ዛሬ ላይ ሆነን ስናየው ብዙዎቻችን ልጅ መሆናችንን እናስታውስበታለን። በተለይም በባህሉ ውስጥ ያለፍን ሰዎች ትልቅ ቦታ እንሰጠዋለን። ልጅነታችንን ወደኋላ እንድናይ ያደርገናል፡፡ የዛሬ ልጆች ከዚህ የተለየ ሁኔታ እንደተፈጠረላቸው ስንመለከት ደግሞ ባለውለታ እንደሆነ ሳናስብ አናልፈውም። ምክንያቱም የዛሬ ልጆች ከዚያ የተሻለ ነገር እንዲያገኙ በዚህ ባህል ውስጥ ያለፈ ያስፈልጋልና ነው። ስለዚህም የአንቀልባ ውለታ በቀላሉ የሚዘነጋ አይደለም።
በእርግጥ አንቀልባ ብቻ ላይሆን ይችላል ብዙዎቻችንን በእናታችን ጀርባ ላይ ታዝለን እንድናድግ ያደረገን። እነነጠላና ጋቢም ይሆናሉ። ግን ከባህል አኳያ ስንመለከተው ልዩ ቦታ ያለውና ምቾቱም የተሻለ የሆነው ይህ አንቀልባ የሚባለው ማዘያ እንደነበር የታዘለበት አለያም አዝሎ ልጆቹን ያሳደገበት ሰው መናገር ይችላል። ለመሆኑ ይህ አንቀልባ የሚባለው ምን አይነት ማዘያ ነው ከተባለ ለታሪኩ ባለቤት መናገሩ ዓባይን በጭልፋ ቢሆንም የማያቅም ሊኖር ይችላልና ማውጋቱ ይበጃል። በተጨማሪም ትዝታ በመፍጠር ባህል እንዳይረሳ ማድረግ ይገባልናም ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች ያገኘናቸውን አብነት በማድረግ እናውጋችሁ።
አንቀልባ ከቆዳ በባህላዊ መንገድ በመንደር ውስጥ የሚመረት በተለያዩ የኢትዮጵያ ገጠሪቱ ክፍሎች እናቶች የሚጠቀሙበት የልጆች ማዘያ ነው። በተለያዩ አካባቢዎችም የተለያየ ስያሜ ተሰጥቶት አገልግሎት ላይ ይውላል። በጎንደርና በጎጃም አንቀልባ፣ ከደሴ እስከ ትግራይ ባሉት አካባቢዎች ደለዎና ማህዘል እየተባለ ይጠራል። በእነዚህ የተለያዩ አካባቢዎች የቆዳው ቀለምና ሽታ፣ አሠራርና የሚያስጌጡባቸው ነገሮችም ይለያያሉ። በሁሉም አካባቢዎች ግን አስተዛዘላቸው በጀርባቸው ነው።
አንቀልባው የሚጌጠው በዛጎል፣ ጉናጉና በተባለ የዛፍ ፍሬ፣ በአዝራር ማለትም በልብስ ቁልፍ አልያም በጨሌ ሊሆን ሲሆን፤ ከጫፉ ተተልትሎ ጫፉ ላይ ነው እነዚህ በሙሉ ለማስጌጫነት የሚሆኑት። ይህ በጀርባ የማዘል ባህል ከኢትዮጵያም ውጪ እንደሚከናወን መረጃዎች ያስነብባሉ። በጀርባ የሚያዝሉ ብዙ የአፍሪካ አገሮች መኖራቸውንም ይጠቁማሉ። የሚጠቀሙበት ባህላዊ ልብስ ‹‹ካንጋ›› የሚባል ሲሆን፤ አስተዛዘላቸው የጀርባ መሆኑ አንድ አይነት ባህል መጋራትን ያመላክታል።
ለመሆኑ እነዚህ የጀርባ ማዘያዎች እንዴት ይሰራሉ የሚለውን የተወሰኑ አካባቢዎችን በመጥቀስ እንመልከት። ወደ ራያ አካባቢ እንሂድ። ራያዎች አንቀልባው እንዲለሰልስና እንዲጠቁር እንዲሁም ሽታው እንዲቀየር ቅቤ እስኪጠግብ ድረስ ይቀቡታል። ከዚያም በአሪቲ፣ አደስ፣ ጉንዲና ቀጠናዩ የተባሉ ዕፀዋትን ከቅቤ ጋር በመቀላቀልም ይታጠናል። ይህንን የሚያደርጉበት ደግሞ የራሳቸው ምክንያት አላቸው። ልጃቸውም ሆነ እነርሱ ጠረናቸው አልባብ አልባብ እንዲሸት ለማድረግ ነው። መጥፎ ሽታ በማዘያው ላይ ካለ ሁለቱም ለህመም ይጋለጣሉና ባህላዊ ነገሮችን በመጠቀም ጠረንን ይከላከላሉ።
ራያዎች የአንቀልባው መለስለስ ለልጁና ለእናቱ ምቹ ያደርገዋል ብለው ያምናሉ። እናት ጡት ብታጠባ፣ ብትፈጭ፣ ብትጋግር አልያም መንገድ ብትጓዝ ልጁ ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት እንዳይደርስበት ይረዳልና አንቀልባው በደንብ እንዲለሰልስ በማድረግ ያለባቸውን ነገር ያደርጋሉ። ለዚህም ነው በዚህ ማዘያ እናቶች ልጃቸውን ከሦስት እስከ አራት ዓመት ዕድሜው ድረስ አዝለው የሚያሳድጉት።
ድሮ እንደውም እናቶች ልጆቻቸውን በስምንተኛው ቀን በአንቀልባ እንደሚያዝሉ ይነገራል። ይህ ደግሞ በሰውነት ላይ የተለያዩ ለውጦች እንዳይኖሩ ለማድረግ ያስችላል ብለው ስለሚያምኑ የሚደረግ እንደሆነ ይወሳል። ለምሳሌ ደረተ ግልብጥ ልጅ ካለ «እናትህ በደምብ አላዘለችህም እንዴ?» ይባላል በባህሉ ዘንድ። በእርግጥ ሌላም ነገር አለ እናቶች ልጆቻቸውን ሁልጊዜ እንዲያዝሉ የሚያስገድዳቸው። ሥራ ሲሰሩ እንዲመቻቸው፤ የሚንከባከብ ሰው ስለሌላቸውና ልጆቻቸው ከእነርሱ ላለመለየት ሲሉ ያደርጉታል።
እንደውም ከዚህ ጋር ተያይዞ እናቶች ልጆችን ለማባበል የተለያዩ ዜማዎችን ሲያዜሙ እንዲህ ይላሉ። በዚህ ውስጥ ደግሞ የአንቀልባ ውለታ በእጅጉ ቦታ ይሰጠዋል።
‹‹ስበላም አዝዬ፣ ስጠጣም አዝዬ
አንቀልባው ወደቀ በል ውረድ ማሙዬ››
በተረትና ምሳሌም አንቀልባ ቦታውን አላጣም።
‹‹ድንች ያለተልባ ልጅ ያለ አንቀልባ›› ይባልለታል። የዘፈን ገጣሚዎችም ቢሆኑ እናቶች፤ ልጆችንና አንቀልባን የማይነጣጠሉ መሆናቸውን ለማውጋት የተለያዩ ዘፈኖችን ሳያስተሳስሩት አላለፉም። ድምፃዊው ጸጋዬ እሸቱ ‹‹ተጓዥ በዓይኔ ላይ›› በሚለው ዘፈኑ፡-
‹‹ፍቅርሽን በአንቀልባ አዝዬ በአካሌ
እኔማ በሌለኝ ጉልበቴ›› እያለ አቀንቅኗል።
አበባ እና ትግስት ‹‹ጎምላልዬ ናና!›› በሚለው ዘፈናቸው፡-
‹‹ልያዝህ በሙዳይ ልዘልህ በአንቀልባ
ሰው እንዳያይብኝ ስትወጣ ስትገባ›› በማለት ለአንቀልባ ቦታ ሰጥተውታል።
የፋሽን ነዳፊ፣ ሠዓሊና የፎቶ ባለሙያ የሆነችው ስፍነ ድንግል እጅጉ በአንድ ዐውደ ርዕይ ላይ የተለያዩ አካባቢዎችን የሚወክሉ በተለያዩ ጌጦች ያሸበረቁ አንቀልባዎችን፣ የወይባ ገልና የቆዳ ምርት የሆኑ ቁሳቁስን ለዕይታ ባቀረበችበት ወቅት እንደተናገረችው፤ እነዚህ አንቀልባዎችና ቁሳቁስ የአካባቢዎቹን ታሪክ፣ ባህልና ወግ እንዲሁም አኗኗር የሚጠቁሙ ናቸው። በእነዚህ የገጠር ክፍሎች እንደ ራያና ደሴ በሰሜን፤ ሐመር፣ ሙርሲና ሱርማ በደቡብና በአማራ አንዳንድ ክፍሎች ምንም እንኳን አሁን በጋቢ፣ በጨርቅና ሌሎች ነገሮች እየተተካ ቢሄድም የቆዳና ሌጦ ምርቶችን ለተለያየ አገልግሎት ያውሉታል።
አንቀልባ ሲቀር ደግሞ ዛሬ ዛሬ በፊት ለፊት የሚታዘልበት ማዘያ መጥቷል። አሁን እናቶች ብቻ አይደሉም የሚያዝሉት። አባቶችም ማዘል ጀምረዋል። ግን እንዳለፈው በጀርባ ሳይሆን በፊት ለፊትና በዘመናዊ መንገድ ነው። ምቾቱ እንዴት ነው ካላችሁ ያለፈውንና የአሁኑን የሞከረው ይናገር። አሁን አደግ ሲባል መታዘል ቀርቷል። በጋሪ መጎተት ነው። ታዲያ ያ ያለፈ ትዝታ ይኖር ይሆን፤ ከዚህም እንዳለፈ የምንመለከትበት ሁኔታ እናትና ልጆችን የሚለያይበት ገጽታ ተፈጥሯል። ምክንያቱም አሳዳጊ ይቀጠራል። የልጆች ማቆያም በተለያየ መልኩ እንዲያሳልፉ ይሆናሉ። ስለዚህ አንቀልባ ቀርቶ ቆዳው በዘመናዊ መንገድ እየተሰራ ምንጣፍ መሆን ጀምሯል። ጫማ፣ ልብስ፣ ቦርሳም እንዲሁ ቦታውን ይዘውታል።
ግን አንዳንድ የገጠር አካባቢዎች ባህሉ ባለመጥፋቱ የተነሳ ቁርበት፣ ለልጆች ማዘያ መሆኑ አልቀረም። የልጆች ለሃጭ መጥረጊያ፣ ለእህል ማጠራቀሚያ የሚሆን አቁማዳ፣ ለመጻፊያነት የሚያገለግል ብራናና ለሌሎች አገልግሎቶችም እንዲውል ይደረጋል።
ራያዎች በተለይም አላማጣ አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች አንቀልባን ከመሠረታዊ አገልግሎቱ ባሻገር የሀብት መገለጫ ያደርጉት እንደነበር በአካባቢው ዘንድ አውደርዕዩ ላይ የአንቀልባ ሥራቸውን ያቀረቡት ሰፍነ ድንግል፤ አንቀልባ ከ250 እስከ 2ሺህ700 ብር የሚገዛ ሲሆን፣ በራያና በአካባቢው እናቶች ባዘሉበት የአንቀልባ ዓይነት የሀብት ደረጃቸው ይለይበታል ብለዋል። እንደ ራያ ባህል አንዲት የራያ እናት አንቀልባዋን ለልጅና ለልጅ ልጅ ለውርስ ታስቀምጣለች እንጂ አትሸጥም፣ አታከራይም ወይም ለሰው እንዲሁ አትሰጥም ይላሉ።
እንደ ሰፍነ ድንግል አገላለጽ፣ ብዙ ሕፃናት ዓለምን እየተቀላቀሉ ባለበት ዘመን የአንቀልባን ባህላዊ እንዲሁም ጊዜ የማይሽረው አገልግሎቱን በ‹‹አንቀልባ ፋብሪካ›› ደረጃ አለመታሰቡ ጥያቄ የሚፈጥር መሆኑና ኢትዮጵያ ካላት የበዛ ሀብት፣ ባህል፣ ወግና ዕውቀቶች ገና ይኸኛው ትውልድ አለመጠቀሙ ትዝብት ውስጥ የሚከት ነው። ቢያንስ ሁሉም ነገር በዘመናዊ መንገድ ቢተካም ያለንን ባህል ማሰብና ማስታወስ ግን ተገቢ ነው። ይህ ትውልድ ዘመናዊነት ያለፈውን ባህል እንዲረሳና ያለውን ባህል እንዳያይ እንቅፋት ቢሆንበትም ወደዚህ ትልቅ ሀብት ፊቱን አዙሮ እንዲጠቀም ማድረግ ግን ከሁሉም የሚጠበቅ ሥራ ነው።
እኛም ያለን ሀብት ብዙ ነውና ማስታወሱ ላይ እንታትር፤ ትዝታን እናጭር አልን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ጥር26/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው