እስማኤል አረቦ
ምርጫ የአንድ ሀገርን መጻኢ ዕድል ከሚወስኑት ጉዳዮች አንዱና ግንባር ቀደሙ ነው። ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ያካሄዱ ሀገሮች በልማትም ሆነ በመልካም አስተዳደር ብሩህ ተስፋ እንደሚጠብቃቸው ይታመናል።
በአንጻሩ ተአማኒነት የጎደለውና ከዴሞክራሲያዊ ሂደት ያፈነገጠ ምርጫ ያካሄዱ ሀገራት ሰላም የራቃቸውና በልማትም ወደ ኋላ የቀሩ እንደሚሆኑ የበርካታ የአፍሪካና ታዳጊ ሀገራት ተሞክሮ ያሳያል።
ለአንድ ምርጫ ስኬታማነት መንግሥትና ፖለቲካ ፓርቲዎች ከሚያደርጉት ጥረት ባሻገር የሲቪክ ማህበራት ሚና መተኪያ የማይገኝለት ነው። የሲቪክ ማህበራት ያልተሳተፉበትና ዕውቅናም ያልሰጡት ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ቢሆንም እንኳን በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት አይኖረውም።
ሆኖም ግን ኢትዮጵያ ባደረገቻቸው አምስት ሀገር አቀፍ ምርጫዎች ለሲቪክ ማህበራቱ የተሰጠው ትኩረት አናሳ ከመሆኑም ባሻገር ከሂደቱ እንዲወጡ የተለያዩ ጫናዎች ሲደረጉባቸው ተስተውሏል።
በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ በተሻለ ዴሞክራ ሲያዊነትን ተላብሷል በሚባለው በ1997ቱ ሀገር አቀፍ ምርጫ እንኳን የተለያዩ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች ምርጫውን እንዲታዘቡ ሲጋበዙ ሀገር በቀል የሆኑት የሲቪክ ማህበራት በበርካታ ክርክርና በፍርድ ቤት ውሳኔ ምርጫውን እንዲታዘቡ ተደርጓል።
ይህ ሁኔታ ደግሞ ከጅምሩ ስለምርጫው ተኣማኒነት ጥያቄ እንዲነሳበት አድርጓል። ከምርጫ 97 በኋላም ምንግሥት የሲቪክ ማህበራትን እንደጠላት በመቁጠርም ማህበራቱን እጅ ከወርች ቀፍድዶ የሚይዝ አዋጅ አወጣ።
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ አዋጅ ቁጥር 621/2001 በሚል የወጣው አዋጅም የሲቪክ ማህበራት ህልውና እንዲያከትም አድርጓል። በብዙዎቹም ላይ የሞራል ውድቀት አሳድሯል። ብዙ ነገርም ገድቧል። በአገሪቱ ላይም ትልቅ የልማትና የዴሞክራሲ ኪሳራ አሳድሯል። መንግሥት ፊት በመንሳቱና እንቅስቃሴያቸውን በአዋጅ በመገደቡ ዓለም አቀፍ ደጋፊዎች ብዙዎቹ ድጋፋቸውን እንዲያቆሙ አስገድዷቸዋል።
በተለይም በሰብዓዊ መብት ዙሪያ፣ በሰላምና በማህበረሰብ ልማት ግንባታ፣ ከዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ፣ ከምርጫና ከመሳሰሉ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ይሠሩ የነበሩ ድርጅቶች በሙሉ ሥራቸውን እንዲያቆሙ ተገደዋል።
ከ1997 በኋላ የተካሄዱ ሁለት ምርጫዎችም ያለሲቪክ ማህበራት ተሳትፎ የተካሄዱና አሸናፊውም መንግሥት፤ታዛቢውም መንግሥት የሆኑባቸው የይስሙላ ምርጫዎች ነበሩ።
በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ግን የሲቪክ ማህበራት ሚና እንደዚሁ ተድበስብሶ የሚቀር መሆን የለበትም፤ ጊዜውም የሚፈቅድ አይደለም።
ከለውጡ ወዲህ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ አዋጅ ቁጥር 621/2001 እንዲሻሻል ተደርጓል። አዲሱ አዋጅም በሲቪክ ማህበራት ላይ ተጥሎ የነበረውን ገደብ ያነሳና ለማህበራቱም ሰፊ ነፃነት የሚሰጥ መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል። በተለይም ዘንድሮ ለሚካሄደው ስድስተኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ሲቪክ ማህበራት ሀገራዊና ሙያዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ በር የሚከፍት ነው።
የሲቪክ ማህበራቱ ለመራጩ ማህበረሰብ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ከመስጠት ባሻገር ከቅድመ ምርጫ እስከ ውጤት ድረስ ያሉትን ሂደቶች በመታዘብና ህጸጾች በወቅቱ እንዲታረሙ በማድረግ ረገድ የሚጫወቱት ሚና በማንም ሊተካ የሚችል አይደለም።
በተለይም በዚህ ረገድ ከጅምሩ እስከ ፍጻሜው ድረስ በሲዳማ ህዝበ ውሳኔ የታየው የሲቪክ ማህበራት ሚና መጪውን ምርጫ የተሻለ ለማድረግ አቅሙ እንዳላቸው ያመላከተ ነው።
ስለሆነም መንግሥትም ሆነ በምርጫው ውስጥ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫው ዴሞክራሲያዊ ሂደቱን ጠብቆ ከፍጻሜ እንዲደርስ የሲቪክ ማህበራት የማይተካ ሚና እንዳላቸው በማመን አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ ሊያደርጉላቸው ይገባል።
ከላይ እንደገለጽኩት የሲቪክ ማህበራት ያልተሳተፉበትና ዕውቅናም ያልሰጡት ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ቢሆንም እንኳን በዓለም ማህበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት አይኖረውምና ከወዲሁ ወገብን ጠበቅ ማድረግ ይገባል። መንግሥትም ቢሆን የመጫወቻ ሜዳውን በማስፋት የሲቪክ ማህበራት ግዴታቸውን እንዲወጡ የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል።
የምርጫውን ስኬታማነት ከሚወስኑትና ዋነኛ ባለጉዳይም ከሆኑት አካላት መካከል የፖለቲካ ፓርቲዎች ዋነኛውን ስፍራ ይይዛሉ። መጪው ምርጫ እንዲከናወን የሚያስችል ይሁንታ በመገኘቱ፣ የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሕዝብ ድምፅ ለመዳኘት ራሳቸውን ከወዲሁ ማዘጋጀት መጀመር ይጠበቅባቸዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚዳኙት የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት እንደሆነ በሚታሰበው የሕዝብ ድምፅ ብቻ መሆኑ መታወቅ አለበት።
የፖለቲካ ፖርቲዎች ሃሳባቸውን ለሕዝብ ለመሸጥ ከመውጣታቸው በፊት፣ የቤት ሥራቸውን መጨረስ ይጠበቅባቸዋል። ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ የሚፈለገውን ዲሲፕሊን ያላሟላ የፖለቲካ ፓርቲ ለሕዝብ ብያኔ መቅረብ አይችልም። የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚመሩ ሰዎች ከፍተኛ የሆነ ብቃት፣ ልምድና ሥነ ምግባር ያስፈልጋቸዋል።
ራሳቸውን ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ጨዋታ ሕግ ማስገዛት የማይችሉና ግልጽና የተብራራ አጀንዳ የሌላቸው ፓርቲዎች፣ ሕዝብ ፊት በመውጣታቸው የሚያተርፉት ነገር እንደሌለ ሊረዱ ይገባል።
ሕዝብን በጉልበት፣ በማታለል፣ የማይጨበጥ ቃል በመግባት ወይም አገር በማተራመስ ሥልጣን መሻት እንደማያዋጣ መረዳት ይገባል። የሐሳብ ልዕልና የሚኖረው በሀቅ፣ በአገርና በሕዝብ ተቆርቋሪነት በሚደረግ ፉክክር ብቻ ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆነው ሕዝብ ፊት ለመቅረብ ይዘጋጁ።
ገዥው ፓርቲም ከመቼውም ጊዜ በተለየ የፖለቲካ ምኅዳሩን ያስፋ። ለመጪው ምርጫ የሚደረገው ዝግጅት ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች በእኩልነት የሚያሳትፍ መሆን ይጠበቅበታል። ባለፉት አምስት ምርጫዎች ገዢው ፓርቲ ያለውን ሀብት፤ ቢርክራሲና የጸጥታ መዋቅር ተጠቀሞ ምርጫው እንዲጨናገፍና ኢፍትሐዊ ውድድር እንዲነግሥ አሉታዊ ሚና ሲጫወት ቆይቷል።
ከዚያም አልፎ ኮሮጆ በመገልበጥና የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን በማሳደድ ጭምር ለስልጣን ያለውን ስግብግብነት በገሃድ አሳይቷል። ይህ ህገወጥ ተግባር በስድስተኛው ምርጫ የደገማል ተብሎ ባይታሰብም ከወዲሁ ግን መንግሥትና ፓርቲ የተለያዩ መሆናቸውን በገሃድ የሚያሳዩ ተጨባጭ ተግባራት ሊታዩ ይገባል። ከማንኛውም አካል ለምርጫው በሰላም መጠናቀቅም ሆነ ፍትሐዊ መሆን ትልቅ ድርሻ እንዳለው ተገንዝቦ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል።
መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በበኩሉ ምርጫም ሆነ ዴሞክራሲ የሚኖረው ሀገር ስትኖር መሆኑን አውቆ ጥላቻና መጠፋፋትን የሚሰብኩ ፓርቲዎችን በማውገዝና ፊት ለፊት በማጋለጥ ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል። ለህዝብ ቆምን የሚሉ ፓርቲዎች ሁሉ መርሐቸው ሰላምና ደህንነት ሊሆን ይገባልና።
አዲስ ዘመን የካቲት 19/2013