ስልጠናው ብዙ ጊዜ በቃላት ብቻ ታጅቦ ይሰጥ ከነበረው በእጅጉ የተሻለ እና በሥራ ላይ ለሚገኙ አካላት እውቀት የሚያስጨብጥ እንደሆነ ነው የምትናገረው፡፡ በተለይ ደግሞ በርካታ የዘርፉ ተዋናዮች በአንድ መድረክ ላይ ሰፊ ውይይትና ረጅም ቀናትን የወሰደ ምክክር ያደረጉ ሲሆን፤ በቀጣይ ይህን እውቀት በየተቋማቸውና በሥራ ላይ የሚተገበር ከሆነ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚመዘገብ ተስፋ ታደርጋለች፡፡
በእርሷ እምነት መሰል ስልጠናዎች መነቃቃትን ከመፈጠርም በላይ ክፍተቶችን በሚገባ ለመለየትና ባለድርሻ አካላት በቀጣይ በጋራ በሚያከናውኗቸው ተግባራት ላይ እንዲያተኩሩ ብሎም ለችግሮችም መፍትሔ ለማበጀት ዓይነተኛ መንገድ እንደሆነ ትገልጻለች፡፡
ተቋማትም ስልጠናዎችን ለመስጠት ሲያስቡ በተዋቡ ቃላት እና ‹‹ፓወር ፖይንት›› የታጀበ ድግግሞሽ ወጥተው በተግባር የተደገፈ ስልጠና ቢከተሉ አገሪቱ የምትፈልገውን ለውጥ ለማምጣት መሰረት ይጥላል የምትለው ከባቱ ከተማ የመጣችው ወይዘሮ በሻሼ አዮ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማናጅመንት ኢንስቲትዩት ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ጋር በመተባበር 400 ለሚሆኑ ዘርፉን ለሚመሩ አመራሮች፣ ሥራ ተቋጮች፣ አማካሪዎችና የምህንድስና ባለሙያዎች ከጥር 20 እስከ 30 ቀን 2011 ዓ.ም በአዳማ ከተማ ሲያካሄድ የነበረው ተግባር ተኮር ስልጠና ትናንት በተጠናቀቀበት ወቅት ነው፡፡
አቶ ሚካኤል አሰፋ በቢሾፍቱ ከተማ የኮንስትራክሽን ባለሙያ ሲሆን፤ ስልጠናው በብዙ መንገድ ልዩነቶችን የሚያመጣ እንደሆነ ነው የሚናገረው፡፡ በተለይም ደግሞ በተቋራጭ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና አማካሪዎች መካከል ያለውን አለመግባባት መቀነስ፤ የኮንስትራክሽን አስተዳደር ለማዘመንና፤ የተንዛዛ የጨረታ ሂደትና የመንግሥት ሀብት ከብክነት ለመታደግ ትልቅ ሚና ይኖረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በግንባታ ላይ የሚሳተፉ አካላት የተቀናጀ አሠራር ዘርግተው ለመሥራት ማሟላት የሚጠበቅባቸውን ብቃትና ታማኝነት ብሎም ተነሳሽነት እንዴት እንደሚመጣ የሚያሳይ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ የዋጋ መዋዠቅ፣የዲዛይን መለዋወጥና የጊዜ ብክነትን ለማስቀረትም ሚናው የላቀ እንደሆነ ይነገራል፡፡
የባሌ ዞን ኮንስትራክሽን ጸህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሙሎ ዱሬቲ በበኩላቸው፤ ስልጠናው ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንዳለው ሁሉ በአገሪቱ የሚካሄደው ግንባታና ፖለቲካዊ ውሳኔ የሚፈልጉ አሠራሮችም በኮንስትራክሽን ላይ እየፈጠረ ያለውን ጫና የሚያሳይ ነው፡፡ ለዚህም ተጨባጭ መፍትሔ ለመስጠት መከተል ስለሚገባው አሠራር በጉልህ የሚያሳይ ነው ይላሉ፡፡ በተለይም ትልልቅ ፕሮጀክቶች እና የከተማ ግንባታዎች በሳይንሳዊ መንገድ እንዴት መካሄድ እንዳለባቸው የሚያሳይ ስልጠና ሲሆን፤ እንደ አገር ሰፊ ክፍተት ስለመኖሩም ለመረዳት መቻላቸውን ይገልጻሉ፡፡ በዚህም ላይ በሰፊው መሠራት አለበት የሚል አቋም አላቸው፡፡
በግንባታ ላይ ያለውን ሙስና ለማፅዳትም መንግሥት ቁርጠኛ መሆን እንዳለበት በመጠቆም፤ ኮንስትራክሽኑ በተማሩ ሰዎች እየተገነባ ወደ ዘመናዊ መንገድ መሄድ አለበት፡፡ በተለይ ደግሞ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ወደ ኋላ የቀረውን አሠራር ለማስተካከልም ሰፊ ኢንቨስትመንት ማካሄድ እንዳለበት ነው የሚጠቁሙት፡፡ በዘርፉ ላይ ዓመቱን ሙሉ ያለውን ጉድለት ለመሙላት በሚደረገው ኦዲት የማስተካከል ጥረትም አገሪቱ ከፍተኛ ገንዘብ እያጣች መሆኑን በመጠቆም ሀብት የማዳን ጉዳይ ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ እንደሆነ ያሳስባሉ፡፡
በኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተሞች ክላስተር አስተባበሪ አቶ አህመድ ቱሳ በበኩላቸው፤ በአገሪቱ ውስጥ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ከአምስት ከመቶ ወደ 25 በመቶ አድጓል፡፡ ከኢኮኖሚው 36 ከመቶ የሚሸፍን ነው፡፡ ዘርፉ ብዙ ካለመዘመኑም በተጨማሪ ለከፍተኛ ሙስና መጋለጡም አደጋ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡ በኢኮኖሚው ላይ መጫወት ያለበትን ሚና አልተወጣም ይላሉ፡፡
የክልሉ ውሃና ልማት ቢሮ ከ10ሺ በላይ ፕሮጀክቶች እንዳሉት የገለጹት አቶ አህመድ፣ በርካቶቹ የህብረተሰቡ ቅሬታ የሚቀርብባቸውና ዘርፈ ብዙ ችግር አለባቸው፡፡ ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው ዘርፉ በዘመናዊ መንገድ አለመምራት እና ሙስና ውስጥ መዘፈቁ ማሳያ በመሆኑ በተቀናጀ አሠራር ከዚህ መውጣት እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማናጅመንት ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር አርጋው አይሻ እንደገለጹት፣ በአገሪቱ ትልቁ ችግር ፕሮጀክቶችን በወቅቱ ያለማጠናቀቅ ነው፡፡ ከሚገመተው በላይ የዋጋ ንረት ያለበት ዘርፍ ኮንስትራክሽን ዘርፍ በመሆኑ አገሪቱን ፈተና ውስጥ እያስገባት ነው፡፡ በመሆኑም ስልጠናውን በዚህ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማቃለል ፣ ምርጥ ተሞክሮዎችንም ወደ ሌሎች ለማስፋፋት እና ለማሳደግ ሰፊ ዕድል የሚሰጥ ነው፡፡
በአገሪቱ የሚካሄዱ በርካታ ግንባታዎች የጥራት ደረጃ በጣም የወረደ እንደሆነ የሚናገሩት ዶክተር አረጋው፤ በዓለም ደረጃ አምስት የጥራት ደረጃዎች ያሉ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን የጥራት ደረጃ በአንድ እና ሁለት መካከል የሚገኝ ሲሆን፤ ይህም በዓለም መመዘኛ እና የጥራት ልኬት አኳያ በጣም ዝቅተኛ ነው ይላሉ፡፡
የኮንስትራክሽን የጨረታው ሂደቶችም የአገሪቱ የራስ ምታት ሆነውባታል፡፡ በውለታ አስተዳደርም ትልቅ ችግር አለበት፡፡ ይህም በአገሪቱ ላይ ትልቅ ጫና ፈጥሯል፡፡ ወደ ከፋ አደጋም ይወስዳታል፡፡ ዘርፉ በብቃት ረገድም የብቃት ጉዳይ ትልቅ ችግር ያለበት ሲሆን፤ አገሪቱን ዋጋ እያስከፈለ በመሆኑ በማናቸውም ደረጃ ያሉ አካት ብቃቱን ያስመሰከረ ሰው በሥራው ላይ ማሰማራት እንዳለባቸው ያሳስባሉ፡፡ ሕንፃ በጥራት እንዲገነባ ብቃት ያለው ሰው ማሠማራትም የአገርን ህልውና በማስቀጠል እና ባለማስቀጠል ላይ እንደመወሰን ነው ይላሉ፡፡ በመሆኑም በስልጠና እና በተሞክሮ መጠናከር እና መስተካከል እንዳለበት ዶክተር አርጋው ያሳስባሉ፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 1/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
_