የዛሬ 125 ዓመት በዚህች ቀን የኢትዮጵያ ሕዝቦች በአንድነት ከፍ ባለ የሀገር ፍቅርና የነፃነት መንፈስ ለመሀላ ማህተማቸውና ከሁሉም በላይ ውድ ለሆነችው ሀገራቸው በከፈሉት ታላቅና አኩሪ መስዋእትነት ፍሬ አፍርቶ ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ጎህ ፈንጣቂ የሆነውን የዓድዋን አንጸባራቂ ድል ለመላው ዓለም አብስረዋል።
በማንም አእምሮ ያልታሰበችው ይህች ቀን የኢትዮጵያውያን የሀገር ፍቅርና የአትንኩኝ ባይነት መንፈስ፣ ከዚህም በላይ የአንድነትና የነፃነት መሻት ጥግ ምን ያህል ለተጋድሎ መስዋዕትነት አቅም እንደሆነና የአይቻልምን የአስተሳሰብ ሸክም መናድ የሚያስችል ብቃት እንዳለው ለዓለም ሕዝብ በተጨባጭ ማስተማር ያስቻለች ነች።
የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ የሚለው ሥም በመላው ዓለም የክብር፣ የሕብረት፣ የአንድነት፣ የነፃነትና የሉዓላዊነት ተምሳሌት እንዲሆን ያደረገ፤ በብዙ አይቻልም አስተሳሰቡ ጫና ውስጥ ጎብጠው ለነበሩ ጥቁር ሕዝቦች ቀና ብለው እንዲሄዱና አዕምሯቸው ላይ ተጣብቆ የነበረውን የአይቻልም ቅርፊት መንግሎ የጣለ፣ ለፓን አፍሪካኒዝም መወለድ እርሾ የሆነና ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች በራስ የመተማመንና የጥንካሬ መሠረት የሆነም ነው፡፡
ከዓድዋ ድል ማግስት በዓለም የፖለቲካ መድረኮች ጥቁሮች ጎልተው መውጣትና አንገታቸውን ቀና አድርገው ድምጻቸውን ማሰማት ጀምረዋል። በአሜሪካና በእንግሊዝ የጥቁሮች ሕብረታዊ ስብሰባዎች መጀመርና የአፍሪካ አንድነት እሳቤ ማቆጥቆጥም የዓድዋ ድል ትሩፋቶች ናቸው፡፡
የኋላ ዘመኖቹ የእነ ማርክስ ጋርቬይ የነፃነት የአስተምህሮ አስኳል፤ የእነ ክዋሜ ንክሩማህ እና የጆሞ ኬንያታ የወጣትነት የትግል ፋና ኢትዮጵያኒዝም የመነጨው ከዚሁ ዓድዋ ድል አንስቶ ነው፡፡ የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እና የአሁኑ የአፍሪካ ሕብረትም የምስረታው ጥንስስ የዓድዋ ድል የወለደው ኢትዮጵያኒዝም ፍሬ ነው፡፡
አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሰንደቅ ዓላማም የጥቁሮች የነፃነት ምልክት የመሆኑ ምስጢር ይኸው አንጸባራቂ ድል በጥቁር ሕዝቦች ልብ ውስጥ የለኮሰው የብርሃን ነጸብራቅ ነው። አብዛኞቹ አፍሪካውያን ሀገሮች ከነፃነታቸው ማግስት ብሔራዊ ምልክታቸው ያደረጉትም ለዚህ ነው፡፡ የዓድዋ የነፃነት መንፈስ ከደቡብ አፍሪካ ጀምሮ በመላው አህጉሪቱ በኢትዮጵያ ሥም በርካታ የጥቁሮች ራስ-ገዝ አብያተ-ክርስቲያናት እንዲመሰረቱ ፋና ወጊም ሆኗል፡፡
ድሉ ከምዕራብና ከምሥራቅ፣ ከሰሜንና ከደቡብ የዘመቱ፤ በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በመልክና በሞያ ኅብር የሆኑ፤ ነገር ግን ኢትዮጵያን ከቅኝ ግዛት የማዳን የአንድነት ዓላማ ያላቸው ኢትዮጵያውያን በአንድነት ተፋልመው በጋራ ያስገኙት አንጸባራቂ ድል ነው።
በዓድዋ ዘመቻ ከ10 ዓመት ሕፃን እስከ 90 ዓመት አዛውንት ተካፍለዋል። ማየት የቻሉት ብቻ ሳይሆኑ ዓይነ ሥውራንም ዘምተዋል። ሴቶች ከስንቅ አዘጋጅነት እስከ ጦር መሪነት ከወንድሞቻቸው ጋር በቆራጥነት የተሰለፉ ሲሆን የድሉ ምስጢርም ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ነበር።
በዚሁ ታላቅ የነፃነት ፍልሚያ ልዩነቶቻቸውን ወደጎን አድርገው የእስልምናና የክርስትና የሃይማኖት አባቶች ከጸሎት እስከ ግንባር በአንድነት ተሳትፈዋል። አዝማሪዎች በአንድ በኩል የሠራዊቱን ሞራል እየገነቡ፣ በሌላ በኩል ታሪኩን በግጥምና በዜማ እየከተቡ ዘምተዋል። ሌላው ቀርቶ ሽምጥ ተጋላቢዎቹ ፈረሶቻችን በወኔ በእሳቱ መሐል ሲገኙ፣ የጭነት አጋሰሶች በፈርጣማ ትከሻዎቻቸው ስንቅ ተጭነው፣ ሌሎችም እንስሳት መሥዋዕት ሆነው ዓድዋን የድል ቦታ፣ ኢትዮጵያን የድል ባለቤት አድርገዋል።
በውጊያው ጊዜ ከቅድመ አያቶቻችን መካከል አንዳቸው ጎድለው ቢሆን ኖሮ ዛሬ ዓድዋም፣ የዓድዋ ልጅነትም ከእናካቴው ባልኖሩ ነበር። የሀገርን ጥሪ እኩል ሰምተው በጋራ ባይዘምቱና ዓድዋ ላይ የድል ሰንደቅ ባይተክሉ ኖሮ፥ ዛሬ የምናከብረው የድል ቀን መሆኑ ቀርቶ እንደሌሎች አፍሪካውያን የነፃነት ቀን በሆነ ነበር።
በድል ቀንና በነፃነት ቀን መካከል ያለው ልዩነት የሰማይና የምድር ያህል ነው። ዓድዋ ከእኛ የድል ሰንደቅነት አልፎ ተርፎ ለብዙ የነፃነት ቀኖች እንደ ምንጭ ሆኖ ያገለገለ፣ ለጸረ ቅኝ አገዛዝ እንቅስቃሴዎች ፋና የለኮሰ፣ በሁለት ዘሮች በጥቁሮችና በነጮች መካከል የተገነባውን የበታችነትና የበላይነት ግንብ ያፈረሰ፣ መልከ ብዙ የድል ቀናችን ነው ብንል ማጋነን አይሆንም!
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2013