(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
ኑ እንዋቀስ፤
ሰሞኑን ሁለት የዓየር ንብረቶች ሲፈራረቁብን እያስተዋልን ነው። የመጀመሪያው እንሞግትህ ብንለውም የማንቋቋመው ወይንም የማንረታው የተፈጥሮ ጣጣ ነው። የቀኑ ሙቀትና ቅዝቃዜ እና የሌሊቱ ዝናብና ወጨፎ ከወትሮው ለየት ብሎ አንድም በወበቅ አለያም በውርጭ ስንሸነቆጥ በአሜንታ ከመቀበል ውጭ ፈጣሪን ብናማ ወይንም ራሷን ተፈጥሮን ብናማርር ምንም እርባና እንደሌለው ስለምንረዳ የዓየር ንብረቱን በአሜንታ በመቀበል ገበርኩ ማለቱ እንደሚሻል አምነን በይሁንታ ተቀብለነዋል።
እኛ ከተሜዎች ለተፈጥሮ፣ ለፍጥረትም ሆነ ለፈጣሪ የማንመች ምሥጋና ቢስ ሆነን እንጂ የገጠሩ ደጉ “ባለሀገር” ግን የእኛን ያህል አምላኩን ለመክሰስ በምሬት ጣቱን ወደ ፀባዖት እየቀሰረ ፊቱንና ልቡን አያጠቁርም። ለምን ቢሉ አንድም የዝናቡ በረከት ለከብቶቹ የመኖ ምንጭ መሆኑን ስለሚያውቅ፣ አንድም የበጋው ብራ አዝመራውን ለመሰብሰብ ስለሚረዳው በሁሉ ያመሰግናል እንጂ እየተነጫነጨ አይበሳጭም።
ግፋ ቢልም ፈጣሪውን በጸሎትና በዱአ እየተማጠነ ልቡን ያራራዋል እንጂ ሽቅብ እየተንጠራራ የማይደፈረውን አይዳፈርም። ይብላኝ ለእኔ መሰሉ ግራ ገብ ከተሜ! ዝናቡን እንደ ፈጣሪ ቁጣ፣ ብራውን እንደ ተፈጥሮ ጊዲራ እየተረጎመ በመነጫነጭ ዕድሜውን ለሚገፋው።
ሁለተኛው “የዓየር ንብረት” ከባድ ደመና አርግዞ የዘረገፈው የፖለቲከኞቻችንን የሰሞኑን የምረጡኝ ቅስቀሳ ዶፍ ነው። ዶፉ በድንገተኛ የበጋ ዝናብ እንደተፈጠረ ጎርፍ በቁጣና በእልህ ድምጸት ተሞልቶ “ልባችንን በፍርሃት ቆፈን” አንጠረጠረው እንጂ ጥበብና መከባበር ታክሎበት ቸሰስ አድርጎ ተስፋችንን ሊያረሰርስ ከቶውንም አልተሳካለትም። የአጀማመሩ ግለትና እብደት፣ በውስጥ ስሜታችን ላይ አመዳይ አዝንቦ ስጋት ላይ ስለጣለንም “አበጃችሁ!” በማለት ልብ ተቀልብ ሆነን “እህ! በማለት” ልናደምጣቸው ጆሮ አልሰጠናቸውም።
ከፖለቲከኞቹ የመጀመሪያው የቅስቀሳ እሩምታ የሰማናቸው አንዳንድ አገላለጾችም ማደነጋገር ብቻም ሳይሆን ቀስቃሽ ፖለቲከኞቹ አስተውለው ስለመናገራቸው እንኳን እርግጠኛ መሆን ስላልቻልን “ምን ማለታቸው ነው?” በማለት በግርታ ውስጥ ወድቀን መንሾካሾካችን አልቀረም። “ዴሞክራሲው” ፈቃድ ስለሰጠንም እንዲህ በአደባባይ የልባችንን ለመዘርገፍ በይሉኝታ አልታበትንም።
አልገባንም ወይንም አልገባቸውም!
ፖለቲከኞቻችን በሙሉ በጅምላና በድፍረት “የፖለቲ ካችን ማኒፌስቶ” እያሉ ቅስቀሳቸውን መጀመራቸውን በጣት ለሚቆጠሩ ቢጤዎቻቸው ካልሆነ በስተቀር በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩት “ጨዋ ዜጎች” ጽንሰ ሃሳቡ ከከተማ እስከ ገጠር ባእድ እንደሚሆን ወይ አልተረዱትም ወይንም ለመረዳት አልፈለጉም። ለመሆኑ ብዙኃኑ የመሃልና የዳር ሀገራት ዜጎች “ማኒፌስቶ ምንድን ነው?” ተብለው ቢጠይቁ ምን መልስ ሊሰጡ ይችላሉ።
እንኳንስ እኔን መሰል ለፖለቲካው ጎራ ከቡድንተኝነት የጸዳን የሩቅ ተመልካች ቀርቶ አብዛኞቹ የፖለቲካ ማጀት አገልጋዮችና ውላጆችም ቢሆኑ የማኒፌስቶ ነገረ ጉዳይ በርግጡ ይገባቸው ይሆንን ብለን ስጋታችንን ብንገልጽ አይፈረድብንም። “ለብዙዎቹ የፖለቲካው የቤት ልጆችም” ይህ የሙከራ ቴስት ቢሰጣቸው የዜሮ ውጤት እንደሚታቀፉ ብንጠረጥር “ሞራል እንደመንካት” አይቆጠርብንም።
ይብላኝ ለስልሳዎቹ ዓመታት ታላላቆቼ። አበስ ገበርኩ ለቻይናና ለቀድሞ የሶቪየት ኮሚኒዩኒዚም አቀንቃኝ የዘመኑ ወጣቶች። “ማኒፌስቶ” በሚል የሚታወቀውን የፖለቲካ ጽንሰ ሃሳብ እንዲገባን ሳይሆን እንዳይገባን አድርገው ተክለውብን ስለሄዱ ዛሬም ድረስ በስሜት ቃር ግራ ተጋብተን ግራ እንድናጋባ ፈርደውብናል። ለመሆኑ የሀገሬ ቋንቋዎች ማህጸን “ማኒፌስቶን” ለመተርጎም መካን ስለሆኑ ይሆን? በግሌ እንጃ!
ለማንኛውም “ማኒፌስቶ” የሚለው ቃል ከሀገራችን ፖለቲካ ጋር “ጡት ተጣብቶ” የግድ “የቤት ልጅነት መብት” እንዲሰጠው ሳይሞቅ ፈላ ፖለቲከኞቻችን ስለፈረዱበት እንጂ “መግለጫ” እየተባለ በዕለት ተዕለት ቋንቋ “ለተራው ዜጋ ተራ ጆሮ” በቀላሉ እንዲደርስ ማድረግ በተቻለ ነበር። ለነገሩ የቃሉን ሥርወ ዘፍጥረት እንፈትሽ ብንል “manifest and manifestation are from Latin manifestus [manus means hand] literary meaning struck by the hand” የሚል ሆኖ እናገኘዋለን።
ይህ ማለት “obvious, clear, evident, plain, apparent, etc.” ወይንም በእኛው ቋንቋ “ግልጽ” የሚለውን ትርጉም ከመሸከሙ አስቀድሞ ኦርጂናል ጽንሰ ሃሳቡ “በቃሪያ ጥፊ መመታት ወይንም በቡጢ መጎሸም ወዘተ.” የመሳሰሉ ትርጉሞችን ያዘለ ግምኛ ቃል ስለመሆኑ መዛግብተ ቃላት ይተነትኑልናል።
የእኛ ፖለቲከኞችም በዚህን መሰሉ የመጀመሪያ ቀናት “በንግግር ቃሪያ ጥፊ ሊያጮሉን” በምርጫ ቅስቀሳ ሰበብ አደባባይ ቢውሉ አንፈርድባቸውም። “በመጀመሪያ በቃሉ ትርጉም እንስማማ” የሚለው የጥንታውያን የግሪክ ፈላስፎች የውይይት መርህ አልገባቸው ይሆንን? ብለን ብንጠይቅ አይፈረድብንም።
“ዴሞክራሲው” ለጊዜው “የመራጭነት ድርሻ” ብቻ ያጎናጸፈን እኛ “ተራ ዜጎች” በሰሞኑ ቅስቀሳ የተደናገጥንበት ሌላው ጉዳይ በቅስቀሳቸው ውስጥ “ማኒፌስቷችን ኮንትራት ሳይሆን ቃል ኪዳን ነው፤ የፖሊሲ ሰነዱም ድርሰት አይደለም…ቃል ኪዳን በሁለትዮሽ ቁርጠኝነት ላይ የሚመሰረት ነው” የሚለው አነጋገር “እንዴት ነው ጎበዝ?” ብለን እንድንጠይቅ ተገደናል።
“ካሸነፍን የመንግሥት ሥልጣን የምንረከበው ለአምስት ዓመታት ነው። ኮንትራት የሰጠን ሕዝብ ኮንትራቱን ካደሰልን ለሌላ አምስት ዓመት እንቀጥላለን። በቃችሁ ካለንም ሥልጣኑን ላስረከበን ሕዝብና ላሸናፊው ፓርቲ አስረክበን በሰላም እንሰነባበታለን” ስንባባል አልነበረም እንዴ!?
ደግሞስ የካቢኔ አባላቱ በፓርላማው ፊት ቀርበው “በዓመቱ ዕቅድ ውስጥ ይሄንንና ያንን እንፈጽማለን” ብለው የባለ አንድ ገጽ የኮንትራት ስምምነት ሲፈራረሙ ማስተዋል ብቻም ሳይሆን አጨብጭበንላቸው አልነበረም እንዴ!? ለመሆኑ ማኒፌስቶ እንደምን የቃል ኪዳን ክብር ሊሰጠው ይችላል? ቃል ኪዳን እኮ አይሻርም፤ የጊዜ ገደብም አይቆረጥለትም። ባህርይው እስከ ወዲያኛው የሚባል ዓይነት ነው።
ቃል ኪዳን በሁለት ግለሰቦች፣ በፈጣሪና በግለሰቦች ወይንም በቡድን መካከል ሊፈጠር ይችላል። ፈጣሪ ለተፈጥሮ ሳይቀር ቃል ኪዳን መግባቱን የሥነ መለኮት ንባቦች ያረጋግጣሉ። እንዲያውም በአንዳንድ እምነቶች የሥነ መለኮት ትምህርት ውስጥ ቃል ኪዳን የሚያያዘው አብዛኛውን ጊዜ “በደም” ወይንም “በመስዋዕት” ማጽኛነት ነው። ዝቅ እናደርገው ካልንም ቃል ኪዳንን ከዕድሜ ልክ የጋብቻ ትስስር ጋር ማነጻጸር ይቻላል።
በዚህ ጸሐፊ የግል እምነት የፖለቲካ አሸናፊነትና የሥልጣን መንበር ሊጸና የሚገባው ሕገ መንግሥት ወስኖ በሚሰጠው የኮንትራት ውል እንጂ “በደም በሚጸና ቃል ኪዳን ከሆነ” ፍጻሜው አምባገነንነትን እንደሚያስከትል ጥርጥር የለውም። ለዚህም ነው “ከአፍ ሲወጣ አፋፍ ሊደርስ ለሚችል” ንግግርና ቅስቀሳ ጥንቃቄ ማድረጉ ብልህነት የሚሆነው።
የፖለቲካ ሰነድ “ድርሰት” ያለመሆኑም ተደጋግሞ ሲገለጽ አድምጠናል። ለሀገሪቱ የድርሰት ማኅበር አፍቃሬና ቤተኛ መሆን ብቻም ሳይሆን ማኅበሩን በከፍተኛ ኃላፊነት እንደመራ አንድ ዜጋ አባባሉ ላይ መለስተኛ አስተያየት መስጠቱ አግባብ ይመስለኛል። ድርሰት ሁሉ ተረት አይደለም።
ተረት ሁሉም ድርሰት ሊሆን አይችልም። ድርሰት አንድ ማኅበረሰብ በዙሪያ ገብ የምልዓት ባህርይው የሚገለጽበት የጥበብ ዘውግ ነው። የዘርፉ ኃያሲያን ድርሰትን የሚበይኑት “የአንድ ማኅበረሰብ የዕለት ተዕለት የሕይወቱ ነፀብራቅ” መሆኑን አጽንኦት በመስጠት ጭምር ነው።
ድርሰት ዓይነቱ ብዙ ነው። የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ስለ ድርሰት ዝርዝር ምንነትና አወቃቀር የጻፋቸውን ሁለት መጻሕፍት (የጥበባት ጉባዔ እና አማርኛ ቋንቋ ከ9 -10ኛ ክፍል) ማንበቡ በቂ እውቀት ይሰጥ ይመስለኛል። ቀደምት የሀገራችን ምሁራን የጻፏቸውን መጻሕፍት አስሶ ማመሳከሩም የዕውቀት አድማስን ይበልጥ ያሰፋል።
እንደ ተክለ ማርያም ፋንታዬ ድንጋጌ “ድርሰት በዓይን የታየውን፣ በዦሮ የተሰማውንና አእምሮ የወለደውን በሥዕለ ቃላት አሳክቶና አስማምቶ በጽሑፍ መግለጽ ነው።” ደራሲው ከማህበረሰቡ የሚቀዳውን ሕይወት በቃላት አርቅቆና በምናብ አምጥቆ ለአንባቢያን ያቀርባል።
ሰዓሊውም በዓይኑ አይቶ በአእምሮው ያብላላውን ድርሰት በኅብረ ቀለማት አዋህዶ ይጠበብበታል። ቀራጺውም እንዲሁ፣ ሙዚቀኛውም እንደዚያው ሕይወትን ተርጉመው የሚያገለግሉን ላማጡበት ድርሰት ነፍስ እየዘሩ ነው።
የዘመነ ፊውዳሊዝምን አስከፊ ሕይወት ለተራ ዜጎች ለማስተዋወቅ ሺህ ምንተ ሺህ የምርምር መጻሕፍትን ከማመሳከር ይልቅ የሚቀለው “የፍቅር እስከ መቃብርን ድርሰት” እንዲያነቡ ማድረግ ነው።
በዚህ ድንቅ የሀገራችን ድርሰት እንባና ሳቅ፣ ኀዘንና ቁጭት እየተፈራረቀባቸው እውነቱን እንዲያውቁት ማድረግ ይቻላል። የብርሃኑ ዘርይሁን “ሦስቱ ማዕበሎች”፣ የበዓሉ ግርማ “የቀይ ኮከብ ጥሪና ኦሮማይ” ድርሰቶች በጥራዝ የቀረቡ የየዘመኑ ሥዕሎችና ሕያው መስታወቶች ናቸው።
ፖለቲከኞች አቅም ኖሯቸው በዓይናቸው ያዩትን ሳይሸፋፍኑ፣ በዦሯቸው የሰሙትን ሳይሸቅጡ የኖሩበትንና የታዘቡትን እውነታዎች አካተው የወደፊቷን የተሻለች ኢትዮጵያን መልክ ከሳሉልን እሰየው።
በተለይም ለቅስቀሳ ብቻ ሳይሆን ጨክነው “በሥዕላዊ፣ በተራኪና በአመዛዛኝ የድርሰት ዓይነቶች” የፓርቲያቸውን የፖለቲካ መዳረሻ ግብና ትሩፋት ለማሳየት ችለው ስሜቴን ከማረኩና የእህህታዬን ሀገራዊ እንቆቅልሽ ለመፍታት ከጨከኑና በቃልና በተግባራቸው ካረጋገጡልኝ ያለጥርጥር የምመርጠው የእነርሱን “አማራጭ ድርሰት” ይሆናል።
ነገር ግን “ሕዝባችን እያሉ” በመሸንግል ለሕዝብ በማይገባና ግልጽ ባልሆነ የተውሶ ቃል ሽፋን “በማኒስፌቶ የድምጽ ማጉያ” የሰለቹንን ጽንሰ ሃሳቦች ደግመው ደጋግመው እየዘመሩና እያዘመሩ ልማት፣ ብልጥግና ዴሞክራሲ፣ ፍትሐዊነት ወዘተ. በሚሉ ማደናገሪያዎች “እኛን ብቻ ምረጡ!” ቢሉ ውስጣችንም ውጭያችንም አይቀበላቸውም።
ምከሩን ካሉ ሀገሬ የምትፈልገው ተግባር ነው። እንድንመርጣቸው ከጓጉም “ሰው ሆነው ይገለጡልን እንጂ ራሳቸውን ከመላዕክት ተርታ አሰልፈው እየተኮፈሱ” አይሸንግሉን። ሕዝባችን የራበው የሚዲያ ዜና ሳይሆን እንደ ሰብዓዊ ፍጡር መደመጥን ነው። ዳቦ ርቦናል።
ይህርሃብ ዛሬ የተከሰተ ሳይሆን ሌማታችን ጦም ውሎ ጦም ማደር የለመደው ከአያቶቻችን ጊዜ ጀምሮ ነው። በንጉሡ ጊዜ ከተሜዎቹ ወላጆቻችን በአምስት ሳንቲም ሁለት ጥምዝ ዳቦ ቁርሳችንን አብልተው ትምህርት ቤት ሲሸኙን በብዙዎቹ የሀገሪቱ ክፍል ደግሞ ድርቅና ርሃብ ብዙ ዜጎችን ሲያረግፍ ግርማዊነታቸው “የተወደድክ ሕዝባችን” እያሉ ይሸነግሉን ነበር። ተቃርኖውን ልብ ይሏል። በአምስት ሳንቲም ሁለት ዳቦው ለከተሜው እየቀረበ ገጠሩ በርሃብ አለንጋ ይገረፍ ነበር።
አልጋ ገልባጩ ደርግም “ዝሆኖቹን” እያስመረጠን በጦርነትና በርሃብ ይቀጣን ነበር። የተናዳፊ ንቧ ኢህአዴግም “የማር ሰፈፍ ሳይሆን የጥላቻ ስልቻ እያሸከመ” አንድንመርጠው ደጋግሞ አደባባይ አውሎናል። የዛሬዎቹ ማኒፌስተኞችም “የዘራቸውን አልተው ብለው ቢንዘረዘሩ” አሜን ለማለቱ አቅማችን መሟጠጡን ሊረዱት ይገባል። ሥልጣኔ ናፍቆናል፤ ስደትም አንገሽግሾናል።
ኑሮው አጡዞ በአፍንጫችን ሊደፋን እያጥወለወለን እንዳለ በግልጽ ቋንቋ ነግረናቸው “የሥልጣን ኮንትራታቸውን ይፈርሙ” እንጂ በሆሆታና በአደባባይ ግርግር ብቻ “እሹሩሩ!” ለማለቱ “የተስፋ አንቀልባችን” መበጠሱን አጥብቀን እናረጋግጥላቸው።
ከሁሉም በላይ ተከባብሮ፣ ተፈቃቅሮና ተደጋግፎ መኖሩ እንደ ሰማይ እርቆን ተፈራርተናል። የምናያቸው አብዛኞቹ ፖለቲከኞች “ላጉርስህ አጉርሰኝ” በሚል መርህ መቀመቅ ከተውን ለከፋ ድህነት እንደዳረጉን ከምርጫ በፊት ነግረናቸው ንስሃ ቢገቡ ይበጃቸዋል። የሙስና ደዌ ከኮረና ብሶ ፈውስ አልባ ሆኖብናል።
ታማሚዎቹ እኛ፤ ቫይረሱ የፖለቲካቸው ውጤት መሆኑን እያቃሰትንም ቢሆን ልንነግራቸው ይገባል። የዜጎች የኑሮ ደረጃ ተራርቆ የተራራና የሸለቆ ያህል ተለያይቷል። አሁን ፖለቲካው ይሄ ይጠፋዋል? ከየትኛውም ዘመን ይልቅ ሀገሪቱ ዛሬ የገነት ምንጭ ከመሆን ይልቅ እንደ ሐሞት የመረረ አስካሪ የወይን ጠጅ ጠጥታ እንድትንገዳገድ የፈረዱባት ራሳቸው የዚህ ዘመን ፖለቲከኞች መሆናቸው አልገባቸው ከሆነ ይግባቸው።
ዳቦ ብርቅ፣ ዘይት ድንቅ፣ መሠረታዊ መጠለያ ማግኘት ቅንጦት፣ መለወጫ ቅያሪ ልብስም ህልም የሆነባቸው ዜጎች የተቃፈችን ሀገር እየሸነገሉ ቢያባብሏት “ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ” እንደሚያስተርትባቸው ከማኒፌስቷቸው ማስተዋወቅ በፊት ለተመራጮቹ እውነቱ ፍንትው ተደርጎ ሊገለጽላቸው ይገባል።
ኢትዮጵያ ዛሬ የምትፈልገው “ኤሌሄ! ኤሎሄ! ላማ ሰበቅታኒ! ፈጣሪዬ ሆይ ለምን ተውከኝ!” እያለች ከምትጮኽበት መስቀል ላይ እንድትወርድ ነው። ስለሆነም የቀጣይ ቀናቱ የፖለቲካ ማዕከል ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ብቻ ይሁኑ እንጂ “የምረጡኝ ባዮቹ” የራስ ከፍታ ቅዠት መሆን የለበትም። “ፖለቲከኞች እንዳይነኩ!” የሚለው የሕግ ከለላ መሸሸጊያ ሆኖም እንዳንነቅፋቸውና “የማኒፌስቷቸውን የዓይን ጉድፍ” እንዳናመለክታቸው አያስፈራሩን አይዛቱብን።
ይልቅስ ሹማምንቶቻችንም ሆኑ ፖለቲከኞቻችን “ተራ ሰው” መሆናቸውን ይንገሩን፤ ከእኛ ጋር ለዘይት መሰለፋቸውን ያረጋግጡልን እንጂ የመጓጓዣ ትራንስፖርት ጥበቃ ፀሐይ እያንቃቃን እያዩ በጥቁር መስታወት በተለበጠው በቪ 8 መኪናቸው ውስጥ ተንፈላሰው እንደተቀመጡ “ይሄ ሁሉ ሰው የምርጫ ካርዱን ቢጥልልኝ በቀላሉ አሸንፍ ነበር” እያሉ የተከፋው ልባችንን ወደ እነርሱ እንዲያዘነብል ፈጣሪን አይፈትኑት።
ለማንኛውም ማኒፌስቶ፣ ቃል ኪዳን፣ ድርሰት፣ ኮንትራት ወዘተ. የሚሉ ቃላት እዚያው መዛግብተ ቃላት ውስጥ አርፈው እንዳሸለቡ ይኑሩ። ለእኛ የሚያስፈልገው ሰርቶ የሚያሰራ የተግባር ተመራጭ ፖለቲከኛ ነው። የሕዝብ አክብሮት፣ የተረጋጋ ሕይወት፣ አርቆ አቃጅነት፣ ከሁሉም በላይ በቅድሚያ ዳቦ! ዳቦ! ዳቦ ነው የራበን። ይህንን ነው የምንፈልገው። ለወሬ ለወሬማ የእሳት ወላፈን የሚተፉ የፌስ ቡክ ካድሬዎች ሞልተውን የለ? አቦ ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን የካቲት 20/2013