
ጌትነት ተስፋማርያም
የኮቪድ 19 በሽታ አሁንም ገዳይነቱን ቀጥሏል። ከህጻናት እስከ አረጋዊያን በርካቶችን ጾታ እና ቀለም ሳይለይ እየጎበኘ የሚገኘው ተላላፊ በሽታ እስከ ህዳር 11 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ብቻ በዓለም ላይ ከ2 ሚሊዮን 42 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል።
በሽታው ክትባት ተገኝቶለታል ቢባልም አሁንም ግን በየቀኑ በቫይረሱ የሚያዙ እና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ነው መረጃዎች የሚያሳዩት። በዓለም ላይ በየቀኑ ከ750 ሺህ እስከ 850 ሺህ ሰዎች በበሽታው እየተያዙ መሆናቸውን ሪፖርቶች ያሳያሉ። ከፍተኛ የህክምና ምርምር በማድረግ የሚታወቁት እና ለበሽታው ክትባት አግኝተናል የሚል ዜና በሚያሰሙት እና በበለጸጉ ሀገራት ላይ ደግሞ ችግሩ መባባሱን ነው ቁጥሮች እያመላከቱ የሚገኙት።
በሃያሏ አሜሪካ ብቻ እንኳን መመልከት ቢቻል በኮቪድ በሽታ በየቀኑ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወታቸውን እያጡ ይገኛል። በአጠቃላይ አሜሪካ 400 ሺህ የሚጠጉ ዜጎቿን በኮቪድ በሽታ ሳቢያ ህይወታቸውን አጥተዋል።
አሜሪካ በበሽታው ስትታመስ ጎረቤት ሀገሯ ካናዳ በአንጻሩ በበሽታው ክፉኛ አለመጎዳቷ ሲታሰብ ዜጎቿ የወሰዱት የአፍና የአፍንጫ መሸፈና የተሻለ አጠቃቀም ውጤት መሆኑ ሲገለጽ የአሜሪካውያን የጥንቃቄ ጉድለት ደግሞ በብዛት እንዲጠቁ ምክንያት ስለመሆኑ በርካታ የዘርፉ ባለሙያዎች ተስማምተውበታል። ይልቁንም የአሜሪካውያን የጥንቃቄ ጉድለት ዓለምንም ዋጋ እያስከፈለ ነው የሚሉ መከራከሪያዎችን የሚያቀርቡ ባለሙያዎች አልጠፉም።
ያም ተባለ ይህ ግን ለወራት ዓለምን ሲያምስ የቆየው በሽታ ዳግም ተጽእኖውን በማበርታት በተለይ ባለፉት ሁለት ቀናት ተጠናክሮ የበርካቶችን ጤና ማቃወሱን ቀጥሏል።
እንደ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ ከሆነ በዓለም ላይ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 95 ሚሊየን ተሻግሯል። በበሽታው ምክንያት የተነሳ ህይወታቸውን ያጡ ዜጎች ቁጥር ደግሞ ሁለት ሚሊዮን መሻገራቸውን መረጃው አሳይቷል።
አሜሪካ እና ህንድ እያንዳንዳቸው 24 ሚሊዮን እና 10 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚሆነው ህዝባቸው በኮሮና በሽታ ምክንያት መያዛቸውን ይፋ አድርገዋል። የላቲን አሜሪካዋ ብራዚል እና ሩሲያ በበኩላቸው ስምንት ነጥብ አምስት እና ሶስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ህዝባቸው በዚሁ በሽታ ምክንያት መጠቃቱን በምርመራ አረጋግጠዋል።
በአንጻሩ በዓለም ላይ በበሽታው ከተያዙ ሰዎች መካከል 68 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑት ማገገም ችለዋል። ይሁንና 111 ሺህ ሰዎች አሁንም በአስጊ ሁኔታ ላይ ናቸው። በተለይ እድሜያቸው የገፉ እና የመተንፈሻ ችግር ያለባቸው ሰዎች በጽኑ ህሙማን መከታተያ ክፍል ውስጥ ሆነው ህክምናቸውን እየተከታተሉ ይገኛል።
አሁንም ግን የህሙማንን አተነፋፈስ ስርዓት ለማስያዝ የሚያግዙ ዘመናዊ መሳሪያዎች እጥረት አለመቀረፉን ከየሀገራቱ የሚወጡ መረጃዎች አመላካች ናቸው። በኮሮና በሽታ የተያዙ ዘመዶቻቸውን እንኳን በአግባቡ በሆስፒታል ተገኝተው መጠየቅ ያልቻሉ ቤተሰቦች አሁንም ጭንቀት ላይ በሚገኙበት ወቅት በአፍሪካ 79 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ለህልፈት መዳረጋቸው ታውቋል።
የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል (ሲዲሲ አፍሪካ) ይፋ በሚያደርገው መረጃ መሰረት በአፍሪካ አህጉር በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ3 ነጥብ 2 ሚሊየን ማለፉን አረጋግጧል።
ሲዲሲ አፍሪካ በድረ-ገጹ በለቀቀው መረጃ በአፍሪካ ከተገኙ የኮሮና ተጠቂዎች ውስጥ ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ከደቡባዊው የአፍሪካ ሀገራት የተገኙ ናቸው። በአንጻሩ መካከለኛው እና ምዕራብ አፍሪካ ላይ የበሽታው ተጽእኖ ቀንሶ ይታያል። የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በበኩላቸው በድምሩ ግማሽ ሚሊዮን ህዝባቸው እንኳ በበሽታው ባለመያዙ ከአህጉሩ በብዛት በተጠቁ ዞኖች አንጻር የሶስተኛ ደረጃ ይዘዋል።
በሀገራት የኮቪድ ተጠቂዎች ደረጃ ደቡብ አፍሪካ ቀዳሚውን ስፍራ ስትይዝ የሰሜን አፍሪካዎቹ ሞሮኮ፣ ቱኒዚያ፣ ግብጽ ተከታዩን ስፍራ ሲይዙ ኢትዮጵያ በርካታ ተጠቂዎች ከአፍሪካ ካስመዘገቡ ሃገራት ተርታ በተከታይነት ተሰልፋለች።
በተለያዩ ህዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ላይ የሚታየው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አጠቃቀም ችግር እና የንጽህና ጉድለት በሽታውን እንዳያስፋፋው ስጋት ከሆነ ሰነባብቷል።
አዲስ ዘመን ጥር 11/2013