መረጃ እንኳን በዚህ ዘመን በቀደመውም ዘመን ከፍ ያለ የአቅም ምንጭ እንደሆነ ነው። በብሄላችን “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” መባሉም ለዚህ ነው። ባለንበት ዘመን ደግሞ የመረጃ ፍሰቱ በብዙ የቴክኖሎጂ ግብአቶች እየተደገፈ ከአቅም ላይ አቅም መጎናጸፉ ስለማቻሉ በእለት ተእለት ህይወታችን እየታዘብነው የመጣነው እውነታ ነው።
ከቀደመው ዘመን ጀምሮ ከጦርነቶች በፊትና በኋላ ሰፊ የመረጃ ጦርነቶች እንደሚካሂዱ የታሪክ መዛግብት በስፋት ያትታሉ:: ይህ ደግሞ አንዱም የስነ ልቦና የበላይነት ለመቀናጀት፤ ሁለትም የተሸናፊነት መንፈስ ሊያስከትል የሚችለውን የስነልቦና ድቀት ለመቀነስ ተፋላሚ ኃይሎች የመረጃ ጦርነት ውስጥ ይገባሉ:: ለስኬታቸውም መረጃዎች ከማዛባት ጀምሮ የውሸት መረጃዎች እስከ መፈብረክ ይሄዳሉ።
በዚህ ዘመን የዚህ አይነቱ ጦርነት የተለመደ ነው። እስትራቴጂክ ጥቅሙም ከቴክኖሎጂው እድገት ጋር ተያይዞ ከፍ ያለ እንደሆነ ይታመናል። መረጃ አልፋና ኦሜጋ የሆነ በሚመስልበት በዚህ የመረጃ ዘመን ፈቅደንም፣ ከፍቃዳችን ውጪም ለመረጃ ተጋላጭነታችን ከፍ ያለ ነው። ይህን ተጋላጭነታችንን መቆመሪያ የሚያደርጉ ቡድኖችና ግለሰቦችም ያንኑ ያህል ብዙ ናቸው።
ሁሉም ነገር ሸቀጥ በሆነበት፣ ሞራላዊ እሴቶች ተሸርሽረው እራስ ወዳድነቱ ጣራ በነካበት፣ ሁሉም ነገር ሊያስገኘ ከሚችለው ግለሰባዊና ቡድናዊ ተጠቃሚነት አንጻር በሚሰላበት በዚህ ዘመን በታቀደና በተጠና መልክ የሚካሄዱ መረጃዎችን የማዛባት እና የውሸት መረጃዎችን የማሰራጨት ሁኔታ ዓለም አቀፋዊ ስጋት ከሆነ ውሎ አድሯል።
የሀሰት መረጃዎችን በመፍጠር የማሰራጨቱ ሁኔታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስምና ዝናን ባተረፉ የመገናኛ ብዙሃን ሳይቀር ማስተዋል ከተጀመረ ውሎ አድሯል። በዚህም ለብዙ አደጋና ኪሳራ የተጋለጡ ሀገራትና ህዝቦች ጥቂት አይደሉም። በተዛባ እና ለሆነ ዓላማ በተፈበረኩ መረጃዎች የፈረሱና እስካሁን ሀገር ሆነው ለመቆም ያቃታቸው ሀገራት ጥቂት አይደሉም።
ከተፈበረኩና ስውር ዓላማ ባላቸው መረጃዎች በስተጀርባ ያሉ ሴራዎችና የሴራዎች ፍጻሜ ያልታያቸው የሀገራት ህዝቦች በብዙ ትውልዶች ተጋድሎና ላብ የገነቧቸውን፣ ዘመናት ያስቆጠሩ ሀገሮቻቸውን በገዛ እጃቸው አፍርሰው ከፍ ባለ ቁዘማ ውስጥ ለመኖር ተገደዋል። በተሳሳቱ መረጃዎች የገቡበት የታሪክ ምእራፍ ከጸጸትና አንገት መድፋት ውጪ ያተረፈላቸው የለም።
በኛም ሀገር በብዙ ዘመናት የተጋድሎና የመስዋእት ታሪክ ህያው ሆና የቆየችውን ሀገር በአንድም ይሁን በሌላ በግልጽ በአደባባይ ሆነ በስውር ውስብስብ ሴራ ማፍረስ የሚያስችል የተሳሳቱ መረጃዎች ባለፉት 27 ዓመታት በተደራጀና በታሰበ መልኩ ወደ ማህበረሰቡ ሲረጩ ቆይተዋል። በዚህም ሀገርና ህዝብ የከፈለው ዋጋ ገና ያበቃ አይደለም። ፈጥነን ካልነቃና ወደፊትም ከዚህ ዘር ልናጭድ የምንችለው መከራ ከፍ ያለ ሊሆን እንደሚችል ለማሰብ አይከብድም።
በውሸት ላይ የተመሰረቱ ሀገር አንድነትና ከዚህ በሚመነጨው የሀገር ሉአላዊነትን አደጋ ውስጥ የሚከቱ ትርክቶች ተፈብርከው ህዝባችን ሊሸከመው በማይችለው መልኩ ተዘርተዋል። የህዝባችን ማህበራዊ ስነልቦና የተዋቀረበት ውቅር ጠንካራ በመሆኑ የታሰበው ያህል ዋጋ ባንከፍልም ዋጋ ከመክፈል ግን አልዳንም::
የዚህ የውሸት ትርክት አርትቴክት የሆነው የጁንታው ቡድን በታመነበት የሴራ መንገድ ወደ መቃብሩ ያቀና ቢሆንም ለቡድኑ ትንሳኤ ለመፍጠር አሁንም በዛው አሮጌ ትርክት የተጠመዱ ተስፈኞችና ባለውለታዎች ዘመቻ በሚመስል መልኩ የተሳሳቱ መረጃዎችን በመፈብረክና በተለያዩ ሚዲያዎች በመልቀቅ ሰፊ ዘመቻ ከፍተዋል። በሚዋሹት ዋሸት መጠን ስኬታማ የሆኑ እስኪመስላቸውም ሆነዋል።
በአንድ በኩል ጁንታው በሀገርና በህዝብ ላይ የፈጸመውን ታላቅ ታሪካዊ ክህደት፣ በዚህ የክህደት መንገዱ የፈጸማቸውን ኢትዮጵያዊ ሊፈጽማቸው ቀርቶ ሊያስባቸው የሚቀፈውን እና የሚከብደውን ኢሰብአዊ ተግባራት ከባለቤቱ ወስደው ለሌላ ባለቤት ለመስጠት ከፍ ባለ የውሸት እና መረጃ የማዛባት ዘመቻ ውስጥ ተጠምደዋል። በአደባባይ በብዙ እብሪትና ትምክህት የፈጸሙትን አስነዋሪ ተግባር መጋረጃ ሊያሰፉለት እየሞከሩ ነው።
በሌላ በኩል ደግሞ ለቀባሪ ለአልቃሽ የማይመቸውን የጁንታውን የአደባባይ ሞት ላለመቀበል እየሄዱበት ያለው ሞቱን ያለመቀበልና በተሳሳቱ መረጃዎች ህይወት ለመስጠት የሚያደርጉት ጥረቶች ጤነኛ አእምሮ ያለውን ሰው ምን ነካቸው? እውነትን መቀበል ይህን ያህል ስቃይ አለው? እያስባለ ካለ ውሎ አድሯል። ለቀባሪ አረዱት እንደሚባለው ደግሞ ውጪ ያለው የጁንታው ተላላኪዎችና ተስፈኞች እውነታው መራራና የማይዋጥ ሆኖባቸዋል።
በእርግጥ በነዚህ ኃይሎች የውሸት መረጃዎች መሰረት አድርገው በየእለቱ የሚፈበረኩ ትርክቶች ቀኑን መሻገር አቅም ባይኖራቸውም፣ አንድ እርምጃ ወደፊት የማራመድ ተፈጥሯዊ አቅም ባይቸሩም ከህግ ማስከበር ዘመቻው ስኬት ማግስት በተጀመረው ትግራይን መልሶ የመገንባት ሄደት ላይ አሉታዊ አስተዋፅኦ የላቸውም ማለት አይደለም።
በዚህ ዘመቻ ውስጥ ከፍ ያለ ስምና ዝና ያላቸው ዓለም አቀፍ የመገናኛና ብዙሃንና ስመጥሩ የሚባሉ ግለሰቦች ተሳታፊ መሆናቸው፣ በተለይም ትግራይን መልሶ በመገንባት ሂደት ውስጥ ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ሊኖረው የሚችለውን አስተዋጽኦ ሊያሳንሰው እንደሚችል መገመት አይከብድም።
ሁሉንም ነገር በልኩ አስቦ መንቀሳቀስ ተገቢ ከመሆን አንጻር፣ ይህን ዓለም አቀፍ ገጽታ የተላበሰ የሚመስለውን ዘመቻ አሸንፎ በስኬት ለመወጣትም ትልቅ አቅም የሚሆነው ትክክለኛ መረጃዎችን ዘላቂነት ባለውና በተደራጀ መልኩ በተለያዩ አማራጮች ለሀገር ውስጥ ሆነ ለዓለም አቀፍ ህብረተሰብ ፈጥኖ ማድረስ ሲቻል ነው።
ይህን ስርአት የመፍጠሩ እውነታ የአገር ውስት ሆነ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ የውሸት ትርክቶች ከሚፈጥሩት ግራ መጋባት መታደግ የሚያስችል ነው። የሀገሪቱን ገጽታ ለማጠልሸት የተከፈተውን ዘመቻ ለመቀልበስ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ያቀረቡትን ጥሪ ተቀብለው እየተንቀሳቀሱ ላሉ የዲያስፖራው ማህበረሰብ አባላትም ትልቅ አቅም ከመሆንም አልፎ በተሻለ እና አስተማማኝ በሆነ መልኩ ዘመቻውን በስኬት ለማጠናቀቅ ይረዳቸዋል።
እዚህ ላይ በቂ ትኩረት የሚፈልገው ሀገር የማጠልሸት ዘመቻው ታቅዶና ታሳቦ የሚደረግ ግብ ያለው መሆኑ ነው። ይህንን ዘመቻ ማሸነፍ የሚቻለው “አቤት ውሸት!” በሚል በውሸቱ በመገረም ሳይሆን፤ የተደጋገመ ውሸት እውነት መስሎ ሊገኝ የሚችልበት እድል እንዳለ በማስተዋል ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 17/2013