ፍቅሬ አለምነው
እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል እንዳለችው እንስሳ የፖለቲካ አስተሳሰብ የተጠናወታቸው ከሰውኛ እሳቤ የተፋቱ ሞልተው ተርፈዋል። ሰው ከእንሰሳ የሚለየው በስክነት በማሰብ፤ በማመዛዘን፤ አርቆ በመመልከት፤ ክፉውን ከደጉ የመለየት ጸጋ የተሰጠው በመሆኑ ነው። ከትልቅ ሀገራዊ ራእይ ተሸቆልቁለው በጠበበ ዓለም ውስጥ ተወሽቀው ከመንደር ወደ ጎጥ በወረደ እሳቤ የሚንቧቸሩ ኃይሎች በምንም ተአምር ለትልቅ ሀገርና ሕዝብ አይበጁም። አይመጥኑምም።
እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል እንዳለችው ዓይነቶቹ ወሰን የለሽ ስግብግቦች ሌላም አስቂኝ የዘወትር ዘፈን አላቸው። ተዋግተን 60 ሺህ ሰው ገብረን ነው ወደስልጣን የመጣነው፤ በመስዋእትነት ያገኘነውን ስልጣን መልቀቅ የለብንም፤ ዝንተ ዓለም መግዛት ይገባናል ባዮችም ናቸው።
እነሱ የወጉት፣ የገደሉት፣ ደሙን ያፈሰሱት የኢትዮጵያ ሕዝብ ልጅ የሆነው ወታደር በቁጥር አጣናቸው ከሚሉት ልጆቻቸው እጥፍ በላይ ቢሆን እንጂ አያንስም። በዘመናቸው ያካሄዱትን ጦርነት በብቸኝነት እንዳሸነፉ የሚነዙት ቅጥ ያጣ ፕሮፓጋንዳም ተረት ተረት ነው።
በብሔራዊና በዓለም አቀፍ ደረጃ የነበረው ፖለቲካዊ አሰላለፍ መቀየሩ፤ ከውጭ ለደርግ መንግሥት ይሰጥ የነበረው ድጋፍ በመቆሙ፤ የዓለም ሶሻሊስት ጎራ ከቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት በኋላ በመናዱ፤ የደርግን መንግሥት በውስጥና በውጭ የሚወጉት ኃይሎች መበራከታቸውና በአንድ ጎራ ተሰልፈው አጣብቂኝ ውስጥ ስለከተቱት፤ አንዳንድ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ ጀነራሎች በምስጢር ከውጭ ኃይሎች ጋር በስውር መሰለፋቸው፤ ዛሬም ያልተኙት የጎረቤት መንግሥታት ከግብጽ ጋር እየተረዳዱ በኢትዮጵያ ሠራዊትና መንግሥት ላይ መዝመታቸው፤ በጦርነቱ 17 ዓመት ሙሉ ሲማገድ የኖረው በሕይወት የተረፈው ሠራዊት ከመዋጋት አለመዋጋትን መምረጡ፤ በጀነራሎቹ እልቂትና ሞት ከፍተኛ የአመራር ክፍተት መፈጠሩ ሁሉ በወቅቱ ለወያኔ ሰተት ብሎ ወደ መሀል ሀገር መግባት ተጠቃሽ መሠረታዊ ምክንያቶች ናቸው። ከዚህ በዘለለ ግን ወያኔ እንደምትቀደደው በወታደራዊ እውቀት፤ ጀግንነት፤ ብቃት፤ ልህቀት ከማንም በላይ ነኝ እንደምትለው አይደለችም። አልነበረችምም።
የወያኔ ቡድን ከማዕከላዊው መንግሥት ሸሽቶ መቀሌ በመክተም በምድር ላይ አሉ የተባሉትን የፖለቲካና ወታደራዊ ሴራዎችን ሁሉ አድብቶ በድብቅ በመሥራት ለመጠቀም ሞክሯል። ይሄም እብሪት ፈጥሮበት ኑና ግጠሙን በአፍሪካ ምርጥ ወታደራዊ ኃይል ገንብተናል፤ ትግራይ የመጣ ኃይል መቀበሪያው ይሆናል፤ የሚፋጅ እሳትና ረመጥ ነን እስከማለት ደርሰው ነበር።
በዚህ ከመጠን ያለፈ እብሪት ተገፋፍተው በሰሜን ዕዝ ላይ ያልተጠበቀ ወረራ በማድረግ ሠራዊታችንን ጨፍጭፈዋል። ገለዋል። የሀገሪቱን ወታደራዊ ንብረት ዘርፈዋል። ብዙ ለጆሮ የሚቀፉ ግፎችን ፈጽመዋል።
አማራና ኦሮሞ መኮንኖችና ወታደሮችን ለይተው ረሽነዋል። አግተዋል። ጫማቸውን አስወልቀው በባዶ እግራቸው መቀሌ ከተማ ሕዝብ በተሰበሰበበት እየተሳቀባቸው እየተተፋባቸው እነሱ እያቅራሩ ጀግና ተጋሩ እያሉ የእኛ ሠራዊት አባላት አንገታቸውን ደፍተው ወገን ተብለው የነበሩት አረመኔዎች ተሳልቀውበታል።
መከላከያውን ሲመቱ ድንበሩን ያለ ጠባቂ አስቀርተውታል። የወያኔ ግፍና ወንጀል ገና ከትውልድ ትውልድ ከዘመን ዘመን ተጽፎ ይተላለፋል። እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ባዮቹ ያን ሁሉ አድርገው መሣሪያ ዘርፈው አከማችተው፤ በገፍ ሠራዊት አሰልፈው፤ በከተማና በገጠር ኮንክሪት ምሽግ ሠርተው ደረቅ ቀለብ፤ ጥይት፤ መድሐኒት፤ ቀላልና ከባድ መኪናዎች ፤ነዳጅ ጭምር ለዓመታት የሚያዋጋ ከመሬት በታችና በመሬት ውስጥ ፤ በተራራ እንዲሁም በዋሻ ውስጥ ደብቀው ቀብረው አዘጋጅተው ነበር።
ሕዝቡን ሕፃናት አሮጊትና ሽማግሌ ሳይቀር አስታጥቀው የኢትዮጵያን ሠራዊት ጨፍጭፈው ጠላት ነው ብለው አውጀው ብዙ ሠርተዋል። የተበተነው ሠራዊታችን መልሶ መደራጀትና መልሶ ማጥቃት በማድረግ ከሱዳን ድንበር መተማ እስከ መቀሌ ከተማ ድረስ ብዙ መቶ ኪሎሜትሮችን በየቦታው እየተዋጋ ተጉዞ በ2 ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ያን ሁሉ የወያኔ ዝግጅትና እብሪት ብትንትኑን አውጥቶታል።
የተደመሰሰው ተደምስሶ የተማረከው ተማርኮ እጁን የሚሰጠው ሰጥቷል። ሠራዊታችን እጅግ አስደማሚ በሆነ የውጊያ ብቃትና ፍጥነት መቀሌ ገብቷል። በየጥሻው በየዋሻው በየገደሉ ያለው የወያኔ ኃይል አብዛኛው በዝንጀሮ ገደሉ ተለቅሟል። የቀሩትም እየታደኑ ይገኛሉ።
ወያኔ ከአፈጣጠሩ ጀምሮ ፀረ ኢትዮጵያ ፀረ ሕዝብ ዘረኛና ጎጠኛ የሆነ ኃይል ነው። እኔ ብቻ በሚል የዘረፋ የምዝበራ የአልጠግብ ባይነት ፖለቲካ የተቃኘ መሰሪ ድርጅት ነበር። ወያኔ ሀገር አጥፍቶ፣ ልማቶችን ከተሞችን አውድሞ፣ ሕዝቡን ለችግር፣ ለረሀብ፣ ለፈተናና መከራ ዳርጎ ራሱ ባመጣው ውድቀት ዛሬ ደግሞ ዓለም አቀፉን ሕብረተሰብ ለማሳሳት ብዙ ርቀት ሄዶ በመሥራት ላይ ይገኛል።
በውጭ የሚገኙትን ጥቅም የቀረባቸውን አባላቱን ልጆቻቸውንና ደጋፊዎቹን አሰባስቦ ትግራይ ሚዲያ ሀውስን የመሰለ ዘረኛና ውሽታም ሚዲያ በመጠቀም እነሱው በዳይ፣ ገዳይና ጨፍጫፊ የሆኑበትን ድራማ ለውጠው ሌላ ታሪክ እያወሩ ነው።
በኢትዮጵያ ውስጥ የዘር ማጥፋት የፈጸመው ወያኔ፤ አማራውንና ኦሮሞውን በገፍ የጨፈጨፈው የወያኔ ቡድን፤ ሴቶችን በመድፈር የሚታወቀው የወያኔ ቡድን፤ ቤተክርስትያናትና መስጊዶችን በመድፍ የደበደበው፣ ያፈረሰው ቅጥረኞች በገንዘብ እየገዛ እንዲቃጠል ሲያደርግ የነበረው የወያኔ ቡድን ፤ ከታላላቅ ሰዎች ግድያና ሞት ጀርባ አቀናባሪውና መሪው የወያኔ ቡድን፤ የሀገር ሀብት የዘረፈውና ካዝና ያራቆተው ዘርፎም አልጠግብ ባዩ የወያኔ ቡድን፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጦርነት ከፍቶ የገደለው የጨፈጨፈው የወያኔ ቡድን፤ በመላው ኢትዮጶያ ቅጥረኞችን እየገዛ ሰላም ሲያደፈርስ ደም ሲያፋስስ የነበረው የወያኔ ቡድን ነው።
ይሄን ሁሉ ይቅር የማይባል ግፍ በአረመኔነት በጭካኔ የፈጸመ ፋሽስት ድርጅት ዛሬ ምንም እንዳላደረገ አስመስሎ ሲያለቅስና ሲያጭበረብር ማየት ያሳፍራል። እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ያለችው እንሰሳና የወያኔ ቡድን አንድ ናቸው።
በሕዝብ ከመጠላትና ከመተፋት የበለጠ ክፉ ነገር የለም። ወያኔ ዛሬ ደግሞ ወደተራ ሽፍትነት፣ ዘረፋና ግድያ ተሰማርቷል። በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ ጭነው ሊያስገቡት የነበረውና ወልዲያ ኬላ ላይ የተያዘው 23 ካርቶን ፈንጂ ራሱን ችሎ ብዙ ይናገራል። መያዙ በጀ እንጂ ቢያልፍ ኖሮ ማድረስ በታሰበበት ቦታ ተቀባይ ሰዎች ነበሩ ማለት ነው። አደጋውንም መገመት አይከብድም።
ሁለተኛውና ትልቁ ነጥብ ፈንጂ ማጥመድ የተለየ ሙያና እውቀት ይጠይቃል። እንደዚህ ዓይነት ሰዎች ተዘጋጅተው ነበር ማለት ነው። የት ነው ያሉት ? እነማናቸው ? አደጋውን ለማድረስ የታቀደው የት የት ነበር ? የሚለውን ያልተመለሰ ጥያቄ ለባለሙያዎቹ እንተወው።
ተስፋ የቆረጠ ኃይል ማንኛውንም ጥፋት ከማድረስ አይመለስም። ከሰሞኑ የመንገደኛ አውቶቡስ አስቁሞ ሰላማዊ ተሳፋሪዎችን አውርዶ መግደል የወያኔን ቀጣይ የጥፋት ጉዞ ያመለክታል። እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ባዮችን ነቅቶ መጠበቅና መከላከል ግዴታ ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 21/2013