በቁምላቸው አበበ ይማም(ሞሼ ዳያን)
ክፍል አንድ
ጌታቸው አሰፋን ባሰብሁ ቁጥር፤ የስድስት ሚሊዮን አይሁዶችን ጭፍጨፋ በፊት አውራሪነት የመራው፣ ያቀነባበረው በጭካኔው፣ በአውሬነቱ ወደር ያልተገኘለትን “የሞት መልዓክ Angel of Death” የሚል ቅፅል የተሰጠውን ዶ/ር ጆሴፍ ሚንጌልን ያስታውሰኛል። አረመኔው ጌታቸው በ21ኛው መ/ክ/ዘ ይሄን ሁሉ ለመስማት የሚዘገንን ግፍ የፈፀመ፤ እንደ ሒትለሩ ዶ/ር ጆሴፍ በዚያ ዘመን ሥልጣን ቢኖረው ከእሱ የባሰ እጅግ እጅግ ዘግናኝ ግፍ ይፈፅም እንደነበር ቅንጣት ታክል አልጠራጠርም። በጌታቸው አሰፋ አጋፋሪነት ለ20 የሰቆቃና የግፍ ዓመታት በወገኖቻችን ላይ የተፈፀመ ዘግናኝ ግፍ፣ ስቃይ ስናሰላስል የሰው ፍጡር መሆኑን እስከ መጠራጠር እደርሳለሁ።
ለ17 ዓመታት የደህንነት ዋና ዳይሬክተር፤ ላለፉት ሦስት ዓመታት ደግሞ ፖለቲካዊ ሥልጣንንም ደርቦ መጀመሪያ በከሀዲው የትህነግ የመማጸኛ ከተማ መቐሌ በኋላ ደግሞ ሞተ እስከተባለበት ጊዜ ዋሻ ለዋሻ እየተሽሎከለከ ብሔርንና ማንነትን ኢላማ ያደረጉ ጭፍጨፋዎችንና ግጭቶችን ለተላላኪዎቹ ሸኔ _ ኦነግ ፣ ለአንዳንድ የ«ቅማንት ማንነት» አስመላሾችና ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ አረመኔዎች ስምሪት እየሰጠና እስፓንሰር እያደረገ ሲያስፈጽም፤ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትርን የግድያ ሙከራ ጨምሮ እንደ አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ያሉ ታዋቂ ሰዎችንና የፖለቲካ መሪዎችን በማስገደል ሀገሪቱን ወደ ማያባራ የብሔርና የማንነት ግጭት ለመዝፈቅ ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም።
ታሪክና ትውልድ ይቅር የማይለውን የሰሜን ዕዝ ክህደትና ጭፍጨፋም ሆነ የጦር መሣሪያ ዘረፋ በፊትአውራሪነት ያቀደና የመራ ከመሆኑ ባሻገር በ72 ሰዓታት ውስጥ አዲስ አበባን ከመቆጣጠርና በኤርትራም መንግሥቱን በኃይል ገልብጦ እንዳሻው የሚዘውረው አሻንጉሊት ከማስቀመጡ የቀን ቅዠት ጀርባ የሞት መልዓኩ ጌታቸው አሰፋ አለ። የቀን ቅዠቱ እፉኝቱን ትህነግ በሬሳ ላይ ተረማምዶ አራት ኪሎ መመለስ ነበር። በዘረፈው ከባድ መሣሪያ ወደ ባህርዳር፣ ጎንደርና አስመራ ሮኬት በመተኮስ ሽብር ከመፈጸሙ በላይ ከ1000 በላይ የማይካድራ ንጹሐን አማራዎች ሳምሬ በተባለ የትህነግ ገዳይ ክንፉ አስጨፍጭፏል። ይሄ የስቃይ መልዓክ Angel of Torture የእፉኝቱ ትህነግ የጭካኔ ጥግ ወካይም ነው። የቀድሞ የትግል ጓዶቹና ሰለባዎቹ ይህን በላኤ ሰብዕነቱንና ሴረኛነቱን ያልዩነት ይስማሙበታል።
የቀድሞ የትግል አጋሩ አይታ
ገብረመድህን አርአያ በአንድ ወቅት ከ «ኢትዮጲስ» ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ስለ ኢትዮጵያዊው ዶ/ር ጆሴፍ ጌታቸው አሰፋ ተጠይቀው «…ጌታቸው ስለ ፈፀመው ግፍና ያጠፋው የንፁሀን ነፍስ ላይ በግልፅ ጥናት ቢደረግ፤ …ከሂትለር ባለሟሎች ተርታ የሚሰለፍ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ከፍየል ውሃ ሁለት ገበሬዎችን አፍኖ ወደ ሀዋላ ወያኔ አስገባቸዋለሁ ብሎ መንገድ ላይ ገድሎ ጥሏቸው አስከሬናቸው በጅብ ተበልቶ የራስ ቅላቸው ወድቆ ተገኝቷል፡፡
የጌታቸው አሰፋ ደስታ የሚመነጨው ከሰው ልጆች ስቃይና መከራ ነው። በጭካኔያዊ ድርጊት የሚደሰት SADIST ነው፡፡ ከቀድሞው የወያኔ የደህንነት ኃላፊ ጋር በመሆን ብዙ ሰላማዊ ሰዎችን የጨረሰ ወንጀለኛ ነው። ከመነሻው አንስቶ እጁ በንፁሀን ደም የተጨማለቀ ነው፡፡ የህወሓት መሪዎች በትግራይ ሕዝብ መካከል የበቀሉ አረሞች እንጂ ከትግራይ ሕዝብ አብራክ የወጡ አይደለም፡፡ ህወሓት ፀረ ኢትዮጵያዊ ብቻ ሳይሆን፤ ፀረ ትግራይም ነው ፡፡…» ይላሉ።
በአወዛጋቢ ሀሳቦቹ፣ በድፍረቱ፣ በአርበኝነቱና አንዳንድ ጊዜም በአፍ ወለምታው የምናውቀው መምህርና ተሟጋች ስዩም ተሾመ ከሁለት ዓመታት በፊት በኢትዮዊኪሊክስ ድረ ገጽ እንዳስነበበን፤ አንድም ሰው ጭራቅን በአካል አይቶት አያውቅም፡፡ ነገር ግን ሁሉም ሰው «ጭራቅ» የሚለውን ስም ያውቀዋል፡፡ «ጭራቅ የለም» እንዳይባል መጠሪያ ስም አለው፡፡ ነገር ግን «ጭራቅ» የሚባል ነገር በእውኑ ዓለም ታይቶ አያውቅም። ስለዚህ ጭራቅ «አለ» እንዳይባል አይታይም፣ «የለም» እንዳይባል ከምናብ አይጠፋም፡፡ ጭራቅ የሚባል ነገር በእውኑ ዓለም እንደሌለ ከታወቀ የጭራቅ አስፈሪ ምናባዊ ምስልና ሃሳብ ህልው አይሆንም።
በደምሳሳው ጭራቅ እንዲፈራ በእውኑ ዓለም መኖሩንም ሆነ አለመኖሩን በተጨባጭ ማወቅ ግድ አይልም፡፡ ምክንያቱም መኖሩም ሆነ አለመኖሩ ታወቀ አልታወቀ መፈራቱን አያስቀረውም፡፡ የአቶ ጌታቸው አሰፋ መሠረታዊ ዓላማ ልክ እንደ ጭራቅ መሆን ነው፤ «ጌታቸው አሰፋ» የሚባል ሰው «የለም» እንዳይሉት በሀገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣን ነው፡፡ ሰውዬው «አለ» እንዳይሉት ደግሞ ከተባራሪ የፎቶ ምስሎች በዘለለ በአካል ታይቶ አያውቅም ፡፡ የሀገሪቱ የደህንነት መስሪያ ቤት ኃላፊ በነበረበት ወቅት ልክ እንደ ጭራቅ በዜጎች ላይ አስፈሪና ዘግናኝ ተግባራት እንዲፈፀሙ አድርጓል፡፡
ልክ እንደ ሰብዓዊ ፍጡር ደግሞ ትዳር፣ ልጆች፣ ወዳጅ-ዘመድ አለው። ኀዘንና ደስታውን ይጋሩታል እንዳይባል ደግሞ በወንድሙ ሞት ኀዘናቸውን የገለፁ ሰዎችን ያስፈራራል፡፡ በዚህ ረገድ የዓረና ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አብረሃ ደስታ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በፌስቡክ ገፁ ላይ ያወጣውን ጽሑፍ እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል። በዶ/ር ደረጀ አሰፋ (የአቶ ጌታቸው አሰፋ ወንድም) ድንገተኛ ሞት የተሰማኝን ኀዘን በገለፅኩ ጊዜ «የጌታቸው አሰፋ ስም ጠቅሰሃል» በሚል ምክንያት በቀድሞ ተላላኪዎች በስልክም በፅሑፍም ዛቻና ማስፈራሪያ ደርሶብኛል ማለቱን በማስታወስ ሰውዬው አይጨበጤና አወዛጋቢ ተክለ ሰብዕና እንዳለው ይነግረናል። የጭካኔ ጥጉ ወደ ጭራቅነት ከፍ ያለመሆኑን ያሳየናል።
አቶ ጌታቸው አሰፋ ላለፉት 17 ዓመታት የደህንነት መስሪያ ቤት ኃላፊ ሆኖ ሳለ ልክ እንደ ጭራቅ ከሕዝብ እይታ ተሰውሮ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት እንዲፈፀም ያደረገው ሳያንስ ህወሓት አላግባብ ይዞት የነበረው የማዕከላዊ መንግሥት ሥልጣኑ ሲቀነስ ወደ መቐሌ ሸሽቶ የፖለቲካ ሥልጣን እንዲይዝ ተደርጓል፡፡ ስለዚህ ከላይ በተገለፀው መሠረት፣ «እንደ እኛ ሰው ነው» እንዳይባል ሰብዓዊ ባህሪ የለውም። ወይም ደግሞ «እንደ ጭራቅ ምናባዊ ፍጡር ነው» እንዳይባል የህወሓት/ኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ነው። ይህ የማናውቀው ፍጡር በሀገርና ሕዝብ ጉዳይ ላይ የመወሰን ሥልጣን ተሰጥቶታል። በዚህ በሰለጠነ ዘመን እንደ ሰው ለሕዝብ ታይቶ የማያውቅ እንደ ጭራቅ አስፈሪ የሆኑ ተግባራት በዜጎች ላይ እንዲፈፀሙ አሊያም በራሱ የፈፀመ ዜጎች እንደ ሰው የማያውቁት ነገር ግን እንደ ጭራቅ የሚፈሩት ምንነቱና ማንነቱ የማይታወቅ «ነገር» የገዢው ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ነው ማለት ምንድን ነው? በየትኛውም ሀገር የመረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት ሹም በሚመራው መስሪያ ቤት ሥራና አሰራር ጉዳይ ላይ ለሚዲያ ቀርቦ ይፋዊ መግለጫና ማብራሪያ ይሰጣል። አቶ ጌታቸው አሰፋ የደህንነት መስሪያ ቤት ኃላፊ እያለ አንድም ጊዜ ይህን አላደረገም፡፡ ይህ ሳያንስ አሁን ደግሞ የገዢው ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
አቶ ጌታቸው አሰፋ እንደ አንድ ፖለቲከኛ በክልል ሆነ በፌዴራል ደረጃ ባሉ ጉዳዮች ላይ ይፋዊ ማብራሪያ ሆነ መግለጫ ሰጥቶ አያውቅም ፡፡ ሌላው ቀርቶ ሰው ይሁን ጭራቅ በእርግጠኝነት የሚናገር ሰው የለም፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ «አቶ ጌታቸው አሰፋ»፤ እንደ ሰው ሰብዓዊ ፍጡር ይሁን እንደ ጭራቅ ምናባዊ ፍጡር የመጠየቅና የማወቅ መብት አለው፡፡ ይህ ጥያቄ ሳይመለስ በልብ ህመም ሕይወቱ ማለፉን በይፋ ባይሆንም እየሰማን ነው። ለዚህ ነው መሞቱ በይፋ በመንግሥት ስላልተረጋገጠ በዚህ መጣጥፍ ርዕስ ላይ እስከ የሚለውን በነጠብጣብ ያለፍኩት።
በእርግጥ ሰውዬው ሞቶ ከሆነ መንግሥት መሞቱን በዲኤንኤ ወይም በሌላ የፎረንዚክ ምርመራ አረጋግጦ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ይጠበቅበታል። መንግሥት እሱን ጨምሮ ሌሎችን በማደን ለሕግ የማቅረብ ጥረቱን እንዲያቋርጥ ሳይሞት ሞቷል ሊባል ይችላልና። የስቃዩ ሰለባ የሆኑ ሁሉ የጌታቸው አሰፋን ሰውነት መቀበል ይቸገራሉ። ከሁለት ዓመታት በፊት እኔን ጨምሮ የ«የፍትሕ ሰቆቃ ! » የተሰኘውን ዘጋቢ ፊልም የተመለከቱ ኢትዮጵያውያን በቀደሙት 27 ዓመታት በግፍ ቀፍቃፊዎች በእነ ጌታቸው አዝማችነት የተፈጸመው ግፍና ሰቆቃ በፈጣሪ አምሳል በተፈጠሩ ሰዎች ሳይሆን በጭራቆች ነው የተፈጸመ ቢሉ እውነት አላቸው ።
ከስቃዩ ሰለባዎች አንዱ የሆነው ዳባ ገሬ በዚሁ ዘጋቢ ፊልም ፤ በዜጎች ላይ ይፈፀም የነበረው ግፍ ወገን በወገኑ ላይ ይፈፅመዋል ተብሎ የማይታመንና ልጅ ሆነን ወላጆቻችን ያስፈራሩበት በነበረው ጭራቅ /ቡልቡል/ የሚፈፅም ይመስለኝ ነበር ያለው ይሄን ያረጋግጣል፡፡ በእነ አንዷለም አራጌ፣ ሀብታሙ አያሌው ፤ ከፍያለውና ሌሎች ላይ የተፈፀመውን ለመስማት የሚሰቀጥጥ፣ ለማየት የሚዘገንን ፤ የህወሓት መራሹን ግፍ በ«የፍትሕ ሰቆቃ» የተመለከትሁ ዕለት ማንባቴን አስታውሳለሁ። ለእራሴ እውን እነዚያ አረመኔዎች፣ አውሬዎች ከሰው ዘር የተፈጠሩ ናቸው ? ብያለሁ። መልሱ ተሟጋች ስዩምና የስቃዩ ሰለባ ዳባ እንዳሉት ጭራቆች ናቸው የሚለው ነው።
ሕገ መንግሥቱን ለሽንት ቤት ተጠቀምበት እያሉ ይሄን ዘግናኝ ስቃይ በወገናቸው ለፈፀሙ አረመኔዎች ነው እንግዲህ እነ ሱዛንና ብሊከን ጠበቃ ሆነው ብቅ ያሉት!? በዛ ዘጋቢ ፊልም የስቃዩ ሰለባ ሆነው የቀረቡ እህት ወንድሞቼን ባሰብሁ ቁጥር ዓለምአቀፉ ማህበረሰብና ምዕራባውያን በሀሰተኛና ሆን ተብሎ በተዛባ መረጃ ከትህነግ ጭፍራና ርዝራዥ ጎን መቆማቸውን ስመለከት በእነሱ ቁስል ላይ እንጨት እየሰደዱ እንደሆነ ስለሚሰማኝ ህመማቸው ያመኛል።
በሮማውያን ዘመን የነበሩ ገዥዎች ሰውን ከአንበሳ፣ ከነብር ጋር እያታገሉ በሰው ልጅ ስቃይ ይዝናኑ እንደነበር ከታሪክ ድርሳናት አንብበን እንዳልተደነቅን፤ በሀገራችን በሶማሊያ ክልል ጅግጅጋ በ «ጄል ኦጋዴን » ! ? ዜጎች ከአንበሳ ፣ ከነብር ፣ ከጅብ ጋር ይታሰሩበት የነበረ ምን አልባት በዓለማችን በ21ኛው መ/ክ /ዘ የመጀመሪያም፣ የመጨረሻም የሆነ ማሰቃያ አዘጋጅቶ ህልቁ መሳፍርት የሌለው ግፍ ይፈጸም የነበረው በእነ ጌታቸው አሰፋ ቡራኬ መሆኑን ያስተዋለ ሰውየውም ሆነ ጭፍራዎቹን ጭራቆች ናቸው ማለቱና ከሰብዓዊነት ቢፍቃቸው አይፈረድበትም።
በክፍል ሁለት መጣጥፌ የፈጣሪ ፈቃድ ከሆነ በምስጢራዊነት ስለተተበተበው ጌታቸው አሰፋ የቀራረምሁትን ይዤ እመለሳለሁ።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖችና ሀቀኛ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !!!
አሜን።
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2013