አንተነህ ቸሬ
ሰሞኑን ስለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የጤንነትና የደህንነት ሁኔታ የተሰራጨው ሐሰተኛ መረጃ ብዙዎችን ስጋት ላይ የጣለና በርካታ ‹‹ትንታኔዎችን›› እና ‹‹ግምቶችን›› የጋበዘ ሆኖ ታዝበናል። ከዚህ ቀደምም የሐሰት መረጃዎችን ሲያሰራጩ በነበሩና ጥፋታቸውን እንዳይደግሙ ተግሳፅ ባልተሰጣቸውና ሕጋዊ እርምጃ ባልተወሰደባቸው ‹‹የሹም ዶሮዎች›› አማካኝነት የተሰራጨው መረጃ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ደጋፊዎች ብቻም ሳይሆን ‹‹ደጋፊያቸው አይደለንም›› የሚሉ ወገኖችንም ጭምር ያስጨነቀና ያነጋገረ ጉዳይ ነበር።
በእርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካላቸው የኃላፊነት ደረጃ አንፃር ስለእርሳቸው የተወራው ጎልቶ ወጣ እንጂ ስለመረጃና ደህንነት አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተርም አደገኛ የሐሰት መረጃ ሲሰራጭ ነበር። ስለሁለቱም ሹማምንት የተወራው መረጃ በሀገር ቤትም በውጭም ያሉ በርካታ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንንና የኢትዮጵያን ወዳጆች አስጨንቋል።
‹‹መንግሥት አጃቢዎቼን ሊያነሳብኝ ነው … በሌሊት ተከበብኩ›› … የብሔር ስም እየጠሩ ‹‹ … ሀጫሉን የገደለው ያ ብሔር ነው፤እርምጃ ውሰዱበት …›› በሚሉ ኃላፊነት የጎደላቸው ቀስቃሽ መረጃዎች ምክንያት በአንድ ጀንበር በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገደሉ፤ ሺዎች ደግሞ ሲዘረፉና ሲፈናቀሉ የተመለከተ ሁሉ ስለጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ስለመረጃና ደህንነት መስሪያ ቤቱ አለቃ ጤንነት/ደህንት የሚሰራጭ አሉታዊ መረጃ ቢያስጨንቀው አያስገርምም።
‹‹የመረጃው ጌቶች›› እነማን ናቸው? ምክንያታቸውስ?
እነዚህ አደገኛ የሐሰት መረጃዎችን የሚያሰራጩ ግለሰቦች ሲያሻቸው የዩኒቨርሲቲ መምህር፣ ሲፈልጉ ዳያስፖራ፣ ሌላ ጊዜ አክቲቪስት ነን የሚሉና በመንግሥት የአስተዳደር መዋቅር ውስጥ ተቀምጠው ያሉ ‹‹የሹም ዶሮዎች›› ናቸው። በእነዚህ ግለሰቦችና ቡድኖች ግንዛቤ መሰረት መረጃን ከእነርሱ በስተቀር የሚያውቅ ሌላ ግለሰብ የለም፤ የምስጢራዊ መረጃዎች ባለቤቶች፣ የመረጃዎቹ ተንታኞችና የመረጃዎቹን ውጤት ወሳኞች እነርሱ ናቸው። ከደህንነት ሰዎች ጋር ግንኙነት እንዳላቸውም ያስወራሉ።
‹‹እነዚህ ‹የሹም ዶሮዎች› እንዲህ ዓይነት መረጃዎችን የሚያሰራጩበት ዓላማና ምክንያት ምንድን ነው›› ብሎ መጠየቅ የጉዳዩን ውል ለመያዝ የሚደረገውን ጉዞ አመቺ ያደርገዋል። መቼም እንዲህ ዓይነት አደገኛ መረጃዎችን የሚያሰራጩ ሰዎች የድርጊታቸው መነሻ/ዓላማ ቀላል ነው ብሎ አለመገመትና ማሰብ ሞኝ አያስብልም።
ከምክንያቶቻቸው መካከል፣ በእነርሱ ጥላ ተከልለው የራሳቸውን ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈፀም የሚፈልጉ አካላትን (ምናልባትም በመንግሥት የአስተዳደር መዋቅር ውስጥ ያሉ) እያስፈፀሙ ነው የሚለው ግምት አንዱ ሊሆን ይችላል። ለዚህ ተግባራቸው የሚበረከቱላቸው ቁሳዊና ሌሎች ጥቅሞችና ማታለያዎች ደግሞ በዚሁ የይሆናል መላምት ስር የሚጠቃለሉ ገፊ ምክንያቶች ተደርገው ሊጠቀሱ ይችላሉ።
ግለሰቦቹ ራሳቸው የሚያራምዱትን አቋም ማስፈፀም ደግሞ ሌላው ምክንያት ነው ተብሎ ይገመታል። ይህኛው ምክንያት አደገኛ የሐሰት መረጃዎችን የሚያሰራጩት ግለሰቦች የሌሎች ተልዕኮ አስፈፃሚዎች ከመሆን ተሻግረው የራሳቸውን ዓላማና አቋም የሚያሳዩበትና የሚተገብሩበት መንገድ ነው። ከላይ ከተጠቀሱት ሁለት ግምቶች በተጨማሪ ሌሎች ምክንያቶችም ሊኖሩ ይችላሉ።
በእርግጥ ምክንያቶቻቸው ሁሉንም ሰው ላያስማሙ ይችላሉ። አንድ የማይካድ ሃቅ ግን አለ። ይኸውም ከሌሎች በተቀበሉትም ይሁን በራሳቸው ፍላጎት፣ እነዚህ አካላት አደገኛ የሐሰት መረጃዎችን ሲያሰራጩ የሕዝብን ደህንነት አደጋ ላይ መጣላቸው ነው። ከቤት በሰላም ወጥቶ ተመልሶ መግባትን እንደቅንጦት የሚያይ ሕዝብ ስለጠቅላይ ሚኒስትሩ ደህንነት መጥፎ ወሬ ሲሰማ ጭንቀቱና መረበሹ የዋዛ አይሆንም።
‹‹ጌታዋን የተማመነች በግ …››
ነገሩን አስገራሚም አስቂኝም የሚያደርገው የሐሰት መረጃዎችን የሚያሰራጩ ግለሰቦችና ቡድኖች በግልፅ እየታወቁ ሳለ የንጹሃንን ሕይወት አደጋ ላይ ሊጥል የሚችሉ መረጃዎችን ሲያሰራጩ እንኳንስ ሕጋዊ እርምጃ ሊወሰድባቸው ይቅርና ኮስተር ባለ ዓይን የሚያያቸው አንድም የመንግሥት አካል አለመኖሩ ነው። መረጃ አሰራጭዎቹን አደብ የሚያስገዛቸው አካል አለመኖሩን ስንታዘብ ‹‹ … እንዲህ ዓይነቱን መረጃ እንዲናገሩ/እንዲጽፉ ተልዕኮ የሚሰጣቸው የመንግሥት አካል አለ እንዴ?›› ወደሚል ግምታዊ ጥያቄ ለማምራት እንደገደዳለን።
ከሁሉም ቅድሚያ የዜጎችን መሰረታዊ ደህንነት ሊጠብቅ የሚገባው መንግሥት፣ የዜጎችን መሰረታዊ ደህንነት አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ አደገኛ መረጃዎችን የሚያሰራጩ አካላትን ዓይቶ እንዳላየ ማለፉ ለብዙ ግምቶችና ይሆናሎች ቢጋብዝ የሚያስገርም አይሆንም።
የመንግሥትን ዝምታ የታዘቡ ሁሉ ግራ ተጋብተው ‹‹ … እነዚህ ሰዎች’ማ የተማመኑትን ተማምነው ነው እንጂ እንዲህ ዓይነት አደገኛ የሐሰት መረጃ አያሰራጩም ነበር። ወንጀል ቢሰሩም መከታ የሚሆንላቸው ባለስልጣን አለ ማለት ነው …›› እያሉ ይገምታሉ፤ተጨማሪ ውዥንብር እንዲፈጠርም ያደርጋሉ። በአጠቃላይ በአንድ በኩል የመረጃዎቹን ሐሰተኛነትና አደገኛነት፤በሌላ በኩል የመንግሥትን ዝምታ የተገነዘበ ሰው ሁሉ ‹‹ጌታዋን የተማመነች በግ ላቷን ደጅ ታሳድራለች›› ቢል አይፈረድበትም።
ችግሩን የበለጠ ውስብስብ የሚደርገው እነዚህን አደገኛ የሐሰት መረጃዎች የሚያሰራጩ ግለሰቦች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተከታዮችና ደጋፊዎች ያሏቸውና እንደታማኝ የመረጃ ምንጭም የሚቆጠሩ መሆናቸው ነው። በተደጋጋሚ የሐሰት መረጃዎችን ሲያሰራጩ ተከታዮቻቸውና ደጋፊዎቻቸው እነርሱን ከመምከርና ከመተቸት ይልቅ ይባስ ብለው የማበረታታቸውና እንደጀግና የመቁጠራቸው አሳዛኝ እውነት ሲደመርበት ደግሞ ጉዳዩ ከውስብስብነት የተሻገረ ትርጉም እንዲኖረውና ከዚህ ቀደም የታዩት አሰቃቂ ክስተቶች እንዲደገሙ የሚያደርግ ይሆናል።
ለመሆኑ መንግሥት ምን አለ?
ከላይ እንደተገለፀው እነዚህ አካላት አገርንና ሕዝብን አደጋ ላይ የሚጥሉ አደገኛ የሐሰት መረጃዎችን ሲያሰራጩ ምንም ዓይነት ሕጋዊ እርምጃ አልጎበኛቸውም። በድርጊታቸው የመፀፀትና እውነተኛ ይቅርታ የመጠየቅ ፍላጎትም አላሳዩም። እንዲያውም አንዳንዶቹ ‹‹የመረጃ ጌቶች›› እገሌ የተባለው ሰው ነው ያሳሳተኝ … ፎቶውን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እለጥፈዋለሁ …›› በማለት የፌዝ ምላሽ ሰጥተዋል።
‹‹የአገሪቱ እንቅስቃሴዎች ሁሉ በዕይታው ስር እንደሆኑ›› የሚገመተው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት (National Information and Security Service – NISS) መሥሪያ ቤት ‹‹ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብታቸውን ያላግባብ ተጠቅመው አገልግሎቱን በተመለከተ ሃሰተኛ መረጃዎችን በማህበራዊ ትስስር ገጾቻቸው በማሰራጨት ህብረተሰቡን ለማደናገር ሲሞክሩ የነበሩ አንዳንድ የማህበራዊ ሚድያ አንቂዎች›› ከህገወጥ ድርጊታቸው ሊታቀቡ እንደሚገባ ከማሳሰብ ባለፈ ሌላ ያለው ነገር የለም። ድንቄም ‹‹የማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎች››¡
በመገናኛ ብዙኃን የተላለፈው የአገልገሎት መሥሪያ ቤቱ አጭር መግለጫ ‹‹ … ከዚህ በኋላ የሀሰት መረጃዎችንና አሉባልታዎችን በማህበራዊ ትስስር ገጾች በማሰራጨት የሀገርን ብሄራዊ ጥቅምና ህልውና ለመጉዳት እንዲሁም የህዝብን ሰላምና ደህንነት ስጋት ላይ ለመጣል የሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ማስረጃዎችን በማጠናቀር በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ እንደሚያደርግ ያስታውቃል። ብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በሀገር ላይ የሚቃጡ የፀጥታና የደህንነት ስጋቶችን በማስቀረት ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ከማንኛውም ጊዜ በላይ ከሁሉም የጸጥታና የደህንነት ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ ይገኛል … ›› ይላል።
ገዥው ብልፅግና ፓርቲ በበኩሉ፤ ህብረተሰቡ ማንኛውንም ጉዳይ አስመልክቶ በማህበራዊ ሚዲያ የሚለቀቁ መረጃዎችን ትክክለኛነት በጥንቃቄ ማጣራት ይኖርበታል›› የሚል ምክር አዘል መልዕክት አስተላልፏል። ፓርቲው በመግለጫው ‹‹ … በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለምም ሆነ በአገራችን በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ ሃሰተኛ ወሬዎች እየተበራከቱ ይገኛሉ። ማንኛውም ዜጋ በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ መረጃዎችን ከመቀበሉ በፊት ከተረጋገጠና ከትክክለኛ ምንጭ የተገኙ መሆናቸውን በጥንቃቄ ማጣራት አለበት።
ከሰሞኑ የፓርቲያችን ፕሬዚዳንትና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑትን ክቡር ዶክተር አብይ አህመድን ጤንነትና ደህንነት አስመልክቶ በማህበራዊ ሚዲያ የተናፈሰው ወሬ ፍጹም መሠረተ ቢስና ሆን ተብሎ ህብረተሰቡን ለማደናገር ኃላፊነት በማይሰማቸው አካላት የተሰራጨ ነውረኛ የሀሰት መረጃ ነው። ህዝባችን ለወደፊቱም ከተመሳሳይ ሀሰተኛ ወሬዎች መጠንቀቅ ይኖርበታል።
ህብረተሰቡን የማደናገርና ውዥንብር የመፍጠር ዓላማ ይዘው ሃሰተኛ ወሬዎችን እየፈበረኩ የሚያሰራጩ የጥፋት አካላትን በጥብቅ ተከታትሎ የህግ ተጠያቂ ማድረግ የመንግሥት ኃላፊነት ይሆናል›› በማለት አደገኛውን መረጃ ያሰራጩት አካላት በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ፍንጭ መሳይ ነገር ሰጥቷል። ‹‹ተገቢው እርምጃ ተወስዶ ሕግ ይከበራል?›› የሚለውን ወደፊት የምናየው ይሆናል።
የሃሳብ ነፃነትና የሕዝብ ደህንነት
የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት መሥሪያ ቤት በጉዳዩ ላይ ባወጣው መግለጫ ‹‹ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብታቸውን ያላግባብ ተጠቅመው …›› የምትል ሐረግ ትገኛለች። በእርግጥ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ከመሰረታዊ የሠው ልጅ መብቶችና ነፃነቶች መካከል አንዱ እንደሆነ የሚካድ አይደለም። ሃሳብን በነፃነት መግለፅ ማለት ግን በሐሰት መረጃ የሕዝብን ደህንነት አደጋ ላይ መጣል ማለት አይደለም! ሃሳብን በነፃነት መግለፅም ቢሆን ገደብ የለውም ማለት አይደለም። በዚህ መሠረታዊ መብትም ላይ ገደብ የሚጣልበት ጊዜ አለ።
ከዚህ ጋር ተያይዞ መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ በሃሳብ ነፃነት ስም የሕዝብን ደህንነት አደጋ ላይ መጣል ተገቢ እንዳልሆነ ሁሉ የሕዝብን ደህንነት በመጠበቅ ስምም ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን አደጋ ላይ መጣል ተገቢ እንዳልሆነ ነው። ሁለቱን ማምታታት የሕዝብን ደህንነት መጠበቅ ያለመቻል ድክመትንና ድብቅ የፖለቲካ ዓላማ የማስፈፀም ሴራን ከመሸፈንና አምባገነንነትን ሕጋዊ ከማድረግ ፍላጎቶች የሚመነጭ አደገኛ አካሄድ ነው። ሃሳብን በነፃነት የመግለፅም ሆነ የሕዝብን ደህንነት የመጠበቅ ስራዎች የሚተገበሩባቸው የየራሳቸው የሆኑ በቂ ወሰኖች አሏቸው።
እንዲያው አንዳንድ ጊዜ ከበድ ያሉ ችግሮች ተፈጥረው ገደብ የሚጣልበት ጊዜ ሊኖር ይችላል አልን እንጂ በዚህ መብት ላይ ገደብ መጣል ሳያስፈልግም የሕዝብን ደህንነት ማስጠበቅ ይቻላል።
እንደመፍትሄ
መንግሥት የሕዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ እጅግ አደገኛ የሐሰት መረጃዎች ሲሰራጩ ዝምታን መምረጡ የሚያስገርምና ተስፋ የሚያስቀርጥ ቢሆንም ሕዝቡም የራሱ ኃላፊነት አለበት። የመረጃዎቹን ምንጮች ታማኝነት መገምገም፣ ምንጮቹ ከዚህ ቀደም ስለነበራቸው ልምድ/ታሪክ ማጣራት፣ የመረጃዎቹ ዓላማዎች ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ ማሰላሰል፣ የታወቀ የመንግሥት አካል ማረጋገጫ እስከሚሰጥ ድረስ መረጃዎቹን ለሌሎች አለማጋራት እንዲሁም አደገኛ የሐሰት መረጃዎችን በሚያሰራጩ አካላት ላይ መንግሥት ተገቢውን ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ ግፊት ማድረግ ከሕዝቡ የሚጠበቁ ኃላፊነቶች ናቸው።
እነዚህ የመፍትሄ እርምጃዎች ሐሰተኛ መረጃዎቹ ሊፈጥሩ የሚችሏቸውን አደጋዎች ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ባይችሉ እንኳ አደጋዎቹን ለመቀነስ ግን ያስችላሉ።
በእርግጥ ‹‹የሹም ዶሮዎቹ›› የሐሰት መረጃዎችን ሲያሰራጩ ከመምከርና ከመተቸት ይልቅ ይባስ ብለው እነርሱን የሚያበረታቷቸውና እንደጀግና የሚቆጥሯቸው ተከታዮቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ግን የሐሰት መረጃዎችን ለማጣራት የሚያስችል ብቃትና ዝግጅት አላቸው ተብሎ አይታሰብም።
እስኪ በዚች ጥያቄ ልሰናበት … አደገኛ የሐሰት መረጃዎችን ያሰራጩት አካላት ድርጊታቸው አደገኛ መሆኑ እየታወቀም ምንም አልተባሉም፤ታዲያ የሰሞኑ አደገኛ የሐሰት መረጃዎቻቸው ከዚህ ቀደም እንደታዩት አሰቃቂ ግድያዎች፣ የአካል ጉዳቶች፣ የንብረት ውድመቶችና ሌሎች ችግሮች አስከትለው ቢሆን ኖሮ ተጠያቂዎቹ እነማን ይሆኑ ነበር?!
አዲስ ዘመን ጥር 24/2013