አንተነህ ቸሬ
ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ እንዲካሄድ የተቆረጠለት ቀን ከሦስት ወራት ያነሰ ጊዜ ቀርቶታል፡፡ በምርጫው የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ይፋዊ የምርጫ ቅስቀሳቸውን ጀምረዋል፡፡ ታዲያ ፓርቲዎቹ የምርጫ ቅስቀሳ መርሃ ግብሮቻቸውን በአደባባይ ቢጀምሩም ሞቅ ያለው የምረጡኝ ዘመቻ እየተካሄደ ያለው በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን፣ በተለይም በፌስቡክ ላይ ይመስላል፡፡ ፌስቡክ አገልግሎት ላይ ከዋለበት ጊዜ ወዲህ፣ በተለይ ባለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት፣ በዓለም ላይ በተለያዩ አገራት የተካሄዱ ምርጫዎችን በዚሁ መድረክ ላይ ከተካሄዱ የሃሳብ ፍጭቶች (ድጋፎችና ተቃውሞዎች) ነጥሎ ማሰብ የሚቻል አልሆነም፡፡ በተለይም በቅርብ ዓመታት ውስጥ በምዕራባውያን አገራት የተካሄዱ ምርጫዎች ከማኅበራዊ ሚዲያ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ትኩረት አግኝተዋል፤ እሰጥ አገባዎችንም አስተናግደዋል፡፡
ከማኅበራዊ ሚዲያ ባህርያት አንፃር መሰል የሃሳብ እሰጥ አገባዎች ተጠባቂ እንደሚሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ማኅበራዊ ሚዲያው ከሚነሱበት ተቃውሞዎች መካከል አንዱ የተጠያቂነትና የኃላፊነት ጉዳይ ነው፡፡ ይህ የሚዲያ ዘርፍ በርካቶች እውነተኛ ማንነታቸውን ደብቀው መልዕክት ማስተላለፍ የሚችሉበት መድረክ እንደመሆኑ መጠን የእነዚህ ግለሰቦችና ቡድኖች ድርጊቶች ለሚያስከትሏቸው ውጤቶች ኃላፊነት የሚወስደው አካል ማንነት ጉዳይ አከራካሪ ሆኖ ዘልቋል፡፡ የሆነው ሆኖ ከዘርፉ ባህርይና ከምርጫ ሰሞን ክስተቶች አንፃር ዓይነተ ብዙ የሆኑ የሃሳብ ፍጭቶች እንኳንስ ሰፊ ነፃነት ባለው የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ይቅርና በመደበኛው የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ (Mainstream Media)ም ሲስተናገድ ይስተዋላል፡፡
በኢትዮጵያም ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሊካሄድ ከ100 ያነሱ ቀናት በቀሩበት በአሁኑ ወቅትም የፖለቲካ ፓርቲዎች ደጋፊዎች በማኅበራዊ ሚዲያ፣ በተለይም በፌስቡክ፣ የሚደግፉት ፓርቲ ተቀባይነት እንዲያገኝ እየተከራከሩና አንደኛው ወገን በሌላኛው ላይ የበላይነት ለመቀዳጀት እየተፋለሙ እንደሆነ ታዝበናል፡፡ ይህ እንቅስቃሴ ደጋፊዎች አመቺ ነው ብለው በመረጡት መንገድ የፓርቲዎቻቸውን ሃሳብ ለመሸጥና ፓርቲያቸውን ተመራጭ ለማድረግ የሚያደርጉት ዘመቻ አካል ነው ተብሎ ይታመናል፡፡ ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድና የሕዝብን ደህንነት አደጋ ላይ በማይጥል መልኩ እንዲከናወን ከተደረገ የሚያሳስብ ጉዳይ አይሆንም፡፡
ይሁን እንጂ ከሰሞኑ በፌስቡክ ሜዳ ላይ የታዘብነው የአንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደጋፊዎች አባላት ሽኩቻ በእውነተኛ የሃሳብ ግብይት ላይ ተመስርቶ ከሚደረግ ክርክር ያፈነገጠ መሆኑን ታዝበናል፡፡ ሁሉም ወገኖች የራሳቸውን ‹‹እውነት›› እያቀረቡ አንዱ በሌላኛው ላይ ነጥብ ለማስቆጠር ሞክረዋል፡፡ የቡድኖቹ መጓተት ምቾት አልሰጠንም ያሉ ሦስተኛ ወገኖችም የፓርቲዎቹ ደጋፊዎችና አባላት በሃሳብ ላይ የተመሰረተ ጤናማ ክርክር እንዲያደርጉና ለሕዝብ የሚጠቅም መንገድ እንዲከተሉ ሲጠይቁ ነበር፡፡
የዴሞክራሲ ስርዓት ባልዳበረባቸው ማኅበረሰቦች ውስጥ መሰል የሃሳብ ንትርኮች ተጠባቂነታቸው የማይካድ ቢሆንም የሃሳብ ፍጭቶቹ ሰላማዊ በሆነና የሕዝብን ደህንነት አደጋ ላይ በማይጥል መርህ ላይ ተመስርተው መካሄድ እንደሚኖርባቸው ማስገንዘብ ይገባል፡፡ ለዚህም ፓርቲዎቹ በኃላፊነት መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ሊዘነጉት አይገባም፡፡
አሉባልታዎች ስር እየሰደዱ ከሄዱ መራጩ ሕዝብ ትኩረቱን ያልረባ ነገር ላይ አድርጎ ድምፁን ለአገር ለማይጠቅም ነገር ላይ እንዳያውለው ያሰጋል፡ ፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ፍትሕ መስፈን የሚችሉት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕዝብን ሲያከብሩ ብቻ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ገዥውም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ራሳቸውን ለሕዝብ ፈቃድና ፍላጎት ማስገዛት አለባቸው፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ ማድረግ ካልተቻለ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ፉክክር ሊኖር አይችልም፡፡ ከዚህ አንፃር ስልጣን ላይ ያለው ገዢ ፓርቲ ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡ ፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአምባገነናዊ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚያደርገው ሽግግር እየተስተጓጎለ ያለው፣ የአሉባልታ መንገድን በመረጡና ኃላፊነት በማይሰማቸው ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሆነ በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡
አሉባልታዎች ሲበዙ ሕጋዊና ሰላማዊ የፖለቲካ ውድድር ችላ ተብሎ የጉልበትና የአሻጥር መንገዶች እንዲመረጡ ምክንያት ይሆናል፡፡ የተወሰነ ቡድንን ጥቅም ለማስጠበቅ በሚደረግ የአሉባልታ ትንቅንቅ በስሙ የሚነገድበት ሕዝብ ወደ ጎን ተገፍቶ የከፈለው መስዋዕትነት ይዘነጋል፡፡ በሕግ ዕውቅና ያገኘው ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በግላጭ እየተደፈጠጠ፣ የጥቂቶች ድምፅ ከመጠን በላይ እየተስተጋባ ችግር ይፈጠራል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ምርጫውን ስኬታማ ለማድረግ ቢያንስ መሰረታዊ የሚባል መተማመን መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት የሕዝብን ደኅንነትና የአገርን ጥቅም ከማስጠበቅ ባለፈ፣ አገር በሕግና በሥርዓት እንድትመራ የማድረግ ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ የሕግ የበላይነት ሲሰፍን ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ከሕገ- ወጥ ድርጊቶች ይታቀባሉ፡፡ ተቋማትን ገለልተኛ አድርጎ በሚፈለገው መጠን ማጠናከርና የሕግ ማዕቀፎችንም ከወቅቱ ቁመና ጋር ማመጣጠን ይገባል፡፡ የመንግሥትና የፓርቲ ሚና መስመሩ መለየት አለበት፡፡ ከሞላ ጎደል እነዚህ ግብዓቶች ሲሟሉ መተማመን ይፈጠርና አሉባልታ ቦታ ያጣል፡፡ አሉባልታዎች ቦታ ሲያጡ ደግሞ የምርጫ ክርክሮችና ውይይቶች በሀቀኛ የሃሳብ ግብይት ላይ አተኩረው እንዲካሄዱና መራጩም ሆነ ሀገር የተሻለ እድል እንዲያገኙ እድል ይፈጠራል፡፡
ስለሆነም ለጤናማ የሃሳብ ግብይት መሰናክል የሆኑ አሉባልታዎችን በመጸየፍ ዜጎች ለአገራቸው የሚጠቅም ውሳኔ እንዲወስኑ እድል መስጠትና አገርም ከሂደቱ ተጠቃሚ እንድትሆን ማድረግ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 13/2013 ዓ.ም