አንተነህ ቸሬ
ለዛሬው ትዝብቴ መነሻ የሆነኝ ወቅታዊውና ከዚህ ቀደም ከአንድም ሁለት ጊዜ እንድጽፍ ያስገደደኝና ትዝብቴን ያካፈልኩበት ጉዳይ ነው። የኢትዮጵያ ጠላት ሆኖ ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ ኢትዮጵያን የገዛው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህ.ወ.ሓ.ት) የኢትዮጵያን፣ በተለይም የትግራይን፣ ሕዝብ ከጠላት በሚጠብቀውና ለትግራይ ሕዝብ ብዙ ውለታ በዋለው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ሰንዝሮ የክፍለ ዘመኑን ዋነኛ ክህደት ፈፅሟል። የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግሥትም ከሃዲውን ቡድን ለሕግ ለማቅረብ በወሰደው የሕግ ማስከበር እርምጃ ቡድኑ ያደራጀው ተዋጊ ኃይል ተደምስሷል፤ሸሽቷል። ከቡድኑ መሪዎች መካከል አንዳንዶቹ እጅ ሰጥተዋል፤ጥቂቶቹ ተይዘዋል፤ሌሎቹ ክህደታቸውን እንደተከናነቡ ከዚህ ዓለም ተሰናብተዋል፤የቀሩት ደግሞ ተደብቀዋል፤እግሬ አውጭኝ ብለው እየሸሹም ያሉ አሉ።
የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል የወሰደው ሕግ የማስከበር እርምጃ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ብዙዎቹ ዓለም አቀፍ (የውጭ) መገናኛ ብዙኃንና ዓለም አቀፍ ተቋማት ስለጉዳዩ የሚያሰራጩት ዘገባ በእውነተኛ መረጃ ላይ ያልተመሰረተ፣ ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ያላስገባና ተገቢ ያልሆነ ፀረ-ኢትዮጵያ ዘመቻ ነው። ይህም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለጉዳዩ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲይዝ (እንዲኖረው) ከማድረጉ ባሻገር የኢትዮጵያ ጠላቶች ‹‹ኢትዮጵያን ለመበታተን ከዚህ የተሻለ ጊዜ/እድል አናገኝም›› ብለው ታጥቀው እንዲነሱና በረጅም ጊዜ ታሪኳ ከጦርነት ይልቅ ሰላምን፤ ከኃይል ይልቅ ንግግርን ለማስቀደም እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ ትብብርንና ወንድማማችነትን የሚያሰፍኑ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲመሰረቱና እንዲጠነክሩ ባላት ቁርጠኛ አቋም የምትታወቀው ኢትዮጵያ ስሟ እንዲጠለሽ በር ከፍቷል።
የቀድሞ ወዳጃቸውን የከሃዲውን የህ.ወ.ሓ.ትን ‹‹ሞት›› አምኖ መቀበል ያቃታቸው ብዙ ምዕራባውያን መንግሥታት፣ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን፣ ጋዜጠኞች፣ ተንታኝ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተብዬዎች በኢትዮጵያ ላይ የከፈቱት ዘመቻ አሁንም ተጠናክሮ ቀጥሏል። ‹‹ውሻ በበላበት ይጮሃል›› እንዲሉ ህ.ወ.ሓ.ት የኢትዮጵያ አድራጊ ፈጣሪ በሆነበት ወቅት የኢትዮጵያን ሐብት እንዳሻቸው እንዲዘርፉት የፈቀደላቸውና ከኢትዮጵያ ሕዝብ ከዘረፈው ገንዘብ እየመዥረጠ ያጎረሳቸው መንግሥታት፣ ድርጅቶችና ግለሰቦች [ውለታቸውን ለመመለስ አልያም ወዳጃቸውን ከሞት አስነስተው በድጋሜ ኢትዮጵያን ለመዝረፍ በማሰብ] ሐሰተኛና የጥላቻ መረጃዎችን፣ ወገንተኛ መግለጫዎችን እንዲሁም አሳፋሪ የክህደት ሪፖርቶችን እያሰራጩና እያወጡ ይገኛሉ።
ከዚህ ቀደም እንደጠቀስኩት ህ.ወ.ሓ.ት በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ባሉ አጋሮቹ በኩል አገሪቱ ልትበታተን እንደሆነና የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ሕዝብ ላይ ጦርነት እንዳወጀ አስመስሎ በርካታ የውሸት መረጃዎች እንዲሰራጩ አድርጓል። እነዚህን መረጃዎች ያዳመጡና የተመለከቱ ብዙ የውጭ አገራት ሰዎችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ደግሞ መረጃዎቹን እንደወረዱ በመቀበል ከእውነት የራቀ ድምዳሜ ላይ ሲደርሱ ተስተውለዋል።
አንድ ጊዜ ተንታኝ፣ ዲፕሎማት፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ጋዜጠኛ፣ ሲያሻቸውም አማካሪ ወይም ተመራማሪ ሆነው የሚንቀሳቀሱ የከሃዲው ቡድን ወዳጆች ያልተደረገውን ነገር እንደተደረገ አድርገው የ‹‹በሬ ወለደ›› ውሸት በማሰራጨት ከሃዲውን ቡድን ከሞት ለማትረፍ ሲጋጋጡ ሰንብተዋል፤አሁንም ቢሆን በአልሞት ባይ ተጋዳይነት እየተፍጨረጨሩ ነው።
እነዚህ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ከህ.ወ.ሓ.ት ጋር ግንኙነት ያላቸው፣ ‹‹ከኤርትራ መንግሥት ጋር ፀብ አለን›› የሚሉ፣ ራሳቸውን ተንታኝ፣ ዲፕሎማት፣ ጋዜጠኛ፣ አማካሪ ወይም ተመራማሪ ብለው የሾሙና በዚሁ ጭምብል የሚንቀሳቀሱ ጥራዝ ነጠቅ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት አምባሳደሮች፤ የሕግ ማስከበር ዘመቻው ከተጀመረበት ቀን ጀምሮ እስካሁን ድረስ የሚያሰራጯቸው መረጃዎች እጅግ አሳዛኝም አሳፋሪም ናቸው። የሀገራችን ሰው ‹‹ነጭ ውሸት›› እንደሚለው ዓይነት መረጃ ሲያሰራጩ ነበር። እነዚህ ህወሓታውያንና ፀረ-ኢትዮጵያውያን የከሃዲውን ወንጀል በመሸፈን ዓለም መላው ኢትዮጵያውያን ስለደገፉት የሕግ ማስከበር እርምጃ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም። አሁንም ይህንኑ እኩይ ተግባራቸው ቀጥለውበታል።
ከዚህ ቀደም ከህ.ወ.ሓ.ት ባለስልጣናት ጋር የቅርብ ግንኙነት እንደነበረው ራሱ የመሰከረው፣ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የአቶ መለስ ዜናዊ አድናቂና ወዳጅ እንዲሁም በዘመነ ህ.ወ.ሓ.ት/ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ የአራት ኪሎ ደንበኞች ከነበሩና ህ.ወ.ሓ.ት ከማዕከል ፖለቲካ በመባረሩ ምክንያት ካኮረፉ የውጭ ሰዎች መካከል አንዱ የሆነውና የመለስ ዜናዊ ፋውንዴሽን ሃሳብ አመንጪው አሌክስ ዲ ዎል፤ ህ.ወ.ሓ.ትን የዲሞክራሲና የመርህ ጠበቃ፤ የኢትዮጵያን መንግስት ደግሞ ፀብ ፈላጊና ራሱን መቆጣጠር የተሳነው አካል አድርጎ ሲያቀርብ ታዝበናል።
በብዙ አገራት የውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ እየገባ በመፈትፈትና ግጭት በመቸርቸር የሚታወቀው፣ ራሱን ‹‹የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አድርጎ›› የሾመውና ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ሰላም ማውረዷ እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተጥሎባት የነበረው ማዕቀብ መነሳቱ ምቾት ያልሰጠውና በአካባቢው ሰላም ከተፈጠረ የሚናገረው እንደሚያጣ ስጋት የገባው ማርቲን ፕላውት፤ ራሱን ‹‹የግጭት ጥናት ፕሮፌሰርና አማካሪ (Professor Of Conflict Studies/Conflict Advisor)›› ሲል የሰየመው፣ የኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ስምምነትን በጥቅሙ ላይ እንደተደቀነ አደጋ ቆጥሮት ስምምነቱን ጥላሸት በመቀባትና ህ.ወ.ሓ.ትን በማሞገስ ተጠምዶ የሚገኘውና የህ.ወ.ሓ.ትን ‹‹የጨረቃ ምርጫ›› የታዘበው የስካንድኔቪያው ሽቲል ትሮንቮል፤ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምስቅልቅል ሴረኛ አሻራቸውን ያኖሩት፣ እ.አ.አ ከ1989 እስከ 1993 ዓ.ም ድረስ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር የነበሩትና ዛሬ የተናገሩትን ነገ የማደግሙት አቋመ ቢሱ ኸርማን ኮኸን፤ ጋዜጠኛና ተመራማሪ ብሎ ለራሱ ሹመት የሰጠው ዊልያም ዴቪሰን፣ ‹‹ተንታኝ፣ ጋዜጠኛ፣ ኢኮኖሚስት … ነን›› የሚሉት ሲሞን ማርክስ፣ ዊል ሮስ፣ ረሺድ አብዲ፣ ዊል ብራውን፣ ዴክላን ዎልሽ፣ ደቪድ ፓይሊንግ፣ ቶም ጋርድነር፣ ሎረን ታይለር፣ ጁሊያ ፓራቪቺኒ፣ ዋሲም ኮርኔት፣ አብዲ እስማኤል ሰመተር፣ ጂዮፍሪ ዮርክ፣ ዛሚራ ራሂም፣ ላቲሺያ ባደር (የሂውማን ራይተስ ዎች የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተር ሆና ሳለች ለወንጀለኞች ጥብቅና የምትቆም)፣ ኒዛር ማኔክ፣ ጀምስ ባርኔት፣ ትሬቨር ትሩማ፣ ቶቢያስ ሃግማን፣ ፊሊፕ ማይን፣ ጀምስ ዶርሴይ፣ አና ካራ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእርዳታ ተቋማት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች … እነዚህና ሌሎች ህወሓታውያንና ፀረ-ኢትዮጵያውያን ቢቢሲን ጨምሮ፣ በሮይተርስ፣ በዘ ጋርዲያን፣ በዘ ቴሌግራፍ፣ በሜይል ኤንድ ጋርዲያን፣ በዘ ኢንዲፔንደንት፣ በሲኤንኤን፣ በዘ ኒው ዮርክ ታይምስ፣ በአሶሺየትድ ፕሬስ፣ በዘ ዋሺንግተን ፖስትና በሌሎች በርካታ መገናኛ ብዙኃን (ድረ-ገፆችን ጨምሮ) እንዲሁም በግል የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቻቸው በኩል የከሃዲውን ወንጀል በመሸፈን ዓለም መላው ኢትዮጵያውያን ስለደገፉት የሕግ ማስከበር እርምጃ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግና ህ.ወ.ሓ.ትን ለማትረፍ ሲጥሩ ከርመዋል፤አሁንም ቀጥለዋል።
በትውልድ/በዜግነት ኢትዮጵያውያን ሆነው ሳለ የህ.ወ.ሓ.ት ጠበቃና የኢትዮጵያ ጠላት ሆነው የቀረቡ የእናት ጡት ነካሽ ባንዳዎችና የታሪክ አተላዎችም የሐሰት ዘመቻውንና ውንጀላውን እያስተባበሩ ይገኛሉ። በኢትዮጵያ መንግሥትና በኢትዮጵያውያን ድጋፍና ይሁንታ የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ዳይሬክተር ለመሆን በቅተው የአገራቸውን ጥቅም አሳልፈው በመስጠት ለአገራቸውና ለወገናቸው ደጀን በሆነው የመከላከያ ሰራዊት ላይ አሰቃቂ ጥቃት የፈፀመውን ህ.ወ.ሓ.ትን ለማትረፍ እንቅልፍ አጥተው እየሰሩ የሚገኙት ዶክተር ቴዎድሮስ ኣድሓኖም፣ የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታና የአቶ መለስ ወዳጆችን ተጠግተው ብራሰልስ እየተመላለሱ ደጅ መጥናት ከጀመሩ የሰነባበቱት አምባሳደር ብርሃነ ገብረክርስቶስ፣ ለብዙ ዓመታት በኒው ዮርክና በዋሺንግተን ዲሲ ‹‹በአምባሳደርነት›› የሰሩትና ረብጣ ዶላሮችን ተቀብለው የመንግሥታትን ገጽታ ለመገንባት ላይ ታች የሚሉ ድርጅቶች መነኻሪያ በሆነው የዋሺንግተን ዲሲ አካባቢ ሲታዩ የከረሙት ፍስሃ አስገዶም፣ የሰላምና ደህንነት ጉዳዮች አማካሪ እንዲሁም የስደተኞች ፖሊሲ አዋቂ ነው የሚባለውና የትግራይን ‹‹ዲ ፋክቶ ስቴት (De Facto State)››ነት የወጠነው እንዲሁም ከበርካታ የአውሮፓና የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ግንኙነት ያለው ዶክተር መሐሪ ታደለ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ‹‹የሐሰት መረጃ እያሰራጩ ስለሆነ በሕግ እፋረዳቸዋለሁ›› ብሎ የእስር ማዘዣ ያወጣባቸው ሌሎች ምሁራን፣ ጋዜጠኛና ተንታኝ ተብዬዎችም … ህ.ወ.ሓ.ትን ወደ መንበሩ ለመመለስ ከሚካሄደው ፀረ-ኢትዮጵያ ዘመቻ መሪዎች መካከል ይመደባሉ። ይህ በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተ የክህደት ዘመቻ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለሕግ ማስከበር ዘመቻው የጠራ መረጃ እንዳያገኝ መሰናክል ሲሆንና በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ቀላል የማይባል ጫና ሲፈጥር ታዝበናል።
የእነዚህ ፀረ-ኢትዮጵያ አካላት የሐሰት ክስ ከማኅበራዊ ሚዲያና ከመገናኛ ብዙኃን ዘመቻ አልፎ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት (State Department) ድረስ ዘልቆ በመግባት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን ቅንጣት ታክል ሳያፍሩና ሳያደናቅፋቸው ‹‹የዐማራ ክልል ኃይሎች ከትግራይ ይውጡ›› እንዲሉ ምክንያት ሆኗል። ይህ የብሊንከን ማሳሰቢያ ደግሞ የህ.ወ.ሓ.ት ሰዎች ደጋግመው የሚናገሩትና ‹‹ከሁሉም ቀዳሚ›› ብለው የሚያስቀምጡት ጥያቄ ነው። ‹‹የዐማራ ክልል ኃይሎች ትግራይ ክልል ውስጥ ገብተዋል ወይንስ አልገቡም›› የሚለው ጉዳይ አስፈላጊ ባለመሆኑ እርሱን ትተነው ስለጥያቄው ተገቢነት እንጠይቅ። የዐማራ ክልል ኃይሎች ትግራይ ክልል፣ የኦሮሚያ ክልል ኃይሎች ደቡብ ክልል፣ የአፋር ክልል ኃይሎች ሐረሪ ክልል፣ የቤኒሻንጉል ክልል ኃይሎች ሱማሌ ክልል ቢገቡ አሜሪካን ምን አገባት?! ይህ የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ መሆኑ ተዘንግቶ ነው ወይንስ ‹‹ህ.ወ.ሓ.ትን ለማትረፍ ማንኛውንም ነገር እንደርጋለን›› የሚል እብሪትና ድንቁርና ነው?! [በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ንፁሃን ዜጎችን መከራ ዝቅ አድርጎ የማየትም ሆነ ‹‹ለዚህ ሁሉ ችግር ምክንያቱ/ተጠያቂው ማን ነው?›› የሚለውን ጉዳይ አደባብሶ የማለት ፍላጎት የለኝም!]
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዚህ አስቂኝ የአሜሪካ ጥያቄ በሰጠው ምላሽ፤ ‹‹አሜሪካ በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ማውጣቷ በተለይም የአማራ ክልል ኃይሎች ስምሪት በመግለጫው መጠቀሱ የሚያሳዝን ነው። እንደ ሉዓላዊት አገር ይህ የኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ ኃላፊነት ነው፤ ኢትዮጵያ በግዛቷ ውስጥ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የትኛውንም የጸጥታ መዋቅር ማሰማራት የመንግሥት ኃላፊነት ነው። የፌደራሉ መንግሥት በሕገ-መንግሥቱ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት ሰላም እና ደኅንነትን በማረጋገጥ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓትን ያስከብራል፤ይህን ኃላፊነት ታሳቢ ባደረገ መልኩ በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ተልዕኮ ተከናውኗል›› ብሏል።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲም ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ ‹‹ሱዳን፤ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ መግባቷን በግልጽ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ባሳወቀችበት ወቅት ጉዳዩን ከቁብ ያልቆጠረ ኃይል በውስጥ ጉዳይ ‹ግቡ … ውጡ› ሲል ይገርማል … ‹ህግ አስከብራችኋል› ብሎ ‹ውጡ፣ ክፈቱ› ሊል አይችልም›› ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በበኩሉ ኢትዮጵያ ወገንተኛ የሆነ ጣልቃ ገብነትን እና በሀገር እና መንግስት ላይ የሚካሄድን ፖለቲካዊ ወገንተኝነት ያለውን ስም የማጥፋት ዘመቻ እንዲሁም ህግን የማስከበር እርምጃውን ዝቅ ለማድረግ የሚካሄድን አሉታዊ ዘመቻ እንደማትቀበል አስታውቋል።
እንግዲህ የብሊንከን መግለጫ ህወሓታውያን ከመንግሥታትና ከተቋማት ጋር ምን ያህል በቁርኝት እየሰሩ እንደሆነ የሚያመለክት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን (አምባሳደሮችና ዳያስፖራው ጭምር) ለኢትዮጵያ ጥቅም መከበር እያደረጉት ያለው ጥረት ደካማ መሆኑን የሚያሳይም ነው።
ከሳምንታት በፊት በዚሁ አምድ ላይ ባሰፈርኩት የትዝብት ጽሑፌ፤ በውጭ አገራት ከሚኖሩ በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን መካከል የውጭ መንግሥታት፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለሕግ ማስከበሩ እርምጃ እውነተኛና ሚዛናዊ መረጃ እንዲኖራቸውና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ለድርድር እንደማይቀርብ የሞገቱ ባለስልጣናት፣ ተቋማት፣ ምሁራን፣ ቡድኖችና ግለሰቦች እጅግ በጣም ጥቂት እንደሆኑ ገልጫለሁ።
በዚህ ረገድ በአውሮፓ የተለያዩ ተቋማት የሚሰሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ ፕሬዝደንት የፃፏቸው ደብዳቤዎች እንዲሁም የኢትዮጵያውያን ዲያስፖራ የኮቪድ-19 ከፍተኛ የአማካሪዎች ካውንስል (Ethiopian Diaspora High Level Advisory Council On COVID-19) እና የኢትዮ-አሜሪካ ሲቪክ ካውንስል (Ethiopian-American Civic Council) ያወጧቸው መግለጫዎች ከቀዳሚዎቹ ተርታ ይጠቀሳሉ። ከእነዚህ መግለጫዎች በኋላ ለረጅም ጊዜያት ያህል ያየነውና የሰማነው ጉልህ እንቅስቃሴ አልነበረም። የህ.ወ.ሓ.ት ደጋፊዎች የፈጠሩት ‹‹ጫና›› ንዝረት ከተሰማ በኋላ ሰሞኑን በተለያዩ የአውሮፓ፣ የሰሜን አሜሪካና የአውስትራሊያ ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ምዕራባውያን አገራት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ለመግባት የሚያደርጉትን ሙከራ እንደሚቃወሙና የህ.ወ.ሓ.ትን ሐሰተኛ መረጃ የማሰራጨት ተግባራት እንደሚኮንኑ በሰላማዊ ሰልፎች ገልፀዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን ምሁራን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ የሚቃወም ደብዳቤ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት፣ ለአውሮፓ ኅብረትና ለሩሲያ ማስገባታቸው ተሰምቷል። የኢትዮጵያ-አሜሪካውያን የዜጎች ምክር ቤት በበኩሉ በመንግሥታቱ ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ለሆኑት ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ በፃፈው ደብዳቤ፤ የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ገንቢ ሚና እንዲጫወት እና ከኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ጎን እንዲቆም ጠይቋል። ምክር ቤቱ ቀደም ሲል ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በፃፈው ደብዳቤም ለተፈጠረው ችግር ሁሉ ተጠያቂው ህ.ወ.ሓ.ት እንደሆነ ገልፆ አሜሪካ የኢትዮጵያን መንግሥት ጥረት እንድትደግፍ ጥሪ አቅርቧል።
ይሁን እንጂ እነዚህ እንቅስቃሴዎች ጅምር እንጂ በቂ የሚባሉ አይደሉም። ህወሓታውያን ካሰማሩት የቅስቀሳ ጫና ስልት መጠን አንፃር እነዚህ ጥረቶች በቂ አይደሉም! በጭራሽ በቂ አይደሉም! ከመጀመሪያው ጀምሮ ይህ የውሸት መረጃን የማሰራጨትና የተሳሳተ ግንዛቤን የመያዝ ችግር የተፈጠረው በመንግሥትና በኢትዮጵያውያን ድክመት እንዲሁም በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንና ተቋማት እንዲሁም በመንግሥታት ዓላማና የግል ፍላጎት ምክንያት ነው።
ሕግ የማስከበሩ እንቅስቃሴ ብዙ የሴራ ትንታኔዎችን የሚጋብዝና ነገሩ የአፍሪካ ቀንድ ጉዳይ ስለሆነ ጠንካራ የመረጃ ዝግጅትና ጥንቃቄን የሚፈልግ ተግባር ነው። ስለሆነም እርምጃው ከመንግሥት ጥረት ባሻገር የምሁራንንና የዲያስፖራውን ኅብረተሰብ ጨምሮ የመላ ዜጎችን ተሳትፎና ንቅናቄ ይፈልግ ነበር። ይሁን እንጂ የምሁራንና በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮያውያን ተሳትፎ እንደተጠበቀው ሳይሆን መቅረቱን ታዝበናል።
ኢትዮጵያን በተለያዩ አገራት ከወከሉ አምባሳደሮች መካከል በተደጋጋሚ በመገናኛ ብዙኃን ላይ ቀርበው ስለሕግ ማስከበር እርምጃው ጥሩ ጥሩ ማብራሪያዎችን የሰጡት በጣም ጥቂቶቹ ናቸው። ይህ በዲፕሎማሲው መስክ ገና ብዙ ስራ እንደሚቀረን ማሳያ ነው።
ህወሓታውያን የቡድናቸውን ክህደት ክደውና የሀሰት መረጃ ይዘው በኢትዮጵያ ላይ ጫና ሲፈጥሩ ‹‹ኢትዮጵያን እወዳለሁ … ኢትዮጵያ አገሬ/እናቴ …›› የሚለው ወገን በዚህ ደረጃ የተዳከመው ለምን እንደሆነ ማወቅ ያስቸግራል። ወትሮውንም ቢሆን ኢትዮጵያ የምትጎዳው በጠላቶቿ ጥንካሬ ሳይሆን ‹‹ኢትዮጵያን እንወዳለን … ባለቤት ነን›› በሚሉት ወገን ደካማነት ነው!
በሕግ ማስከበር እርምጃው ወቅት የታየው የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን መረን የለቀቀ ፀረ-ኢትዮጵያ ዘመቻ እንዲሁም ኢትዮጵያውያን ለዘመቻው የሰጠነው ደካማ ምላሽ፤ የዓለም ፖለቲካን፣ በተለይም ኢትዮጵያ የተጋረጡባትን ዘርፈ ብዙ ችግሮችን፣ የመረዳት ችሎታችንንና በዲፕሎማሲው ዘርፍ ያለን አቅም ያመላከተ በመሆኑ አሁኑኑ የሁሉም አገር ወዳድ ወገን አስቸኳይ ተሳትፎና ትጋት ይፈለጋል!
አዲስ ዘመን መጋቢት 6/2013