ጽንፈኝነትና ውሸት ኢትዮጵያን ዋጋ ሲያስከፍል ኖሯል፤ እያስከፈላትም ነው። በተለይ ባለፉት 30 ዓመታት ይህ እኩይ ባህርይና ድርጊት ሕግ ተበጅቶለትና መዋቅር ተደራጅቶለት ሲቀነቀንና ሲተገበር ከመቆየቱ አንፃር ነገም ዋጋ ማስከፈሉ የማይቀር ይመስላል። የሰው ልጅ ከታሪክ መማር እንጂ በታሪክ መማረር እንደሌለበት ያልተገነዘቡ ከማሰብ ደጅ የራቁ አላዋቂዎችና ሴረኞች የዚሁ ሰለባ ሆነው አገሪቱን እስካሁን ድረስ ያላባራ የግጭት አውድማ ውስጥ ዘፍቀዋታል። በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ተቆጥረው የማያልቁ ግድያዎች፣ መፈናቀሎች፣ የንብረት ውድመቶችና ሌሎችም በርካታ ችግሮች ተከስተዋል። ኢትዮጵያም ፊቷን ወደ ልማት አዙራ ከበለጸጉ አገራት ተርታ እንዳትሰለፍ ሆናለች።
ይህ የጽንፈኝነትና የውሸት አምልኮ አባዜ ባለፉት 30 ዓመታት መዋቅራዊ ሽፋን አግኝቶ በሕግና በተቋም ታግዞ ሲተገበር ኖሯል። ፌዴራሊዝም ለኢትዮጵያ ጥሩና የተሻለ የመንግሥት አወቃቀር እንደሆነ ባይካድም የጽንፈኝነት እሳቤ በ‹‹ፌዴራሊዝም›› ስም ሽፋን አግኝቶ ስር የሰደደ ችግር ለመሆን በቅቷል።
ይህ የጽንፈኝነትና የውሸት ታሪክ አቀንቃኝነት አባዜ እየቀዘቀዘ ይሄዳል ተብሎ ተስፋ ቢደረግም ከመቀዝቀዝ ይልቅ እየባሰ ሲሄድ ተስተውሏል። ሃሳቡ በተግባር ተተርጉሞ በሺዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ውድ ሕይወታቸውን እንዲያጡ፣ ለዓመታት ለፍተው ያፈሩት ንብረታቸው በደቂቃዎች ውስጥ እንዲቃጠልና እንዲዘረፍ እንዲሁም ቤተሰባቸው ተበትኖ የሁልጊዜም ፀፀትና የሞራል ስብራት እንዲደርስባቸው ሆኗል። በዚህ የጥላቻ ነገሥታት አሳፋሪ እሳቤና ተግባር ምክንያትም ኢትዮጵያ በአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ብዛት ከዓለም ቀዳሚ እንድትሆን ያደረጋትን አሳፋሪ ታሪክ ለማስመዝገብ ተገዳለች።
ኢትዮጵያ ዛሬም ከዚህ አዙሪት አልወጣችም። ላለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያን አምርሮ እየጠላ ኢትዮጵያን ሲገዛ የነበረው ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህ.ወ.ሓ.ት) መሰሎቹ እንዲደረጁ በማድረግ ይህ የጽንፈኝነት አስተሳሰብ ስር እንዲሰድ በማድረግ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል።
ምንም እንኳ ህ.ወ.ሓ.ት ዛሬ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በኖረበት የስልጣን መድረክ ላይ ባይኖርም አስተሳሰቡ ግን አገር የሚገዛውን መንግሥት እንቃወማለን ከሚሉ አካላት አልፎ መንግሥታዊ ስልጣን በያዙ ብዙ ግለሰቦችና ቡድኖችም ውስጥ ተንሰራፍቶ ተቀምጧል። በአሁኑ ወቅት የሚታዩት የሰላምና መረጋጋት አለመኖር፣ የንፁሃን ግድያ፣ መፈናቀልና የንብረት ውድመት ለዚህ ከብዙ በጥቂቱ ማስረጃዎች ናቸው። መንግሥታዊ መዋቅር ውስጥ ሆነው ‹‹አገር እናስተዳድራለን፤ሕዝብ እንመራለን›› የሚሉ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ‹‹ሰዎች›› ሕዝብን ለማጋጨትና ርካሽ ዓላማቸውን ለማሳካት ላይ ታች ሲሉ ይታያሉ።
ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ መጋቢት 14 ቀን 2013 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ስለወቅታዊ ጉዳዮችና የአስር ዓመቱ መሪ የልማት እቅድ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት የታዩ አንዳንድ ክስተቶች እጅግ የሚያስተዛዝቡ ሆነው አልፈዋል። በጥቂት የምክር ቤት አባላት ላይ የታዩ እጅግ ዋልታ ረገጥ የሆኑና በተጨባጭ ሃቅ ላይ ያልተመሰረቱ ጽንፈኛ አመለካከቶችና ድርጊቶች የአገሪቱን ችግሮች ከድጡ ወደ ማጡ እንዳያደርጉት ያስፈራል። በእርግጥ አገሪቱ አሁን ወዳለችበት ችግር የገባችው በመሰል ጽንፈኛና የውሸት አስተሳሰቦች ነው። ነገሩን እጅግ አስገራሚም አሳዛኝም የሚያደርገው ካለፉት ዓመታት በተሻለ ስለአገራዊ አንድነት በሚሰበክበት ወቅት ከፍተኛ ሕዝባዊና መንግሥታዊ ኃላፊነት በያዙ ‹‹ሰዎች›› ይህ የጽንፈኝነትና የውሸት አምልኮ እሳቤና ተግባር መቀንቀኑ ነው።
ይህ ተግባር በተጨባጭ መረጃ ላይ ያልተመሰረቱ የውሸትና የሴራ መረጃዎችን በማስጮህና በማስተጋባት ለዘመናት ተከባብረውና አንድ ሆነው በኖሩ ሕዝቦች መካከል አላስፈላጊ ግጭቶችን ይፈጥራሉ። ሕዝቦቹ የገነቧቸውን ተቋማት በማፍረስ ተቋም አልባ ያደርጋሉ።
ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ ለምክር ቤቱ አባላት በሰጡት ማብራሪያ ስለጽንፈኝነትን ችግር ትኩረት ሰጥተው ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚንስትሩ በማብራሪያቸው፣
‹‹ … ትልቁ የኢትዮጵያ ካንሰር፣ ነቀርሳ፤እንዳናድግ፣ እንዳንለወጥና እንዳንሻሻል እያደረገን ያለው ከሰፈራችን የዘለለ ነገር ማሰብ አለመቻል ነው። ከሰፈራችን የዘለለ ነገር ማሰብ አለመቻላችን እየገደለን ያለው ማንም በሰፈሩ አስቦ ኢትዮጵያን ማሸነፍ አይችልም። ይህ ደግሞ ዛሬም ተረጋግጧል፤ነገም የምታዩት ነውⵆ በሰፈር ሃሳብ ኢትዮጵያን ማሳነስ እንጂ ማሳደግ አይቻልም። እባካችሁ ቢያንስ የፓርላማ አባላት ከዚህ ውጡ። አሁን ሰው ያለው፤ሰፈር ያለው ይደመጣል … በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ልጆች በማያውቁት በሽታ፣ በጁንታው ምክንያት ስቃይ ላይ ነው ያሉት። ትግራይ ውስጥ ስትሄዱ ‹ኢትዮጵያ ውስጥ ከእኛ ውጪ የተበደለ የተገፋ የለም፤የምንገፋ የምንባረር እኛ ነን› ይላሉ። ቤንሻንጉል ብትሄዱ፣ መተከል ብቻ፣ ሰሞኑን ከ90ሺ በላይ የጉሙዝ ብሔረሰብ አባላትን ከጫካ መልሰናል። አንድም ሚድያ አይናገርላቸውም። ይሄ አገር እኮ የኦሮሞና የአማራ ብቻ አይደለም። ሌሎች ብዙ ብሄሮች አሉ። ኦሮሞዎችና አማራዎች በቁጥር ብዙ ናችሁ፤ግን ሰከን ብላችሁ ኢትዮጵያን በሚገነባ ነገር ላይ ብታተኩሩ ጥሩ ነው። ሁልጊዜ የእኛ የሆነ ነገር ውድ፤የሌላው ደግሞ የረከሰ ከመሰለን አይሆንም።
ኢትዮጵያን ከወደድን ሁሉም ዜጋ እኩል እድል የሚያገኝበት፣ የሚከበርበትና ወጥቶ የሚገባበት መሆን አለበት። የአንዱ ሕይወት ሲሆን ውድ የሚሆንበት የሌላው ሲሆን ደግሞ የሚረክስበት ከሆነ ዋጋ የለውም። ይህ ይጎዳናል። በዚህ መንገድ የምትነግዱ የፖለቲካ ነጋዴዎችም እባካችሁ አስቡበት። ኦሮሞና አማራ ተጋደለ ብላችሁ በጣም የምታጯጩሁ አክቲቪስቶችና ሚዲያዎች ኦሮሞና አማራ የሚጋደሉ ከሆነ እኮ ኢትዮጵያ የለችም። እነርሱን እያባላችሁና እያጋደላችሁ እናንተ ምን ልታስተዳድሩ ነው? የሚባላ ህዝብ ምን ያደርግላችኋል? እንኳን የሚባላ ህዝብ የቆመ ፕሮጀክት ጭንቅላታችንን አዙሮናል። አገር እያፈረሱ አገር እመራለሁ ማለት ዋጋ የለውም።
ይህ በሁሉም ቦታ አለ። እባካችሁ ከዚህ እንውጣ። ማስተዋል መልካም ነው። በመባላታችን ኦሮሞ፣ አማራ ወይም ጉራጌ አይጠቀምም። በቃ ይሞታል፤ እናለቅሳለን፤እንቀብራለን፤ የሰው ቤተሰብ እናፈርሳለን ከዛ ደግሞ ህይወት ይቀጥላል። ይህ ጭንቅላት፣ ለመኖርና ለመስራት የማይመች በመሆኑ እባካችሁ ሰከን ብለን ብናስብና ለጠላቶቻችን ሲሳይ ባንሆን። ኦሮሞና አማራን ለማባላት ገንዘብና ጊዜያቸውን ሰውተው የሚሰቃዩ ኃይሎች እንዳሉ እያወቃችሁ በተቀደደ ቦይ የምትገቡ አመራሮች ትገርሙኛላችሁ።
ህዝቡን ካላባላን የምንፈልገውን አናሳካም ለሚሉ ሀይሎች እድል መስጠት ጥሩ አደለም። የሁሉም ብሄር ሲሞት ጉዳቱ እንደ አገር ነው። የዜጎች መበደል፣ መዘረፍና መሞት እኩል ካላሳዘነን የጋራ አገር አንገነባም። ይህ ፖለቲከኞችንም የሚመለከት ጉዳይ ነው። ይህች አገር የ80 ብሔሮች አገር አንደሆነችና ሁሉም ከኖረ ብቻ ኢትዮጵያ እንደምታድግ በመረዳት ለጋራ ነገር ልናስብ ይገባናል። ለጋራ ነገር ልናስብ ይገባናል።
… በማንኛውም መመዘኛ ጦርነት ሲታሰብም ሲሰራም ሲጠናቀቅም ኪሳራ እንጂ ጥቅም የለውም። የጦርነት ጥቅሙ የሚታየው ካለመጀመር ብቻ ነው። ጦርነት ከተጀመረ ውርደትና ሞት ነው። ጦርነት ከባህሪው ፍራቻን፣ ጥላቻንና መገፋትን የሚፈልግ ነገር ነው። ጦርነት ጥቁር ጥላ ነው … እብሪት ውድቀትን ታስቀድማለች። ይህ ምናልባት ህወሓት ብቻ ሳይሆን አሁን ያለን ፖለቲከኞች ከዚህ መጠበቅ አለብን … ሕዝቡ ከማንም በላይ የሚተዋወቅ ህዝብ ነው። እኛ ነን በዞን ከፋፍለን የያዝነው። የሰው ደም እንደፈለገ ማፍሰስ ይቁም። በረሃብ የሚሰቃየው አንሶ በእኛ የፖለቲካ ሽኩቻ ምክንያት ሰው መሞት ይቁም።
ነቅተን ተባብረን ስለብሄር ክፍፍል ሳናነሳ እንደ አንድ ህዝብ ሆነን ነገርየውን በሂደት ማረምና ማስተካከል ያስፈልጋል። ሕዝብ እንዳይጎዳና ክፍፍል እንዳይፈጠር አንድ ሆኖና ተከባብሮ ወደ ልማት እንዲሄድ ማድረግ ነው የሚጠበቅብን …
በጣም ወደ ጫፍ የሄደን ነገር ሰከን ብሎ ማየት ጠቃሚ ይሆናል። ጠቃሚ የሚሆነው እኛ ሰክነን ሞት መቀነስ ነው። በእያንዳንዱ ሞት ውስጥ በትክክል ያለውና የሚነገረው ይጋነናል። ትግራይ ስትሄዱ፣ ጉሙዝ ስትሄዱ የተጋነነ ነው። በየቦታው እንደዚያ ነው፤ ሰው የራሱ ብቻ ጠበቃ ሆኖ ስለሚቆም። አይጠቅመንም ሰላም ያስፈልጋል፤የጋራ ልማት ያስፈልጋል። በኦሮሞና በአማራ መካከል ወሎም ይሁን ወለጋ ሸዋም ይሁን ጎጃም ግጭት ካለ ጠላት ይጠቀማል እንጂ ኦሮሞም፣ አማራም ሌላውም አይጠቀምም። ይህን አስቦ በትብብርና በሰከነ መንገድ ማየት ይሻለናል። እባካችሁ በዘር መባላት፣ በእምነት መባላት አይመጥነንም፤ ታሪካችን አይደለም፤ ምንም አይፈይድም። ጥፋት ያስከትላል፤ ለጠላቶቻችን ሲሳይ ያደርገናል፤ ጥንቃቄ እናርግ። ይህን የምታራግቡም ኃይሎች እባካችሁ ኢትዮጵያን በማባላት ጥቅም አታገኙም። ሰክናችሁ ለማየት ሞክሩ። ተነስ አማራ፣ ተነስ ኦሮሞ የምትሉ ኃይሎችም ጥንቃቄ አድርጉ … ›› ብለዋል።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው በኢትዮጵያ እየተስፋፋ የመጣውን የጎጠኝነት እና ራስ ወዳድነት ችግር ዜጎች በአንድ ልብ ሊቃወሙት እንደሚገባ አሳስበዋል። ፕሬዚዳንቷ ሰሞኑን የአስተዳደር ወሰን እና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ከሰላም ሚንስቴር እና ከደህንነት ጥናት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ባዘጋጀው አገር አቀፍ የጥናትና ምርምር ሲምፖዚየም ላይ ‹‹ … በጎጠኝነት እና በራስ ወዳድነት ተተብትቦ እርስ በእርስ በመጋጨት ለዓለም መዘባበቻ መሆን ለኢትዮጵያ እና ለዜጎቿ የሚመጥን አይደለም። በኢትዮጵያ ሰላም አደጋ የሆነውን የጎጠኝነት እና የራስ ወዳድነት ችግር ዜጎች በአንድ ልብ በመቃወም ከእንዲህ አይነቱ አባዜ መውጣት የግድ ይለናል …›› ብለዋል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ የብዝሀነት አገር መሆኗን ጠቁመው በጎጠኝነት አስተሳሰብ ለነጋሪ የሚያሳፍር ግጭት፣ አሰቃቂ ሞትና የንብረት መውደም እንዲሁም መፈናቀል ማስከተሉ የአደባባይ ሀቅ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
ይህ ላለፉት 30 ዓመታት በተደራጀ ሁኔታ ንፁሃንን ለሞት፣ ለአካል ጉዳትና ለመፈናቀል እንዲሁም አገርን ለኪሳራና ለክፍፍል የዳረገ እጅግ አደገኛ የጽንፈኝነትና የውሸት መረጃ (ታሪክ) የማምለክ እሳቤ ዛሬም ከህ.ወ.ሓ.ት እጣ ፋንታ ትምህርት ባልወሰዱ አሳፋሪ ‹‹ፖለቲከኞች››ና ተከታዮቻቸው አማካኝነት መዋቅራዊ ሽፋንና ሕጋዊ ከለላ አግኝቶ የሚዘልቅ ከሆነ ውጤቱ እስከዛሬም ካየነው እጅግ የከፋ እንደሚሆን ለማወቅ ነብይ መሆን አያስፈልግም። ስለሆነም አገርን ለከባድ ኪሳራ የዳረገውን ይህን አደገኛ እሳቤ ማስቆም ይገባል!
አዲስ ዘመን መጋቢት 20/2013
ፖለቲካ እና ልዩ ልዩ