ዋቅሹም ፍቃዱ
አዲስ አበባ፡- በኬንያ ድንበር አቅራቢያ የሚገኘው በሶማሊያ ከተማ በጁባ ላንድ ግዛትና በሶማሊያ መካከል ከባድ ውጊያ መከሰቱን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።
እንደ ዘገባው፣ የሶማሊያ የማስታወቂያ ሚኒስትር በኬንያ የሚታገዙ የጁባ ላንድ ታጣቂዎች የሶማሊያን ድንበር ቡሎ ሀይዎ ከተማ ጥሰው በመግባት በሶማሊያ ወታደሮች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ገልጸዋል።
ነገር ግን የጁባ ላንድ ምክትል ፐሬዚዳንት መሀመድ ሰይድ አዳን በበኩላቸው እንዳሉት የሶማሊያ ወታደሮች በሶማሊያ ቀጥተኛ ትዕዛዝ በከተማው ውጭ የፀጥታ ማስከበር ላይ የነበሩ የአገራቸው ወታደሮች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተናግረዋል።
ምንም እንኳ ሁለቱ ወገኖች እርስ በእርሳቸው እየተወነጃጀሉና አሸናፊነታቸውን እየገለጹ ቢሆንም ጦርነቱ እየቀጠለ በመሆኑ የአገሪቱ ዜጎች ጦርነቱን በመሸሽ መሰደድ መጀመራቸውን በዘገባው ተገልጿል። በተደረገው ውጊያ የቡሎ ሀይዎ ከተማ በሶማሊያ ቁጥጥር ስር ማቆየት መቻሉ የአገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስትሩ ገልጸው በውጊያ የደረሰ ጉዳት በዝርዝር ከመግለጽ መታቀባቸውን ዘገባው ያትታል። በእርግጥ የደረሰው ጉዳት በሁለቱም ወገኖች ባይገለጽም ከባድ መሆኑ ከአካባቢ የወጡ መረጃዎች እያሳዩ መሆናቸው ዘገባዉ ጠቁሟል።
ሶማሊያ ከኬንያ መንግስት በሉዓላዊነቷ ዙሪያ እንደሚገጥማት በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች። ሶማሊያ የጁባ ላንድን እንደ ግዛቷ ብትመለከትም፣ ኬንያ ግን በተቃራኒው ለጁባ ላንድ ሉዓላዊነት ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገች እንደምትገኝ ከሶማሊያ ከባድ ወቀሳ ይደርስባታል። ከወቀሳ በዘለለም ባለፈው ወርሃ ታህሳስ ሶማሊያ ከኬንያ ጋር ያላትን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ማቋረጧ ይታወሳል። ይህ የሶማሊያ አቋም የአገሪቱን አንድነት፣ ሉዓላዊነትና ሰላም ለማስጠበቅ ተብሎ ቢሆንም
ኬንያ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ኬንያ በአገራቸው ጉዳይ እጇን በማስገባት ችግር እየፈጠረች መሆኗን የሶማሊያ ፕሬዚዳንት መግለጻቸውን በዘገባው ተብራርቷል። ኬንያና ሶማሊያ ወደ ህንዲያን ውቅያኖስ የሚዘልቀው በተፈጥሮ ጋዝና በነዳጅ የበለጸገ 100 ሺህ ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሆነው መሬት ይገባኛል በማለት በተደጋጋሚ እየተጋጩ እንደሆነ ዘገባው ጨምሮ አብራርቷል።
እንደ ዘገባው ሶማሊያ በቀጣዩ ወር ምርጫ ለማድረግ ዝግጅት ላይ ባለችበት በአሁኑ ወቅት ውጊያው መቀስቀሱ የምርጫው ሂደት ላይ ከፍተኛ ጫና ይኖረዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ፑንት ላንድም ሆነ ጁባ ላንድ በምርጫው ለመሳተፍ ፍቃደኞች አይደሉም። ባለፈው መስከረም ፕሬዚዳንት አብዱላህ መሀመድ አብዱላህ በጁባ ላንድና በፑንት ላንድ ባደረጉት ውይይት የሶማሊያን ወታደሮች ከጁባ ላንድ ከጌዶ ቀጠና ለማስወጣት ወስነው ነበር። ነገር ግን ቃላቸውን በለማክበራቸው የሶማሊያ ወታደሮች ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ የተቆጣጠሩት የቡሎ ሀይዎ ከተማ ባሉበት እንዲቆዩ ተደርጓል። ሬዚዳንቱ ይባስ
ብሎም በጁባ ላንድ እውንታ በኬንያ የሚደገፍ አዲስ ኮሚሽነር የጌዶ ቀጠና አስተዳዳሪ አድረገው ሾመዋል።
ጁባ ላንድም ኬንያ የተለያዩ የአፍሪካ ሰላም አስከባሪ የጸጥታ ሃይሎች የሚሰማሩባት፣ ስትራቴጂያዊ የሆነችውን የኪስማዮን ወደብ የራሷን ለማድረግ ከፍተኛ ተጋድሎ እያደረገች ትገኛለች። ጽንፈኛ የአልሸባብ ቡድን መካከለኛን የጁባ ላንድ ግዛት በቁጥጥሩ ስር ማስገባት ለሶማሊያም ሆነ ለቀጠናው አገራት ስጋት መሆኑ እንደ ቀጠለ ነው።
አዲስ ዘመን ጥር 18/2013