ዋቅሹም ፍቃዱ
አዲስ አበባ፡- አሜሪካ በዶናልድ ትራፕ ውሳኔ ወታደሮቿን ከሶማሊያ ማስወጣቷ ጋር ተያይዞ በሽብርተኝነት ላይ የሚደረገው ዘመቻ በማላላቱ ምክንያት የሶማሊያ የፀጥታ ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ፤ አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የሶማሊያን ጉዳይ እንደገና እንዲያጤኑ የአለም ማህበረሰብ እያሳሰበ መሆኑ ኦልአፍሪካን ድረ ገጽ ዘግቧል።
እንደዘገባው፣አሜሪካ ጽንፈኛው የኢስላማዊ ሽብርተኛ ቡድን፣የአልሸባብን የሽብር ጥቃት ለመከላከል ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቁ ብቁ ወታደሮችን በመላክ በተለያዩ ጊዜያት የቡድኑን ይዞታ በመደብደብ አመርቂ ውጤት ስታስመዘግብ ቆይታለች። ቡድኑ የተቆጣጠረባቸውን ቦታዎች በማስለቀቅ በኢኮኖሚና በመረጃ እንዲዳከም ከማድረግ አኳያ የአሜሪካ ሚና ከፍተኛ ነበር።
ሆኖም ግን የዶናልድ ትራፕ የመጨረሻ ውሳኔዎች አንዱ የሆነው የአሜሪካ ወታደሮች ከሶማሊያ ማስወጣት፣ ባለፈው ዓመት በወርሃ ጥር የአሜሪካ ወታደሮች ሙሉ በሙሉ ሶማሊያን ለቀው እንዲወጡ ከተደረገ ወዲህ፣ የአገሪቱ የጸጥታ ሁኔታ ጥሩ እንዳልሆነ እየተነገረ ይገኛል።
በእርግጥ፣ የሶማሊያ የጸጥታ ጉዳይ የጆ ባይደን ፈጣን ውሳኔ ከሚባሉት ጉዳዮች አንዱ እንደሚሆኑ የአለም አገራት ግፊት እያደረጉ መሆናቸው ተብራርቷል።
የአልሸባብ እንቅስቃሴ በሶማሊያ ወታደሮች አቅም ብቻ የሚገታ ጉዳይ ባይሆንም የአሜሪካ ወታደሮች ሶማሊያን ለቀው መውጣት ተከትሎ የአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ሀይል/አሚሶም በአገሪቱ መቆየት እርግጠኛ ሆኖ መናገር እንደሚያስቸግር ዘገባው ጠቁሟል።
የአሜሪካ ወታደሮች መውጣት ተከትሎ ከአልሸባብ ጥቃት ይልቅ የቀጣዩ ምርጫ ሁኔታ ለብዙ ሶማሊያ ዜጎች ስጋት እየሆኖባቸው መጥተዋል። ምክንያቱም በክልልና በፌዴራል መንግስት መካከል ያለመተማመንና ያለመግባባት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። የበፊቱ ምርጫም ቢሆን ተዓማኒነቱ አጠያያቂ እንደነበር የብዙ የአገሪቱ ዜጎች ሃሳብ ነበር። ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ተጠያቂ አገሪቱን አሁን እየመሩ ያሉ ፕሬዚዳንት መሀመድ አብዱላይ ፈርማጆ እንደሆኑ ተገልጿል።
አሁንም ቢሆን ፕሬዚዳንቱ ተመሳሳይ ስህተት ለመድገም እንቅስቃሴ እንደጀመሩም በዘገባው ተጠቅሷል። ይህ ደግሞ የሚፈጥረው ውጥረት ከባድ መሆኑ እንዳለ ሆኖ በአገሪቱ ህግና ፍትህ የሚተገበርበት ሁኔታ አድሎአዊ በመሆኑ ለጸጥታው መናጋት ሚና ስለሚኖር ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል የሚሉ ሰዎች መኖራቸውን ዘገባው ጠቁሟል።
እንደ ዘገባው፣ አንዳንድ ወገኖች፣ የአገሪቱ መሪዎች ሶማሊያ የተረጋጋች፣ሰላምና ዴሞክራሲ የሰፈነባት አገር እንድትሆን ልዩነታቸውን ወደ ጎን በመተው የአገሪቱ ሰላምና ዕድገት ማነቆ የሆነውን ጽንፈኛው ቡድን አልሸባብ ላይ የሚደረገውን ዘመቻ እውን ለማድረግ ከልባቸው እንዲሰሩ ያሳስባሉ።
እንዲያውም የአሜሪካ ወታደሮች ወይም የሌሎች አገራት ወታደሮች በሶማሊያ መኖራቸው ብቻውን የሶማሊያ መረጋጋት አያመጣም ብሎ የሚናገሩ ወገኖች ብዙ መሆናቸዉን ዘገባው ይገልጻል።ከሁሉም በላይ የአገሪቱ መሪዎች በሚወስዱት እርምጃ፣ በሚያስተላልፉት ውሳኔና በሌሎችም ጉዳዮች ግልጽ መሆን ይጠበቅባቸዋል።
በክልልና በፌዴራል መንግስታት መካከል መግባባት፣ ስልጣናቸውን በተዋረድ በአግባቡ እየተናበቡ ወደ ስራ መተርጎም ለአገሪቱ ሰላም አስፈላጊ ነው። በተለይ በፌዴራል ጥላ ስር ለአገራቸው መስራት የአገሪቱ የዘመናት የዴሞክራሲና ሰላም እንደሚቀርፍ ዘገባው ያስረዳል። ህዝቡም በሰላም አብሮ የመኖር እንቅስቃሴ ላይ በሰፊው መሳተፍ ይጠበቅበታል።
ምንም እንኳ ፈታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም ለሶማሊያ ዘላቂ ሰላም፣ መፍትሄው ሶማሊያውያን ራሳቸው ናቸው።ምክንያቱም የውጭ ሀይል በሚፈለገው ደረጃ ለሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት መስራት አይችልም።
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ለሶማሊያ አለመረጋጋት ጣታቸውን ወደ ኬንያ ቢቀስሩም እውነታው ከኬንያ ይልቅ ሶማሊያ እንዳትረጋጋ የሰሩ ሌሎች አገራትም እንደነበሩ ተጠቁሟል።
የገልፍ አገራት የፖለቲካ አለመረጋጋት በሶማሊያ ሰላምና ጸጥታ ሁኔታ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሲያደርግ ነበር። በአጠቃላይ የሶማሊያ ህዝብና መንግስት ለሶማሊያ ሰላምና ልማት ቁርጠኛ ከሆኑ ስለሶማሊያ ጉዳይ የሌላ አገር እርዳታ የሚፈለግ ጊዜ ያበቃል። የወደ ፊቷ ሶማሊያ ሰላም እጣ ፈንታ በሶማሊያውያን እንደሆነም ዘገባው አስረድቷል።
አዲስ ዘመን ጥር 17/2013