ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በወራሪው የጣልያን ጦር ላይ የዓድዋ ድልን ከተጎናጸፉ ነገ 125 ዓመቱን ያከብራል። ይህ ታላቅ ድል በኢትዮጵያውያን ዘንድ ሁሌም ልዩ ስፍራ ያለው ሕብረ ብሔራዊ አንድነት የተንፀባረቀበት እና የኢትዮጵያውያን የአሸናፊነት ስነልቦና መሰረት ጭምር ነው።ኢትዮጵያውያን የውጭ ወራሪ ኃይል ለመመከት በአንድነትና በሀገር ወዳድነት ወኔ ተሰልፈው ያስመዘገቡት ወርቃማ ድል ነው።ድሉ ለአፍሪካውያንና ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች ጭምር የአሸናፊነት ስነልቦና ምልክት በመሆን ሲያገልግል የቆየ ነው።
ጣልያን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ውጫሌ ላይ ያደረገችው ስምምነት የእንግሊዝኛው ቅጂ ኢትዮጵያን ለቅኝ ግዛት የሚዳርግ መሆኑንና ጣልያን በሰሜን ኢትዮጵያ እየገባች ወረራ መፈጸሟን የተገነዘቡት የወቅቱ ንጉሰ ነገስት አጼ ምንሊክ ወራሪውን የጣልያን ጦር ለመመከት ዜጎች እንዲዘጋጁ የጠሩትን ክተት ተከትሎም ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከ ዳር ተነቃንቀው ዓድዋ ላይ በመገኘት ወራሪውን ጦር አይቀጡ ቀጥተውታል፡፡
ኢትዮጵያውያን በዓድዋ ድል በሀገራቸው ለመጣ ጠላት እንደማይንበረከኩና ዳር ድንበራቸውን እንደማያስደፍሩ ለጠላት ብቻ አይደለም ለወዳጅም ማረጋገጫ ሰጥተዋል።ኋላቀር የጦር መሳሪያ በመጠቀም ዘመናዊ መሳሪያ እስከ አፍንጫው የታጠቀውን የጣልያን ጦር ድል ማድረጋቸው አሸናፊው የጦር መሳሪያ ሳይሆን፣ ዓላማ አንግቦ አንድ ሆኖ መንቀሳቀስ መሆኑንም ለዓለም ጭምር አሳይተዋል።ኢትዮጵያውያን ድሉ የሀገራቸውንን ዳር ድንበር ያስጠበቁበት ብቻም ሳይሆን ለቅኝ ገዥዎች እጃቸውን እንደማይሰጡ ያረጋገጡበት ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ወራሪውን የጣልያን ጦር በዓድዋ እንደመከቱትና በታላቅ ታሪካዊ ተጋድሎ ወደ መጣበት እንደመለሱት ሁሉ፤ አሁንም የጀመሩትን የልማትና ብልጽግና ጉዞ በስኬት አጠናቀው መጪውን ጊዜ ብሩህ ማድረጋቸው የማይቀር ነው። ይህ የልማትና የብልጽግና ጉዞ ገና ከጅምሩ ብዙ ተግዳሮቶችን እያስድተናገደ ቢሆንም፤ እንደ ዓደዋው የተጋድሎ ታሪክ በአሸናፊነት ተውጥተነው በድህነት ውስጥ ላሉ ጥቁር ህዝቦች ድህነት እጣፈንታቸው እንዳልሆነ የምናሳይበት ጊዜው ሩቅ አይሆንም።
ኢትዮጵያውያን የቱንም ያህል አስቸጋሪ ሁኔታ ቢገጥማቸው ከቀደመው የየዘመናት ታሪካቸው መረዳት እንደሚቻለው የሚከፈለው ዋጋ ሊከብድ ይችል ይሆናል እንጂ ካሰቡት መድረሳቸው አይቀርም።ለእዚህም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን በአብነት መጥቀስ ይቻላል።የግድቡ ግንባታ ገና ከጅምሩ ብዙ ተግዳሮቶችን እያስተናገደ ቢሆንም ለግንባታው ያለው ሀገራዊ ቁርጠኝነት ግን ከተግዳሮቶቹ በላይ ሆኖ ግንባታው ተጠናክሮ ቀጥሏል።በዚሁ አስቸጋሪ ወቅት እንኳን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከፍተኛ መጠን ያለው የገንዘብ ድጋፍ እየተደረገ ነው።
ሀገሪቱ ጥቅማችን ተነካ ባሉ የገዛ ከሀዲ ልጆቿ በግጭት ውስጥ እንድትማቅቅ ለማድረግ ቢሞከርም ነገሩ የዓለም አቀፉን ህብረተሰብ ሳይቀር ለማመን በተፈታተነው ታሪካዊ ተጋድሎ ከሽፏል ፣ በእዚህ አስቸጋሪ ወቅትም የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በማስቀጠል ትርጉም ያለው ስኬት እየተመዘገበ ነው።በገበታ ለሸገር ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በማዋጣት ለሀገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ሦስት ፓርኮች በአዲስ አበባ ተገንብተዋል፡፡
በገበታ ለሀገር ፕሮግራምም በጎርጎራ፣ በወንጪ እና በኮይሻ ተመሳሳይ ሥራዎች ለመሥራት ለተያዘው ሥራ ከሚጠበቀው ሦስት ቢሊየን ብር በላይ አራት ነጥብ ሁለት ቢሊየን ብር ገንዘብ ተሰብስቧል።ፕሮጀክቱም በኮይሻ በይፋ ተጀምሯል።በጁንታው ላይ የተወሰደው ዕርምጃና የተገኘው ድልም ኢትዮጵያውያን የጠላቶቻቸውን ሴራ እየበጣጠሱ ልማታቸውን እንደሚያስቀጥሉ ያረጋገጠ አንድ ታሪካዊ እውነታ ነው።
በቀጣይም በሌሎች የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መስኮች ተመሳሳይ ድሎችን ለመጎናጽፍ አይገዳቸውም።በጠላቶቻቸው እዚህም እዚያም የሚጠነሰሱ ሴራዎች ከዋናው ጉዟቸው ጠልፎ አያስቀሯቸውም።የዓድዋን ድል እንዳስመዘገቡ ሁሉ በልማትና በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ በኩል የተያዙትን እቅዶች ዳር በማድረስ የሀገሪቱን ብልጽግና ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል።ለእዚህም የዓድዋውን የአንድነት መንፈስና ጥንካሬ መጠቀም ይገባል።
የዓደዋን የተጋድሎ ታሪክ በልማቱ በመድገም በድህነት ላሉ የዓለም ጥቁር ህዝቦች ድህነት ዕጣ ፈንታቸው እንዳልሆነ፤ ድህነትን ማሸነፍ የሚያስችል የይቻላል መንፈስ መፍጠር የሚያስችል አዲስ አንጸባራቂ ድል በማብሰር በልማቱ ፋና ወጊ የምንሆንበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። የዓደዋ የተጋድሎ ታሪካችንም ለመጪው ድል ስነልቦናዊ መሰረታችን ነው!
አዲስ ዘመን የካቲት 22 ቀን 2013 ዓ.ም