ግርማ መንግሥቴ
የልጆች የወደፊት መልካም ሰብዕና ከሚመሠረትባቸው መንገዶች አንዱ “አርአያነት” ነው።
ልጆች የመልካም ሥነ ምግባር ባለቤት፣ ብቁ ዜጋ ሆነው እንዲያድጉና በአካልም ሆነ በመንፈስ ጠንካራ እንዲሆኑ የሚያደርጓቸው ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ሁኔታዎች አሉ። ከእነዚህም አንዱ ከላይ የጠቀስነው “አርአያነት” ነው።
“አርአያነት” ማለት በብዙ መልኩ፤ ከሥነ ምግባር እስከ የሙያ ዘርፍ፣ ከአለባበስ እስከ አረማመድ፣ ከአነጋገር እስከ አጎራረስ ወዘተ… ድረስ የሚዘልቅ የሰዎች ሰብዕና ሲሆን፤ ይህ ዓይነቱ አርአያነት ትውልድን ለመቅረፅ ያለው ፋይዳ ቀላል አይደለም። ብዙ ጊዜም ልጆች ሲጠየቁ ወይም ራሳቸው ሲናገሩ እንደሚሰማው የሚፈልጉት ያዩትን ነው፤ የሚናገሩትም የሰሙትን ነው፤ የሚመኙትም ከእነሱ በላይ የሆኑ ሰዎች ከሆኑት ተነስተው ነው። እነዚህ ሁሉ ደግሞ ለእነሱ በግብርም ይሁን በባህርይ አርአያቸው ናቸው ማለት ነው።
ችግሩ እነዚህ “አርአያ” ሆነው የቀረቡት ማለትም “አርአያ” ይሆኑ ዘንድ የሚጠበቅባቸው ወገኖች (ፊልሞች፣ ጌሞች ወዘተ) ምን ዓይነት ባህርይን የተላበሱ ናቸው፤ ምን ዓይነት ሞዴል የሚሆን ተግባርስ እያከናወኑ ነው? የሚለው ነው።
ሁላችንም በሚባል ደረጃ እንደምናውቀውም ሆነ እንደምናምነው እንዲሁም በጉዳዩ ላይ ሰፊ ጥናትና ምርምሮችን ያደረጉ ምሁራንም እንደሚያረጋግጡት ለልጅ (ልጆች) ቤተሰብና በቤተሰብ መካከል የሚደረግ መስተጋብር ቀዳሚውና ዋናው አርአያቸው ነው። በቤት ውስጥ ያለውና በዚያ የሚከናወነው ተግባር ሁሉ የነገውን ልጅ ከመቅረፅ አንፃር ድርሻው ከፍተኛ ነው። አካባቢ፣ ትምህርት ቤት፣ ማህበረሰብ ወዘተ…ሁሉ የየራሳቸው ድርሻ ቢኖራቸውም የበላይነቱን የሚይዘው ግን ቤተሰብና በቤት ውስጥ የሚከናወኑ ተግባራት ናቸው።
የነገው ትውልድ እሱነቱ በቤተሰቡ ማንነት ላይ ይመሠረታልና የቤተሰብ አባላቱና ተግባራቸው የነገውን አገር ተረካቢ ትውልድ ከመፍጠር አኳያ ታስቦበት መከናወን አለበት ማለት ነው። ቤተሰብም ይህንኑ አውቆ ልጅ ከመውለድ ባሻገር መልካም ሰብዕናን የተላበሰ እንዲሆን ቤተሠባዊ ወይም አካባቢያዊ ብቻ ሣይሆን መልካም ዜጋን ከማፍራት አኳይ ሀላፊነቱ አገራዊ መሆኑን ተገንዝቦ ማሣደግ ይጠበቅበታል ማለት ነው።
ከቤተሠብ ሣንወጣ የልጆችን መልካም ሰብዕና ከሚቀርፁ ተግባራት አንዱ ፊልም ወይም ጌም የሚሉት የጨዋታ (ዎች) ዓይነት ነው። ልጆች የሚመለከቷቸው ኪነ ጥበባዊ ሥራዎች ለልጆች የተመጠኑ፣ ልጆችን የሚያዝናኑ ብቻ ሣይሆን የተሻለ ትውልድን ከመፍጠር አኳያም ሊታዩና ለልጆች ሊቀርቡ ይገባል። ከዚሁ አኳያ ባደጉት አገሮች ይህንን የሚያሟሉ በርካታ ሥራዎች (online play / online games የሚባሉት አሁን ደግሞ ማዝናናቱን ከማስተማር ጋር አጣምረው በመያዛቸው ምክንያት “edutaining” games እየተባሉ ሲሆን 160 ሚሊዮን የተመዘገቡ ተጠቃሚዎች ያሉትና “Animal Jam” ድረገፅ የሚያቀርባቸውና ስለ ሥነ ምህዳር፣ አፈር ጥበቃና ተመሣሣይ ርዕሰ – ጉዳዮች ላይ በማተኮር የሚቀርቡት ሥራዎች ተጠቃሽ ናቸው።
“Prodigy” እና “Captain Toad: Treasure Tracker”ም ልክ እንደ “Animal Jam” ሁሉ የልጆችን መልካም ስብዕና ከመገንባት አኳይ የተመሠከረላቸው ሲሆኑ፤ በተለይ ከአምስት ዓመት ዕድሜ በላይ የሆኑ ልጆችን ታሣቢ አድርገው መሠራታቸው እነዚሁ ልጆች እንዲመለከቷቸው ይበረታታሉ።
በሉ ልጆች እንግዲህ ጌም ስትጫወቱም ይሁን ፊልም ስትመለከቱ ልክ ከላይ እንዳልናችሁ ሁሉ የሚያስተምሩትና መልካም ስብዕና እንዲኖሯችሁ የሚያደርጉት ላይ አተኩሩ። ቤተሰብም እንዲመርጡላችሁ ጠይቁ።