ልጆች እንዴት ሠነበታችሁ? ትምህርት ከተጀመረ ሠነባበተ አይደል? አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ፈተና መጀመራቸውንም ሠምቻለሁ። እና ልጆች በኮሮና ምክንያት ለረጅም ጊዜ የተዘጋው ትምህርት ቤት ተከፍቶ በመማራቸው በርካታ ልጆች ደስተኛ መሆናቸውን ይናገራሉ። ልጆች ትምህርት ቤት ከመመላለስ ባለፈ ሁልጊዜ ትምህርታችሁ ላይ ትኩረት አድርጋችሁ መማር ይኖርባችኋል። ያለምንም ምክንያት ውጤታማ ተማሪ ለመሆን መጣር ይኖርባቸኋል።
በሀገራችን ከሚነገሩ በርካታ ተረቶች መካከል ስለሠነፉ ተማሪ የተነገረውን ልንገራችሁ። በድሮ ጊዜ ነው። ምንም ዓይነት ትምህርት የማይወድ ትምህርት አይገባኝም ብሎ ስለሚያስብ አንድ ቀላል ሂሣብ እንኳን የማይገባው ሠነፍ ተማሪ ነበር፡፡ አንድ ቀን ታዲያ መምህሩ ስለመቀነስ እያስተማሩ ሣለ ተማሪው ስላልገባው መምህሩ ምሣሌ ይሰጡት ጀመር፡፡
እንዲህም አሉት “አምስት በጎች በረት ውስጥ ቢኖርህና አንዱ ሾልኮ ቢያመልጥ ስንት ይቀርሃል?”
ተማሪውም “ጌታው ኧረ ምንም አይቀረኝ” አላቸው። መምህሩም በመበሣጨት “ይህ እንዴት አይገባህም?” ብለው ጮሁበት፡፡ ተማሪውም እያለቀሰ
“ኧረ ጌታው የበጎችን አመል ጠንቅቄ ነው የማውቀው፤ አንዲቷ ካመለጠች ሌሎቹም ተከትለዋት ነው የሚጠፉት። ” አላቸው፡፡
በዚህም ጊዜ መምህሩ ሲስቁ ክፍሉ በሙሉ ሣቀ። ልጆች ያልገባችሁን ነገር ለመረዳት መጣር ሲኖርባችሁ እንደሠነፉ ተማሪ ያልሆነ ምክንያት እየደረደራችሁ ራሣችሁን በሥንፍና ማሠር አይኖባችሁም።
ሌላው አሁን ባለው ችግር ምክንያት በፈረቃ ስለምትማሩ ትምህርት በማይኖራቸሁ ቀን ከትምህርት ቤት የተሰጠውን የቤት ሥራ በአግባቡ ከመሥራት ባሻገር ጨወታ ሣያታልላችሁ ሌሎች መፅሀፍትን በማንበብ በቂ እውቀት እንዲኖራችሁ ማድረግ ይኖርባቸኋል፤ እሺ ውዶቼ።
ወላጆቻችሁን ታዘዙ፤ ሁልጊዜ የተሻለውን መልካሙን በመመኘት የምታልሙት ዓላማ ላይ ለመድረስ ጥረት አድርጉ። ራዕያቸሁ ተሣክቶ የነገዋን ኢትዮዽያ ከፍ ያለ ደረጃ የምታደርሱ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ምኞቴ ነው። መልካም የትምህርት ሣምንት ቻው።
አዲስ ዘመን ጥር 16/2013 ዓ.ም