በአሥመረት ብሥራት
የኖቬል ኮሮና ቫይረስ የመተንፈሻ አካልን የሚጎዳ በሽታ ነው፡፡ በርካታ ሰዎች ቀለል ያሉ ወይም ጠቅላላ ምልክቶች ላይታዩባቸው ይችላል። አንዳንዶች ደግሞ በጽኑ ይታመማሉ፡፡ በተለይ አረጋዊያንና ሌሎች በሽታዎች ያሉባቸው ሰዎች በበሽታው የመጠቃት ወይም ሞት ሊያጋጥማቸው ይችላል። በዚህም የተነሣ ከፍተኛ ሥጋት ያድርባቸዋል። እንደሌሎች የወረርሽኝ መቆጣጠሪያ ዘዴዎች የኮሮና ቫይረስ ክትባት የኮቪድ-19 በሽታን ይከላከላል። ክትባቱን የመውሠድ ዓላማውም ሕይወትን እና ጤናን መጠበቅ ነው። ስለዚህም ክትባቱን መውሰድ የግድ ይሆናል።
የኮሮና ወረርሽኝ ክትባትን በተመለከተ ለጋዜጠኞች በተሰጠ የግንዛቤ ማሣደጊያ ሥልጠና ላይ ስለኮሮና ወረርሽኝ ክትባት ጉዳይ መነሻ ሐሳብ ያቀረቡት በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የእናቶች ሕፃናት ጤና ዳይሬክቶሬት የክትባት ባለሙያ ወይዘሮ ፀጋነሽ ገድሉ ማብራሪያ ሰጥተዋል። እንደሚከተለው ይቀርባል።
የኮሮና ክትባት እንዴት ይሠራል?
ክትባቱ በኮሮና ቫይረስ ላይ ላሉት መሸፈኛዎች መልዕክተኛ (ሜሴንጀር አር.ኤን.ኤ) የያዘ ነው። ይህን መጠቀሙ ሰውነት እነዚህን መሸፈኛዎች አባዝቶ የበሽታ መከላከያ አቅሙን እንዲለማመድ ያደርገዋል። በዚህ መንገድ የተፈጥሮ በሽታ መከላከል ሥርዓቱ የኮረና ቫይረስ መሸፈኛዎቹን በማወቅ እንዲሁም ቫይረሱ የሚጎዳ እንዳይሆን ሰውነት መከላከል እንዲችል ያደርጋል፡፡ የሚሴንጀር አር.ኤን.ኤ በፍጥነት በሰውነት ይሠበራል፡፡ እንዲሁም በጂን ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት የለውም፡፡ ክትባቱ በሕይወት ያለውን ቫይረስ አይዝም፡፡ እንዲሁም ለኮቪድ 19 በሽታም ምክንያት አይሆንም። የኮረና ቫይረስ ክትባት በሽታን ለመከላከል የሚሠራ ነው፡፡ ከዚህ በፊት እነዚህን ክትባቶች ለመሥራት በሚያገለግለው ዘዴ ለበሽታዎች ማዳኛ አገልግሎት ላይ ውሎ አያውቅም፡፡ ነገር ግን ቴክኖሎጂው ይታወቃል፡፡ እንዲሁም በነቀርሣ (ካንሠር) በሽታ ሕክምና አገልግሎት ላይ ውሏል፡፡ ይህ ክትባት እንዴት በጥሩ ሁኔታ ይሠራል? ይህ ክትባት በኖቬል ኮሮና ቫይረስ ምክንያት የሚመጣውን በሽታ ይከላከላል።
በክትባቱ ላይ የተደረጉ ጥናቶች ውጤት የሚያሣየው ሁለተኛ መጠን ከተወሰደ ከአንድ ሣምንት በኋላ፣ ክትባቱን ከተከተቡት ውስጥ ወደ 95% ያህሉ በሽታውን መከላከል ችለዋል። ለአረጋዊያን ያለው መረጃ እጅግ ጥቂት ነው። የሆስፒታል ሕክምና ሊጠይቅ የሚችል ክብደት ያለውን የኮሮና ቫይረስ በሽታንም መከላከል እንደሚችሉ ጥናቶች ያመላክታሉ። መከላከያው ምን ያህል እንደሚቆይ እስካሁን አልታወቀም። መከላከያው ከጊዜ በኋላ የሚጠፋ ከሆነ፣ ከፍ የሚያደርግ የመድኃኒት መጠን መውሰድ ሊያስፈልግ ይችላል።
ክትባቱ የሚያስከትለው የጎንዮሽ ጉዳት አለን?
የጎንዮሽ ጉዳቶችን በተመለከተ ከተከናወኑት ጥናቶች መረዳት የተቻለው ከተከተቡት ሰዎች መካከል በዋናነት እና አልፎ አልፎ የጐንዮሽ ጉዳቶች የሚታዩ መሆኑ ነው። አብዛኞዎቹ የጐንዮሽ ጉዳቶች ከተከተቡ በኋላ ባሉት የመጀመሪያ ቀናት ላይ ታይተው ከዚያ በኋላ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ይጠፋሉ፡፡ አብዛኞዎቹ የተከተቡት ሰዎች መድሃኒቱን የተወጉበት ቦታ ላይ ሕመም እንደሚሰማቸው ሪፖርት አድርገዋል፡፡ ሌሎች የተለመዱ የጐንዮሽ ጉዳቶች፣ ድካም፣ የራስ ምታት፣ የጡንቻ ሕመሞች፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ የመገጣጠሚያ ሕመሞች እና ትኩሣትን ይጨምራሉ፡፡ እነዚህ የጐንዮሽ ጉዳቶች ሁለተኛውን የመድሀኒት መጠን ከወሰዱ በኋላ የሚታዩ ናቸው፡፡ የጐንዮሽ ጉዳቶቹ ከወጣቶች ይልቅ በአረጋዊያን መካከል ያነሱ ሆነው ይታያሉ፡፡
የጐንዮሽ ጉዳቶች ሲኖሩ ምን መደረግ አለበት?
ያልተጠበቁ፣ ከባድ ወይም ለረዥም ጊዜ የቆዩ እና በክትባቱ ምክንያት የመጡ ናቸው ብለው የሚያስቧቸው ምልክቶች ካጋጠመ ለሕክምና ወይም ለምክር ሐኪምን ወይም ሌላ የጤና አጠባበቅ ሠራተኛን ማማከር ተገቢ ይሆናል። የጤና አጠባበቅ ሠራተኞች በክትባት ምክንያት የመጣ ነው ብለው የሚጠረጥሯቸውን ማናቸውንም ከባድ ወይም ያልተጠበቁ ምላሾችን ሪፖርት የማድረግ ግዴታ አለባቸው፡፡ በአብዛኛው ግን በአንድ ቀን ወይንም በሁለት ቀን የሚጠፋ የሕመም ምልክት በመሆኑ መጨነቅ አይገባም።
የኮሮና ቫይረስ ክትባት ማግኘት ያለባቸው እነማን ናቸው?
ክትባቱ በሽታው ላለበት ሰው የሚሰጠው በሽታው ከተያዘበት ከአራተኛው ሣምንት በኋላ ነው፡፡ ይህም የሆነው ተፈጥሯዊውን በሽታ የመከላከል ኃይል ከአራተኛው ሣምንት ጀምሮ ስለሚጨምር ነው። የበሽታው ምልክት የታየባቸው ሰዎች ክትባቱን ባይወስዱ ይመከራል። ከ16 ዓመት በታች ለሚገኙ ሕፃናትና ለነብሠ ጡር እናቶች የኮሮና ወረርሽኝ ክትባት አይሰጥም። ይህም ጉዳት እንደማያስከትል በጥናት የተረጋገጠ ነገር ባለመኖሩ ነው።
የኮሮና ወረርሽኝ ክትባት ብቻ ሣይሆን ማንኛውም ክትባት ሲሠራ መጀመሪያ የሚሞከረው በጤነኛ አዋቂ ሰዎች ላይ ነው። ነብሠ ጡሮችና ሕፃናት ላይ ስለማይሞከር ጽንሥ ላይ የሚያስከትለው ተፅዕኖ አይታወቅም፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ በተለየ ሁኔታ ነብሠ ጡሮችና ሕፃናትን የሚያጠቃ ስላልሆነም ክትባቱን ይውሰዱ የሚል አሥገዳጅ ሁኔታ አይኖርም፡፡ በተለይ የሥራቸው ሁኔታ አሥገዳጅ የሆነባቸው እናቶች ለበሽታው ወደማያጋልጣቸው ቦታም እንዲዘዋወሩ ይመክራሉ።
ክትባቱ እንዴት ይሰጣል?
የኮሮና ቫይረስ ክትባት በላይኛው ክንድ ላይ በመውጋት የሚሰጥ ነው፡፡ ቢያንስ በየ21 ቀናት ሁለት ጊዜ ክትባቱን የሚወስዱ ይሆናል፡፡ በተቀመጠው የጊዜ ሠሌዳ ለሁለተኛ የሚሰጠውን የመድኃኒት መጠን መውሰዱ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ክትባቱ ከመወሰዱ በፊት ጤንነት ስለመሠማቱ ይጠየቃል። ከዚህ በፊት ክትባቶችን ወስደው ስላሳዩት የሰውነት ምላሽም እንዲገልጹ ይጠየቃል፡፡
ነፍሠ ጡር ከሆኑ፣ ምንም ዓይነት ከመድኃኒት ጋር የሚገናኝ የሰውነት መቆጣት ካለ፣ መድኃኒቶችን የሚጠቀሙ ከሆነ ወይም ሌላ የጤና ችግር ካለ ለሐኪም መግለፅ ይገባል። ከፍተኛ ደረጃ የደረሠ ሕመም ካጋጠመ ወይም የሙቀት መጠን ከ38 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ በላይ ከሆነ ክትባቱን ማቆየት የተለመደ ነው። ክትባቱ ከተወሰደ በኋላ ለ20 ደቂቃዎች መጠበቅ ይጠይቃል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 20/2013