አንተነህ ቸሬ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመሬት ወረራ እንዲሁም በህገ ወጥ የቤት ይዞታና ባለቤትነት ላይ ሰሞኑን ይፋ ያደረገው የጥናት ሪፖርት ብዙዎችን እንዳስገረመ ታዝበናል።ከተማ አስተዳደሩ ከኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያካሄደው ጥናት ግኝቶች እጅግ የሚያስገርሙ፣ የሚያስቆጩና የሚያሳፍሩም ናቸው፡፡
የጥናቱ ግኝቶች ምን ይላሉ? ትርጉማቸውስ?
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አበቤ ጥር 18 ቀን 2013 ዓ.ም ይፋ ባደረጉት ‹‹የጥናት ውጤት›› በግኝቱም አንድ ሺ 338 ሄክታር መሬት በህገ ወጥ መንገድ መወረሩን፤ 322 ግንባታቸው ያለቀና ያላለቀ ህንፃዎች ባለቤት አልባ ሆነው መገኘታቸውን፤ 21 ሺ 695 የጋራ መኖሪያ ቤቶች በተለያየ ህገ-ወጥ ሁኔታ ላይ ያሉ መሆናቸውን እንዲሁም 14 ሺ 641 የመኖሪያና ለንግድ የተከራዩ የቀበሌ ቤቶች ያለ አግባብና በህገ-ወጥ ይዞታነት እንደሚገኙ ገልፀዋል።
እንደ ‹‹ጥናቱ ግኝት››፣ በህገ-ወጥ ወረራ የተያዘው መሬት (አንድ ሺ 338 ሄክታር) በገንዘብ ሲተመን በ14 ቢሊዮን ብር የሚገመት መሆኑንና መሬቱ በሪል ስቴት አልሚዎች፣ በግለሰቦች እንዲሁም በሀይማኖት ተቋማት በቡድን በመደራጀትና መንደር በመመስረት ጭምር ወረራ ተፈፅሞበታል።
ቀደም ካሉት ጊዜያት ጀምሮ ብዙዎችን ሲያነጋግርና ሲያወዛግብ የቆየው የጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም) ጉዳይ በጥናቱ ግኝት ውስጥ በዝርዝር ተብራርቷል።በዚህም መሰረት፤ በህገ ወጥ መንገድ የተያዙ የጋራ መኖርያ ቤቶች ጠቅላላ ብዛት 21 ሺ 695 ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል 16 ሺ 315 የጋራ መኖሪያ ቤቶች በህገ ወጥ መንገድ የተያዙ፤ 4530 ባዶ የሆኑ (ያልተላለፉ)፤ 850 ዝግ የሆኑ (በአንድ ወቅት ሰዎች የነበሩባቸው ሲሆን ረጅም ግዜ የተዘጉ) እና 424 ቤቶች ደግሞ በህገወጥ መልኩ በግለሰቦች ተይዘው ይገኛሉ።
‹‹ቤት እናገኛለን፤ ይደርሰናል›› በሚል ተስፋ ገንዘባቸውን እየቆጠቡ ለበርካታ ዓመታት ሲጠብቁ የኖሩ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ይህን የጥናት ግኝት ሲሰሙ ምን ዓይነት ስሜት ይሰማቸው ይሆን? ‹‹ቤት ይደርሰናል›› ብለው በተስፋ የጠበቁባቸውን ዓመታት ‹‹የባከኑ የእድሜያቸው ክፍሎች›› እንደሆኑ አድርገው ቢቆጥሯቸው ያስገርማል!
132 ሺ 678 ቤቶች ደግሞ በቤቶች ኮርፖሬሽን ተመዝግቦ የሚገኘው ባለዕጣዎች የስም ዝርዝር እና በመስክ በተገኘው የተጠቃሚዎች የስም ዝርዝር መካከል ልዩነት ያላቸው ናቸው።በተጨማሪም 18 ሺ 423 ቤቶች የቤት ባለቤት ስም የሌላቸው ሲሆኑ በእነዚህ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ ግለሰቦች መረጃቸውን እንዲያቀርቡ በተደጋጋሚ ቢጠየቁም መረጃ ማቅረብ ያልቻሉ ወይም ያልፈለጉ በመሆናቸው ቤቶቹ በህገወጥ መንገድ የተያዙ ስለመሆናቸው ተገልጿል።
በሌላ በኩል 28 ብሎኮች ማለትም ከ782 እስከ 842 የሚሆኑ ቤቶች እና 83 የጋራ መጠቀሚያ ህንፃዎች ሳይገነቡ የተገነቡ መስለው የተመዘገቡ ነገር ግን የተባሉት ግንባታዎች በአጥኚዎቹ ቆጠራ (ምልከታ) ወቅት ሊገኙ አልቻሉም።ለእነዚህ ሳይገነቡ ተገንብተዋል ተብለው ለተመዘገቡ ሕንፃዎች የቦርድም ሆነ የስራ አመራር የውሳኔ ቃለ ጉባኤ ካለመገኘቱ ባሻገር ለግንባታዎቹ ክፍያ አልተከፈለም ብሎ መደምደም እንደሚያስቸግር በጥናቱ ላይ መገለፁ ነገሩን እጅግ አስገራሚ ያደርገዋል።በእርግጥ ጥናቱ ‹‹ምንም እንኳን መረጃ ባይገኝም ለግንባታዎቹ ክፍያ አልተከፈለም ብሎ መደምደም ያስቸግራል›› ብሎ ይገልፀዋል።ይህ ማለት ላልተገነቡ ሕንፃዎች በብዙ ሚሊዮኖች ብር የሚቆጠር የሕዝብ/የመንግሥት ሀብት ባክኗል ማለት ነው።
በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ ባሉ ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች ከሚገኙና በጥናት እንዲለዩ ከተደረጉ 138 ሺ 652 የቀበሌ መኖሪያና ንግድ ቤቶች መካከል 10 ሺ 565 በህገወጥ መንገድ የተያዙ የቀበሌ መኖሪያ ቤቶች ተገኝተዋል።እነዚህ ቤቶች ውል በሌላቸው ህገወጥ ነዋሪዎች፣ በሶስተኛ ወገን እና የኮንዶሚኒየም ቤት በደረሳቸው ሰዎች የተያዙ እንዲሁም ታሽገው የተቀመጡ፣ የጠፉ ቤቶች፣ አድራሻቸው የማይታወቁና በምን ምክንያት እንደፈረሱ ያልታወቁ ተብለው ተመድበዋል።በህገወጥ መንገድ ወደ ግል ቤትነት የዞሩ የቀበሌ ቤቶችም ተገኝተዋል።
‹‹ባለቤት አልባ›› ቤቶች
ከጥናቱ ግኝቶች መካከል የሚያስገርመው ‹‹ባለቤት የላቸውም›› ተብለው የቀረቡት ቤቶች/ሕንፃዎች ጉዳይ ነው።ጥናቱ እንደሚያመለክተው 322 ቤቶች ባለቤታቸውን ሊያሳይ የሚችል መረጃ ባለመገኘቱ ‹‹ባለቤት አልባ›› ተብለው ተለይተዋል።ከነዚህ ውስጥ 58 ቤቶች ግንባታቸው የተጠናቀቀ፤ 264 የሚሆኑት ደግሞ በተለያየ የግንባታ ደረጃ ላይ ያሉ ነገር ግን ግንባታቸው ለረጅም ጊዜ ቆሞ የሚገኝ ናቸው።
ሕንፃዎቹ ያረፉበት መሬት ስፋት ደግሞ 229 ሺ 556 ካሬ ሜትር ነው።ሕንፃዎቹ የያዙት (ያረፉበት) መሬት ለሌላ አገልግሎት እንዳይውል ማድረጋቸውም ሌላ ተደራቢ ኪሳራ እንዳስከተለ መገመት አያዳግትም።ለእነዚህ ሕንፃዎች ግንባታ ወጪ የተደረገው ገንዘብም ኪሳራውን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል።በእርግጥ የባከነው ገንዘብ የፈረደበት የሕዝብ/የመንግሥት ገንዘብ መሆኑ አይቀርም።
ለመሆኑ ከተማዋ መንግሥት ነበራት?
በጥናቱ ይፋ የተደረጉትን መረጃዎች የሰማና የተመለከተ ሰው ‹‹ይህ ሁሉ ሌብነት ሲፈፀም ከተማዋ መንግሥት አልነበራትም? አስተዳደሯ የት ሄዶ ነበር? …›› ብሎ መጠየቁ አይቀርም።በእርግጥ እንዲህ ዓይነት አስገራሚና አሳፋሪ ነገሮችን እየሰሙ ይህን ጥያቄ ማንሳት የሚያስገርም ሊሆን አይችልም።የሚያስገርመው ነገር ይህ ሁሉ መሬትና ቤት በሕገ ወጥ መንገድ ሲያዝ ‹‹ከተማዋን አስተዳራለሁ›› ብሎ ስልጣን ላይ የተቀመጠው አካል ‹‹አላወቀም፤ አልሰማም›› ብሎ መከራከር ነው።በዚህ ልክ በተፈፀመ ወንጀል ውስጥ የመንግሥት መዋቅር የለበትም ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው።
የአስተዳደሩ መዋቅር ‹‹ከወንጀሉ ንፁህ ነው›› ማለት ከተማዋ የሚመራትና የሚቆጣጠራት አስተዳደር አልነበራትም ከማለት ተለይቶ ሊታይ አይችልም።እንኳን የወንጀሉ ዋነኛ ፈፃሚዎች፣ ድርጊቶቹ ሲፈፀሙ ዝም ብለው የተመለከቱ ግለሰቦችና ተቋማትም የዚህ ወንጀል ተባባሪ ናቸው።
ግልጽ ያልሆነው ‹‹ውሳኔ›› እና ‹‹እርምጃ››
የጥናት ሪፖርቱ ይፋ ከተደረገ ከቀናት በኋላ የከተማው ካቢኔ ስብሰባ አካሂዶ ‹‹ … በጥናቱ የተገኙ 322 ባለቤት አልባ ህንጻዎች የከተማ አስተዳደሩ እንዲወርስና በግልፅ ጨረታ ተሽጠው ገቢው ለህዝብ ልማት እንዲውል፤ በህገ-ወጥ መንገድ የተያዙ፣ ባዶና ዝግ ሆነው የተቀመጡ 21 ሺ 695 የኮንዶሚኒየም ቤቶችን ለ1997 ተመዝጋቢ ለሆኑና በቋሚነት እየቆጠቡ ላሉ ነዋሪዎች በእጣ እንዲተላለፉ፤ በህገ-ወጦች የተያዙ የቀበሌ መኖሪያ ቤቶች ግልፅ የሆነ መስፈርት ወጥቶላቸው ለድሆች፣ ለአቅመ ደካሞችና ለተለያየ ችግር ለተጋለጡ የከተማው ነዋሪዎች እንዲሰጡ፤ በህገ-ወጥነት የተያዙ የቀበሌ የንግድ ቤቶችን አስለቅቆ ለስራ አጥ ወጣቶች በእጣ እንዲሰጡ›› የሚሉ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።ይህ እስከሚከናወን ድረስም ቤቶቹ ታግደው ባሉበት እንዲቆዩ ለፌዴራል የሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ኤጀንሲ ውሳኔውን ማሳወቅ እንዳለባቸውና የከተማው ዓቃቤ ሕግ ጉዳዩን እየተከታተለ ሪፖርት እንዲያደርግ ስለመወሰኑ ተነግሯል።
የካቢኔው ውሳኔ በበጎ ጎኑ የሚታይ ቢሆንም ከጉዳዩ ውስብስብነት አንፃር ዝርዝር አፈፃፀሙ ግን ግልፅነትንና ተጠያቂነትን ያሰፈነ መሆን እንዳለበት ታዝበናል።ምክንያቱም በዚህ ወንጀል ውስጥ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፎ እንደሚኖርበት የሚያጠራጥር ባለመሆኑ ችግሩን ለማስተካከል የሚከናወኑ ተግባራት ለችግሩ ኃላፊነት መውሰድ ያለባቸውን አካላትን በግልፅ የሚያሳዩና ተጠያቂነትን ያሰፈኑ መሆን ስለሚገባቸው ነው።
ተጠያቂነትን ያሰፈነ ስርዓት በሌለበት ሁኔታ በከተማ አስተዳደሩ የሚወረሱት፣ ‹‹በግልጽ ጨረታ›› የሚሸጡትና ከሽያጫቸው የሚገኘው ገቢ ለሕዝብ ጥቅም እንዲውል የተወሰነባቸው የ‹‹ባለቤት አልባ›› ሕንፃዎች፤ ለድሆች፣ ለአቅመ ደካሞችና ለተለያየ ችግር ለተጋለጡ የከተማው ነዋሪዎች የሚሰጡት የቀበሌ መኖሪያ ቤቶች፤ ለስራ አጥ ወጣቶች በእጣ የሚሰጡት በህገ-ወጥነት የተያዙ የቀበሌ የንግድ ቤቶች እንዲሁም ለ1997 ተመዝጋቢ ለሆኑና በቋሚነት እየቆጠቡ ላሉ ነዋሪዎች በእጣ የሚተላለፉት በህገ-ወጥ መንገድ የተያዙ፣ ባዶና ዝግ ሆነው የተቀመጡ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ጉዳይ አሁንም አሳሳቢ ነው።
‹‹ለጨረታ የሚሆን፣ ድሆችን፣ ስራ አጦችንና ለችግር የተጋለጡ ግለሰቦችን ለመለየት የሚያስችል ‹ግልጽ መስፈርት› ሲባል ምን ማለት ነው? ይህን ወንጀል የፈፀሙ አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ ቁርጠኝነት ከሌለና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ካልተጀመረ የካቢኔው ውሳኔዎች ተፈፃሚነትና ውጤታማነት ምን ያህል አስተማማኝ ይሆናል? …›› የሚሉት ጥያቄዎችና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጠንካራ ምላሽ ይፈልጋሉ።‹‹ህገወጥ ተግባሩ እንዳይደገም የአሰራር ስርዓት ዘርግተን እንሰራለን›› የሚለው የምክትል ከንቲባዋ ቃል በተግባር የተደገፈና ግልፅ የሆነ እርምጃ ይፈልጋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር ዓባይ በበኩላቸው፤ በከተማዋ የመሬት ወረራ ሲፈፀም ኃላፊነታቸውን ባልተወጡ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ላይ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዷል፤ በቀጣይም እርምጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። የጥናቱን ግኝቶች ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እና ለፌደራል ፖሊስ ምርመራ እንዲጀመር የከተማ አስተዳደሩ አቅጣጫ መስጠቱን አቶ ጃንጥራር ጠቁመዋል። እነማን ላይ ምን ዓይነት እርምጃ እንደተወሰደባቸው ግን በግልፅ የተባለ ነገር የለም።
‹‹አሁን ከተማ አስተዳደሩ ያስጠናው ጥናት ሕዝብ የሰጣቸውን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው በህገ ወጥ ተግባር ለሚሳተፉ አመራሮች ትምህርት የሚሆን ነው።አስተዳደሩ አጥፊዎች በህግ እንዲጠየቁ ለማድረግ ቁርጠኛ አቋም ይዟል›› ብለዋል። ይህ የአስተባባሪው ቃልም ግልፅነት ይፈልጋል፤ ተግባራዊ እርምጃንም ይሻል!
ተጠያቂነት አለማስፈንና መዘዙ
እንግዲህ የዚህ ሁሉ ነውር ምክንያት ሐቀኛነት፣ ግልፅነት፣ ተጠያቂነት የሰፈነበት ጠንካራ የአሰራር ስርዓት ባለቤት አለመሆናችን ነው።ወንጀል እንደሰሩ ማስረጃ የተገኘባቸው ግለሰቦች ጭምር ለተሻለ ስልጣን/ሹመት በሚታጩበት ኅብረተሰብና አሰራር ውስጥ እንዲህ ዓይነት አሳፋሪ ድርጊቶች መፈፀማቸው ሊያስገርም ይችላል!
ችግሩ እንዳይደገም መፍትሄው ተጠያቂነትን ማስፈን ነው።ወንጀል መስራት የተሻለ ሹመት ለማግኘት እንደመስፈርት የተቆጠረ ይመስላል።የሕዝብን/የመንግሥትን ሐብት የዘረፉ ሰዎች ሹመት ሲያገኙ የተመለከቱ ሌሎች ግለሰቦች የተሿሚዎቹን ሌቦች ወንጀል እጥፍ አድርገው መስራታቸው አይቀርም።በዚህ ሁሉ መሐል ተጠያቂነት ካልሰፈነ ወንጀሉም ሆነ በሕዝብ/መንግሥት ንብረት ላይ የሚደርሰው ውድመት ተባብሶ ይቀጥላል።ይህ ደግሞ የአገራዊ ድህነት ምንጭ ይሆናል።
ይህ ዓይነቱ ችግር የንብረት ውድመትና ብክነትን በማስከተል ብቻ የሚያቆም እንዳልሆነ መገንዘብ ለችግሩ ሊሰጥ የሚገባውን ትኩረት ከፍ ለማድረግ ያግዛል።ተጠያቂነትን አለማስፈን አገርን ለመበተን ፈቃድ እንደመስጠት ይቆጠራልና ከዚህ ችግር የመውጫ አስተማማኙ መፍትሄ ወንጀለኛን ለወንጀሉ ተጠያቂ ማድረግ ነው!
አዲስ ዘመን የካቲት 01/2013