በ ላንዱዘር አሥራት ዘለቀ ጋዜጠኛና ከፍተኛ የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያ
ኢትዮጵያ አገር ሆና በዓለም ላይ ከታወቀችበት ረጅም የአገረ መንግሥትነት ታሪክን ጨምሮ ፋሽስች ሀገራት የኢንዱስትሪ አብዮት መፈንዳትን ተከትሎ ለቅኝ ግዛት በወታደራዊ አቅም የሚበልጡዋቸውን የዓለምን ደካማ ሀገራት በስፋት ካለአንዳች ሞጋች ወረው መያዝ እስከቻሉበት የሀያኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ እንኳ ያለውን የኢትዮጵያን የአውደ ውጊያ ታሪክ ብንመለከት እጅግ በርካታ የጦር ሜዳ ድሎች ተሰንደው ተቀምጠዋል።
ለአብነት ያክል በፈረንጆቸ ማርች 1875ና ከማርች 7-9/1876 ኤርትራ ውስጥ ጉንዴትና ጉራ ሀማሴን መረብ መላሽ አቅራቢያ ግብጾች በእስማኤል ፓሻ እየተመሩ ከቱርክ መዳከም በኋላ ቀጠናው ላይ ሃያል ለመሆን በማለም ዘመናዊ ጦር በመገንባት ጥቁር አባይን ከምንጩ ለመቆጣጠርና ግዛታቸውን ወደ ኢትዮጵያ ለማስፋት ሁለት ተከታታይ ጦርነት በኢትዮጵያ ላይ ከፍተው ድል ሆነው ተመልሰዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያን በዮሃንስ iv እና በሻለቃ ራስ አሉላ እንግዳ እየተመሩ በ1875 በኤርትራ አቅራቢያ ጉንዴት ላይ ግብጽን ጦርነት ገጥመው ኢትዮጵያ ጦርነቱን በተቀናጀ የአውደ ውጊያ አመራርና በህዝቡ አንድነት ድል ያደረገች ቢሆንም ዳግም ጉራ ሀማሴን መረብ መላሽ አቅራቢያ ግብጾች ሽንፈታቸውን ላለመቀበል አሻፈረን ብለው በእስማኤል ፓሻ እየተመሩ በፈረንጆች ከማርች 7-9 በ1876 ከሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ብዙ እልቂት ያስከተለ ጦርነት አድርገዋል፡፡ ሆኖም ግን ኢትዮጵያውያን በታላቅ ወኔና ጀብደኝነት አገራችንን አሳልፈን ለባዕድ አንሰጥም በሚል ልክ እንደ አንድ ሰው ሆነው በመዋደቅ ለሁለተኛ ጊዜ አንፀባራቂ ድል በግብጾች ላይ ተጎናጽፈዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሁለቱም ጦርነቶች በፈርኦኖች ላይ አኩሪ ድል ተጎናጽፋ ለነገም አስተማሪና አይቀጡ ቅጣት ቀጥታ መክታ ወደ መጡበት መልሳቸዋለች፡፡
ካራማራን፤የማሃዲስት ሱዳን ወረራን ማርች 1/ 1896 በፈረንጆች አቆጣጠር የተደረገውን የዓድዋ አውደ ውጊያን ጨምሮ ኢትዮጵያ ከወራሪዎች ጋር ሉዓላዊነትዋን አጽንታ ላለማስደፈር ያደረገቻቸውን የሕልውና ጦርነቶችን ሁሉ አጠቃሎ በውጭም በውስጥም ተሰንደው የተቀመጡ የኢትዮጵያን የአውደ ውጊያ ጀብዶች እንዲሁም የውትድርና ታሪኮች በጥልቀት በምንመረምርበት ወቅት ሕዝቡ ከቡድን፤ከግለሰብና ከአንድ ወግን ፍላጎት ይልቅ አገሬን ብሎ ከአራቱም አቅጣጫ በነቂስ በመትመም የአገሩን ሁለንተናዊ አንድነትና ነጻነት አስከብሮ ፤የጊዜው ትውልድ ልክ እንደ አንድ ሰው ቆሞና ተናቦ ዘወትር ትውልድ የሚያስታውሰውን የሀገር ፍቅር ታሪክን በደማቅ ጽፎ አልፏል፡፡
የኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ መጀመሪያ ተደርጎ በብዙሃኑ ጻፍት ዘንድ እስከታመነበት የጎርጎሮሳዊያኑ የዘመን አቆጣጠር (1855 )፤አሊያም ዘመነ መሳፍንት መቋጫውን እስካገኘበት እንዲሁም ንጉሠ ነገሥት አጼ ቴዎድሮስ ሁለተኛው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ከመሆናቸው አስቀድሞና ማዕከላዊ መንግሥት በይፋ ከመመስረታቸው በፊት የአካባቢ ገዥዎች አንዳቸው ከአንዳቸው ጋር በመተባበር ኢትዮጵያ ከውጭ የሚቃጣባትን የጠላት ወረራና መስፋፋት በተቀናጀ አኳኋን በጋራ በታላቅ ጀብድ የመከቱ መሆናቸውን በጊዜው የተደረጉ የሕልውና ጦርነቶችን ጠቅሶ ታሪክ በሚገባ ያስረዳናል ።
እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር በ1966 በርካታ ሀገራት ኢትዮጵያኒዝም የሚል የትግል መፈክርን አንግበው ከኢትዮጵያ የአወደ ውጊያ ድሎችና ታሪኮች ልምድ በመውሰድ ብዙሃን የአፍሪቃ፡የላቲን አሜሪካ፡የሩቅ ምስራቅ ሕዝቦች እንዲሁም በመላው ዓለም ላይ የሚገኙ ጭቁን ሕዝቦች ከቅኝ ግዛት ነጻ መውጣት እንደሚቻል ከኢትዮጵያ አበረታች ተሞክሮ በመውሰድ አገራቸውንና አጠቃላይ ግዛቶቻቸውን ከቅኝ ግዛት ነጻ ማድረግ ችለዋል፡፡
በትግላቸው ወቅት ኢትዮጵያኒዝም ብለው እንደጀመሩ ሁሉ ከድል አጥቢያ ማግስት ቦኋላ አብዛኞቹ የአፍሪቃ ሀገራት ኢትዮጵያን የፓን አፍሪካኒዝም(የአፍሪቃ የነጻነት ብቸኛ ተምሳሌት አድርገው በመቀበል) የአገራቸውን ሰንደቅ_ዓላማ በሚያዘጋጁበት ወቅት በቀጥታ ኢትዮጵያውያን በአወደ ውጊያ ግንባሮች ሁሉ ይዘው የተዋደቁለትንና ኢትዮጵያ ከሀገረ መንግሥት ምስረታ ማግስት አንስቶ ስትጠቀምበት የነበረችውን
የኢትዮጵያን አርንጓዴ፣ብጫና ቀይ ሰንደቅ_ዓላማ ለነሱ በሚያመች መልኩ የቀለሞቹን ቦታ በመቀያየር እስከዛሬ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ ።
ኢትዮጵያ ውስጥ ከ1983 ወዲህ ስልጣን ላይ የነበረው ከፋፋዩ ህወሓት ኢሕአዴግና የሱ ተላላኪ የሀሴት ታሪክ ፈብራኪ ደራሲያን አጣመው ወደ ትውልዱ በነዙት ጭብጥ አልባ የሀሴት ትርክቶች፤ ሊሕቃኑ የታሪክ እሽቅድምድም ውስጥ በመግባታቸውና ሒሊናቸውን ስተው በጎሣ በመጠለፋቸው ምክንያት እንደ አንድ ሕዝብ የሚያስተሳስሩን አንጸባራቂ ጥቅል የጋራ ድሎች ሁሉ በቀላሉ እየደበዘዙ እንዲሄዱ የማድረግ ልዩ ልዩ ሙከራዎች በአፍራሽ ኃይሎች ድጋፍ በውስጥም በውጪም በስፋት እየተሰራባቸው መሆኑ ይስተዋላል፡፡
ጥናት ባይደረግበትም በገሚስ ለማለት በሚያስደፍር መልኩ አዲሱ ትውልድ የየራሱን ጎሣ የታሪክ ሊሕቃን ተከትሎ ጭልጥ ብሎ በመጥፋት በጭንቅላቱ ውስጥ በገሀዱ ዓለም ላይ የሌለችን ኢትዮጵያ ስሎ ሊታረቅ የማይችል የልዩነት ንትርክ ውስጥ ገብቶ ይገኛል ።
ደርግ መንበረ ስልጣኑን በተቆጣጠረበት ወቅትምጥቂት ወታደሮች በከፊል እያፈነገጡ የሕዝቡ ጭቆና አንገብግቧቸው በከፊል ለህዝቡ የመወገን አዝማሚያ ያሣዩ ከመሆናቸው በስተቀር ቀደም ሲል ጀምሮ በብዛት ወታደሩ በወቅቱ የሕዝቡን ሁለንተናዊ ፍላጎት አዳምጦ ተገቢውን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ የስርዓቶቹ ታማኝ ጠባቂ ሆኖ እንዲያገለግል ተደርጎ ይገነባ ነበር።
የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ )ስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜም ወታደሩን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጠባቂነት ይልቅ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስመር ጠባቂ አድርጎ በመገንባት ወታደሩ አስፈላጊውን መስዋዕትነት ሁሉ እየከፈለ ስርዓቱን ከሚገጥሙት አደጋዎች እንዲታደግ አድርገው ያንጹትም እንደነበር ሠራዊቱ ራሱ ከህወሓት ውድቀት ማግስት አንስቶ በመመስከር ላይ ይገኛል ።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ተዋጽኦ የተመሠረተውንና በዓለም አቀፍ ደረጃ ታላቅ ክብርና ዕውቅናን ከአራቱም ማዕዘናት የተረፈውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ልክ እንደ “ዶሮዋ ዘወትር እኔ ብቻዬን ጭሬ ካልበላሁት ጭሬ ልበትነው እንደ አሕያዋም እኔ ከሞትኩኝ ሰርዶ አይብቀል” የሚሉ ጥቂት ከጊዜው ጋር መራመድ የተሳናቸው ቆሞ ቀር ቡድኖች በሚያገኙት የሚዲያ አማራጭ ሁሉ ሲያብጠለጥሉት ይስተዋላል።
ለአብነት ያክል የሀገር መከላከያ ሠራዊቱን ሲያሻቸው የፓርቲ ውግንና እንዳለውና በብሔር የተከፋፈለ እንደሆነ አስመስለው ሕዝቦችን የማደናገር ከጅምሩ የጨነገፈ ሙከራ በማድረግና በሠራዊቱ ላይ በየጊዜው በሚከፍቱበት ልዩ ልዩ የሀሴት ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ሊያሸማቅቁት አልፎም ተግቶ ለዓላማው እንዳይንቀሳቀስ የስነልቦና ጫና ውስጥ ሊከቱት ቢጥሩም ሠራዊቱ ከተደረገበት የለውጥ ማሻሻያዎች በኋላ በፍጹም ለሕገ መንግሥቱና ለባንዲራው እንዲሁም ለመተዳደሪያ ደንቦቹ በመታመን የተከፈተበትን የሀሴት ፕሮፓጋንዳ ከፍ ባለ የዓላማ ጽናትና ቆራጥነት በማያዳግም መልኩ እስከወዲያኛው ተግዳሮቶችን ቀብሮ ወደ ፊት ለዓላማው በጽናት መገስገስ ችሏል ።
ይህ ከፋፋይና በታኝ ጥቂት ሴረኛ ቡድን ሠራዊቱን የማጥቃት ስራውን አጠናክሮ በመቀጠል በመከላከያ ሠራዊቱ መካከል በሚገኙ ብሔሮች መካከል የሀይማኖትና ዘር ተኮር ጥርጣሬን ለመፍጠር በማለም የጥፋት ኃይሎችን መልምሎ በማሰልጠን ሀገር የማፈራረስ እኩይ ዓላማውን እንዲያስፈጽሙለት በገንዘብ ግለሰቦችን በመደለል በአንዳንድ የአገራችን ክልሎች ከባድ የንብረት ውድመትና ኢሰብዓዊ ብሎም አረመኔያዊ ጥቃቶችን ንጹሃን ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ግንኙነት የሌላቸውን ለፍቶ አዳሪ ዜጎች ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት እየፈጸመ ይገኛል ፡፡
እነዚህ ከምስረታቸው አንስቶ በታሪካቸው ሕዝባዊ ዓላማ ኖሯቸው የማያውቅ ጥቂት ነብሰ በላ የጥፋት ኃይሎች ምንም እነሱ አንግበው ከሚንቀሳቀሱት ዘውግ ተኮር ፖለቲካዊ ዋልታ ረገጥነት ጋር ግንኙነት የሌላቸውን ንጹሃን ወገኖቻችንን በጅምላ በዘመናዊና ባሕላዊ መሳሪያዎች በመታገዝ ለተላላኪዎቻቸው ስምሪት በመስጠት ላለፉት ሦስት ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ተሰምቶ በማይታወቅ መልኩ የውክልና ጦርነት ከፍተው ዜጎችን በገዛ አገራቸው በሐይማኖትና በማንነታቸው እየለዩ ወራሪዎች ደፍረው ያላደረጉትን ኢሰብዓዊ ጭፍጨፋ እየፈጸሙ ይገኛሉ፡፡
ከሕግ ማስከበር እርምጃው አስቀድሞ የሰሜን እዝ ሠራዊታችንን አግተው በክህደት በዶዘርና ግሬደር አስፓልት ላይ አስተኝተው ገጭተው በመግደል በጅምላ ቆፍረው መቅበራቸውም በቅርቡ የሚታወስ ነው።
መከላከያ ሠራዊቱ ለሕገ መንግሥቱና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለገባው ቃልኪዳን በፍጹም በመታመን ስጋቶቹን በአጠቃላይ በአስተማማኝ ሁኔታ በማያዳግም መልኩ በመመከቱ የነዚህ ጥቂት የየትኛውም ሕዝብ ውክልና የሌላቸው ስግብግብና ራስ ወዳድ ቡድኖች ሴራ በሠራዊታችን በእጅጉ የተወዳጀ አንድነትና የጠነከረ የባንዲራ ፍቅር በቅርቡ ድል እንዲመቱ ተደርጓል ።
የሀገር መከላከያ ሠራዊቱ የአገሪቱ ለውጥ ወደተባለው ምዕራፍ ከተሸጋገረች በኋላ በዘርፈ ብዙ ውስብስብ ወታደራዊ ሥልጠናዎችና ዓለም አቀፋዊ ጥብቅ ወታደራዊ ዲስፒልኖች ተቋሙን በመግራት የሀገርን ሁለንተናዊ ሰላም ለማስጠበቅ የበኩሉን ጥረቶች እያደረገ የሚገኝ መሆኑን ከሚያደርጋቸው ልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎች መረዳት ይቻላል ፡፡
ሠራዊቱ እራሱን ለውስብስብ ቀጠናዊ፤አሕጉራዊ፤ እንዲሁም በዓለም ዘሪያ ዋስትናው የተረጋገጠ ሰላም የማስፈን ወታደራዊ ግዳጆቹን የኢትዮጵያን ክብር በሚያጎላ መልኩና የመከላከያ ሠራዊቱን ወታደራዊ ተልዕኮዎችን የማከናወን ብቃት ፍንትው አድርጎ ለዓለም በሚያሳይ አኳኋን ሰላም ለማስከበር በሄደበት ሁሉ በአጭር ጊዜ የተቻለውን መስዋዕትነት ከፍሎ የተሰማራበትን አካባቢ ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ በመመለስ እየሰራ መሆኑን ከልዩ ልዩ ምንጮች መረዳት ይቻላል፡፡
ከኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ምስረታ ዘመን አንስቶ የነበረው ሠራዊት የግዳጅ ተልዕኮ ተሰጥቶት በተሰማራበት ሁሉ ሰላምና ሰላም ፈላጊውን ሕዝብ በአስተማማኝ ሁኔታ በማቆራኘት ለዓለማችን ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚሆን ደማቅ አሻራውን በደምና አጥንቱ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል የሠላም ዘብ መሆኑን በማረጋገጥ ለአበርክቶውም ከዓለም ዙሪያ ፈርጀ ብዙ አበረታች አውቅናዎችን እንዲያገኝ አስችሎታል፡፡
ከዓለም አቀፍ አበርክቶው በላቀ መልኩ በሀገር ውስጥም ሉአላዊነታችን ለሴኮንድ ሳይሸራረፍ እንዲጠበቅ በድንበሮች አካባቢ የሚሰነዘሩ የጠላት ኢላማዎችንና ጥቃቶችን በብቃት ለመመከት እንዲያስችለው የቀበሮ ጉድጓዶችን መኖሪያው አድርጎ በታላቅ የዓላማ ጽናት ለሀገሩ ዘላቂ ልማት ምቹና ሰላማዊ መደላድል ለመፍጠር ብሎም ሕገ መንግሥቱን ለመጠበቅ የገባውን ቃል ኪዳን ዘወትር በላቀ የዓለማ ጽናት ገቢራዊ ለማድረግ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን በሚያስመዘግባቸው ውጤቶች መነሻነት መገምገም ይቻላል ።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰላምን በመላ ሀገሪቱ ከማረጋገጥ ሥራው ጎን ለጎን አቅሙ በሚፈቅደው ሁሉ ተሰማርቶ ሰላምና ጸጥታን በሚያስከብርበት አካባቢ ሁሉ በሥፍራው ከሚኖሩ ኗሪዎች ጋር በመናበብ በአካባቢው የሚስተዋሉ የልማት ውስንነቶች ላይ በመሰማራት ላይ ይገኛል፡፡ ለአብነት ያክል በጉልበቱ የአቅም ደካማ አርሶ አደሮችን ማሳ በእርሻ ሥራ ከማገዝ አንስቶ የዓመቱ አጠቃላይ ምርት እስከሚሰበስቡበት ጊዜ ድረስ በመደገፍ ይታወቃል፡፡
በዚህም ብቻ ሳይወሰን ከሚከፈለው ደመወዝ ቀንሶ በማዋጣት የትምርትና ጤና ተቋማትን የመሳሰሉ የሕዝብ አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎችን በመገንባት ምን ግዜም ከክብሩና ከጥቅሙ ባለፈ የሕዝብ አለኝታ መሆኑን ግብሩን መሠረት አድርገው ብዙሃን ካለ አንዳች ሀፍረት የሚመሰክሩለት ያልተድበሰበሰ እውነት መሆኑ አያጠያይቅም ።
የጥፋት ኃይሎች ለዓመታት ሲዘጋጁበት ቆይተው በሰሜን እዝ የሠራዊቱ ክንፍ ላይ ፍጹም ከወገን የማይጠበቅን ጥቃት የፈጸመው ቢሆንም ሠራዊቱ ሦስት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ንጹኃንን እና መሠረተ ልማቶችን ኢላማ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ አድርጎ የሕግ የማስከበር ግዳጁን በድል አጠናቋል ።
መከላከያ ሠራዊቱ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ሕግ የማስከበር ዘመቻውን በታላቅ ኃላፊነት እንደተወጣው ሁሉ በአንዳንድ የሀገራችን ክልሎች የዜጎችን በሕይወት የመኖር ሰብዓዊ መብት የሚጋፉና በዜጎች ላይ ማንነትን ማዕከል ያደረገ ጭፍጨፋ የሚፈጽሙ የቀድሞው የህወሓት ቡድን ከፋፋይ የጡት ልጆች በፈጸሙት በደል ልክ የሚያስተምራቸውን የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ የሁልጊዜም የሕዝብ አለኝታነቱን በጀመረበት አኳሃን በጽናት ያረጋግጥ ዘንድ ይጠበቅበታል።
የኢትዮጵያ ሕዝቦች በውስጥም በውጪም የሚኖሩ በቅርቡ ለሠራዊቱ ሲያደርጉት በነበረው መልኩ ድጋፋቸውን በሚቻላቸው ሁሉ አጠናክረው በመቀጠል ሠራዊቱ ከማንኛውም አካል ጣልቃ ገብነት በፀዳ መልኩ ተቋማዊ ቅርጽ እንዲኖረውና በአገር ውስጥና በጎረቤት ድንበሮች አካባቢ የሚስተዋሉ የፀጥታ ስጋቶችን በማያዳግም መልኩ መመከት እንዲቻለው የሁሉም ወገን ያልተቋረጠ ድጋፍ ዘወትር ያስፈልገዋል ተብሎ ይታሰባል ምክንያቱም ሠራዊቱን መደገፍ የአገሪቱን ሕልውና እንዳትናወጥ አድርጎ ማጽናት ነውና ፡፡
ኢትዮጵያውያን ዛሬም ወደ ፊትም ሕግ ማስከበርን ጨምሮ የሀገርን ሕልውና ለማስጠብቅ የምታከናውናቸውን የውስጥ ጉዳዮች ላይ ሰሞኑን ጠቅላይ ሚንስትሩ ለዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ ባስተላለፉት መልዕክት መሰረትና በሌሎች ሀገሮች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባትን ዓለም አቀፍ መርህን ማዕከል አድርገው አገራት ለጋራ ብልጽግናና አገራዊ ልማት በሚጠቅም መልኩ የሁለትዮሽ ግኑኝነታቸውን እንዲያደርጉ ኢትዮጵያ በመሪዋ በኩል አሳስባለች።
አዲስ ዘመን የካቲት 19/2013