እየሩስ አበራ
የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ትግል መገለጫ የሆነው የዓድዋ ድል ሲወሳ ልዩና ልብን ፈንቅሎ የሚወጣ ስሜት ይሰማኛል።የዓድዋ ድል ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን አባቶቻችንና እናቶታችን የአገር ሉአላዊነት ለማስጠበቅ በከፈሉት መስዋዕትነት የተገኘ ታላቅ ድል ነው።
የዓድዋ ድል ኢትዮጵያዊያን ባህር አቋርጦ የመጣውን የፋሽስት ጣሊያን ጦር በጦርነት ሜዳ ተፋልመው የአሸናፊነት ድል የተጎናፀፉበት፣ በአፍ ሪካ ልዩ ህዝቦች የሚያደርጋቸውን አኩሪ ታሪክ ያስመዘገቡበት ነው።
አድዋ።ነጮች አፍሪካን በቅኝ ግዛት እንደ ቅርጫ ስጋ ሲከፋፈሏት ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን ባደረጉት ተጋድሎ አይደፈሬነታቸውን አስመስክረው ጠላት ደግም እንዳያንሰራራ ድባቅ የመቱበት ነውና በአይነቱ ለየት ያደርገዋል ፡፡
ጦርነቱ በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ የኢትዮጵያ ህዝቦች በዘር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋና በጎሳ ሳይከፋፈሉ፣ ሳይለያዩ ከዳር እስከ ዳር በአንድነት ሆ! ብለው የዘመቱበት ነው ። ይህ በአንድነት መሠረት ላይ የታነጸ የነጻነት ድል ኢትዮጵያዊያንን ከቅኝ ግዛት ነጻ በማውጣት ለአፍሪካ ህዝቦች ኩራት ለመሆን አስችሏል።
ለሀገር አንድነት ቆመው ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰው ለዚህ ትላቅ ክብር ያበቁን የነጻነት ፋና ወጊ አያት ቅድመ አያቶቻችን ጀግኖቻችን ናቸውና ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል። ዛሬ የነጻነት ተምሳሌት የሆነች ሀገር አስረክበውን በነጻነት ጎዳና እንድንራመድ በኩራት አንገታችን ቀና አድርገን በዓለም አደባባይ በክብር ከፍ ብለን እንድንታይ አድርገዋል።
የዓድዋ ጀግኖች ታሪክ መቼም ቢሆን ታሪክ የማይረሳው፣ ከትውልድ ትውልድ፣ ሲዘከር የሚኖር፣በአንድነት መሠረት ላይ የፅና የኢትዮጵያውያን የድል ብስራት ነው። የዚህ አኩሪ ታሪክ ባለቤት የሆኑት ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች ታሪክ ሲወሳም በአብዛኛው የወንዶች ጀግንነት ጎልቶ ይነገራል።በአንጻሩም ጥቂት ሴቶች ብቻ በምሳሌነት ይጠቀሳሉ።
ምንም እንኳን በጦርነቱ ስማቸው በጉልህ የተጠቀሱ ሴቶች መኖራቸው ባይካድም የአብዛኞቹ ሴቶች ታሪክ ሳይመሰከር ሲዘከር ቀርቷል፡፡ እኔም ብሆን ታሪካቸው ሳይነገር እንደዋዛ ተድበስብሶ የቀረበት ምክንያት ምን ይሆን የሚለው ጥያቄ ዘወትር ወደ አዕምሮዬ ይመላለሳል።
የሁሉም ኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈበት የዓድዋ ድል የጥቂቶች አልያም የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ብቻ አይደለም።ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ በነቂስ ወጥቶና፤ ተዋግቶ መስዕዋት በመሆን በጋራ ያስመዘገበው ድምር ውጤት ነው።
ከህብረተሰቡ ግማሽ ያህል የሚሆኑት ሴቶች ደግሞ ምንም እንኳን በጦርነቱ ግንባር ለግንባር ባይገጥሙም ከውጊያ ባልተናነሰ ተጋድሎ በጦርሜዳ ውሎ ያበረከቱት ድንቅ አስተዋፅኦ በታሪክ ሲታወስና ሲወሳ የሚኖር ነው።
ሴቶች በጦርነቱ ባይዋጉም የነበራቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን የሚናገሩት የታሪክ ጸሐፍት ‹‹ክተት ሠራዊት፤ ምታ ነጋሪት›› ተብሎ አዋጅ ከተነገረ ከመስከረም ወር ጀምሮ እስከ የካቲት ወር ባለው ጊዜ ዓድዋ እስከ ሚደርሱ ብዙ ኪሎሜትሮች ተጉዘው እንደነበር ያወሳሉ።በጦርነቱ ለተሳተፈው ከመቶ ሺህ በላይ የሚቆጠር ሠራዊት ፍላጎትን ማሟላት የሚችሉት ሴቶች ብቻ እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡
የታሪክ ተመራማሪዎች እንደሚያወሱት በዓድዋ ጦርነት ከተዋጊው ጦር ጀርባ ከ20 እስከ 30 ሺ የሚጠጉ ስንቅ አቅራቢ ሴቶች መሳተፋቸውን ነው። ምንም እንኳን የዓድዋ ጦርነት ግማሽ ቀን የተካሄደ ቢሆንም የዓድዋ ድል ያለሴቶች ተሳትፎ እውን አልሆነም ነበር ።
በዓድዋ ጦርነት ወቅት አፈር እየላሱ ድንጋይ ተንተርሰው ከተዋጉ ኢትዮጵያውያን በተጨማሪ ከዓድዋ ጋር ተያይዞ ስማቸው ሳይነሳ የማይቀረው እቴጌ ጣይቱ የውጫሌውን ውል ሲቃወሙ ‹‹ እኔ ሴት ነኝ፤ ጦርነት አልወድም፤ ግን እንደዚህ አይነት ውል ከመቀበል ሞትን እመርጣለሁ›› በማለት አጼ ሚኒልክን ለጦርነት አነሳሰተዋል ።
የጦርነቱን ስልት በመቀየር ብልህ መላ በመዘየድ ዝነኛ ምሳሌ የሆኑት እቴጌ ጣይቱ በዓድዋ ጦርነትም በማጀት ሳይቀሩ በጀግንነት በማዋጋት ለሌሎችም ሴቶች መነሳሳት ምሳሌ መሆን ችለዋል ።
እቴጌ ጣይቱ በጦርነቱ የጠላት ጦርን ውሃ ቢቆጣጠሩ በውሃ ጥም ሊያልቁ እንደሚችሉ በመናገር የአመራር ስራን ይከውኑ ነበር።መቀሌ ላይ ባለው የጠላት ምሽግም ብልሃት በመዘየድ ጠላትን ለሽንፈት ዳርገው በርካቶች ሰው ሊሞቱበት የሚችለውን ጦርነት በማስቀረት ሕይወታቸውን መታደግ ችለዋል።
በዓድዋ ጦርነት በርካታ ሴቶች በስንቅ አቅራቢ፣ ወኔ ቀስቃሽነት፣ የቆሰለውን በማከምና የመጀመሪያ ደረጃ እርዳታ በመስጠት፣ እንዲሁም በሰላይነት ትልቅ ተሳትፎ በማድረግ የድርሻቸውን እየተወጡ እንደነበር ይጠቀሳል።
በጠላት እሳቤም ሴቶች ደፍረው ይዋጋሉ ወይም ይሰልላሉ ተብሎ ስለማይገመት መረጃዎችን በማቀበልና የፋሽስት ጣሊያኖችን መገናኛ መስመሮች በመቁረጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸው ይነገራል።
ፀሐፊ ትዕዛዝ ገብረ ስላሴ ‹‹ አጼ ሚኒልክ በአዳራሽ፣ እቴጌ ጣይቱ፣ ባለሟሎቻቸውና ወይዛዝሩን በእልፍኝ ይዘው ግብሩን አንድ ቀን ሳያጎድሉ ይዘምታሉ።ከዘመቻ ላይ ጠጁ ማሩ አለመጎደሉ ስለምንድነው ያልክ እንደሆነ ይህንን ታሪክ መመልከት ነው።
በስድስት ድንኳን እንጀራው ሲጋገር ሲያድር፣ በአራት ድንኳን ወጥ ሲሠራ ሲያድር፣ ጠጅ በኮዳ ሦስት መቶ ስድስት የሚሆን ገንቦኛ ሲጓዝ ይጎድል ይመስላል›› በማለት ሴቶች ወታደሮችን ለመመገብ ቀን ከሌት ያለ ድካም መልፋታቸው ያሳ ያሉ፡፡
ፊት አውራሪ ተክለሀዋርያትም በመጽሐፋቸው እንዳሰፈሩት፣ ሴት አገልጋይ ወለተ አማኑኤልን ጠቅሰው ያለመታከት ከጠዋት እስከ ማታ ታስተናግዳቸው እንደነበር በማውሳት ‹‹የብዙ ሴቶችን ድካምና ጥረት አይቼ እነሱ ባይሳተፉ ኖሮ ዓድዋ ድል አይመዘገብም ነበር›› የሚል ድምዳሜ አስፍረዋል፡፡
በዓድዋ ጦርነት ታሪክ ሴቶች ሚና በደፈና የተቀመጠ በመሆኑ ከተነገረላቸው ታሪክ ብዙ ያልተነገረላቸው መኖሩን ያሳያል ።የእናቶች ጀግንነት የታየበት የዓድዋ ድል ሴቶች ልጅ ወልዶ ከማሳደግ በዘለለ የሀገር ሉዓላዊነትን በማስጠበቅ ለነጻነት የከፈሉትን ዋጋ ከፍ ብሎ የሚያታይ ነው፡፡ጀግኖች እናቶች እነሱ ጀግነው ሌላውን በማጀገን ለሀገር የከፈሉት ውለታቸው ከቶም ልንረሳው የሚችል አይደለም።
በአሁኑ ወቅት ይህን የድል በዓል በየዓመቱ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዘንድ በደመቀ ሁኔታ ያከብራል። እነሆ ኢትዮጵያውያን በወራሪው ጣሊያን ላይ ድል ከተቀዳጀ 125ኛው ዓመት ሆኖል ። እነዚህ በዓድዋ ድል የዘከርናቸው ጀግኖች ሴቶች ዛሬ በተሰማሩ መስክ ሁሉ አመርቂ ውጤት በማስመዝገብ ፤ የሀገርን ሰላም በመጠበቅና በማስጠበቅ ለሀገር አንድነት ከፊት ለፊት የሚሰለፉ መሆናቸው እያሳዩ ይገኛል።
የሴቶች የሀገርን አንድነት በማስጠበቅ ሰላም እንዲሰፍን በማድረግ በኩል ያላቸው ሚና ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ላቅ ያለ ነውና።ሴቶች በሀገራችን የታየውን ለውጥ መሠረት በማድረግ አዲስ ኢትዮጵያን በጠንካራ መሰረት ላይ በመገንባት፣ ትውልድን በማነጽ ኃላፊነት አለባቸው።
በዓድዋው ድል የደመቀውን የነጻነት ትግል ድህነት ለማሸነፍ በመስራት ሀገራቸውን አንድ እርምጃ ወደፊት ለማራመድ የበኩላችንን የምንወጣበት መሆን አለበት መልዕክቴ ነው አበቃሁ።ክብር ለዓድዋ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ይሁን።
አዲስ ዘመን የካቲት 20/2013