ከገብረ ክርስቶስ
መቼም ይህቺ አዲስ አበባ በየጊዜው ለመታመን የሚከብዱ ጉዳዮችን ማስተናገድ ልማዷ ሆኗል::
የከተማዋ መስተዳድር ከሰሞኑ ከመሬት ወረራ፣ ከባለቤት አልባ ሕንጻዎች፣ ከቀበሌ ቤቶች እንዲሁም ከኮንዶሚኒየም ቤቶች ጋር በተያያዘ የተፈጸሙትን ሕገ-ወጥ ተግባራት በተጨባጭ ለማሳየት ሞክሯል::
በተለይም የዚህ ጽሁፍ ማጠንጠኛ የሆኑት የባለቤት አልባዎቹ ሕንጻዎችና የቀበሌ ቤቶቹ ጉዳይ ከመሬት ወረራው ባልተናነሰ መልኩ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል::
እንደ ከተማዋ መንግሥት ጥናት ከሆነ በመዲናዋ 322 ባለቤት አልባ ቤቶችና ሕንጻዎች ተገኝተዋል:: እነዚህ ሁሉ ቤቶችና ሕንጻዎች ታዲያ ባለቤት ነኝ ብሎ ሕጋዊ ማስረጃ ያቀረበ አካል ያልተገኘባቸው ናቸው ማለት ነው::
ከአስር ሺ የሚበልጡና በተለምዶ የቀበሌ ቤቶች የሚባሉት ደግሞ በሕገ-ወጥ መንገድ ተይዘዋል:: ከአራት ሺ የሚበልጡ የቀበሌ የንግድ ቤቶችም በሕገ-ወጦች እጅ ተገኝተዋል::
እርግጥ ነው በከተማዋ እንዲህ ያሉ ሕንጻዎች መገኘታቸው እና በርካታ የመንግሥት ቤቶችም አላግባብ በሕገ-ወጦች እጅ እንዳሉ ማረጋገጥ በራሱ መሰረታዊ ጉዳይ ነው::
ይሁንና የባለቤት አልባዎቹ ሕንጻዎች መገኘት ሕጋዊ አንድምታ እንዲሁም ዕጣ ፋንታቸው ምን መሆን አለበት የሚለው ነጥብ ደግሞ ቁልፍ መወያያ መሆን ይኖርበታል::
ምክንያቱም በተለይ የባለቤት አልባ ሕንጻዎቹ ዕጣ ፋንታ በሕግ አግባብ መወሰን ስለሚገባው ነው:: የቀበሌ ቤቶቹንም በተመለከተ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል::
በዚሁ መሰረት ከፍትሐብሔር ሕጉና ከወንጀል ሕጉ እንዲሁም ከሌሎች ጉዳዩን ከተመለከቱ የአገራችን የሕግ ማዕቀፍ አንጻር የባለቤት አልባዎቹን ቤቶችና የቀበሌ ቤቶቹን ጉዳይ እንቃኛለን::
የባለቤት አልባዎቹ ሕንጻዎች ዕጣ ፋንታ ንብረትን በተመለከተ ድንጋጌዎችን ያስቀመጠው የፍትሐብሄር ሕጉ ቁጥር 1194 በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ጠፍ የሆኑና ባለቤት የሌላቸው የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች የመንግሥት ንብረቶች እንደሚሆኑ በግልጽ ያመለክታል::
የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ተብለው በሕግ ትርጓሜ የተሰጣቸው መሬትና ሕንጻዎች ናቸው:: ከዚህ ድንጋጌ መረዳት እንደሚቻለው ታዲያ በማንም ባለቤትነት ያልተያዙ ወይም ማንም ሰው (አካል) ባለቤት ለመሆኑ ማስረጃ ሊያቀርብባቸው ያልቻሉ ንብረቶችን ሁሉ መንግሥት በእጁ እንደሚያደርግ ነው::
የዚህ ድንጋጌ የፖሊሲ መሰረቱ ደግሞ መንግሥት ለብዙሃኑ ጥቅም እንደሚቆምና ለአገር የጋራ ልማት እንደሚሰራ ስለሚታመን ባለቤት የሌላቸውን የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን በእጁ በማድረግ ለብዙሃኑ ጥቅም እንዲያውለው ያስፈልጋል የሚል ነው::
በዚሁ መነሻ ታዲያ አሁን በመዲናዋ ባለቤት አልባ ሆነው የተገኙትን ሕንጻዎች ለብዙሃኑ ጥቅም ሲል በባለቤትነት በመያዝ እንዲያስተዳድራቸው የፍትሐብሔር ሕጉ የፈቀደለት መንግሥትን ነው ማለት ነው::
መንግሥት እነዚህን ባለቤት አልባ ሕንጻዎች በባለቤትነት እንዲወስድ መብት የሚሰጠው የፍትሐብሔር ሕጉ ብቻ እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባዋል::
ወደፊት እያንዳንዱን ባለቤት አልባ ሕንጻ በተመለከተ ዝርዝር መረጃዎችና ማስረጃዎች ተጠናቅረው ሊወጡና ሊሰነዱ እንደሚገባ ግልጽ ነው:: እንዲህ በሚሆን ጊዜ ታዲያ አንዳንዶቹ ሕንጻዎች ባለቤት አልባ መሆናቸው ብቻ ላይሆን ይችላል ቁልፉ ጉዳይ፤ ይልቁንም በወንጀል የተገኙ አልያም ራሳቸው የወንጀል ፍሬ የሆኑ ንብረቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ ከወዲሁ ምክንያታዊ ግምት መውሰድ ይቻላል::
ምክንያቱም ያለፉት ሶስት አስርት ዓመታት በዚህች አገር በተለይም በአዲስ አበባ የተደራጀ ዘረፋና በመንግሥታዊ መዋቅርም ጭምር የተደገፈ ውስብስብ ወንጀል ሲፈጸም ኖሯል::
እናም ከእነዚህ ባለቤት አልባ ሕንጻዎች ጥቂት የማይባሉቱ የዚሁ የተደራጀ ዘረፋ ውጤት እንደሚሆኑ አይጠረጠርም:: በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በወንጀል የተገኙ ሊሆኑ ይችላሉ ማለት ነው::
እንዲህ ከሆነ ደግሞ “ከመርዛማ ዛፍ የሚለቀመው ፍሬ መርዛማ ነው” እንደሚባለው ባለቤት አልባዎቹ ሕንጻዎች የሚታዩበት የሕግ መነጽር የተለየ ይሆናል ማለት ነው::
በአገራችን በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረትን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ራሱን የቻለ የተሟላ የሕግ ማዕቀፍ የተሰናዳው በ2005 ዓ.ም. ነው::
በዚሁ በአዋጅ ቁጥር 780/2005 መሰረት ማንኛውም ሰው ንብረቱ የወንጀል ፍሬ መሆኑን እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው የንብረቱን ሕገ-ወጥ ምንጭ ለመደበቅ ወይም ለመሸፈን ወይም አመንጪውን ወንጀል (ለወንጀል ፍሬ ምንጭ የሆነ ድርጊት) የፈጸመውን ሰው ከሕግ ተጠያቂነት እንዲያመልጥ ለማድረግ ንብረቱን ከለወጠ ወይም ካስተላለፈ በወንጀል ይጠየቃል::
ይህ ብቻም ሳይሆን ንብረቱን፣ የንብረቱን ትክክለኛነት፣ ምንጩን፣ ቦታውን፣ ዝውውሩን ወይም የባለቤትነት መብቱን የደበቀ ወይም እንዳይታወቅ ያደረገ ሰውም በተመሳሳይ የወንጀል ተጠያቂነት አለበት::
እንዲህ ያለውን ንብረት መረከብ፣ በይዞታ ማድረግ ወይም መጠቀም በራሱ በወንጀል ያስቀጣል:: ከላይ የተዘረዘሩትን የወንጀል ድርጊቶች መፈጸም ብቻ ሳይሆን ደግሞ ለመፈጸም ማደም፣ መሞከር፣ መርዳት፣ ማመቻቸት ወይ ማማከርም የወንጀል ተጠያቂነትን ያስከትላሉ::
በእነዚህ ያሉ የወንጀል ድርጊቶች የተገኙ ንብረቶችን በተመለከተ ደግሞ ንብረቶቹን መንግሥት በእጁ የሚያስገባው በሁለት ዓይነት መንገዶች ነው::
በአንድ በኩል በወንጀል ድርጊት የተገኘን ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብ ወንጀል አልያም በአመንጪው ወንጀል ክስ ተመስርቶ የጥፋተኝነት ውሳኔ የሚሰጥ ከሆነ የወንጀሉ ፍሬ የሆነው ንብረት ወይም ተቀላቅሎት ወይም ተለውጦበት የተገኘ ንብረት እንዲወረስ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ይሰጣል::
ከዚህ ሌላ ከወንጀሉ ፍሬ የተገኘውን ገቢ እና ሌሎች ጥቅሞች እንዲሁም ለወንጀሉ መፈጸሚያነት የዋለ ሌላ ንብረትም ከተገኘ በመንግሥት ይወረሳል::
ይህ ብቻም ሳይሆን የወንጀሉ ፍሬ የሆነውን ንብረት በተለያየ ምክንያት መውረስ የማይቻል ቢሆን (በቅን ልቦና ለሌላ ተላልፎ ከሆነ) ከወንጀሉ ፍሬ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ግምት ያለው የወንጀል ፈጻሚው ንብረት እንዲወረስ ይደረጋል::
አጥፊዎችን በወንጀል ከሶ የጥፋተኝነት ውሳኔ በማሰጠት ንብረቱን ከመውረስ በተጨማሪ መንግሥት ንብረቱን የራሱ የሚያደርግበት የሕግ አማራጭም ተቀምጧል::
ይኸውም የወንጀሉ ፈጻሚ ባለመታወቁ ወይም በመሰወሩ አልያም በመሞቱ ምክንያት በፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ውሳኔ ማሰጠት ባይቻልም አመንጪው ወንጀል ወይም በወንጀል የተገኘ ንብረትን ሕጋዊ አስመስሎ የማቅረቡ ወንጀል መፈጸሙ ከተረጋገጠና የተያዘውም ንብረት የወንጀል መፈጸሚያ መሆኑን የሚያሳይ በቂ ማስረጃ ከቀረበ መንግሥት ንብረቱን እንዲወርስ ይደረጋል ማለት ነው::
በእነዚህ የአዋጁ ድንጋጌዎች መሰረት ታዲያ በአሁኑ ወቅት በከተማዋ የተገኙትን ባለቤት አልባ ሕንጻዎች መንግሥት አንድም አስፈላጊውን ማጣራትና ምርመራ በማድረግ ወንጀል ፈጻሚዎቹን ለፍርድ በማቅረብ ንብረቶቹንም ሊወርሳቸው ይገባል::
በሌላ በኩል ወንጀል ፈጻሚዎቹን ለፍርድ አቅርቦ ማስቀጣት የማይቻለው ከሆነም ወንጀሎቹ መፈጸማቸውን በማረጋገጥና ሕንጻዎቹም የወንጀል ፍሬ ስለመሆናቸው በቂ ማስረጃዎችን በማቅረብ ንብረቶቹን በእጁ ማስገባት ይጠበቅበታል::
እነዚህ ባለቤት አልባ ሕንጻዎች ሌሎች ምክንያቶች እንዳሉ ሆነው የፋይናንስ ስርዓቱ የተረጋጋ ብሎም ግልጽነት ኖሮት ጤናማና ቀልጣፋ እንዳይሆን የራሳቸውን አሉታዊ አስተዋፅኦ ስለማበርከታቸው መናገር ጉንጭ አልፋ ይሆናል::
እናም የባለቤት አልባዎቹን ሕንጻዎች ጉዳይ በእንዲህ ዓይነት ሕጋዊ አካሄድ መውረስ የሚገባ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ከወዲሁ ግን መሰራት ያለበት ቁልፍ ጉዳይ እንዳለም የከተማ አስተዳደሩ ሊገነዘበው ይገባል::
ይኸውም እነዚህ ባለቤት አልባ ሕንጻዎች አሁንም ሌላ ወንጀል እንዳይፈጸምባቸውና ሕገወጥነታቸው ተሸፋፍኖ ዳግም ሕጋዊ መስለው እንዳይቀርቡ ከወዲሁ ተጠብቀው እንዲቆዩ የማገድ ወይም የመያዝና ሌሎች አግባብነት ያላቸውን እርምጃዎች በዓቃቤ ሕግና በፍርድ ቤት እንዲወሰዱ ማድረግ ይኖርበታል::
የቀበሌ ቤቶች ጉዳይ
በተለምዶ የቀበሌ ቤቶች የሚባሉት በአዲስ አበባ የከተማ ቦታና ትርፍ ቤትን የመንግሥት ንብረት ለማድረግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 47/1967 መሰረት የተወረሱ ቤቶች ናቸው:: የከተማዋ አስተዳደር በተለያዩ መንገዶች የራሱ ያደረጋቸው ቤቶች የቀበሌ ቤቶች ይሰኛሉ::
እነዚህ የቀበሌ ቤቶች የመኖሪያ፣ የንግድ፣ ለቢሮና ለሌሎችም አገልግሎቶች የሚውሉ ሲሆኑ ብዛታቸውም 150 ሺ እንደሚልቅ የመንግሥት መረጃዎች ያሳያሉ::
እነዚህ የመንግሥት ቤቶች ለረጅም ዓመታት ትኩረት ያልተሰጣቸው ናቸው:: የዚህ ማሳያው ደግሞ መረጃቸው በአግባቡ የተጠናቀረ አለመሆኑ ነው:: ይህም የቤቶቹን ቁጥጥርና ክትትል የተወሳሰበ ከማድረጉም በላይ ሕገ-ወጥነት እንዲሰራባቸው አድርጓል::
ለዚህ ደግሞ ሩቅ መሄድ ሳያስፈልገን ከሰሞኑ የከተማዋ አስተዳደር ያወጣውን ሪፖርት ማየቱ በቂ ነው:: በሪፖርቱ መሰረት ከአስር ሺ በላይ የቀበሌ መኖሪያ ቤቶች እንዲሁም ከአራት ሺ የሚልቁ የቀበሌ የንግድ ቤቶች የሕገ-ወጥነቱ ሰለባ ሆነዋል::
እርግጥ ነው መንግሥት በቀበሌ ቤቶች ዙሪያ ያለውን ሕገወጥነት ለመፍታት በሚል በ1996 ዓ.ም እና በ2004 ዓ.ም. የመንግሥት ቤቶች አስተዳደር ደንብ አውጥቷል:: ቤቶቹን በማዕከላዊነት የሚከታተልና የሚያስተዳድር የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ የተሰኘ ተቋምም መስርቷል:: ይህ ተቋምም የመንግሥት ቤቶች አስተዳደር መመሪያ በማውጣት ተግባራዊ አድርጓል::
ይሁንና ደንብና መመሪያዎቹም ሆኑ የተቋቋመው መንግሥታዊ አካል የቀበሌ ቤቶችን ከምዝበራ ሊያድኗቸው አልቻሉም:: ስለሆነም በመሪ ድርጅቱም ሆነ በመንግሥት መዋቅሮቹ ውስጥ ያሉትን የሕግ፣ የአሰራርም ሆነ የአመራር ሳንካዎች ነቅሶ ማውጣትና እርምት መውሰድ ይጠበቅበታል::
ከሁሉም በላይ አሁን በተጀመረው አግባብ የቀበሌ ቤቶቹን ብቻ ሳይሆን የሚጠቀሙባቸውን ሰዎችንም በተመለከተ በአግባቡ የተደራጀና የተሰነደ ማስረጃ ማደራጀት የግድ ነው::
በእያንዳንዱ ቤት ዙሪያ የሚሰባሰቡት ማስረጃዎች ደግሞ በየቤቶቹ ላይ የተፈጸሙት የሕገ-ወጥነት ዓይነቶች ለየቅል መሆናቸውን አስረግጠው እንደሚያሳዩ እሙን ነው ማለት ነው::
በዚሁ መነሻነት በማስረጃዎቹ በመመርኮዝ እንደየችግሮቹና በእያንዳንዱ ቤት ላይ እንደተፈጸመው ሕገ-ወጥ ድርጊት የተመጣጠነ ሕጋዊ ርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል::
በደህና እሰንብት!
አዲስ ዘመን የካቲት 17/2013