ከዓለም ሀገራት ቻይና፣ ማሊዢያ፣ ታይዋን፣ ሲንጋፖር፣ አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሣይ እና ጀርመን የመምህርነት ሙያ ትልቅ ክብር ከሚሰጥባቸው ሀገራት መካከል ይጠቀሳሉ። በሀገራቱ ለመምህራን የሚከፈለው ክፍያ ከፍተኛ ከመሆኑ ባሻገር፤ ብቃቱ እና ተሠጥኦው ያላቸውን መምህራን በማምጣት የተማሪዎቹን ተወዳዳሪነት ከፍ ማድረግ እንደቻሉ መረጃዎች ያመለክታሉ። በእነዚህ ሀገራት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወላጆች ልጆቻቸው መምህር እንዲሆኑ ይመክሯቸዋል።
በተመሣሣይ እንግሊዛዊቷ የ20ኛው ክፍለ ዘመን ገጣሚና ሐያሲ ጆርጅ ኢሊዮት በ1860 በጻፉትና ስለ አውሮፓ ትምህርት በሚያወራው ‹The Mill in the Folss› በተሠኘው ልብ-ወለድ ነክ መጽሀፋቸው፤ «ሀገራት አዋቂና ተመራማሪ ትውልድን የመፍጠር ሕልማቸውን የሚያሣኩትም ሆነ የትምህርትን ጥራት ማስጠበቅ የሚችሉት ለምሁራን ተገቢውን ክብርና ትኩረት መስጠት ሲችሉ” እንደሆነ አመላክተዋል፡፡ በትምህርት ጥራት አንቱ የተባሉ ሀገራትን የትምህርት ሂደት ስንመረምር የምናገኘው ይህንኑ ነው፡፡ ሀገራት ለመምህራን ክብር በመስጠት የትምህርት ጥራትን ማረጋገጥ የመቻላቸው ሚስጥር ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሀቅ ምን ይመሥላል? የሚለውን ከትናንት እስከ ዛሬ ያለውን መመልከት ፈለግን።
ክብር የተነፈገው፤ የተከበረው ሙያ
በኢትዮጵያም በተመሣሣይ የመምህርነት ሙያ ትልቅ ክብር ይሰጠው እንደነበር ይታመናል። ለዚህ ደግሞ ከአንድ ዓመት በፊት ሕይወታቸው ያለፈው የማይክሮሊንክ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኮሌጅ መሥራች እና የኢትዮጵያ ነጻ-ፕሬስ አለኝታ በሚል የሚታወቁት አቶ ዳኛቸው ይልማ ከሁለት ዓመት በፊት ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ «ይድረስ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ» ሲሉ በጻፉት ደብዳቤ ላይ ያሠፈሯቸውን ነጥቦች ማስታወስ ይገባል።
አቶ ዳኛቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገራችን ለመምህራን ትምህርትና ሥልጠና ተገቢውን ክብርና ትኩረት መስጠት የሚገባ መሆኑን ባሳሰቡት በዚህ ደብዳቤ፤ ቀደም ባሉት ጊዜያት ሙያው የተከበረ እንደነበር፤ «ከ1966 ዓ.ም በፊት መምህር ለመሆን የምርጦች ምርጥ መሆንን
(cream of the cream) ይጠይቅ ነበር። በዚህም መሠረት ወደ መምህራን ማሠልጠኛ ይገቡ የነበሩት ከየትምህርት ቤቶቻቸው የላቀ ውጤት ያመጡት ነበሩ። መምህራኑም ከተማሪዎቻቸው አልፈው ለአካባቢው ኅብረተሰብ ጭምር አርአያ (role models) ነበሩ። በኋላኛው ዘመን ግን መምህሩ መኩሪያን ሣይሆን ማፈሪያ እስከመሆን ደረሠ» ሲሉ አስታውሰዋል።
አቶ ዳኛቸው እንደሚሉት የመምህርነት ሙያና መምህርነት የነበረው ቦታ ክብር ዛሬ ላይ የሚገኝ አይደለም፤ «ኢትዮጵያችንን እርስዎ ወዳለሙላት ደረጃ ለማድረስ ሊቀድሙ ከሚገባቸው ተግባራት አንዱ ስለሆነ ይህንን አስረግጠው በተግባር የሚያውሉበትን ዕለት እናፍቃለሁ» ነበር ያሉት። በሀገራችን መምህርነት የተከበረ ሙያ እንደነበር የአቶ ዳኛቸውን ሐሳብ ይዘን ወደ ኋላ መለስ ካልን፤ በማህበረሰቡ ዘንድ ሣይቀር የነበረውን ቦታ መረዳት እንችላለን። በጊዜው የነበረው ማህበረሰቡ የነበረው የክብር ከፍታ እንዲያውም፡-
የእኛ ሙሽራ ኩሪ ኩሪ
አገባሽ አስተማሪ፤
ወሰደሽ አስተማሪ፤ ይባል ነበር፡፡
በኢትዮጵያ በማህበረሰቡ ዘንድ ለጋብቻ ሣይቀር መምህር መሆን ተፈላጊ የነበረው ሙያ ዛሬ ላይማ ገና መምህር መሆኑ ሲታወቅ ሰው እስከ መሸሽ ሲደርስ ለመታዘብ ችለናል። በሀገራችን የመምህርነት ሙያ ተገቢውን ክብር አለማግኘቱም፣ ማህበረሰቡ ለመምህራን ቦታ ማጣቱን ብዙዎች ሲናገሩ ነበር፤ እየተናገሩም ይገኛሉ። የኢትዮጵያ ነጻ-ፕሬስ አለኝታ የተባሉትን አቶ ዳኛቸው ይልማ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፍት ደብዳቤ፤ «… የመምህርነት ሙያ የነበረው ክብር በጊዜ ሂደት እየተሸረሸረ መጥቷል።
በተለይ ላለፉት 27 ዓመታትም የመምህሩ ጉዞ ከድጡ ወደ ማጡ የመጣ ሲሆን፤ የመምህርነት ሙያ መኩሪያ ሣይሆን ማፈሪያ እስከመሆን ደርሷል።» ማለታቸው ለዚሁ ይመስላል። በሀገራችን መምህራን በሙያቸው እያፈሩ፤ እውቀታቸውን እየሰሰቱ፤ መምህራን ጫንቃቸው ጎብጦ ነገን በደበዘዘ ተሥፋ የሚጠባበቁ ‹ምሥኪኖች› ወደ መሆን ተሻግረዋል። ይህም ‹የመምህራንን ማሕበራዊ ዋጋ እንዲያሽቆለቁል ያደረገው ምንድን ነው?› የሚል ጥያቄን
ይወልዳል። ከተለያዩ አቅጣጫ የሚሰጡት ምላሾችን ስንመለከት ‹የችግሩ መነሻም ሆነ መድረሻ መንግሥት› መሆኑን በመጥቀስ፤ መንግሥትን ተጠያቂ ያደርጋሉ።
የደመወዝና የመግቢያ ነጥብ
የመምህራን ደመወዝ ማነሱ ያስከተለው መዘዝ፤ በሥራ ዘርፉ ብቃታቸው ከፍ ያሉ ባለሙያዎች ወደ ዘርፉ እንዳይገቡ አድርጓል። ውስጡ ያሉትም ሸሽተው እንዲወጡ፣ ባይወጡም ኃላፊነታቸውን በትጋት እንዳይወጡ ለሞራል ልሽቀት ዳርጓቸዋል፡፡ የመንግሥት ሆነ የግል ትምህርት ተቋማት በሙያው የተካነ መምህራን ፈልገው እንዲያጡ ያደረገ ሲሆን፤ ይህም «ጋኖች አለቁና ምንቸቶች ጋን ሆኑ» እንደተባለው የቆየ አባባል በየትምህርት ቤቱ ብቁ መምህራን እንዲጠፉ ሆኗል። ከአቅም በታቸ በሆኑ መምህራን ገበያው ለመወረሩ ምክንያት የፈጠረ ሲሆን፤ ይህም ሙያተኞቹ ብቁ ዜጎችን እንዳያፈሩ አድርጓል።
በሀገራችን በተለይ ላለፉት 27 ዓመታትም የመምህሩ ጉዞ ከድጡ ወደ ማጡ መሆኑን ያመላክታሉ። ወደ መምህራን ማሠልጠኛ የሚገቡት አመልካቾች በማንኛውም መመዘኛ ወደቀ/ች የሚያሠኝ ውጤት ማለትም ሴቶች 1.2/4.0 ወንዶች 1.4/4.0 በሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ያመጡ መሆናቸውንም ይገልጻሉ:: «የነገውን የአገር ተሥፋ ሊሆን የሚችለውን ትውልድ በለጋ ዕድሜው ሊኮተኩቱት ቀርቶ ሊያጣምሙት የሚችሉ ተገቢ ሥልጠናና ክህሎት የሌላቸው ዜጎች ናቸው ዛሬ ለመምህርነት የሚታጩት (ከመካከላቸው አንዳንድ ጎበዞችም በሁኔታዎች አለመመቻቸት ውጤታቸው ዝቅ ብሎ ለመምህርነት የበቁና መልካም አፈጻፀም ያላቸው እንደማይጠፉ እሙን ነው)» ሲሉ ነበር ነባራዊ ሀቁን ያሠፈሩት።
የኢሕአዴግ የክፋት በትር
መንግሥት ራሱ ሙያውን ከክብር በታች እንዲሆን ከመፈለጉ ጋር በማያያዝ፤ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ መምህራንን ከማንኛውም ለውጥ ለማግለል ሆን ብሎ የሰራቸው ሥራዎች መኖራቸውን የሚያነሱ ሲሆን፤ በሀገራችን በቀደመው ጊዜ መምህራን ግንባር ቀደም የለውጥ ጠንሳሾችና አንቀሳቃሾች እንደነበሩ ያስታውሣሉ። «በወቅቱ መምህራን በራሣቸው መብታቸውን ያስከበሩና ለሐገርም አለኝታ ነበሩ፡፡
የፈነጠቀው ተስፋ
በኢትዮጵያ መምህራን ላይ በተለይ የቀደመው መንግሥት በሙያው ላይ ያሣረፈውን ሀገር ገዳይ አካሄድ፤ ከባለፉት ሦስት ዓመታት በኋላ የተስተካከለ ስለመሆኑ በተጨባጭ ለመመልከት ተችሏል። በመጀመሪያ ደረጃ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ቀጭን ትዕዛዝ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተባረሩትን መምህራን፤ በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የዶክተር አብይ አህመድ መንግሥት የወሠደውን ርምጃ አተያዩን የቀየረው ነበር።
ዶክተር አብይ፤ «ቀድሞ ተገቢ ባልሆነ መንገድ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተባረው የነበሩት መምህራን ይቅርታ ተደርጎላቸው ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ ያደረጉ ሲሆን፤ ይህ ውሣኔ በለውጡ መንግሥት ለምሁራን ክብር የተሠጠ መሆኑን ያረጋገጠ ሆኗል። በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት ብቃት ሣይኖርና ያለ ዕውቀት ማስተማር ብክነት እና ኢ-ፍትሃዊነት መሆኑን ከማመን ባሻገር፤ የመምህርነት ሙያው ክብደትና አክብሮት መስጠት አስፈላጊ እንደሆነ ስለመረዳቱ ጭምር አመላካች ይሆናል።
መንግሥት አዲስ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት ሌላው ርምጃ ነው። በተመሣሣይ የመምህራን ቀን በየዓመቱ እንዲከበር ተደርጓል። አሁንም የመምህራን ክብር ወደነበረበት ከፍታ ተመልሶ “የእኛ ሙሽራ ኩሪ ኩሪ አገባሽ አስተማሪ፤ ወሠደሽ አስተማሪ” የሚባልበት ጊዜ እንዲመጣ ምኞታችን ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 22 ቀን 2013 ዓ.ም