አስናቀ ፀጋዬ
የራሱን ቢዝነስ የጀመረው ከወላጅ እናቱ ጋር በመሆን ነው። የቢዝነስ ህይወቱን እንደጀመረ ባገኘው ገቢ እንደብዙዎቹ ወጣቶች አልተዘናጋም። ዋነኛ ትኩረቱም ሥራው ላይ ብቻ ነበር። እምብዛም ባልተለመደው የ‹‹ኢንቴሪየር ዲዛይን›› ሥራ ውስጥ በድፍረት ገብቶም አንዴ ከፍ ሌላ ጊዜ ዝቅ ብሏል።
በአነስተኛ ካፒታልና የሰው ኃይል ያስጀመረው የ‹‹ኢንቴሪየር ዲዛይን›› ሥራ በሂደት እያደገ መጥቶ ሰፊ ገበያ ያገኘ ቢሆንም የኋላ ኋላ በአሠሪዎች ሙሉ ክፍያ ለመክፈል ማመንታት ችግር ምክንያት መፈተኑ አልቀረም። በዚህም ኩባንያው የመዘጋት ዕጣ ፈንታ ገጥሞት ነበር።
በሂደት ግን ወጣቱ የቢዝነስ ሰው ኩባንያው ከአሠሪዎች በኩል የገጠመውን ውጣውረድ በመቋቋምና በውስጡ ያሉትን ችግሮች በመፍታት ወደ ቀድሞው ውጤቱ እንዲንደረደር አድርጎታል። በአሁኑ ጊዜም በኢንቴሪየር ዲዛይን ሥራ ውስጥ ካሉ ሌሎች መሰል ኩባንያዎች መካከል አንዱና ዋነኛ ተፎካካሪ እንዲሆን አድርጎታል – የኤይሮ አይረን ኮንስትራክሽንና ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍሬዘር ተሾመ።
አቶ ፍሬዘር ተሾመ ዕድገትና ውልደቱ በሰሜን ሸዋ ዞን ዓለም ከተማ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በዓለም ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በአርበኞች ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሯል። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግቢያ ፈተና ወስዶ ባገኘው ውጤት ወሎ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ በሂሳብ በ2002 ዓ.ም የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል። በመቀጠለም አዳማ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በሲቪል ምህንድስና ትምህርቱን ተከታትሎ በሌላ ዲግሪ ተመርቋል።
በጊዜው በሲቪል ምህንድስና ዘርፍ የሥራ እጥረት መኖሩን በመገንዘብ ዩ አይ ኤች በተሰኘ የኢንተሪየር ዲዛይንና ፊኒሽንግ ሥራዎችን የሚሠራ ኩባንያ ውስጥ ተቀጠረ። በዚህ ኩባንያ ውስጥም በሞያው ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር አገለገለ። በኩባንያው የነበረው ቆይታም ከኢንተሪየር ዲዛይንና የፊኒሽንግ ሥራዎች ጋር በተያያዘ በቂ ልምድ መቅሰም ቻለ። የራሱን የኢንቴሪየር ዲዛይንና የፊኒሽንግ ሥራዎችን የሚያከናውን ድርጅት የማቋቋም ፍላጎትም በውስጡ አደረ።
ከአምስት ዓመት በፊት አይሮ አይረን የተሰኘ የኢንቴሪየር ዲዛይን ሥራዎችን የሚያከናውን ኩባንያ ከእናቱ ጋር በመሆን በአንድ መቶ ሺ ብር መነሻ ካፒታልና በአምስት የሰው ኃይል አቋቋመ። በጊዜው ኩባንያውን ሲያቋቁም በኢትዮጵያ የኢንቴሪየር ዲዛይንና ፊኒሽንግ ሥራዎች ብዙም ያልተለመዱ በመሆናቸውና ሰዎችም ይህን ሥራ እንደቅንጦት የሚመለከቱት በመሆኑ ሥራውን እንደጀመረ ብዙም ገበያ አላገኘም። ይሁንና በሂደት ሰዎች የሥራውን አስፈላጊነት እየተገነዘቡና የማሠራት ፍላጎታቸው እያደገ ሲሄድ የኩባንያው ገበያ እየተሟሟቀ መጣ።
ዘመኑ የደረሰበት ደረጃና በተለይ ደግሞ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አነሳሽነት የተጀመሩ አዲስ አበባን የማስዋብ ፕሮጀክቶችና የመንግሥት ተቋማት ሕንፃዎችን የማደስ ተግባራት የኩባንያው ገበያ እንዲደራ አስተዋፅኦ አበረከተ። ከዚህም ጋር በተያያዘ የኢንቴሪየር ዲዛይንና የፊኒሽንግ ሥራ በህብረተሰቡ ዘንድ ተፈላጊ እየሆነ በመምጣቱ የኩባንያው ገበያም ይበልጥ አደገ።
ኩባንያው ሥራውን እንደጀመረ የግለሰብ መኖሪያ ቤቶችን፣ ቢሮዎችን ፣ልዩ ልዩ ሕንፃዎችና የጋራ መኖሪያ ቤቶችን የውስጥ(ኢኒቴሪየር) ዲዛይን ሥራዎችን ማከናወን ቻለ። ቀስ በቀስም አፓርትመንቶችን፣ ቪላ ቤቶችንና ትላልቅ ሕንፃዎች ላይ አሻራውን አሳረፈ። ሥራው በትስስር የሚሠራ ከመሆኑ አኳያም በዚሁ ዘርፍ ካሉ ሰዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ኩባንያው የተለያዩ የኢንቴሪየር ዲዛይን ሥራዎችን በማከናወንም ውጤታማ ሆነ። የዘርፉን ገበያም በቀላሉ ለመቆጣጠር ብዙ አልተቸገረም።
ለኢንቴሪየር ዲዛይን ከአሠሪዎቹ የተሰጠውን ቦታ በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል፣ እሴት በመጨመርና ውበትን አላብሶ ሥራዎችን በማጠናቀቅ ለደንበኞቹ ማስረከቡንም ተካነበት። የኢንቴሪየር ዲዛይን ሥራዎች በሀገር ውስጥ ጥሬ እቃዎች መከናወን እንደሚችሉም በተግባር ሠርቶ አሳየ። የደምበኞቹንም ፍላጎት እያደመጠ እነሱ በሚፈልጉት ልክና የባህል እሴቶችን ባሟላ መልኩ ሥራዎችን ሠርቶ ማስረከቡን ቀጠለ።
ቦታን በአግባቡ በመጠቀም፣ ሳይንስና ጥበብን በማጠማር ውበትን በመስጠት እንዲሁም ወጪን በአግባቡ በመጠቀም ለአምስት ዓመታት ያህል የኢንቴሪየር ዲዛይን ሥራዎችን ሲያከናውን የቆየው ኩባንያው በኮቪድ 19 ምክንያት የሥራ መቀዛቀዝ አጋጠመው። በዚህ ፈተና ውስጥ ሆኖ ግን የሠራተኞቹን ቁጥር አልቀነሰም። ይልቁንም በነበሩት ሠራተኞች ላይ ተጨማሪ ሠራተኞችን ቀጠረ። በአሁኑ ወቅትም ከሠላሳ በላይ ለሚሆኑ ጊዜያዊና ለስምንት ቋሚ ሠራተኞች የሥራ ዕድል ፈጥሯል። ፕሮጀክት ተኮር በሆኑ ሥራዎች ላይ የሚያሳትፏቸው የሠራተኞች ቁጥርም አስከ ሃምሳ ድረስ ይጠጋል። አጠቃላይ ካፒታሉም 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ደርሷል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካቶች በኢንቴሪየር ዲዛይን ሥራ ውስጥ ገብተው እየሠሩ ቢሆንም ኩባንያው ፈጠራ የታከለባቸው ሥራዎችን በመሥራት፣ የሀገር ውስጥ ጥሬ እቃዎችን በመጠቀምና ባህላዊ እሴቶችን በጠበቀ መልኩ ሥራዎችን በማከናወን እንዲሁም በተሻለ ዋጋና ጥራት ሥራዎችን ሠርቶ ለደምበኞቹ በማስረከብ ላይ ይገኛል። ጥሩ የፊኒሺንግ ሥራዎችን አሴት ጨምሮ ለደምበኞቹ በመሥራትም ከተፎካካሪ ኩባንያዎች በልጦ ለመገኘት ይጥራል።
ኩባንያው በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ የአርክቴክቸር ዲዛይን ሥራዎችን ይሠራል። የኢንቴሪየርና የዲዛይን ስትራክቸራል አናሊሲስ ሥራዎችንም ያከናውናል። በዋናነት ግን በኢንቴሪየር ዲዛይን ሥራዎች ላይ አተኩሮ ይሠራል። በቅርቡ ደግሞ በደረጃ ሁለት የሕንፃ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጭነት ዘርፍ እህት ኩባንያ አቋቁሞ ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅቱን አጠናቋል።
‹‹መቆሚያ በሌለውና በየወቅቱ እየተለዋወጠ በሚሄደው የኢንቴሪየር ዲዛይን ሥራ ዘርፍ ኩባንያው ሁሌም አዳዲስ ሥራዎችን ለመጨመር ፍላጎት አለው›› የሚለው አቶ ፍሬዘር የግንባታው ዘርፍ ሁሌም ያለ በመሆኑና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ በቀጣይ በኢንቴሪየር ዲዛይን ሥራ በስፋት ገብቶ የመሥራት እቅድ እንዳለው ይጠቁማል።
በተለይ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢንቴሪየር ዲዛይን ሥራ በህብረተሰቡ ዘንድ ተፈላጊነቱ እየጨመረ በመምጣቱት ሰፊ ገበያ እንደሚኖር ከግምት ውስጥ በማስገባት የባለሞያዎቹን አቅም በስልጠና፣በእውቀትና ዓለም አቀፍ ስልጠናዎችን እንዲወስዱ በማድረግ የማሳደግ ሃሳብ እንዳለውም ይጠቅሳል። ከውጭ ሀገር ከሚመጡ ጥሬ እቃዎች ይልቅ በሀገር ውስጥ በሚመረቱ ጥሬ እቃዎች የኢንቴሪየር ዲዛይን ሥራዎችን የመሥራት ውጥን እንዳለውም ይናገራል። አዳዲስ ፈጠራዎችን በማከል የኢንቴሪየር ዲዛይን ሥራዎችን የማከናወን ፍላጎት እንዳለውም ያመለክታል።
ኩባንያው ከጊዜ ወደ ጊዜ ዋጋው እየናረ የመጣውን ሲሚንቶ ከግምት ውስጥ በማስገባት ግርግዳዎችን ያለ ሲሚንቶ ለመገንባት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ለማምጣት ጥናትና ምርምር እያደረገ እንደሚገኝም ጠቁሞ፤ ይህ በቀጣይ የሚሳካ ከሆነ አዳዲስ የኢንቴሪየር ዲዛይን ሥራዎችን ይዞ እንደሚመጣም ያስረዳል።
በመንግሥት ደረጃ የኢንቴሪየር ዲዛይን ሥራዎች መሥራት መጀመራቸው በበጎ ተግባር መሆኑንም የሚገልጸው አቶ ፍሬዘር፤ የዘርፉን የገበያ ድርሻ ከማሳደግ በዘለለ በግለሰብ ደረጃም የማሠራት ፍላጎት እንዲጨምር አስተዋፅኦ ማድረጉን ይጠቁማል። ከዚህ አኳያም ዘርፉ ያለበት ደረጃና የገበያ ሁኔታም መልካም መሆኑን ይጠቅሳል።
የአርክቴክቸርና የኢንቴሪየር ዲዛይን ሥራ ከመንግሥት ጀምሮ አስከ ግለሰብ ድረስ እየተለመደና እየተፈለገ መምጣቱ በበጎ የሚታይ ቢሆንም በተለይ ወጣቶች በዚህ አዲስ ዘርፍ ተሰማርተው በሁለት እግራቸው አስኪቆሙ ድረስ የግብር እፎይታ እንዲኖራቸው ከማድረግ አንፃር ሰፊ ክፍተት እንደሚታይ ይጠቁማል። ከዚህ አኳያ መንግሥት ለወጣቶች የግብር እፎይታ በማድረግ ዘርፉን ማበረታታት እንዳለበት ይናገራል።
በሌላ በኩል ደግሞ ከአሠሪዎች በኩል ለኢንቴሪየር ዲዛይን ሥራ ያለው ግምት የወረደ መሆንና የሥራውን ሙሉ ክፍያ በጊዜው ለመፈፀም ዝግጁ ያለመሆን ችግር እንደሚታይም ጠቅሶ፤ በዚህ ምክንያት አሠሪዎች ለግንባታ የሚሰጡትን ትኩረት ያህል ለኢንቴሪየር ዲዛይን ሥራም ተገቢውን ዋጋ በመስጠት ሊያሠሩ እንደሚገባም ያመለክታል። በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረትም የዘርፉ ሌላኛው ተግዳሮት በመሆኑ መንግሥት ይህን ክፍተት ለመሙላትና በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሞያዎችን ቁጥር በማሳደግ ረገድ የበኩሉን አስተዋፅኦ ሊያበረክት እንደሚገባ ይጠቁማል።
‹‹እስከአሁን ባለው የአምስት ዓመታት ጉዞ ያሰብነውንና የልፋታችንን ያህል ውጤታማ መሆን አልቻልንም›› የሚለው አቶ ፍሬዘር፤ በተለይ ኩባንያው ከአሠሪዎች በኩል ሙሉ ክፍያዎችን ያለመክፈል ችግሮች በተደጋጋሚ ገጥሞት የነበረ በመሆኑ የመዘጋት ስጋት አንዣቦበት እንደነበር ያስታውሳል። በዚህ ችግር ምክያትም ኩባንያው ወደ ስኬት በሚያደርገው ጉዞ ላይ እንቅፋት ፈጥሮበት እንደነበርም ይጠቁማል። አብዛኛዎቹን ሥራዎችም በስጋት ሲያከናውን እንደቆየ ያስረዳል።
ሆኖም በአሁኑ ወቅት እነዚህን ውጣውረዶች በማለፍና አንዳንድ አሠራሮችን በማስተካከል ወደ ውጤት እየተንደረደረ ያለ ኩባንያ መሆኑን አቶ ፍሬዘር ይመሰክራል። በኩባንያው በኩል የነበሩ የማኔጅመንት ክፍቶችን እንደተሞሉና ከህግ ባለሞያ ጋር በመሆን ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙም ያብራራል። ለእነዚህ ችግሮች እንደዋና መንስኤ የነበሩ የውል አስሮ መሥራት ክፍተቶችን በማረም ሁሉም ሥራዎች ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው ድረስ በውል ታስረው የሚከናወኑበትን መንገድ መፈጠሩንም ይጠቅሳል። እያንዳንዱ ሥራዎች የሚከናወኑባቸው ጥሬ እቃዎች ደምበኞች አውቀዋቸው የሚሠራበት ሁኔታም እንደተፈጠረ ያስረዳል።
ኮቪድ -19 በኩባንያው ላይ የፈጠረውን ተፅእኖ ለመቀልበስና ከዋጋ ግሽበቱ ጋር በተያያዘም በጥሬ እቃዎች ላይ የተፈጠረውን የዋጋ ጭማሪ ለማስተካከል ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙም አቶ ፍሬዘር ገልፆ፤ ከዚህ አኳያ ኩባንያው ትልቅ ተስፋ ያለው መሆኑንና ተፎካካሪ የአርክቴክቸራልና የኢንቴሪያር ዲዛይ ሥራዎች በስፋት መሥራት በሚያስችለው ደረጃ ላይ መድረሱን ይጠቁማል። በሥራዎች ላይ ፈጠራ በማከለም ውጤት ለማምጣት ተስፋ የሰነቀ ኩባንያ መሆኑንም ይጠቅሳል።
‹‹ወጣትነትና ቢዝነስ በፈተናዎች የተሞላ ነው›› የሚለው አቶ ፍሬዘር፤ በተለይ እሱ ከአሠሪዎች በኩል ከገጠመው ፈተና ውስጥ አንዱ የኢንቴሪየር ዲዛይን ሥራውን በትክክል ይሠራዋል የሚልው ጉዳይ በመሆኑ በተመሳሳይ በዚህ የሥራ ዘርፍ ውስጥ ላሉም ሆነ ወደፊት መግባት ለሚፈልጉ ወጣቶች በአሠሪዎቻው በኩል ታአማኒነት እንዲኖራቸው በሰከነ መልኩ ስለሥራቸው ማስረዳትና ማሳመን እንዳለባቸው ይመክራል።
የቅድመ ክፍያዎችን ከአሠሪዎቻቸው ሲቀበሉም በውል በተደገፈ መልኩና ገንዘቡ ለምን ፍጆታ እንደ ሚውል በዝርዝር ማስረዳትና ይህንንም አሳምኖ ገንዘቡ ሥራ ላይ እንዲውል ማስገንዘብ እንደሚኖርባቸው ይጠቁማል። በውስጣቸው ያለውን እምቅ ኃይልና እውቀት መጠቀም እንዳለባቸው ነገር ግን የቢዝነስ ውሳኔዎችን በተሰላና ከችኩልነት በፀዳ መልኩ ማሳለፍ እንደሚገባቸውም ያመለክታል። የገንዘብ ወጪዎቻቸውን መቀነስ እንዳለባቸው በተለይ ደግሞ የቢዝነስ ተቋማቸውን ገቢ ከራሳቸው ገቢ መለየት እንደሚገባም ይጠቅሳል።
መንግሥትም የጀመረውን የኢንቴሪየር ዲዛይን ሥራዎችን ማስቀጠል እንዳለበትና ህብረተሰቡም ለግንባታ የሚሰጠውን ትኩረት ያህል ለዚህ የሥራ ዘርፍ ዋጋ መስጠት እንዳለበትም ያመለክታል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2013