ምህረት ሞገስ
የኮቪድ 19 ክትባት ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ሰምተናል። በነገው ዕለት ማለትም መጋቢት 4 ቀን 2013 ዓ.ም ክትባቱ እንደሚጀመር የተገለፀ ቢሆንም፤ ክትባቱ ምን ያህል አስተማማኝ ነው? የሚሰጠው ለማን እና በምን መስፈርት እንደሆነ በቂ መረጃ ባለማግኘታችን መረጃውን ብትሰጡን የሚል ጥያቄ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ቀርቧል።
ምንም እንኳ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ክትባቱ የሚሰጠው ለጤና ባለሞያዎች፣ ተጓዳኝ ህመም ላለባቸው ሰዎች እና በዕድሜ ለገፉ ሰዎች ነው ቢባልም፤ እነዚህም ቢሆኑ ቁጥራቸው ከፍተኛ በመሆኑ የሚለዩት እንዴት ነው? በማለት ምላሹን ለማግኘት በቀጥታ ይመለከታቸዋል ብለን ወዳመንንባቸው ጤና ጥበቃ ሚኒስትር እና ወደ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጥያቄውን አቅርበን ምላሽ አግኝተናል።
የጤና ሚኒስትሯ ክትባትና ተያያዥ ነገሮች ከፍተኛ አማካሪ ዶክተር ሙሉቀን ዮሃንስ እንደተናገሩት፤ ለመንግስትም ሆነ ለጤና ሚኒስቴር ክትባቱ ለሁሉም ለማዳረስ ከባድ የሆነበት ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ የክትባት እጥረት በመኖሩ እንጂ መንግስትም ሆነ ጤና ሚኒስቴር ሁሉንም ሕዝብ መከተብ ቢቻል ጥሩ እንደነበር ያምናሉ። ነገር ግን ኮቫክስ የተሰኘው ዓለም አቀፍ ትስስር ኢትዮጵያን ጨምሮ ለ92 በማደግ ላይ ላሉ እና ለታዳጊ አገሮች ክትባቱን ያቀረበው በጣም ተጋላጭ ለሆኑ 20 በመቶ ለሚደርሱ የህብረተሰብ ክፍሎች ብቻ ነው።
እነዚህ ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች እነማን ናቸው? የሚለዩትስ በምን መስፈርት ነው? የሚለው ትልቅ አጀንዳ ሆኖ የቆየ መሆኑን በማስታወስ፤ ብዙ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈውበት የተቀመጠ መሆኑን ያመለክታሉ።
እንደዶክተር ሙሉቀን ገለፃ፤ ዋናው እና ትልቁ ጉዳይ ክትባቱ አነስተኛ በመሆኑ ከክትባቱ የሚገኘውን ጥቅም ከፍ ማድረግ ትልቅ ቦታ ተሰጥቶታል። እንዲሁ የተገኘው ሁሉ ይከተብ ከተባለ ከክትባቱ የሚገኘው ጥቅም ከፍተኛ ላይሆን ይችላል። ለምሳሌ አንድ ህፃን ልጅ ወይም ወጣት ልጅ ቢከተብ ተጓዳኝ በሽታ እንዳለበት ሰው ያን ያህል ላይጠቅመው ይችላል። ምክንያቱም ክትባቱ ሞትን ለመቀነስ በመሆኑ ቢከተብ የተሻለ የሚሆነው በበሽታው የበለጠ ተጎጂ የሚሆነው ሰው ነው። ይህ አንደኛው መርህ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ፍትሃዊ ተደራሽነትን በሚመለከት ነው።
በአዲስ አበባም ሆነ በየትኛውም አካባቢ ያለ የጤና ችግር ያለበት ሰው ክትባቱን ማግኘት እንዳለበት ይታመናል። ስለዚህ ክትባቱ ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ተደራሽ ይሆናል ማለት ነው ይላሉ። በሌላ በኩል ግልፅነትም መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን በማስታወስ፤ ያገባኛል የሚሉ ባለድርሻ አካላት በሙሉ እንዲሳተፉበት የተደረገ መሆኑን ያብራራሉ።
ከአጠቃላይ ከማህበራዊ ህይወት እና ከጤና አንፃር በመመልከት መጀመሪያ ሊታዩ የሚገባቸው የጤና ባለሞያዎች መሆናቸውን መወሰኑን በማስታወስ፤ ሌሎችም በቅድሚያ ተጠቂ ይሆናሉ ተብለው የተገመቱ በዕድሜ የገፉ ዕድሜያቸው 60 አካባቢ የደረሱ ሰዎችም ክትባቱን የሚያገኙበት ሁኔታ እንደሚኖርም ያብራራሉ።
ተጨማሪው ጉዳይ ተደራራቢ የጤና ችግር ያለባቸው ሰዎች መሆናቸውንም በመጠቆም፤ ይህ ሲባል ሁሉም የጤና ችግር ያለባቸው በሙሉ ይካተታሉ ማለት እንዳልሆነ፤ ያለው ሁኔታ እንደሚሳየውም የተወሰኑ የጤና ችግር ያለባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በይበልጥ ተጋላጭ መሆናቸው የተለየ መሆኑን ይገልፃሉ።
እንደ ዶክተር ሙሉቀን ገለፃ፤ ለምሳሌ እንደአስም ያለ ለረዥም ጊዜ የቆየ የመተንፈሻ አካል ችግር ያለባቸው ሰዎች ክትባቱን ያገኛሉ። ምክንያቱም የዓለም አቀፉ ተሞክሮም የሚያሳየው ለከፍተኛ አደጋ የሚጋለጡት በተደጋጋሚ የመተንፈሻ ችግር ያለባቸው ሰዎች በመሆናቸው ነው።
ሌላው የረዥም ጊዜ የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች፤ እነዚህም በደረጃ የሚታዩበት ሁኔታ ይኖራል። የደም ግፊት ያለባቸው ሰዎች በሽታው ከልብ ጋር የሚገናኝ በመሆኑ ለአደጋ የመጋለጣቸው ዕድል ሰፊ በመሆኑ እነርሱም ክትባቱን ከሚያገኙት መካከል ተጠቃሾች ናቸው። ሌላው የካንሰር ህክምና የወሰዱና ረዥም ጊዜ የቆዩ ኬሞ ቴራፒ እና ራዲዮ ቴራፒ የወሰዱ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም የኤች አይ ቪ ኤድስ መድኃኒትን እየወሰዱ ያሉ ወገኖችም ክትባቱ የሚሰጣቸው መሆኑን ያስረዳሉ።
እንደዚህ በዝርዝር ቢለዩም፤ እነዚህስ የሚዳረሱት እንዴት ነው? በሚለው ላይ በደንብ ለመስራት የተዋቀረ ክሊኒካል አድቫይዘሪ ቲም መኖሩንም ያመለክታሉ። ቡድኑ ውስጥ በጣም የተለያዩ በሽታዎች ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች የተካተቱበት ሲሆን፤ በቡድኑ የተዘጋጀ መመሪያ መኖሩን ያመላክታሉ። መመሪያው ቅድሚያ ይሰጣቸዋል የተባሉትን አካላት በመረጃ በመደገፍ በሚያወጣው መሰረት ክትባት የሚሰጥ መሆኑን አብራርተዋል።
መነሻውን ቻይና እንዳደረገ የሚነገርለት ኮቪድ እስከ አሁን ከ118 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን በክሏል። በበሽታው ከተያዙት መካከል በዓለም ላይ የ2 ሚሊዮን 600ሺህ ሰዎች ሕይወት አልፏል። 94 ሚሊዮን 270 ሺህ ሰዎች ቢያገግሙም አሁንም ድረስ በበሽታው የተያዙ የህሙማን ቁጥር 21 ሚሊዮን አካባቢ መሆናቸውን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያመላክታል። በሽታው በፍጥነት የሚተላለፍ በመሆኑ ከሟቾች ቁጥር ባሻገር የህሙማን ቁጥር መጨመር የዓለም ስጋት እንደሆነ ቀጥሏል።
ነገር ግን በተወሰነ መልኩ ስጋቱን የሚቀንስ የክትባቱ መፍትሔ መገኘቱ ቢያስተነፍስም፤ እጥረት በመኖሩ አሁንም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ቀድሞ መከላከል ላይ መሰራት እንዳለባቸው እየተገለፀ ይገኛል። ክትባቱን በአስተማማኝ መልኩ በማግኘት ለዓለም መፍትሔ ካስገኙት መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሱት አሜሪካ፤ ጀርመን ፤ ሩሲያ፣ እንግሊዝ እና ስዊድንን አስከትለው ሙሉ ለሙሉ ኮቪድን መከላከል የሚያስችል ክትባት ማምረት የቻሉት፤ ቻይናን ጨምሮ ብራዚል እና ህንድም ክትባቱን ማምረት ቢችሉም ዛሬም መፍትሔያቸው ለመላው ዓለም በቂ አለመሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ክትባቶቹ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው ኮቪድን ለመከላከል ፍቱህነታቸው ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም። ለዚህም ይመስላል በመላው ዓለም መድኃኒቱ እየተሰራጨ የሚገኘው። እስከ አሁን ወደ 340 ሚሊዮን ሰዎች ክትባቱን ወስደዋል። ኢትዮጵያም 2ነጥብ 2 ሚሊዮን የኮቪድ-19 ክትባት አስገብታ ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ለማሰራጨት ዝግጅቷን አጠናቃለች።
በዚህ ገፅ ላይ አንባቢያን በሚፈልጉት ጉዳይ ላይ ጥያቄ የሚያቀርቡበት እና እኛም የሚመለከተውን አካል መልስ ጠይቀን የምናስነ ብብበት ሲሆን፤ ማንኛውም ሰው በስልክ ቁጥር 0111264326 በመደወል ጥያቄ እና አስተያየት ማቅረብ ይቻላል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 3/2013