ዘላለም ግርማ
አዲስ አበባ ፡- በሞሮኮ ሉዓላዊነት ስር የምትገኝ ምዕራብ ሰሃራ ራስ ገዝ አስተዳደር ዕቅድን ለመደገፍ የተሰበሰበው የሚኒስትሮች ጉባኤ ዕቅዱ የሰሃራ ክልላዊ ውዝግብን ለመፍታት ብቸኛ ማዕቀፍ መሆኑን የጠቆመ ሲሆን የሞሮኮ ሰሃራን ራስ ገዝ አስተዳደር በተመለከተ የሚነሱ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለመደገፍ ያላቸውን ቁርጠኝነት ሁሉም ተሳታፊ ሀገሮች መግለፃቸውን በኢትዮጵያ የሞሮኮ ኤምባሲ ገልጿል።
ጥር 07 ቀን 2013 ዓ.ም. ጉባኤውን በጋራ የመሩት በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ የምስራቅ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ዴቪድ ስቼንከር እና የሞሮኮው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናስር ቡሪታ ናቸው።
በመክፈቻ ንግግራቸው ዴቪድ ስቼንከር በሰጡት አስተያየት፣ ሞሮኮ ያላትን ሉዓላዊ ግዛት በተመለከተ ከአሜሪካ ዕውቅና ማግኘቷ ሞሮኮ በ2007 ያቀረበችው የራስ ገዝ አስተዳደር ዕቅድ ለግጭቱ ፍትሃዊና ዘላቂ መፍትሔ ብቸኛው መሠረት መሆኑን በግልጽ ያሳያል ብለዋል።
በተጨማሪም ስቼንከር የሞሮኮን የሰሃራን ራስ ገዝ አስተዳደር እቅድን “ለድርድር ብቸኛው ተዓማኒ እና ተጨባጭ መሠረት” በማለት ገልፀው አለም አቀፉ ማህበረሰብም እንዲደግፈው ጥሪ አቅርበዋል።
27 ሚኒስትሮችን ጨምሮ የ42 አገራት ተወካዮች የሞሮኮ ሰሃራን የይገባኛል ጥያቄ ለቀጣናው ውዝግብ ፍትሃዊና ዘላቂ መፍትሄ ብቸኛው መሰረት በመሆኑ ጠንካራ ድጋፍ ማድረጋቸውን በጉባኤው ወቅት ገልጸዋል።
በዚሁ ዝግጅት ላይ የተናገሩት አብዛኛዎቹ ተሳታፊዎች ለሞሮኮ የራስ ገዝ አስተዳደር ዕቅድን እንደ ቁርጠኛ፣ ተዓማኒ እና ተጨባጭ እንዲሁም ለክርክሩ ትክክለኛ እና ዘላቂ መፍትሄ ብቸኛው መሠረት መሆኑን ያረጋገጠውን የአሜሪካን አዋጅ አስታውሰዋል።
በተጨማሪም የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ አዋጅ የተባበሩት መንግስታትን ገለልተኛ የፖለቲካ ሂደት በመደገፍ ረገድ አቅጣጫ ከመስጠቱ ባሻገር ዓለም አቀፍ መግባባትን እንደሚያጠናክር አስረድተዋል።
የተለያዩ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችም የሞሮኮ የራስ-ገዝ ይገባኛል ዕቅድን ለአፍሪካ ሀገሮች እና ለመላው የሰሃራ ክልል ትክክለኛ አቅጣጫ መሆኑን በአፅንኦት ገልፀው በደቡባዊ ሰሃራ ክልል በሞሮኮ አዲስ የልማት ሞዴል ማዕቀፍ ውስጥ የተጀመሩ የልማት ጥረቶችን አድንቀዋል።
ተሳታፊዎቹ እንዳስረዱት አዲሱ የደቡብ ሰሃራን ክልሎች የልማት ሞዴል ለማግሬብ ክልል ኢኮኖሚያዊና ደህንነት ትብብር እንዲሁም ለአፍሪካ ሃገራት መረጋጋት እና ብልጽግና መንገድ የሚከፍት ተጨባጭ እርምጃ ነው።
በላዌን እና ዳህላ ከተሞች ቆንስላዎችን ለመክፈት የታቀደው የ20 አገራት ውሳኔዎች ለአካባቢው ኢኮኖሚያዊ እና የንግድ ዕድሎችን እንደሚያጎለብት፣ የሰሃራ አካባቢን
የአህጉሩ የኢኮኖሚ ማዕከል ለማድረግ የሚደረገው ጥረትን እንደሚያጠናክር እና በቀጣናው የሚታየውን ውዝግብ ለመፍታት ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረውን የመጨረሻ የፖለቲካ መፍትሄ የማምጣት ሂደትን እንደሚያፋጥን በጉባኤው ተብራርቷል።
አዲስ ዘመን ጥር 13/2013