በአስመረት ብስራት
የሰው ልጆች ፈተና በበዛበት በዚህ ወቅት ስለ አለማችን አሳሳቢው በሽታ የሆነው ኤች አይ.ቪ ኤድስ እየተረሳ መጥቷል። በሽታው አሁንም አፍላ ወጣቶችን እያሳጣን ባለበት በዚህ ወቅት ስለበሽታው ማንሳት ተገቢ ነው ብለን ስላመንን በኤች አይ ቪ ላይ የሚሰሩ አንድ ባለሙያ አናግረናል።
ብሩክታዊት ታዲዎስ ለኤች አይ ቪ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የነፃ ኤች አይ ቪ ምርመራና ህክምና አገልግሎት የሚሰጥ ሀገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅት ውስጥ አማካሪ ሆና የምትሰራ የማህበረሰብ ጤና ባለሙያ ናት።
ኤች አይ ቪ ኤድስ ዕድሜ፡ የቆዳ ቀለም፡ ባህልና ልማድ ወይም ሐይማኖት ሳይመርጥ ማንንም ሊይዝ ይችላል። በአለም ከሠላሳ አራት (34) ሚሊዮን ህዝብ በላይ በኤች አይ ቪ ኤድስ እንደተያዘ ይታመናል። በወንድና በሴት የሚደረገው የግብረ ሥጋ ግንኙነት አንደኛቸዉ ቫይረሱ ካለባቸዉ ኤች አይ ቪ ኤድስን ለማስተላለፍ የተለመደ መንገድ ነው ትለናለች።
ኤች አይ ቪ እና ኤድስ ብዙ ጊዜ እንደ አንድ ቃልና አንድ ትርጉም ሲጻፍና ሲነገር ቆይቷል፣ ነገር ግን ኤች አይ ቪ እና ኤድስ የተለያየ ትርጉም አላቸው። ኤች አይ ቪ የፊደሉ ትርጉም (Human Immune-deficiency Virus) ማለት ሲሆን የሰው ሕመምን ተከላካይ የአካል ክፍልን አጥቂ በሽታ ማለት ነው። ይህ በሽታ (ቫይረስ) የሚያጠቃው በሽታ ተከላካይ የሆነውን የአካል ክፍልን ነው፣ አንድ ሰው በኤች አይ ቪ ተመረዘ ወይም ኤች አይ ቪ ያዘው የምንለው በደሙ ውስጥ ገብቶ መሰራጭት ሲጀምር ነው።
ኤች አይ ቪ የሕመም ተከላካይ የሰውነት ክፍልን ያጠቃል፣ መከላከያ ካልወሰዱበት ኤች አይ ቪ የበሽታ ተከላካይ የሰውነት ክፍልን በመጉዳት ወደፊት ምንም ዓይነት በሽታ ሰውየው ቢይዘው መከላከል እንዳይችል ያዳክመዋል፣ ስለዚህም ሰውየው በትልቅ አደጋና በሽታ ላይ ይወድቃል፣ ሊሞትም ይችላል። እንግዲህ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ኤድስ/AIDS (Acquired Immune Deficiency Syndrome) በመባል ይታወቃል።
አንድ ሰው ኤች አይ ቪ አለበት ማለት ኤድስ ይዞታል ወይም ይሞታል ማለት አይደለም፣ ያለ መከላከያ እንኳን ቢሆን ብዙ ሰዎች ኤች አይ ቪ ይዟቸው ለብዙ ዘመናት ሊኖሩ ይችላሉ፣ በተጨማሪ ግን መከላከያ መድኃኒት ተዘጋጅቷል። በሽታው ተከላካይ የሰውነት ክፍልን ጎድቶ ወደ ኤድስ እንዳይቀየር የበሽታውን ኃይል አዳክሞ እንዲዘገይ (ቀስ እንዲል) ያደርገዋል። ብዙ ሰዎች ኤች አይ ቪ እያለባቸው በሕክምና በጤንነት ኑሯቸውን በመምራትና ያሰቡትን ግብ መተው በሥራና በኑሮ ሕይወታቸውን አሟልተው ይኖራሉ። ብሩክታዊት የምትሰራበት ሀገር በቀል ግብረ ሰናይ ደርጅትም ሰው ራሱን አውቆ የተረጋጋ ሀይወት እንዲኖር የሚሰራ መሆኑን ትናገራለች።
ኤች አይ ቪ ሊተላለፍ የሚችለው የግብረ ሥጋ ግንኙነት ያለኮንዶም ሲደረግ፤ መርፌ ስሪንጅና ሌላ የሕክምና መውጊያ መሣሪያዎችን በጋራ በመጠቀም፤ በደንብ ባልጸዱና አዲስ ባልሆኑ የመነቀሻና ሰውነትን መብሻ መሣሪያዎች በመጠቀም፣ ከእናት ወደ ልጅ በእርግዝና ጊዜና በመውለድ እንዲሁም ከተወለደ በኋላ ጡትን በማጥባት፣ ደም በመቀበልና በመውሰድ ሂደት ውስጥ ሊያጋጥም ይችላል።
በሽታው በማሳል፣ በመሳሳም፣ በማስነጠስ፣ በመትፋት፣ በለቅሶ፣ መመገቢያ ቁሳቁሶችን በጋራ በመጠቀም፣ የመጠጫ ዕቃዎችንም በጋራ በመጠቀም፣ በጋራ አንሶላ በመጠቀም፣ ሽንት ቤትና የመታጠቢያ ቤቶችን በጋራ በመጠቀም፣ ከሰው ጋር ስለተቀራረቡ አይተላለፍም። ተናዳፊ ነፍሳት እንደ ቢንቢ ዓይነቱ ኤች አይ ቪ አያስተላልፉም።
ይሄን ካልን በኋላ በድርጅቱ በዋነኝነት አገልግሎት የሚሰጠው የወሲበ ንግድ ላይ ለተሰማሩ ሴቶች፤ ተገላጭ የሆኑ ወንዶች፤ እንዲሁም በጣም በአፍላ ወጣትነት እድሜ ላይ ያሉ ሴቶች ላይ ነው የምትለን ብሩክታዊት ለእነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች ነፃ የኤች አይ ቪ ምርመራና ህክምና አገልግሎት፤ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት፣ ኮንዶምን የማሰራጨት ስራ፤ በወሲብ ንግድ ላይ ለተሰማሩ ሴቶች ማቆያ ቦታ የሚሰጥ ግብረ ሰናይ ደርጅት መሆኑን ነው የምትናገረው።
እነዚህ ወደ ህክምና የሚገቡ ሰዎች ከምርመራ በፊትም ሆነ ከምርመራ በኋላ በሚሰራባቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ በበቂ ሁኔታ በአብዛኛው ተረጋግተው ህይወታቸውን ለመቀጠል የሚያስችላቸው ስነልቦናዊ ድጋፍ ይደረግላቸዋል። አንድ ሰው ተመርምሮ ራሱን ሳያውቅ ነፃ ወይም ከቫይረሱ በደሙ ውስጥ ያለመኖሩን ካወቀ በኋላ ራሱን በአግባቡ ጠብቆ ይኖራል። ቫይረሱ ደግሞ በደሙ ከተገኘ ራሱን አውቆ የአናኗር ዘዬውን ቀይሮ ጤነኛና የተረጋጋ ህይወት እንዲኖር ድጋፍ ይደረግለታል።
በተጨማሪም አንድ ሰው ቫይረሱ በደሙ ውስጥ መኖሩን አውቆ ፀረ ኤች አይ ቪ መድሃኒት በአግባቡ ከተጠቀመ የቫይረሱ መጠን ከሰድስት ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ በፍጥነት ስለሚቀንስ ለሌሎች የማስተላለፍ እድሉ 97 በመቶ ይቀንሳል። ስለዚህ ይህ ፕሮጀክት የኤች አይ ቪ ምርመራና ህክምና አገልግሎት በሰፊው በመስጠቱ ስርጭቱን ለመግታት የራሱን አስተዋፅኦ አድርጓል።
በኤች አይቪ ላይ መስራት በዋነኛነት ሶስት አበይት ተግባራት አሉት። የመጀመሪያው ሁሉም ሰው ራሱን እንዲያውቅ ማድረግ፣ ሁለተኛው ደግሞ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ያሉ የማህበረሰቡ አካላት ቫይረሱ ከፍተኛ የሆነ የጤና እክል ወይም የጎንዮሽ ችግር ከማስከተሉ በፊት መድሀኒት ማስጀመር ሲሆን ሶስተኛው ደግሞ መድሀኒቱን ከጀመሩ በኋላ የቫይረሱ መጠን ከስድስት ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ እንዲቀንስ ማድረግ መሆናቸውን ተናግራለች። ከዚህ በተጨማሪ ለማህበረሰቡ በበሽታው ዙሪያ የግንዛቤና የማህበረሰብን ንቃተ ህሊና የመጨመር ተግባራት እናከናውናለን።
በፕሮጀክቱ ተጠቃሚ የሚሆኑት ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰቡ ክፍሎች ላይ እንደመሆኑ ለሴተኛ አዳሪዎች የማረፊያ ቦታ አዘጋጅቶ ማንኛውም በዚህ ስራ የሚተዳደሩ ከጠዋት አስራ ሁለት ሰአት እስከ ማታ አስራ ሁለት ሰአት ድረስ ልብሳቸውን በማጠብ እርስ በእርስ በመመካከር እረፍት የሚያደርጉበት አገልገሎት ያገኛሉ።
ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ በአግባቡ መስራትም የስርጭቱን መጠን ለመቀነስ ከፍተኛ ጠቀሜታ ከመኖሩም በሻገር ሌላው ማህበረሰብ ጥንቃቄን የእለት ከእለት ኑሮው አካል በማድረግ ጤናውን መጠበቅ የሚኖርበት መሆኑን መክራለች።
አዲስ ዘመን መጋቢት 27/ 2013 ዓ.ም