በትግራይ ክልል የተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ከተጠናቀቀ ከሦስት ወራት በላይ ተቆጥረዋል። የዘመቻውን መጠናቀቅ ተከትሎ መንግሥት በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን፣ የተፈናቀሉና ለተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚዊ ችግሮች የተጋለጡ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም የተለያዩ ሰብዓዊ ድጋፎችን ሲያከናውን ቆይቷል።
ይሁን እንጂ ለዓመታት በትግራይ ህዝብ ጫንቃ ላይ ሆኖ ህብረተሰቡን ሲያጉላላና የራሱን ቡድን ሲያደራጅ የኖረው የህወሓት ጁንታ ቡድን አባላትና ደጋፊዎች በየጥሻውና በየጫካው ተበታትነው አካባቢው ላይ ሰላም እንደሌለ ለማስመሰል ጥረታቸውን አላቋረጡም።
በሌላ በኩል መንግሥት በአካባቢው ላይ የወሰዳቸው የህግ ማስከበር ዕርምጃዎችና ህብረተሰቡን ወደሰላማዊ ሁኔታ የመመለስ እንቅስቃሴን ለማደናቀፍ የሚጥሩ በርካታ ኃይሎች ከውስጥም ሆነ ከውጭ ሆነው የራሳቸውን ሚና መጫወታቸው አሁንም እንደተቀጠለ ነው።
በተለይ አጋጣሚውን ሁሉ በመጠቀም የህግ ማስከበር ዘመቻውን ውጤት ለማጠልሸትና በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ የተለየ ገፅታ ለማላበስ በህጋዊነት ስም እየተንቀሳቀሱ ህገወጥ ተግባራት የሚሠሩ ድርጅቶች አሁንም አሉ። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ነው።
አመነስቲ ኢንተርናሽናል የያዘው ስም ትልቅ ነው። ድርጅቱ ሰዎች በመንግሥትም ሆነ በተለያዩ ቡድኖች ኢሰብዓዊ ድርጊት እንዳይፈፀምባቸው ለመከታተል፤ ከተፈፀመባቸውም ያንን በማጣራት ትክክለኛውን መረጃ ለዓለም ማህበረሰብ ለማሳወቅና ለዚያ ተጠያቂ የሚሆኑ አካላት እንዲጠየቁ እንዲሁም ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ተገቢውን ፍትህ እንዲያገኙ መሥራት ዋነኛ ሥራው ሊሆን ይገባል። ለዚህም በመረጃ እና ማስረጃ ላይ ተመስርቶ በሐቅ መሥራት ይጠበቅበታል።
ይሁን እንጂ ይህ ተቋም አንዳንድ ጊዜ የሚያወጣቸው መረጃዎች ከየት እንደመጡ የማይታወቁና አንዳንዴም ሆን ተብሎ ወይም በተለየ ተልዕኮ ተይዘው ከእውነታና ከሳይንሳዊ የመረጃ አሰባሰብና አተናተን መርሆዎች ባፈነገጠ መንገድ ሲሠራና ያንን ተመስርቶም ያልተጣሩ መረጃዎችን ይፋ ሲያደርግ ይስተዋላል። ለዚህም ሰሞኑን በአክሱም ቤተክርስቲያን ላይ ተፈፀመ ባለው ሰብዓዊ መብት ጥሰት ላይ ያወጣው ሪፖርት ማሳያ ነው።
ተቋሙ በዚህ ሪፖርቱ ላይ በአክሱም ቤተክርስቲያን በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መገደላቸውንና ከዕነዚህ ውስጥ የሃይማኖት አባቶች እና ምዕመናን እንዳሉበት ማረጋገጡን ይፋ አድርጓል።
ይሁን እንጂ ይህ ሪፖርት የተጠናቀረበትና መረጃው የተሰበሰበት መንገድ የተሳሳተና እውነታውን ለማግኘት የሚያስችል ባለመሆኑ ተቋሙ ያወጣው ድምዳሜ በመረጃ ላይ ያልተደገፈ እንዲሆን አድርጎታል። ይህ ደግሞ ተአማኒ ሊሆን አይችልም።
ተቋሙ መረጃውን ለማሰባሰብ የተጠቀመው የመረጃ አሰባሰብ ስነዘዴ በስልክ ሲሆን፤ ሪፖርቱን ለማጠናቀር በምንጭነት የተጠቀማቸው ደግሞ በምሥራቃዊ ሱዳን በስደት ላይ የሚገኙ ተፈናቃዮች እና በአክሱም ከተማ ነዋሪ የሆኑ ግለሰቦችን እንደሆነ አሳውቋል። ይሁን እንጂ እነዚህ መረጃ ሰጪዎች በትክክል ያለውን እውነታ የሚያሳዩ አለመሆናቸውን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማስረጃ በማስደገፍ አቅርቧል።
በዚህ መሰረት በስልክ ከተሰጠው መረጃ ጋር ተያይዞ የተሳሳቱ መረጃዎች ሆን ተብለው ስለመሰጠታቸው አሳውቋል። ለአብነትም ራሱን ቄስ ነኝ ያለ አንድ ግለሰብ በሰጠው መረጃ እሱና ሌሎች የቤተክርቲያኗ አባቶች በቅዳሴ ላይ እያሉ ችግሩ መከሰቱን ቢገልጽም በተጨባጭ ሲጣራ ግን ሰውየው በአሜሪካ በቦስተን ከተማ ነዋሪ መሆኑን መረጋገጡ ተቋሙ ምን ያህል ትክክለኛ መረጃ ለመያዝ እንዳልተጓዘ የሚያሳይ ነው።
በሌላም በኩል ከዚህ ቀደም በማይካድራ በተካሄደው የጅምላ ጭፍጨፋ ላይ እንደተሳተፉ የሚጠረጠሩና ወደሱዳን የሸሹ፣ ከፊሎቹም የህወሓት ታጣቂዎች የዚህ ሪፖርት የመረጃ ምንጭ መሆናቸው ሪፖርቱ የተሳሳተ ለመሆኑ አመላካቾች እንደሆኑ መንግሥት አሳውቋል። ይህ ደግሞ ትክክለኛ መረጃ ለመስጠት አዳጋች ያደርገዋል።
እንዲህ ዓይነት መረጃዎች በእውነት ላይ ተመስርተው ቢሠሩ ለሁሉም ጠቃሚ ይሆናሉ። በአንድ በኩል መንግሥት በህግ ማስከበር ሥራው ወቅት የተፈፀሙ ችግሮችን ለማጣራትና ተገቢውን የእርምት ዕርምጃ ለመውሰድ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው በተደጋጋሚ አሳውቋል።
በዚህ መሰረት አምነስቲም ሆነ የሌሎች አካላት ትክክለኛ መረጃ በተገቢው ሁኔታ መሰብሰብና ይፋ ማድረግ ለመንግሥት ጠቀሜታ ይኖረዋል። ነገር ግን በዚህ መልኩ በሐሰት ላይ የተመሰረቱ ሪፖርቶች ለመንግሥትም ሆነ ለአካባቢው ነዋሪ ጠቃሚ ስለማይሆን መታረም አለበት።
ከዚህም ባሻገር በግጭት ወቅት ከተለያዩ አካባቢዎች የሚረጩ የተለያዩ መረጃዎች እንደሚኖሩ ይታወቃል። በትግራይ የተካሄደውን ይህን የህግ ማስከበር ዘመቻ ተከትሎ ከሃገር ውስጥና ከውጭ ሃገር የተለያዩ ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች የተሳሳቱና ከእውነታ የራቁ መረጃዎችን ጭምር ሲያሰራጩ እንደነበር የሚታወስ ነው።
አብዛኞቹም መረጃዎች ከስልክ የሚገኙ መሆናቸውም ለተሳሳተ ውጤት ሊዳርግ ይችላል። በመሆኑም ትክክለኛ መረጃዎችን ለማግኘት መሬት ላይ ያለውን መረጃ በቦታው ላይ በመሆንና በማሰባሰብ እንዲሁም በሐቅና በስነምግባር ላይ ተመስርቶ መስጠቱ ጠቃሚ ነው።
በአሁኑ ወቅትም መንግሥት ሰባት ዓለምአቀፍ ሚዲያዎች ወደስፍራው ሄደው እንዲዘግቡ እውቅና ሰጥቷል። በመሆኑም እነዚህ ሚዲያዎች ትክክለኛን መረጃ በቦታው ላይ በመገኘትና እውነታው ላይ በመመስረት በሐቅ ከሠሩ ተገቢውን መረጃ መስጠት ይችላሉ።
አሁን ባለው ሁኔታ ግን እንደነ አምነስቲ ኢንተርናሽል ዓይነት ተቋማት የሄዱበትና መረጃውን የሰበሰቡበት እንዲሁም መረጃውን ያጠናቀሩበት መንገድ የተሳሳተ እና ተአማኒነት የሚጎድለው በመሆኑ አሁንም ትክክለኛውን ነገር ማጣራትና እውተኛ መረጃዎችን መስጠት ይጠበቅባቸዋል።
ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ግን የወጣው ሪፖርት ከሐሜት የዘለለ በመሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ ለመረዳት አዳጋች ያደርገዋል፤ የተቋሙንም ተአማኒነትና ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 21/2013