ብስለት
ዓድዋ የሰው ልጅ ክቡር መሆኑ የታየበት እውነተኛው ለኢትዮጵያ ነፃነት የተደረገ ተጋድሎ በመሆኑ ስለዓድዋ ሲነገር ሁልጊዜ ኩራት ልቤን ሰቅዞ ይይዘዋል። ሰው መሆን ክቡር ነው፡፡
ጥቁር ሆነ ነጭ ሰው ሰው መሆኑ የታየበት፤ ሰው ከሰውነት ባህሪ ውጪ የሆነ ነገር ሊደረግበት ሲል በእምቢተኝነትና በአልበገር ባይነት መስዋዕትነት እንደሚከፍል ማሳያ ነው፡፡ የአልታፈንም አልረገጥም ባይነት ስሜት የተንጸባረቀበትና ገንኖ የወጣበት ድል ነው ዓድዋ።
የሉአላዊነታችን ተምሳሌት የማንነታችን መለኪያ ልክ፤ በዓለም መድረክ ላይ ኢትዮጵያ እንድትወደስ ከፍ ከፍ እንድትል ያደረገ፤ ቀና ብሎ የመሄዳችን ሚስጥር ስለማንነታችን መተረኪያ አንደበት የሆነ ድል ነው ዓድዋ።
ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ ተብሎ የተነገርለትን የንጉሥ አዋጅ ተከትሎ ከየአቅጣጫው ስለነፃነቱ የተመመው ምድረ ሀበሻ ታሪካችንን በደማቅ ቀለም ሊያደምቅልን ወደ ሰሜናዊቷ ዓድዋ ሲተም መመልከት ለወራት ከተደረገ ጉዞ በኋላ ሰለተቀዳጀነው ድል ሲተረክ የመስማትን ያህል ልብ የሚሞላ ነገር ከወዴት ይገኝ ይሆን።
ሰው ሞቶ ሰው ሊያድን ሰው ጠፍቶ ሰው ሊያቆም ካለቆራጥነት በቀር የረባ መሳሪያ እንኳን ሳይታጠቅ ሰው ሲሞት ሰውን ሊያከብር ከዚህ በላይ የሀገር ፍቅር ከዚህ በላይ የኢትዮጵያዊነት መለኪያ የሀገር ፍቅር መስፈርት የት ይገኝ ይሆን።
ዓድዋ የሀገር ክብር መለኪያ ለንጉሡ ፍቅር ምላሽ ጉልበት ለሌለው እንኳን ‹‹በሀዘንህ እርዳኝ በፀሎትህ አግዘኝ›› የተባለለት በደግነት በፍቅር በክብር ተጠርቶ በክብር ይሄዳል ሰው ሊኖር ሰው ሞቶ።
ሞት ክፍያ ደሞዝ ሆኖለት ዛሬ ለሚታየው ቀና ብሎ መሄድና ነፃነት፤ ዓድዋ የፍቅር ጥሪ ምላሽ የነፃነት ዋጋ ልዩ ድል ነው። የእውነት የውጭ ወራሪን ለመመከት የተቀናጀ ክንድ የመተባበር አምሳያ የእኔነት ምሳሌ ታላቅ ድል የሆነው ዓድዋ።
ለእኛ ለድሉ ባለቤቶች አይደለም የመላው ጥቁር ኩራት፤ የተሰጠን ህይወት ዛሬ በነፃነት፤ የደም ዋጋ የደም ሂሳብ የተከፈለበት፤ ላብ ፈሶለታል አጥንት ተከስክሶ ግንብ ቆሞለታል። የዛሬው እርምጃ የትናንት መሰረት ሰው ተከፍሎበታል ከደም እና ከአጥንት የደም ቋጠሮ የደም ውል ላይፈታ ላይበጠስ በአንድ አስሮ ክፈለ ዘመንን ያሻገረው የመሰባሰብ ውጤት ነው አድዋ።
ስንት ወገን ወድቆ በነፃነት ምድር ፤ ይናገር አሞራው፤ ይናገር አፈሩ፤ ለነፃነታችን ለዛሬው ክብራችን የስንት ሰው ደም የስንት ሰው ላብ እንደፈሰሰባት ፤ትናገር አድዋ ትናገር ትመስክር።
ትናገር ዓድዋ ትናገር ሀገሬ እንዴት እንደቆምኩኝ ከፊታችሁ ዛሬ፤ በኩራት፤ በክብር፤ በደስታ፤ በፍቅር፤ በድል እኖራለሁ ያው በቀን በቀን፤ በቀን በቀን ደሞ መከራውን ያን ሁሉ ሰቀቀን አይደል ያለችው ከያኒዋ ፡፡የሰው ልጅ አኩልነት መሳያ የሆነው ዓድዋ ሰው እንደቅጠል ረግፎ ጥላ የሚሆን ዛፍ ያበቀለበት ድል ነው ፡፡
ዓድዋ ዛሬ ነው፡፡ ዛሬ የተከፈለውን ዋጋ መመልከት የቃተን ቀን ነውና። ሰው የመሆን ትርጉም ጥቁር ቀይ ነጭ ብሎ ነገር የሌለበት፤ ዓድዋ ትናንትም፤ዛሬም ፤ነገም ነው፡፡። የዛሬው ትውልድ ግን ይህንን ድል የተረዳው አይመስልም፡፡
ትርጉሙ ጠፍቶ የዓድዋ አንፀባራቂ ድል ባለቤቶችን አንገት ያስደፋ ልጆቻቸው በልጆቻቸው ላይ እየፈጸሙት ያለው መፈናቅል፤ግድያ፤ስደት፤ጭፈጨፋ ዋ ዓድዋ ዛሬ እንድል አሰኝቶኛል።
የትናንት ማንነታችን ፀሀፊዎች የወዳደቁት መች ተነስተው ነው መች ቆመው ዘክረናቸው በቅቶን ነው ድሉን ልናራክስ የወደድን? የትላንቱን አንድነት የት ጥለነው ነው ዛሬ እንዲህ የተለያየነው፤እንዲህ የተራራቅነው፡፡
የዓድዋ ጀግኖች ዛሬ ምን ይሉን ይሆን?፡፡እነሱ ባቆዩልን ምድር ስንባላ፤ስንተጣጣ፤ስንገዳደል፤ ባንዳ ስንሆን፤ሀገራችንን ለውጭ ኃይል አሳልፈን ስንሰጥ፤ምን ይሉ ይሆን? እስኪያስጠላኝ መፈጠሬ የሀገርን አንገት ያስደፋ ተግባር እየፈፀምን ምስጋና ቢስ ትውልድ ለሆንን ለኛ ምን ይሰማቸው ይሆን ?ምን ይሉን ይሆን? እምዬ ሚኒልክ በማሪያም ከማሉ የማይመለሱት ምን ብለውን ይሆን? እቴጌ ጣይቱ በእናት አንደበታቸው ጦርነት እንደሚጠሉ የተናገሩት ምን ይሉን ይሆን? የዛን ጊዜ ወጣቶች እምቢ ላገሬ ብለው ለዘመቱት ዳር ድንበር ሳይገድባቸው ጎሰኝነት ልባቸውን ሳያጠለሸው አንድ ነን በሀገር ድርድር የለም ላሉት እንዲህ እንደገና ዳቦ ልንቀራመታት የተነሳንላትን ሀገራችንን ሲመለከቱ ምን ይሉን ይሆን? ምን ያህል ያፍሩብን ብዬ ሳስብ አንገቴን እደፋለሁ።
የባለድል ልጅ ነኝ እኔ የባለ ኒሻን ብዬ አልናገር ነገር አፌ ተሸብቧል። በተራ ክፍፍልና ህገ ወጥነት ክብረነክ ስራዎችን ለምንሰራው ለኛ የባለኒሻን ልጅ ነን ለማለት ምን ድፍረት ምን ማንነት ይኖረን ይሆን ? ብቻ ዛሬም አልረፈደም ዛሬም ሀገር አለች የእውነት በባህል በመከባበር የተቃኘች ሀገር አለች።
በኔ እምነት መሪ ከፈጣሪ ነው። ፈጣሪ ያስቀመጠውን መሪ በጥበብ ህዝቡን የቃኘ ከትናንቱ ዓድዋ የላቀ ድል መመዝገብ ይችላል። በየተቀመጥንበት ሰፈራ በየተሰለፍንበት የስራ ጦር ሜዳ ድል አድርገን ዓድዋን እናስቀጥል ዘንድ እየተመኘሁ ለታላላቆቹ ምስጋናን ልቸር እሻለሁ።
ምስጋና ቀና ብዬ እንድራመድ ላደረጉኝ፤ ምስጋና ለትናንት ጀግኖች አባቶች፤ ምስጋና ስለ ኢትዮጵያዊነቴ ስናገር እንዳላፍር ላደረጉኝ፤ ምስጋና ለነሱ ለዓድዋ ጀግኖች፤ ለዛሬ ነፃነት ላበቁኝ ወገኖች፤ የጥቁር ድል እንባ ዓድዋ፤ አፍሪካ፤ እምዬ ኢትዮጵያ፤ ተናገሪ ተናገሪ የድል ታሪክሽን አውሪ ጮክ ብለሽ ስለድልሽ አብስሪ የሞቱልሽን ልጆች ዘክሪ፤ እያልኩ አበቃለሁ። የሚያስመሰግን እንጂ የሚያሳፍር ታሪክ ሰሪ እንዳንሆን ፈጣሪ ይጠብቀን።
አዲስ ዘመን የካቲት 18/2013