ዋቅሹም ፍቃዱ
አዲስ አበባ፡- ማንነታቸው ለጊዜው ያልታወቀ ታጣቂዎች፣ በሱዳን የዳርፉር ግዛት አስተዳዳሪ መኖሪያ ቤት ላይ ያደረጉት የጥቃት ሙከራ በአስተዳዳሪው ጠባቂዎች መክሸፉን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
እንደ ዘገባው ታጣቂዎቹ በምዕራባዊ ዳርፉር በኤልጊና ግዛት በሚገኘው የግዛቱ አስተዳዳሪ፣ በመሀመድ አብደላ መኖሪያ ቤት ላይ ተኩስ ቢከፍቱም በሰውም ሆነ በንብረት ላይ ምንም ጉዳት ሳያደርሱ በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
በአካባቢው ባለፈው ሳምንት የተቀሰቀሰው የብሔር ግጭት ወደ 200 የሚጠጉ ሰዎች በመገደላቸው አሁን ላይ ከፍተኛ ውጥረት ነግሷል፡፡ በዚሁ መሃል ታጣቂዎቹ ተኩስ መክፈታቸው በአካባቢው የፈጠረው ድንጋጤ ከባድ ከመሆኑም በላይ በታጣቂዎቹና በአስተዳዳሪው ጠባቂዎች መካከል የተደረገው የተኩስ ልውውጥ ለሰዓት ያህል በመቆየቱ ብዙዎቹን ለስጋት እንደዳረጋቸው ዘገባው ያትታል፡፡ አሁንም ቢሆን የአካባቢው የጸጥታ ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆኑ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
በጥቃቱ እስካሁን ሀላፊነት የወሰደ አካል እንዳሌለና ታጣቂዎቹም ማን እንደሆኑ እንዳልታወቀ የሱዳን ዜና ወኪልን ጠቅሶ አልጀዚራ ዘግቧል፡፡ በግዛቱ ባለፈው ዓርብ በዓረብ ሪዚህጋት የጎሳ አባላትና በዓረብ ያልሆኑ የማሳሊት ጎሳ መካከል በተፈጠረው ግጭት ህጻናትና ሴቶችን ጨምሮ በሁለቱም ወገን 159 ሰዎች ተገድለዋል፡፡
ከተገደሉት መካከልም ሶስቱ የተባበሩት መንግስታት የዕርዳታ ማስተባበሪያ ድርጅት ሰራተኞች መሆናቸው በሱዳን የድርጅቱ ተጠሪ ባባካር ሲሴ ገልጸዋል፡፡ በግጭቱ ሳቢያ ወደ 90 ሺህ የሚጠጉ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ትምህርት ቤቶችና የመንግስት ህንጻዎች ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ፡፡
በተመሳሳይ መልኩ ባለፈው ሰኞ በፋለታና በሪዚህጋት ብሔሮች መካከል በተፈጠረው ግጭት ቢያንስ 55 ሰዎች ሲገደሉ 37 የሚሆኑት ደግሞ ቆስለዋል፡፡ የግዛቱ ባለስልጣናትም ግጭቱ እየተባባሰ በመምጣቱ ህዝቡ ቤቱ እንዲቆይ የ24 ሰዓት የጊዜ ገደብ አውጀዋል፡፡ የሰላሙን ሁኔታ ወደ መደበኛ ለመመለስም የጸጥታ አካላት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡
ግጭቱ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ እንዲቆም እንዲሁም በብሔሮች መካከል ሰላም እንዲወርድ የዓለም ማህበረሰብም እያሳሰበ ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 14/2013