መርድ ክፍሉ
የሰው ልጅ አንዱ በሌላው ላይ ጥገኛ ነው። እንደ ሰው ልጅ በአለማችን አንዱ ከሌላው ፈላጊ የሆነ ፍጡር አይገኝም። አንድሰው በጫካ አለያም በዋሻ ተገልሎና ፍራፍሬ እየተመገበ ከዱሩ ሳይወጣ የሚኖር ካልሆነ በስተቀር በከተማ ወይም በመንደር ኑሮ መስርቶ ያለ ሌሎች እገዛ ፈፅሞ መኖር አይችልም።
ማኅበራዊ ህይወት ከውልደት እስከ ሞት የሚኖር እና ቀጣይነት ያለው ሂደት ሲሆን በትምህርት እና ከሌሎች ሰዎች ጋር በሚኖረን ግንኙነት የሚዳብር ነው። የሰው ልጅ ስለራሱ እና ስለሚኖርበት ማኅበረሰብ የሚኖረውን ዕውቀት በተለያየ መልኩ ማለትም የመግባቢያ ቋንቋ በመማር፤ አካባቢያዊ ሁኔታውን በመመልከት እንዲሁም ማኅበራዊ ክህሎቶችን በመማር እያሳደገ ይሄዳል። ይህ የማኅበራዊ ህይወት ክህሎት በአግባቡ መዳበር ለተሟላ ስብዕና እና ዕድገት ወሳኝነት አለው።
በጎ ፍቃድ አገልግሎት ማለት በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ተሳትፎ በማድረግ ውስጣቸው ከሚሰማቸው ሰብአዊ አመለካከት ተነስተው ለሚኖሩበት ማህበረሰብ ሰፊ የልማት አውታሮችን በመዘርጋት የዜግነት ኃላፊነትን የሚገነዘቡ ሃገራዊና ብሄራዊ ግዴታዎችን የሚያውቁበት በማህበራዊ ሚናዎች ስር ግንባር ቀደም የሚሆኑና የሃገርና የወገን ፍቅርን የሚያዳብሩበት ትልቅ ሚና ያለው ተግባር ነው።
እነዚህ ወጣቶችም ባላቸው የእረፍት ጊዜያቸውን መስዋዕት አድርገው ልማትን ለማምጣትና ለአካባቢ ደህንነት ነጻ ጊዜያቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ጉልበታቸው እና እውቀታቸውን በተጨማሪም በጎ አመለካከትን የሚያውሉበት ስራ ሲሆን ሌሎችን ከመርዳት አኳያም በጎ ምኞትን ተላብሰው ከማህበረሰባቸው ጎን ሁነው የሚያውቁትን የሚያስተምሩበትና ከሌሎች አካላትም የህይወት ክህሎት የሚቀስሙበት ዋነኛ መንገድ ነው።
በመሆኑም የበጎ ፍቃደኝነት አገልግሎት ጽንሰ ሃሳብ እንደየ ህብረተሰብ የእድገት ደረጃ አካባቢያዊ ሁኔታ የሚለይና አንድ ወጥ የሆነ ትርጉም ባይኖረውም ወጣቶች በራሳቸው ተነሳሽነትና በመልካም ፍቃደኝነት ላይ መሰረት ያደረገ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በመሳተፍ ያልተዳሰሱ ስራዎችን በማየት አመርቂ ውጤት የሚያበረክቱበት ሊሆን ይገባል። ይህም ዕድሜና ጾታና ማህበራዊ ደረጃ መልካምድራዊ ወሰን ሳይገድብ ሰብአዊነትን ተመስርቶ የሚሰጥ አገልግሎት ነው።
በወጣትነት እድሜ ብዙ ስራዎች ለመስራት እቅድ የሚያዝበትና ዝግጅት የሚደረግበት እድሜ ነው። በወጣትነት ጥሩም ይሁን መጥፎ ነገሮች ቢደርሱ ትምህርት ተወስዶ ለቀጣይ እምርታ ከማምጣት መሰረት የሚጣልበት ወቅት ነው። ዛሬ በወጣትነት እድሜያቸው በጎ ስራ እያከናወኑ ስለሚገኙ ማህራት አወጋችኋለሁ። ወጣቶቹ ከአንድ አመት በፊት መባ በጎ አድራጎት ማህበር በሚል አምስት ወጣቶች ተሰባስበው መሰረቱ። ማህበሩ የተቸገሩ ወገኖችን ከመደገፍ ባሻገር የደም ልገሳም ያከናውናል።
የዚህ ማህበር አባል ሰዎችን ለመርዳት እድል በማግኘታቸው እጅጉን ደስተኞች ናቸው። ምክንያቱም ማህበሩም የተቸገሩ ሰዎችን መደገፍ ላይ አተኩሮ የሚሰራ ሲሆን፤ አባላቱም ትኬት በመሸጥና ስፖንሰር በመጠየቅ የታመሙ ይጠይቃሉ፤ የተራቡን ያበላሉ፤ የታረዙንትም ያለብሳሉ፤ በችግር ውስጥ ያሉም ሲያገኙ የአስቤዛ ድጋፍ ያደርጋሉ። በበዓል ወቅትም አቅም የሌላቸውን እየጎበኙ አለንላችሁ በማለት በዓል አብረውም ያከብራሉ።
አጠቃላይ ሰዎች በችግራቸው ምክንያት ከሚሰማቸው ሀዘንና ቁዘማ ወጥተው ደስተኛና ስኬታማ እንዲሆኑ ማገዝ ላይ አተኩረው ይሰራሉ። እንደ መባ በጎ አድራጎት ማህበር መልካም ዓላማን ሰንቀው የሚሰሩ ወጣቶች እየተበራከቱ መጥተዋል። ለዚህ ዓላማቸው መሳካትም ህጻናትና አዛውንቶችን ብሎም በተለያየ መልኩ ራሳቸውን ማገዝ ያልቻሉ ሰዎችን ከመደገፍ ባለፈ መሃል ላይ ያሉ ሰዎች (ወጣቶች) ላይ ትኩረት አድርገው በመስራት ላይ ናቸው።
የማህበሩ አመሰራረትና ያከናወናቸው ተግባራት
የመባ በጎ አድራጎት ማህበር ስራ አስፈፃሚ የሆነችው ወጣት ፍሬህይወት መርጊያ፤ማህበሩ የተመሰረተው ከአንድ ዓመት በፊት ሲሆን አምስት ጓደኛማቾች ተሰባስበው የተመሰረተ መሆኑን ትናገራለች። ማህበሩ ህፃናትና አረጋውያን ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ነው። ድጋፍ የሚደረግላቸውን ሰዎች ቤት በመጎብኘት፣ የወር አስቤዛ በመስጠት እንዲሁም አብሮ በማሳለፍ እስካሁን ዘልቋል። ማህበሩ ስምንት የተቸገሩ ሰዎችን በመርዳት ስራውን የጀመረ ሲሆን የወር አስቤዛ በመስጠት፣ በዓላትን አብሮ በማሳለፍ፣ ቤታቸውን በማፅዳትና ሌሎች ስራዎችንም ማህበሩ እንደሚያከናውን ገልፃለች።
በማህበሩ ውስጥ የሚገኙት አባላት የቴሌግራም ግሩፕ ያላቸው ሲሆን የግሩፑ አባላት በአቅራቢያቸው የተቸገሩ ሰዎች ሲያዩ ወይም ሲሰሙ ተወያይተውበት ጉብኝት በማድረግ አስፈላጊ ድጋፍ እንደሚያደጉ ትናገራለች። ሁሉም የማህበሩ አባላት ውስጥ ሰውን የመርዳት ስሜቶች በመኖራቸው ቀደም ብሎም በሌሎች በጎ አድራጎት ማህበራት ውስጥ ተሳትፎ ያደርጉ እንደነበር ታስታውሳለች። በዚህም ጓደኛማቾቹ ተሰባስበው የበጎ አድራጎት ማህበር መስርተው የተሻለ ስራ ለመስራት መነሳሳታቸውን ትጠቅሳለች።
ሰሞኑንም ድጋፍ ለሚደረግላቸው ቤተሰቦች አስቤዛ የመስጠት ስራ መከናወኑን የጠቀሰችው ወጣት ፍሬህይወት፤ ለአስራ አምስት ቤተሰቦች አስቤዛ መሰጠቱን ተናግራለች። በቀጣይ ድጋፍ ለሚደረግላቸው ሰዎች የተሻለ ነገር ለማድረግ መታሰቡን ትገልፃለች። ወደ ሜክሲኮ አካባቢ የሚገኙ በላስቲክ በተሰራ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ባልና ሚስት አዛውንቶች ለጸበል ብለው አዲስ አበባ የመጡ ቢሆንም ችግር ውስጥ ናቸው። ሰዎቹ በአሁኑ ወቅት የአስቤዛ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን በመጥቀስ፤ በዘላቂነት ለመደገፍ ማህበሩ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ጠቁማለች።
ማህበሩ ድጋፍ ለሚያደርግላቸው ሰዎች አስፈላጊ ነገሮችን ለመግዛት እንደ ገቢ ምንጭ የሚጠቀመው ትኬቶችን በመሸጥ፣ ስለማህበሩ የሰማ ሰው ደግሞ በሚያደርገው የገንዘብ ድጋፍ፣ በአቅራቢያ የሚገኙ ሰዎች ለአንድ ቤተሰብ ሙሉ አስቤዛ ገዝተው በማምጣት እንዲሁም በእርዳታ የሚገኙ ልብሶች ድጋፍ ለሚደረግላቸው የሚሆኑትን በማስቀረት ሌላውን በመሸጥ ለማህበሩ ገቢ እንደሚደረግ ትናገራለች።
የገና በዓል በተከበረበት ወቅት ሰፊ ፕሮግራም በማዘጋጀት ከ500 በላይ ድጋፍ ከሚፈልጉ ሰዎች ጋር ማሳለፍ ተችሏል። ይህን ፕሮግራም ከሌላ በጎ አድራጎት ማህበር ጋር በቅንጅት የተሰራ ነው። በዚህም ድጋፍ የሚፈልጉ ሰዎችን በማብላትና ልብስ በማልበስ ሲሆን ስራውን ለማሳካት የትኬት ሽያጭ፣ ስፖንሰሮችን በማናገር ለተጨማሪም ድጋፎች መሰባሰባቸውን አስረድታለች።
ሌላዋ የማህበሩ አባል የሆነችው ወጣት ኤደን አዲስ እንደምትናገረው፤ የበጎ አድራጎት ማህበሩን አምስት ሆነው መሰረቱት። ሁሉም አባል በውስጣቸው የበጎ ስራ ለማከናወን ሀሳብና እቅድ ስለነበራቸው ተሰባስበው ማህበሩን ለመመስረት ቻሉ። ማህበሩ ከተመሰረተ በኋላ ድጋፍ ለሚፈልጉ ቤተሰቦች አስቤዛ መስጠት፣ በአላትን ማሳለፍ እንዱሁም ለገና በዓል ለአምስት መቶ ጉዳና ተዳዳሪዎችና አረጋውያን የመመገብ ስራ ተከናውኗል።
የህብረተሰቡ አቀባበል
ማህበሩ ስራውን በጀመረበት ወቅት የህብረተሰብ አቀባበል ችግር ነበረበት። ለዚህ ደግሞ ወጣቱ የተለያዩ ጥያቄዎች ስለነበሩበት አለመተማመኖች ነበሩ። በተሰሩ በርካታ ስራዎች ምክንያት አብዛኛው ህብረተሰቡ ማህበሩን ተቀብሎ እገዛ እያደረገ ይገኛል። ነገር ግን የማህበሩን አባላት ቢያበረታቱም ልመና በዛ በሚል የሚያማርሩ ሰዎች እንዳሉ ገልፃለች። ድጋፍ ለማግኘት የሰው ዓይን ማየት ቀላል አለመሆኑን በመግለፅ፤ አብዛኛው ሰው ግን ጥሩ የሆነ አመለካከትና ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቅሳለች።
ማህበሩን ያጋጠሙት ችግሮች
ማህበሩ ከተመሰረተ በኋላ እንደ ችግር አጋጥሞት የነበረው ሁኔታ ወጣት ፍሬህይወት ስትናገር፤ ማህበሩ ሲመሰረት በበጎ የሚረዳና የማይረዳ ሰው ይኖራል። ማህበሩ በተመሰረተ ወቅት ለግል ጥቅም የተቋቋመ ነው ብሎ የሚያስቡ ሰዎች ነበሩ። በአሁኑ ወቅት ግን ህብረተሰቡ የማህበሩ ስራዎችን ስላየ ተረድቷል። ማህበሩ ገንዘብ ለማግኘት በዋነኝነት የትኬት ሽያጮች ያከናውናል። ይህ ሁኔታ አብዛኛው ሰው ላይ ተቀባይነት የማይኖረው ሲሆን ለተለያዩ ችግሮችም እንደሚያጋልጥ ጠቁማለች። በተጨማሪነት ደግሞ ስራዎች በሚከናወኑበት ወቅት አባላት በተፈለገው ደረጃ አይገኙም። በዚህም የስራ መደራረቦች ይኖራሉ።
ወጣት ኤደን እንደምትናገረው ደግሞ፤ ማህበሩ ከተመሰረተ በኋላ በርካታ ችግሮች አጋጥመዋል። በጎ አድራጎት ማህበር ተመስርቶ ወደ ተግባር ሲገባ ህብረተሰቡ የሚረዳበት መንገድ የተሳሳተ ነው። ህብረተሰቡ የበጎ አድራጎት ማህበር የመሰረቱ ሰዎች ለራሳቸው ሊጠቀሙ ነው የሚል እምነት አላቸው። ችግሮች ሲያጋጥሙም የማህበሩ አባላት በትዕግስት ያሳልፉታል።
የማህበሩ ቀጣይ እቅድ
ማህበሩ በቀጣይ ለመስራት ያሰባቸው ብዙ ስራዎች እንዳሉት የጠቀሰችው ወጣት ፍሬህይወት፤ ረዳት የሌላቸውን ሰዎች ድጋፍና እንክብካቤ መስጠት እንዲሁም ማህበሩ ባለው አቅም እርዳታ ለማድረግ ጥረት እደረገ መሆኑን ታስረድታለች። እንዲሁም ስለማህበሩ እውቅና ለሌላቸው ሰዎች ግንዛቤ ለመስጠት ሀሳብ አለ። የተቸገሩ ሰዎችን በምን አይነት መንገድ እርዳታ ማድረግ ይቻላል በሚለው ላይም ሰፊ ስራ እንደሚሰራም ታብራራለች።
ማህበሩ ‹‹እኛ እያለን ድሀ መኖር የለበት›› በሚል እየተንቀሳቀሰ ሲሆን አባላቱ አብዛኛዎቹ ወጣቶች በመሆናቸው ትምህርትና ስራ ቢኖርባቸውም ያንን ጫና ተቋቁመው እየሰሩ እንደሚገኙ ታመለክታለች። ሁሉም የማህበሩ አባላት አሁን ባሉበት እድሜ የተሻለ ነገር ለመስራት ተነሳሽነት ያላቸው መሆኑን ትናገራለች። በሌላ በኩል አባላቱ በቀጣይ በግል ህይወታቸው የሚመጡ ለውጦችን ከማህበሩ ስራ ጋር አጣጥሞ ለመሄድ ማሰባቸውን ታስረዳለች።
ለተቸገሩ ወገኖች በሙያም፣ የስራ እድል በመፍጠር እንዲሁም በቋሚነት የደም ልገሳ በማከናወን ማህበሩን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ጠቁማለች። በቀጣይም ማህበሩን በማሳደግ ትልቅ የእርዳታ ድርጅት ለማድረግ ሀሳብ እንዳላቸው ተናግራለች። ማህበሩ ፈቃድ አውጥቶ የሚንቀሳቀስ ሲሆን የተሻሉ ስራዎችን ለመስራት ሀሳቦች እየመጡ መሆኑንም ታመለክታለች።
ወጣት ኤደን እንደምታብራራው፤ በቀጣይ ማህበሩ ካሰባቸው ስራዎች መካከል መረዳት አለባቸው ተብለው የተለዩ ሰዎችን ቤት ማስተካከል፣ ህክምና የሚያስፈልጋቸውን ማሳከም፤ ስራ መስራት የሚፈልጉ ሰዎችን ወደ ስራ ለማስገባት ሀሳቦች አሉ።
አዲስ ዘመን ጥር 14/2013