የሲዳማ ክልል የምሥረታ ሥነ-ሥርዓት በትናንትናው ዕለት የክልል ፕሬዚዳንቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎችና የክብር እንግዶች በተገኙበት በሃዋሳ ተከብሯል። ሲዳማ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ብሄሮች አንዱ ሲሆን በህገ መንግሥቱ ከተቀመጠው የብሄር ብሄረሰቦች መብት አንፃር በእጅጉ የተጠቀመ ብሔር ነው::
በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 47 መሰረት ባለፈው ዓመት በተደረገው ሕዝበ ውሳኔ አዲስ የተመሠረተው የሲዳማ ክልል ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በቀጥታ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ስር ከሚገኙት ዘጠኝ ክልሎች በተጨማሪ አስረኛው አባል ሆኗል።
የሲዳማ ሕዝብ ከሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በቋንቋ እና በባህል የሚጋራ፣ በሰላምና በአብሮነት የኖረ ሲሆን፣ ወደ ፊትም አብሮ ለመቀጠል ያለውን ኃላፊነት ከፍ ማድረግ ይኖርበታል።
የሲዳማ ህዝብ በህገ መንግሥቱ የተሰጠውን ክልል የመሆን መብት ከጠየቀ ረጅም ዓመታትን ቢያስቆጥርም በነበረው አፋኝ የፖለቲካ ስርዓት ጥያቄው ሳይመለስለት መቆየቱ እርግጥ ነው።
በመሆኑም አሁን በተፈጠረለት ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ተጠቅሞ ከሌሎች እህትና ወንድም ህዝቦች ጋር ለሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ለልማት ፊቱን በማዞር ለኢትዮጵያ ዕድገትና ብልጽግና ከሁሉም ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጋር በጋራ መስራት ይኖርበታል።
ምክንያቱም ሰላምና ልማት የማይነጣጠል ትስስር አላቸው። ሰላም ከሌለ ልማት የለም። ግጭት፣ ሁከትና ግርግር ባለበት ሃብቱን ሥራ ላይ የሚያውል ባለሃብት አይኖርም። ስጋት ሲኖር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ይቋረጣል።
ሰላምና ልማት፣ ነብስና ስጋ እንደሆኑም የሚታሰበው ለዚሁ ነው። ስጋት ባለበት ፋብሪካዎችም ሥራቸውን ለማቋረጥ ይገደዳሉ። ግጭቶች እየተባባሱ ሲሄዱ ደግሞ የልማት ሥራዎች ይደነቃቀፉና ድህነት፣ ረሃብና ስደት መከሰቱ አይቀርም።
ስለዚህ ወጣቱ ትውልድ የአገሪቱን ልማት ወደፊት ማራመድ፣ ሕጋዊ ጥያቄዎቹ እንዲፈቱለት ማድረግ የሚችለው ከመንግሥት ለውጥ እንዲመጣለት በመጠበቅ ብቻ ሳይሆን ከመንግሥት ጎን ቆሞ በጋራ ሲሰራ መሆኑን ከሲዳማ ክልል ተሞክሮ መማር ይቻላል።
ክልሉ የልማትና የሰላም ጥያቄዎቹን ሲያቀርብ ቆይቶ አግኝቷል። አሁን ወጣቱ ሊገነዘብ የሚገባው ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን፣ የተጀመረው ልማት እንዲቀጥል፣ የዴሞክራሲ ስርዓቱ የበለጠ እንዲጠናከር፤ እንዲሁም ከፍትሃዊነትና ከልማት ፍላጎት ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ ችግሮች እንዲፈቱለት፣ በሰላም መንገድ ለልማት መትጋት ይኖርበታል።
እንዲህ ካልሆነ በሕዝቡ ተገቢ ጥያቄዎች ተከልሎ፣ በህዝብ ስም እየማለ የተጀመረውን የኢትዮጵያ የዕድገት ጉዞን ለማደናቀፍ የሚወራጨው ጠላት በር የሚከፈትለት ይሆናል። ከዚህም በላቀ ወጣቱ ንቁ ሆኖ ሰላሙን በመጠበቅ ለአገርና ለህዝብ ዘብ መሆን ይኖርበታል። እጅና ጓንት የሆኑትን ሰላምና ልማትንም አጥብቆ ሊይዛቸውም ይገባል።
በግጭት ውስጥ የመንግሥትና የህዝብ ንብረት ይወድማል፣ በሰላም ግን ልማት፣ እኩልነት፣ ወንድማማችነት፣ ነፃነት፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ ይፈጠራሉ። ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ ዳግም በጥፋተኞች እጅ መውደቅ አይኖርባትም፤ ይልቁን ህዝቦቿ አንድነቷን የምታጠናክርበት፣ ከድህነት የምትወጣበትን መንገድ በጋራ መደልደል አለባቸው።
ለዚህም የሲዳማ ህዝብ የራሱን ጥቅም ከማስከበር ባለፈ ከእህት ወንድሞቹ ጋር አብሮ በመኖር እና በጋራ በመስራት ሰላሟ የተጠበቀ፣ ብልፅግናዋ የተረጋገጠ አገር የመገንባት ኃላፊነት አለበት።
ለዚህ ግብ ደግሞ በመላው አገሪቱ ከሚገኙ ብሄሮችና ህዝቦች ጋር ይበልጥ ተቀራርቦ በመስራት ከድህነት የተላቀቀች አገር ለቀጣይ ትውልድ የማስተላለፍ የቀደመ ልምዳቸውን አጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል።
የሲዳማ ህዝብ ጥያቄ መልስ ማግኘቱ በአገሪቱ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮች በቀጣይ ደረጃ በደረጃ እየተፈቱ እንደሚሄዱ የሚያመላክት በመሆኑ ስኬቱን የመላው ኢትዮጵያ ህዝቦች የጋራ ጥረት ውጤት አድርጎ መውሰድ ይቻላል።
በቀጣይ የኢትዮጵያ ህዝቦች አንድ ላይ ተገናኝተው በጋራ ችግሮቻቸው ላይ አብረው መክረውና መፍትሄ ባሏቸው ሀሳቦች ላይ ተስማምተው በጋራ በመስራት ዴሞክራሲያዊት አገር በመገንባት ሂደት ውስጥ በጋራ መንገዱን መጥረግ ይኖርባቸዋል!
አዲስ ዘመን የካቲት 16/2013