አስናቀ
ህብረት ሥራ ማህበራት ሰዎች ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊና ሌሎች የጋራ ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት እና በተናጥል ሊፈቱ ያልቻሏቸውን ችግሮች በጋራ ለማቃለል የሚያስችሉ በመሆናቸው ተመሳሳይ ዓላማ ያላቸው ሰዎች በፈቃደኝነት የሚያቋቁሟቸው ፣ በጋራ ባለቤትነት የሚያስተዳድሯቸው፣ በኅብረት ሥራ መርህ መሠረት የሚመሯቸውና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የሚቆጣጠሯቸው ራሳቸውን የቻሉና ሕጋዊ ሰውነት ያላቸው እንደሆኑ የህብረት ስራ ማህበራትን በተመለከተ የወጣው አዋጅ ያመለክታል።
በኢትዮጵያም 22 ነጥብ 6 ሚሊዮን አባላት ያሏቸው 92 ሺ የህብረት ስራ ማህበራት እንዳሉና የማህበራቱ አጠቃላይ ካፒታልም 28 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር መድረሱን ከፌዴራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ የወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በእነዚሁ ህብረት ስራ ማህበራት ስር 1 ሺ 60 የሚሆኑ ኢንዱስትሪዎች እንደሚገኙና ከ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች በቀጥታና በተዘዋዋሪ የስራ እድል መፈጠሩን መረጃዎቹ ያሳያሉ።
የህብረት ሥራ ማህበራት ዩኒየኖችም ተመሣሣይ ዓላማ ባላቸው መሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማህበራት በኅብረት ሥራ አዋጅ በተወሰነው አነስተኛው የአባላት መነሻ ቁጥር መሠረት ከመሠረታዊ ኅብረት ሥራ ማህበራት በላይ የሆነ የማምረት፣ አገልግሎት የመስጠት ወይም ሁለቱንም የማከናወን ተግባር ያላቸው ሲሆን እስከ 2011 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ ቁጥራቸው 388 እንደደረሰ እነዚሁ መረጃዎች ያመለክታሉ።
የህብረት ስራ ማህበራት የአባላቶቻቸውን ፍላጎት ለማርካትና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የየራሳቸውን ስልት ነድፈው እየተንቀሳቀሱ ቢሆንም አንዳንዶች ግን ሙሉ አባላቶቻቸውን ከዳር ዳር በማነቃነቅ ከመንግስት ብድር ሳይጠይቁ ወደ ኢንቨስትመንትና የግብርና ምርቶችን አቀነባብረው ለገበያ የማቅረብ ሂደት ውስጥ ለመግባት ጥረት የሚያደርጉ አልጠፉም። ከነዚህ ውስጥም አንዱ በአማራ ክልል ምእራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ከተማ አስተዳደር ውስጥ የሚገኘው ዳሞት ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን ነው።
አቶ ጌታቸው እሸቱ የዳሞት ሁለገብ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን ስራ አስኪያጅ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት ዩኒየኑ ህዳር 21 ቀን 1993 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን በሁለት ወረዳዎችና በስድስት መሰረታዊ ማህበራት 185 ሺህ መነሻ ካፒታል ስራ ጀምሯል። በግዜው ዩኒየኑ እንቅስቃሴ የጀመረውም 8 ሺ የሚሆኑ አባል አርሶ አደሮችን ይዞና ሶስት ሰራተኞችን ቀጥሮ ነበር። የዩኒየኑ ምስረታ መነሻ ምክንያትም የአርሶ አደሮች የግብርና ግብአት እጥረትና የሸቀጣ ሸቀጥ እቃዎች ተደራሽ ያለመሆን ነበር።
እስካሁን ባለው የሃያ አመታት ጉዞውም ካፒታሉ ወደ 179 ሚሊዮን ብር ማድረስ ችሏል። በርካታ ውጣ ውረዶችንም አልፏል። ቀጥሮ የሚያሰራቸው ሰራተኞች ቁጥርም 114 ሰራተኞች ናቸው ። አገልግሎቶቹንም በሰባት የገጠር ወረዳዎችና በሶስት ከተማ አስተዳደሮች ውስጥ ይሰጣል። በውስጡም 79 የሚደርሱ መሰረታዊ ማህበራትንና በነዚሁ መሰረታዊ ማህበራት ውስጥ የታቀፉ 180 ሺ አባወራና እማወራዎችን ይዟል።
የስራ አድማሱንም ሲቋቋም ከነበረበት እየጨመረ በመሄድ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ለአባል አርሶ አደሮቹና ለሌላውም የአካባቢው ማህበረሰብ ተደራሽ ማድረግ ችሏል። አባላት ያመረቷቸውን ምርቶችንም ገበያ አፈላልጎ በሚፈለገው መጠንና የጥራት ደረጃ ለተጠቃሚው ያቀርባል። ምርትና ምርታማነትን ለመጨመርም የሜካናይዤሽን አገልግሎት ለአባል አርሶ አደሮች ይሰጣል። 12 የሚሆኑ ማረሻ ትራክተሮችና ሁለት ኮምባይነሮችም አሉት። በነዚህ ማሽኖችም ለአባል አርሶ አደሮች እህሎችን የማጨድና የመውቃት እንዲሁም የእርሻ መሬቶችን የማረስና የመከስከስ አገልግሎቶችን ያከናውናል።
እንደ ስራ አስኪያጁ ገለፃ ይህንኑ የሜካናይዜሽን ዘርፍ አገልግሎት ለማሳደግ ዩኒየኑ በቡሬ ከተማ የሜካናይዜሽን ማእከል ግንባታ ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ጋር በመሆን እያከናወነ ይገኛል። የማእከሉ ግንባታ አርባ ከመቶ የደረሰ ሲሆን ግንባታው ሲጠናቀቅ የማሽን ኦፕሬተሮችን የማሰልጠን፣ ማሽኖችን የመጠገንና የማሽን መለዋወጫዎችን ለአካባቢው ማህበረሰብ የማቅረብ ስራዎችን እንደሚያከናውን ይጠበቃል። በአጠቃላይ ግንባታው 12 ሚሊዮን ብር ይፈጃል።
በሌላ በኩል ደግሞ በዛው በቡሬ ከተማ በሚገኘው የአንድ ማእከል አገልግሎት መስጫ ማእከሉ አነስተኛ የእርሻ መሳሪያዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለአባል አርሶ አደሮችና ለአካባቢው ማህበረሰብ ይሸጣል። ኬሚካሎችን፣ የአትክልትና የደን ዘሮችን፣ የድህረ ምርት ማሸጊያ ከረጢቶችንና የእንስሳት መድሃኒቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለአባላቱና ለአካባቢው ማህበረሰብ ያቀርባል። በ2005 ዓ.ም በ 9 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ያተቋቋመው የስንዴ ዱቄት ፋብሪካም በቀን 420 ኩንታል የመፍጨት አቅም ያለው ሲሆን ስንዴውን ሙሉ በሙሉ ከአባል አርሶ አደሮች ይረከባል። በአካባቢው በአነስተኛና ጥቃቅን ተደራጅተው ዳቦ በመጋገርና በመሸጥ ለሚተዳደሩ ሰዎች የዱቄት ግብአት በማቅረብም የበኩሉን አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል።
ዩኒየኑ የትምህርትና ስልጠና አገልግሎት ለአባላቱ የሚሰጥ ሲሆን ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ አንፃር ግንዛቤና እውቀት እንዲኖራቸው አግዟል። በተያያዥነትም በዩኒየኑ ስር ያሉ ማህበራትና ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን አስችሏል።
ከዚህ በዘለለ ዩኒየኑ በየአመቱ ከሚያገኘው ትርፍ የማህበራዊ አገልግሎቶችንም ለአካባቢው ማህበረሰብ ይሰጣል። እስካሁን ባለው ሂደትም በ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ደጋ ዳሞት ላይ አንድ ብሎክ ትምህርት ቤት ገንብቶ አስረክቧል። በተመሳሳይ በደምበጫ ወረዳ 452 ሺ ብር ወጪ አድርጎ የእንስሳት ጤና ኬላ ገንብቷል። በቡሬ ከተማም ዙሪያ ግንባታው እየተከናወነ ለሚገኝ አንድ ትምህርት ቤትም የ300 ሺ ብር ድጋፍ ሰጥቷል። በዛው ቡሬ ከተማ ለሚገኝና እድገት በህብረት ለሚባል ትምህርት ቤትም 70 የተማሪዎች መቀመጫ ወንበሮችን አሰርቶ አስረክቧል። በዚህም ዩኒየኑ ለማህበራዊ አገልግሎት ዘርፍ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ጎልቷል።
ስራ አስኪያጁ እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት ዩኒየኑ ወደኢንቨስትመንትና አግሮ ፕሮሰሲንግ ስራዎች ውስጥ ለመግባት በቡሬ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ውስጥ ገብቶ የበቆሎ ምርትን ለማቀነባበር የ 450 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ቀርፆ ለክልሉ ኢንቨስትመንት ቢሮ ገቢ አድርጎ ምላሽ እየተጠባበቀ ይገኛል። ለፕሮጀክቱም የአዋጭነት ጥናት ተጠንቶና በሞያተኞች ተገምግሞ የቅድመ ዝግጅትና የገንዘብ ማሳባሰብ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። ለዚህም አብዛኞቹ አባል አርሶ አደሮች እጣ ገዝተው ማቀነባበሪያውን እንዲገነቡ ጥረት እየተደረገ ነው። ዩኒየኑ በቆሎን ወደማቀነባበር ስራው ሲገባም 50 ከመቶ ያህሉን የበቆሎ ዱቄት፣ 25 ከመቶውን ቅንጬ እንዲሁም ቀሪው 25 ከመቶውን ለውጪ ገበያ የሚሆን ስታርች የማምረት እቅድም ይዟል።
በአነስተኛ ዋጋና በስፋት በተለይ ደግሞ በአራት ወረዳዎች ላይ የሜካናይዜሽን አገልግሎቶችን ለአባላቱና ለአካባቢው ማህበረሰብ መስጠቱና ሌሎች ዩኒየኖች ካሏቸው ተለምዷዊ አሰራር በመውጣት ወደ ኢንቨስትመንትና አግሮ ፕሮሰሲንግ ስራዎች በመግባት የአርሶ አደሩ ምርት በጥሬው ከሚልክ ይልቅ እሴት ታክሎበት ለገበያ እንዲቀርብ በሂደት ውስጥ ያለ መሆኑ ዩኒየኑን ከሌሎች መሰል ዩኒየኖች ልዩ ያደርገዋል።
ከመንግስት ብድር ሙሉ በሙሉ ነፃ ሆኖና በአባል አርሶ አደሮች ተሳትፎ ብቻ የበቆሎ ማቀነባበሪያውን ለመገንባት መነሳቱም ከሌሎች ዩኒየኖች እንዲለይ አድርጎታል። ለዚሁ ግንባታም እስከመጪው መስከረም ወር ድረስ ከአባል አርሶ አደሮች 123 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ቃል ገብተዋል። ለዚሁ ስራ በቅርቡ በተዘጋጀ መድረክም ከተሳታፊ አባል አርሶ አደሮች 336 ሺ ብር ለመሰብሰብ ተችሏል።
በወቅታዊነት ዩኒየኑ አሉብኝ ከሚላቸው ችግሮች ውስጥ አንዱ ከመሬት አቅርቦት ጋር የተያያዘ ሲሆን በህብረት ስራ አዋጅ መሰረት የክልሉ ህብረት ስራ ኤጀንሲ አዋጅ 220/2007 ማህበራትና ዩኒየኖች መሬት በሚፈልጉበት ግዜ አዋጭነቱ ታይቶ በሊዝ መነሻ ዋጋ እንዲሰጣቸው ያዛል። ይሁን እንጂ በየአካባቢው ያሉ አስተዳደሮች ይህን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት መሬቱን ፈጥኖ በመስጠት ረገድ ውስንነቶች ይታያሉ። ከዚህ አኳያም ዩኒየኑ አዋጁን የማስረዳትና በአዋጁ መሰረት መሬት እንዲቀርብ የማድረግ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል። በአዋጆቹ ዙሪያ የበለጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችም ተጠናክረው ይቀጥላሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ወደ ኢንቨስትመንት ስራዎች ውስጥ አይገቡም የሚል አስተሳሰብ ያላቸው በመሆኑ ዩኒየኑ በተለይ ከዚሁ ጋር የተገናኙ ጉዳዮችን ለማስፈፅም ሲሄድ የሚገጥሙት ችግሮች ናቸው። ከዚህ አንፃር ችግሩ በትግል የሚፈታ በመሆኑና ከግንዛቤ ጋር በተያያዘ የሚነሳ በመሆኑ ዩኒየኑ ስራዎችን በተግባር ሰርቶ እያሳየ ወደፊት የሚሄድበት እድል ይኖራል።
ዩኒየኑ በቀጣይም የጀመራቸውን የግብርና ምርቶች ወደ ውጪ ሀገር የመላክ ስራዎች የማጠናከርና የማስፋት አቅድ አለው። የግብርና ማሽነሪዎችን ቁጥር በመጨመር ምርቱን የማስፋት ውጥንም ይዟል። ወደውጪ ሀገራት በሚልካቸው የግብርና ምርቶች ከሚገኘው ገቢም ለመንግስት ተገቢውን የውጭ ምንዛሬ የማስገኘት ፍላጎትም አለው።
ዩኒየኑ አባላቱንና የአካባቢውን ማህበረሰብ በማሰልጠን የሜካናይዜሽን ስራዎችን የማሳደግ ብሎም በግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት መስጫ ማእከሉ አማካኝነት ከሌሎች ተቋማት ጋር የጋራ ጥምረት በመፍጠር የመገጣጠሚያ ፋብሪካ ለማቋቋም እቅድ አለው።
በሃያ አመታት ቆይታው ዩኒየኑ ለዚህ ውጤት ሊበቃ የቻለውም የህብረት ስራ ትክክለኛ አዋጆችን፣ መመሪያዎችንና ደንቦችን በአባላቱ ውስጥ በማስረፅና እነርሱን ይዞ መጓዝ በመቻሉ ነው። የህብረት ስራ እሴቶችን በተከተለ መልኩና አባላቱን ባሳተፈ ሁኔታ ስራዎችን መስራቱ ብሎም እነዚሁ እሴቶች በአባላት ውስጥ እንዲሰርፁ ማድረጉም ለዩኒየኑ ውጤት የራሱን አስተዋፅኦ አበርክቷል።
ህብረት ስራ ማህበራት በትክክል ከተተገበሩ የድህነት መውጪያ መንገዶች ከመሆናቸው አኳያም አባል ያልሆነ መላው አርሶ አደር በህብረት ስራ ማህበር አባልነት ውስጥ ገብቶ የራሱን አስተዋፅኦ የሚያበረክትበትን እድል መጠቀም እንደሚኖርበት ዩኒየኑ ይመክራል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 25 ቀን 2013 ዓ.ም