ዋለልኝ አየለ
አዲስ አበባ፡- ፓኪስታን ከአንድ ወር በፊት ጡረታ ወጥቶ የነበረውን ሌተናል ጀኔራል ቢላል አክባርን የሳውዲ ዐረቢያ መልዕክተኛ አድርጋ መሾሟን አልጀዚራ ትናንት ዘግቧል፡፡
ይህም ፓኪስታን ከባህረ ሰላጤው ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ፈልጋ እንደሆነ ያሳያል ተብሏል፡፡ የደቡብ እስያ ዜጎች የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለመጠገን ብዙ እንደሰሩም የፓኪስታኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናግረዋል፡፡
ሌተናል ጀኔራል አክባር በፓኪስታን ጦር ውስጥ ከ20 ዓመት በላይ በተለያዩ የጦር መሪነት ደረጃዎች አገልግሏል።፡ የጦር መኮንኑ በሳውዲ ዐረቢያ የፓኪስታን መልዕክተኛ መደረጉ የባህረ ሰላጤውን ግንኙነት ያጠናክራል፡፡ ከዚህ በፊት ሁለቱ አገራት በካሽሚር ጉዳይ ላይ እሰጥገባ ውስጥ ይገቡ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ፓኪስታን በካሽሚር ጉዳይ ላይ ለሳውዲ ዐረቢያ ተደጋጋሚ የእንወያይ ጥያቄዋን በእስላማዊ ትብብር ድርጅት በኩል አቅርባለች፡፡ በሌሎች ገንዘብና ነዳጅ ነክ ጉዳዮች ላይም ሳውዲ እና ፓኪስታን አንድ ጊዜ የሻከረ ሌላ ጊዜ የለሰለሰ ግንኙነት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡
ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ ግን ሁለቱ አገራት የጥንት ንትርኮቻችንን ‹‹ይቅር እንባባል›› ያሉ ይመስላል፡፡ ባለፈው የህዳር ወር ውስጥ ፓኪስታን ለሳውዲ ያቀረበችውን ‹‹በካሽሚር ጉዳይ እንወያይ›› ሳውዲ በመቀበሏ ፓኪስታን አመስግናለች፡፡
ሁለቱ ሃገራት ግንኙነታቸውን ለማጠናከርም መልዕክተኛዋን ሾመች፡፡ የሌተናል ጀኔራል ቢላል አክባር መሾም ሁለቱ አገራት በሪያድ እና በኢስላማባድ አምባሳደር እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 14/2013