የህወሓት ጁንታ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ አገር የማዳን እና ህግ የማስከበር እርምጃ በትግራይ ክልል ተካሂዶ በአጭር ጊዜ በድል ተጠናቋል።
የህግ ማስከበር እርምጃው በ15 ቀናት ውስጥ መጠናቀቁን ተከትሎም፤ ወንጀለኞችን ለህግ የማቅረብ፣ አካባቢውን መልሶ የማደራጀትና የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረስ ትኩረት ተሰጥቷቸው ተከናውነዋል። በዚህም የጁንታውን አመራሮች ይዞ ለህግ ከማቅረብ ባለፈ፤ የክልሉን አስተዳደርም፣ መሰረተ ልማቶችም መልሶ ማደራጀት ተችሏል።
ቀጣይነት ባለው መልኩ እየተከናወነ ባለው የሰብዓዊ ድጋፍም ቢሆን፤ መንግሥት ባለው አቅም አስፈላጊውን የምግብ፣ የመድኃኒትና አልባሳትን የመሳሰሉ ድጋፎችን ሲያደርስ ቆይቷል።
አሁንም ከኢትዮጵያውያን እንዲሁም ዓለምአቀፍ ተቋማት ጋር በመሆን እያደረሰ ይገኛል። እስካሁን ባለው ሂደትም ከሶስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ ደርሷል።
በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ግን በሴራ ተወልዶ በሴራ ያደገው እና ይሄንኑ የሴራ ተግባሩን እስከ ሞት ጉድጓዱ ይዞ የዘለቀው የህወሓት ጁንታ፤ ዛሬም በርዝራዦቹ አማካኝነት ጥፋቱን ቀጥሎበታል። ይሄን ተግባሩን የከፋ የሚያደርገው ደግሞ ሲገድለውና ሲዘርፈው ብሎም በስሙ ሲነግድበት የኖረውን የትግራይ ህዝብ ዛሬም መቃብር ውስጥ ሆኖ በርዝራዦቹ አማካኝነት “ከአብይ የተላከልህን ድጋፍ ተቀበልክ” ብሎ የማሳደድና የመግደል ተግባር ውስጥ ገብቷል። ይህ የሚያሳየው የትግራይን ህዝብ የፖለቲካ ቁማር መጫወቻ ካርዱ አድርጎ ሊጠቀምበት ማሰቡን ነው።
ይህ ዘራፊ እና ከሀዲ ጁንታ የትግራይን ህዝብ ለዓመታት ሲዘርፍ እና ሲገድል መኖሩ ሳያንሰው፤ ራሱ ባመጣው ጦስ ለችግር ለተጋለጡ የክልሉ ነዋሪዎች እየቀረበ ያለውን የእለት ደራሽ ድጋፍ በተባባሪዎቹ አማካኝነት ከጉሮሯቸው ነጥቆ ሊያስወጣ ሲል በቁጥጥር ስር ውሏል።
በከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ላይ በፈጸመው ጥቃትም ክልሉንና ህዝቡን ዳግም ለጨለማ ዳርጎታል። ይህና መሰል እውነታዎች ጁንታው ምን ያህል የክልሉን ህዝብ ለመበደል እየሰራ መሆኑን አመላካች ነው። ሞቶም ቢሆን ከህዝብ ይልቅ “እኔ” ባይነቱ በገሀድም የታየባቸው አጋጣሚዎች ናቸው ማለት ይቻላል።
በዚህ ሁሉ ሂደት ግን የጁንታው ተቀላቢ የሆኑ የማህበራዊ ሚዲያ ሰራዊቶች በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ሆነው እውነትን የማዛባት፣ ሀሰትን የማሰራጨት፣ ህዝብንም ሆነ ዓለማቀፍ ተቋማትና ማህበረሰቡን እያደናገሩ የጥፋት ዘራቸውን ለመዝራት ለአፍታም እንቅልፍ አልያዛቸውም።
“ሀሰት ሲደጋገም እውነት ይመስላል” እንዲሉም፤ የተቀናጀ እና የተናበበ የሀሰት መረጃን በማሰራጨት የሆነውን አልሆነም፤ ያልሆነውን ሆኗል፤ የሞተውን ህያው ነው፤ ወዘተ. እያሉ በተለይ የውጪውን ማህበረሰብ እና ዓለምአቀፍ ድርጅቶችን በኢትዮጵያ መንግሥት እና እውነቱን አይተው ከሚዘግቡ የመገናኛ ብዙሃን የሚሰሟቸውን እውነቶች እስከመጠራጠር የሚያደርስ ዘመቻ ሲያካሂዱ ተስተውሏል።
በዚህ የማደናገሪያ የሀሰት መረጃ ዘመቻቸው በክልሉ ያለውን በደልና ችግር የውጭ መገናኛ ብዙሃንና ዓለምአቀፍ ተቋማት ገብተው እንዲያዩ ሲወተውቱ መቆየታቸውም ይታወሳል። ይሄን ማለታቸው ግን ከልባቸው እንዳልሆነ እና የኢትዮጵያ መንግሥት ለእነዚህ ተቋማትና ድርጅቶች በሩን አይከፍትም ከሚል የሞኝ ሀሳብ የመነጨ እንደነበር ለመረዳት ይቻላል።
መንግሥት ግን የአካባቢውን ደህንነት ካረጋገጠ በኋላ አስቀድሞ ቃል በገባው መሰረት ከ130 በላይ ለሚሆኑ ዓለምአቀፍ ተቋማት ወደስፍራው ሄደው የሰብዓዊነት ሥራውን እንዲያግዙ አድርጓል፤ ሰባት ዓለምአቀፍ የሚዲያ ተቋማትም በአካባቢው ያለውን እውነታ እንዲዘግቡ ፈቅዷል። ይሄንን ተከትሎ የጁንታው ቅልብተኛ የማህበራዊ ሚዲያ ሰራዊቶች እያሰሙት ያለው ጩኸት አሳዛኝም አሳፋሪም ነው።
እነዚህ የሀሰት መረጃ ቀበኞች ዛሬ ላይ በክልሉ ስላለው ነገር ከሚያሰራጩት የሀሰት መረጃ በላቀ መልኩ የሚዲያዎቹ ወደአካባቢው መግባት አሳስቧቸዋል። ምክንያቱም ሚዲያዎቹ ህብረተሰቡ ጋር ደርሰው ሲወራ ስለነበረው የሴቶች መደፈር ታሪክ፤ ስለሰብዓዊ ድጋፍ ሂደቱ፤ ስለወደሙ የመሰረተ ልማቶች ጉዳይ እና ሌሎችም ማጣራት የሚችሉበት እድል ተፈጥሮላቸዋል። ይህ ሲሆን ደግሞ የሀሰት ቀበኞቹ የበሬ ወለደ ጫጫታ መጋለጡ አይቀሬ ነው።
እናም ገና ካሁኑ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚገኙ የጁንታው ርዝራዦች የሚዲያ ተቋማት ባለሙያዎቹን እንዲያገኙ እና የእነርሱን ውሸት የሚያጠናክርላቸው የተሳሳተ መረጃ እንዲያቀብሏቸው የሚዲያ ባለሙያዎችን ስልክና አድርሻ ሳይቀር በማቀበል እየወተወቱ ይገኛል። ይህ ጥረታቸው ምን ያህል ይሳካል የሚለው ግን በስፍራው የሚገኙ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች መረጃን የማጥራትና እውነትን የመፈለግ አቅምና ፍላጎት ላይ ይመሰረታል።
በስፍራው ያሉ የመገናኛ ብዙሃን በክልሉ ስለሆነውና እየሆነ ስላለው ነገር ሁሉ ትክክለኛ መረጃን አውጥቶ የማሳየት ታሪካዊ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን ተገንዝበው መስራት አለባቸው። በመሆኑም በስፍራው የተሰማሩ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትና ባለሙያዎች በተለያየ መልኩ ከሚለቀቁና ከሚነገሩ ወፍ ዘራሽ አሉባልታዎች ራሳቸውን አንጽተው፤ ሙያዊ ስነ ምግባርንና የሞራል ልዕልናቸውን ጠብቀው ሊንቀሳቀሱ ይገባል።
እውነት የምትገኘውም እኔ ልንገርህ በሚሉ ሰዎች እጅ ሳይሆን፤ ነገሮች ተፈጠሩ ተከናወኑ ከተባለበት ስፍራ፣ ህዝብና ሰው መሆኑን መረዳት ይኖርባቸዋል። እናም በክልሉ የተሰማሩ የሚዲያ አካላት በተባለ ላይ ሳይሆን የሆነውን ደርሶ በማየትና በተጨባጭ ማስረጃ ላይ በመመስረት ያለውን እውነት አውጥተው ለዓለም ህዝብ የማሳወቅ እና ውሸትን የማጋለጥ ታሪካዊ ኃላፊነት መወጣት ይኖርባቸዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 20/2013