ዋቅሹም ፍቃዱ
አዲስ አበባ፡ በዘንድሮ ምርጫ በአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ ዋነኛው ተቀናቃኛቸው የነበረው፣ የሙዚቃው ንጉስ የቦብ ዋይን የቤት እስራት ሂደት እንደተቋረጠ የአገሪቱ ፍርድ ቤት ማሳወቁን አልጀዚራ ዘግቧል::
በተለይ ከፍተኛው የአገሪቱን ወጣት ድጋፍ ያለው ይህ የሙዚቃ ንጉስ፣ በተለያዩ ምክንያት ረብሻ ከተነሳ የምርጫው ሂደት ይዛባል ተብሎ ቦብ ዋይን ከቤቱ እንዳይወጣ ቤቱ በበርካታ የአገሪቱ የጸጥታ ሀይል ሲጠበቅ እንደ ነበር በዘገባው ተገልጿል::
ያም ሆኖ ግን መንግስት ታዋቂውን ግለሰብ በቤት ያገደው የምርጫ ውጤትን ለማዛባት እንዳልሆነ ይልቁንስ ለግለሰቡ ደህንነት ታስቦ መሆኑን በተደጋጋሚ ቢገልጽም፣ ቦብ ዋይንና ደጋፊዎቹ መንግስት እርምጃውን የወሰደው ጫና በግለሰቡ ላይ ጫና በማሳደር ምርጫውን በማጭበርበር ምርጫውን ለማሸነፍ እንደ ነበር እየገለጹ ይገኛሉ::
ባለፈዉ ሳምንት የተካሄደዉ የአገሪቱ የምርጫ ዉጤት እንደሚያሳይ ከሆነ ለ34 ዓመት ያህል ዩጋንዳን ያስተዳደሩ ዩዌሪ ሙሴቪን 59 በመቶ የድምጽ ብልጫ ሲያገኙ ተቀናቃኛቸዉ ቦብ ዋይን 35 በመቶ ድምጽ አግኝተዋል:: ሆኖም ግን ምርጫው እጅግ የተጭበረበረ በመሆኑ ዉጤቱ ተቀባይነት እንደሌለዉ ተቃዋሚዉ መናገሩ ዘገባዉ አብራርቷል::
ቦብ ዋይን በአገሪቱ የተንሰራፋዉ የሙስናና የምዝበራ ሁኔታ ያለምንም ፍርሃት በሙዚቃዉ ለህዝብ ይፋ ሲያደርግ በመቆየቱ በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ አድናቆት ተችሯል:: በምርጫዉ ያሸንፋል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረዉ በመሸነፉ ምክንያት በተፈጠረዉ ግርግር በርካታ የቦብ ዋይን ደጋፊዎች ታስረዉ ይገኛል::
ወደ ቦብ ዋይን የሚወስደዉ መንገድም በ6 መቶ ሜትር ላይ ተዘግቶ ቢቆይም ከፍርድ ቤቱ ውሳኔ በኋላ መከፈቱ ተዘግቧል:: ቦብ ዋይንም አዲስ የተመረጡ የአገሪቱ የፓርላማ አባለት ጋር ስለ አገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ምክክር ሲያደርግ መታየቱም ተገልጿል::
ቦብ ዋይን ከምዕራባዉያን ብዙ ድጋፍ ነበረዉ:: ነገር ግን የቀድሞ የአማጺያን መሪ የአሁኑ የዩጋንዳ ፕሬዚዳንት የ76 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋው፣ ዩዌሪ ሙሴቪኒ በተለያዩ ጊዜያት የሰላም አስከባሪ ሀይል ወደ የተለያዩ አገራት በመላኩ የምዕራባዉያን ቀልብ ከመሳብ አኳያ የሰራዉ ስራ ቀላል አልነበረም::
የምዕራባዉያኑ ተገዳዳሪ፣ ጽንፈኛዉ የአልሸባብ በድን ከመደምሰስና ከማዳከም አኳያም የዩዌሪ ሙሴቪኒ ድርሻ ከፍተኛ ነበር:: ሆኖም ግን አሁን ላይ የፕሬዚዳንቱ የስልጣን ዕድሜ ከሚገባዉ በላይ መርዘሙና በተቃዋሚ ቡድኖች ላይ በሚያደርገዉ ጫና የአለም መሪዎች ፊት እየነሱ ይገኛሉ::
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የቦብ ዋይን መታሰር አስመልክቶ ባወጣዉ ጠንከር ያለ መግለጫ አውጥቷል:: በመግለጫዉም ዩጋንዳ ቦብ ዋይን ማሰሯ ህገ ወጥና ያለ ምክንያት መሆኑን በመግለጫዉ አመላክቷል::
ታዋቂዉ የናይጀሪያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ፌሚ ፋላና የዩጋንዳ ፖሊስና መከላከያ ቦብ ዋይን ከቤት እንዳይወጣ መከልከላቸዉ ኢ ሰብዓዊ ከመሆኑም በላይ ፍጹም ህገወጥነት የተሞላበት ጭካኔ ተግባር በመሆኑ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ በዩዌሪ መሴቪኒ ላይ ጫና እንዲያድር የበኩሉን ጥረት እንደሚያደርግ ተናግረዋል:: በተመሳሳይ ሁኔታ የሰብዓዊ ተሟጋች ድርጅት ምርጫዉ አስመልክቶ ባወጣዉ መግለጫ፣ ምርጫዉ በከፍተኛ ዛቻና ማስፈራሪያ የተሞላበት ከመሆኑም በተጨማሪ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የተፈጸመበትና በነዉጥ የታጀበ እንደ ነበር ገልጾ ነበር::
በነዉጡ ምክንያት ኢንተርኔት መቋረጡና ብዙዎች ለእስራት መዳረጋቸዉም ጠቁሟል:: በድርጅቱ የአፍሪካ ጉዳይ ተመራማሪ፣ ኦሪዬም ኔይኮ እንዳሉት፣ ምርጫዉ ዴሞክራሲያዊ የዉድድር ሜዳ ያልታየበት፣ ነጻና ገለልተኝነት የጎደለዉ እንደ ነበር ገልጿል::
በመጨረሻም የዩጋንዳ መንግስት የመናገር፣ የመንቀሳቀስና የመሰብሰብ ነጻነት ላይ መጫኑን ትቶ ለሰብዓዊ መብት መከበርና የዴሞክራሲን ምዕዳር በማስፋት ላይ ተጨባጭ ለዉጥ እንዲያመጣ አሳስቧል::
አዲስ ዘመን ጥር 20/2013