ኢትዮጵያ በ1888 ዓ.ም የጣሊያን ቅኝ ገዥ ያዘመተውን ጦር ድል በማድረግ በዓድዋ ጦርነት በዓለም እጅግ ወሳኝ ድል አስመዘገበች፡፡ የዓድዋ ድል ሊሳካ የቻለው እኛ ኢትዮጵያውያን የምንታወቅባቸው አንድነታችን እና ህብረታችን መንፈስ ነው።
ዛሬ ላይ ሆነን ዓድዋን ስንዘክር የእኛ የአንድነት መንፈስ ለጦርነት መዝመት ብቻ ሳይሆን ልማትንና ብልፅግናን ለማረጋገጥ የሚያስችል አቅም የሚፈጠርበት እንደሆነ በማሰብ ነው።
ኢትዮጵያ እንደ ቀደም ገናናነቷ የሚመጥናትን ዕድገትና ብልፅግና ለማስመዝገብ በርካታ ሀገር በቀል ፕሮጀክቶች ተቀርፀው ግማሾቹ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቁ ገሚሶቹ በፈጣን ግንባታ ላይ ያሉ ሲሆን ጥቂቶች ደግሞ በዝግጅት ምዕራፍ ላይ ያሉም አሉ። የእነዚህ ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ ሀገሪቷ ከድህነት የምትላቀቅበት ምዕራፍ ላይ መድረሷን የሚያበስር ነው።
የዓድዋ ድል በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ አዲስ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መነቃቃትን የፈጠረ የለውጥ ሂደት ሲሆን የመጀመሪያው የዓድዋ ጦርነት ድል ፀረ-ቅኝ አገዛዝ እንቅስቃሴዎችን እና ትግልን ያነቃነቀ እንደነበረ ሁሉ በዚህ ዘመን ደግሞ በሀገሪቷ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ የፍትህ ንቅናቄዎችን የሚያነሳሳ ሆኖ እናገኘዋለን።
ስለሆነም በኢትዮጵያ ያሉ ሁሉም ማህበረሰቦች እንደቀድሞው ሁሉ አንድነታችንን ጠብቀን ለልማት ከተነሳንና ድህነትን አሸንፈን የምንጠብቀውን ብልፅግና ካመጣን ዳግማዊ የዓድዋ ድል አድርገን ልናስበው እንችላለን፡፡
ከዓድዋ ድል መቶ ዓመታት በኋላ ግንባታው የተጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ድህነትን አሽቀንጥረው የሚጥሉበት አንዱ ትልቅ ፕሮጀክት ሲሆን በገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ውስጥ ተግባራዊ ከሚደረጉት የወንጪ፣ ጎርጎራ እና ኮይሻ ፕሮጀክቶች በውስጣቸው የሚይዟቸው የቱሪስት መስህቦች እና የሚፈጥሩት የሥራ ዕድል ወደ ዕድገት የምንሸጋገርባቸው ምዕራፎች ናቸው።
ነገር ግን የሕዝቦችን አንድነት የሚሸረሽሩ የሃሰት ትርክቶች፣ ያንን ተከትሎ ብሔርን መሠረት ያደረጉ እዚህም እዚያ የሚከሰቱ ግጭቶች፣ በውይይት ችግርን የመፍታት ልምድ አለመኖር፣ ለሕግ ተገዢ መሆን አለመቻልና ሌሎች ውስጣዊና ውጫዊ መንስዔዎች ከፊት ለፊታችን የተደቀኑ የልማት ተግዳሮቶች እንደሆኑ እሙን ነው። እነዚህን ተግዳሮቶች ለማለፍ የተጀመረውን አገር በቀል የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ተግባራዊ ከማድረግ ባለፈ ዘላቂ የሆኑ የኢኮኖሚ አማራጮችን መፈለግና ማስፋት ያስፈልጋል።
በአሁኑ ወቅት ያጋጠሙንን ተግዳሮቶች መፍታት፣ አዳዲስ ዕድሎችን መፍጠርና እስካሁን የተገኙ ስኬቶችን ቀጣይነት ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑ ላይ ሊተኮርበት ይገባል። የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባቶችን ማስተካከል፣ መዋቅራዊ ማነቆዎችን መፍታት፣ አዳዲስ ዕድሎችንና የዕድገት ምንጮችን ለመፍጠር አስፈላጊውን መደላድል ማበጀት ተገቢ ነው።
የእስካሁን ስኬቶቻችንን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የፖሊሲና ተቋማዊ ማዕቀፎችን ደረጃ ማሻሻል የግድ የሚል ነው። ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ቀጣይነት የሚረጋገጠው ደግሞ በመንግሥት የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን በቶሎ ለማጠናቀቅ በትጋት ሲሰራ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።
ዕድገቱም ዘላቂነት እንዲኖረው የማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛን መጠበቅ የግድ የሚል በመሆኑ የዕድገቱን ምንጭ ዘላቂነት ባለው መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ ድል የጋራ ትግልን ስለሚጠይቅ መንግሥትም ሆነ ሁሉም ኅብረተሰብ ኃላፊነቱን ሲወጣ ፈጣንና ቀጣይ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ እንደሚቻል እሙን ነው።
የዓድዋን ድል ልንደግመው የምንችለው ከሃሰት ትርክቶች ተላቀን ዳግም በድህነት ላይ አሸናፊነትን ስንቀዳጅ በመሆኑ ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ ፕሮጀክቶችን መደገፍ ከሕዝብ የሚጠበቅ ነው። መሠረታዊ የኅብረተሰብ አገልግሎቶችን ማሟላት ደግሞ እስከታችኛው የመንግሥት መዋቅር የሚደርስ ኃላፊነት መሆኑን መዘንጋት የለበትም።
የዓድዋ ጀግኖች የዚህ ዓይነት መስዋዕትነት ባይከፍሉ ኖሮ ዛሬ ላይ የምናገኛት ኢትዮጵያ በዚህ ሁኔታ የራሷን ባህልና ትውፊት ጠብቃ ባልተገኘች ነበር። ከዓድዋ የምንወስደው አንዱ ነገር ነፃነት ምን እንደሆነ የገባው የዚያን ዘመኑ ትውልድ በከፈለው መስዋዕትነት በዚህ ዘመን ላለነው ትውልድ ክብር አውርሰውን እንዳለፉ ሁሌም የማይዘነጋ መሆኑ ነው።
የድል መንፈስና አልፋና ኦሜጋ የሆነው የዓድዋ ድል በተለይም ውስጣዊ ችግሮችን ወደ ጎን በመተውና በውይይትና በመነጋገር በመፍታት ዋነኛ ተግዳሮታችን የሆነውን ድህነት ለመፋለም በብሔር፣ በሃይማኖት ወዘተ ሳንከፋፈል በአንድነት ለመስዋዕት መዘጋጀትና በጋራ ትግል ሁሉን አካታች የሆነን ብልፅግና ማምጣት እንደሚኖርብን የሚያስተምር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል!
አዲስ ዘመን የካቲት 25/2013