገር ማብቃት ነው:: ሰዎች ከሰዎች ሳይሆን ከእግዚአብሔር የሚገኘውን በረከት አስበው የሚሰሩ ከሆነ ችግረኞችን ማገዝ የበለጠ ያተርፋቸዋል ብለው ስለሚያምኑም ይንን ማድረግ የቀጣይ ሀሳባቸው ነው::
መልዕክት
የህክምና ሙያ ከሚፈቅደው ውጪ ገንዘብ ለመሰብሰብ በማሰብ አላስፈላጊ የላብራቶሪ ምርመራ የሚያዙ አካላት ካሉ በተሳሳተ መንገድ ላይ ያሉ ባለሙያዎች ከዚህ ስህተታቸው ቢመለሱ:: ነገ የህሊና እስረኛ ላለመሆንም ህግና ሙያችንን እናክብር የመጀመሪያ መልዕክታቸው ነው::
ሌላው መልዕክታቸው የበሽታው መለያየትና መደራረብ ኢትዮጵያን እያስጨነቀ መሆኑ ሲሆን፤ ድሮ የእኛ በሽታዎች አይደሉም የሚባሉት ዛሬ የእኛ ሆነዋል፤ ተላላፊውም ሆነ የማይተላለፈው በሽታም ቅርባችን ከሆነ ሰንብቷል:: ለዚህ ደግሞ ዋና መንስኤው ህግንና ሥርዓትን ተከትሎ አለመስራት ነው:: እናም አሁን እንንቃና ከህክምና ባለሙያው እስከ መንግስት መዋቅር ድረስ በህግ እንስራ:: አሰራሮችም ይስተካከሉ:: በተለይ ሀኪሙ ሰውን ትቶ ገንዘብ ከማሰብ፤ ባለሀብቱም እንዲሁ ከማድረግና መንግስትም ቢሮክራሲ ከማብዛትና ከከተማ ተኮር ሥራ ይላቀቅ መልዕክታቸው ነው::
በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያነሱት ደግሞ ሁሉም በፖለቲከኛ ጎራ ተሰልፎና አሰልፎ መልካም ሰዎችን አይቅበር የሚለውን ነው:: ነገን ተስፋ አድርጎ የማይኖር ትውልድ እየፈጠሩ አገርን ወደፊት ማስኬድ አይቻልም:: እናም ወደፊት እንጂ ወደኋላ መሄድ ትርፋማ አያደርገንምና ያለፈውን ዓመት ለመማር እንጂ ለመኖር አንረባረብ:: ምክንያቱም ወደኋላ ማየት እንደ ሎጥ ሚስት የጨው ሀውልት መሆን ነው:: ተስፋንም ማጨለም ነው:: ያለቀ ነገር ውስጥ መግባት ለመጣላት የሚያበቃ ልዩነትን ማስፋትም ነው:: ስለሆነም አሁን እያጣላን ያለው ያለፈውን በመኖራችን እንጂ ልዩነታችን ገዝፎ ስላልሆነ ይህንን እናርመውም ይላሉ::
የሚያፋቅሩን ብዙ ነገሮች አሉን:: እነሱን ማብዛት፤ አስተማሪዎቻችንን ከንግግራቸውና ከተግባራቸው እያዩ መቀነስ ያስፈልገናል:: ሰው በአዕምሮው እንጂ በከርሱ ማሰቡን አቁሞ ወገኖቻችንን ማሰብና በእነርሱ ጎዳና መጓዝ ይገባናል:: ለዚህ ደግሞ ወደፊት እንመራችኋለን የሚሉ አካላት፤ ተው የሚሉ አባቶች ያስፈልጉናልና ፍርሀታቸውን ትተው ወደፊት ይምጡ:: ለህዝባችን ፣ ለሀገራችን ፣ ለሙያችን መልካሙን ብቻ እናድርግ ሲሉም ምክራቸውን ይቋጫሉ:: ሰላም!
አዲስ ዘመን ሚያዚያ 10/2013