
በኃይሉ አበራ
ኢንዶኔዥያ የመሬት መንሸራተት ባስከተለ ጠንካራ የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተትን ተከትሎ በሱዋሌሲ ደሴት የሚኖሩ ሰዎች በምሽት ጭምር ከቤታቸው ወጥተው እየፈለሱ መሆኑን ቲ.አር.ቲ ዎርልድ ዘግቧል።
በዘገባው መሰረት ቢያንስ 34 ሰዎች መሞታቸው የተረጋገጠ ሲሆን፤ ባለስልጣኖች እስከአሁን አደጋው በተከሰተባቸው አካባቢዎች መረጃዎችን እያሰባሰቡ መሆኑ ተገልጿል::
ስድስት ነጥብ ሁለት ሬክተር ስኬል በተመዘገበው ከባድ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋው ከ600 በላይ የቆሰሉ ሲሆን፤ ይህም ብዙ ሰዎች በእኩለ ሌሊት ጭምር ከቤታቸው ለቀው እንዲወጡ ያደረጋቸው ሲሆን፤ ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት በከባድ የመሬት መንቀጥቀጥና ሱናሚ በደረሰው በሺዎች የሚቆጠሩትን የደሴቲቱ ነዋሪዎች በገደለበት መካከል መሆኑ ድንጋጤን አስነስቷል።
የአካባቢው አደጋ መከላከል ኤጀንሲ ኃላፊ የሆኑት አሊ ራህማን በበኩላቸው “አሁን የደረሰን የቅርብ ጊዜ መረጃ የሚያሳየው በማሙጁ ከተማ ውስጥ 26 ሰዎች መሞታቸውን ነው ” ቁጥሩ ሊጨምር ይችላል፤ ከሟቾች መካከል ብዙዎች በፍርስራሽ ስር ተቀብረዋል” ብለዋል።
የሀገሪቷ አደጋ ኤጀንሲ በተናጠል እንዳስታወቀው የምዕራብ ሱላዌሲ ግዛት በሆነችው እና የ110 ሺህ ሰዎች መኖሪያ በሆነችው ማሙጁ ከተማ በስተደቡብ በሚገኘው አካባቢ ቢያንስ ስምንት ሰዎች መሞታቸውን የገለጸ ሲሆን፤ አጠቃላይ የሟቾች ቁጥር 34 መድረሱን አስታውቋል።
ዓርብ ጠዋት ስድስት ነጥብ ሁለት በሆነው ርዕደ መሬት ከምዕራብ ሱላዌሲ ግዛት ማሙጁ አውራጃ በስተደቡብ 36 ኪ.ሜ. መነሻ ያደረገው፣ 18 ኪ.ሜ ጥልቀት ያለው መሆኑን የአሜሪካ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ አስታውቋል። ርዕደ መሬቱን ተከትሎም ከባድ የመሬት መንሸራተት ሊከሰት እንደሚችል የኢንዶኔዥያ ሜትሮሎጂ እና ጂኦፊዚክስ ኤጀንሲ ተናግረዋል።
ድዊኮሪታ ካርናዋቲ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ከሐሙስ ከሰዓት ጀምሮ ሁለት ጠንካራ ርዕደ መሬቶች ከደረሱ በኋላ ቢያንስ 26 የምድር መናወጦች ነበሩ። 62 ቤቶችን፣ የጤና ዩኒት ማዕከልን እና ወታደራዊ ጽህፈት ቤትን ጨምሮ በማጀኔ የሚገኙ በርካታ ሕንፃዎች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል። እንዲሁም ጠንካራው ርዕደ መሬቱ የመብራት ኃይል እና የስልክ አገልግሎት መቆራረጥና በመንገዶች ላይ የመሬት መንሸራተት ምክንያት ሆኗል።
በኤ.ኤፍ.ፒ ዘገባ መሰረትም እ.አ.አ. ጥር 15 ቀን 2021 በ6.2 መጠን ከተመዘገበው የመሬት መንቀጥቀጥ በኋላ የነብስ አድን ሠራተኞች በኢንዶኔዥያ የሱላዌሲ ደሴት በማሙጁ ከተማ በተደረመሰ ሕንፃ የተረፉ ሰዎችን ይፈልጉ ነበር። በምዕራብ ሱላዌሲ አውራጃ 110 ሺህ መኖሪያ በሆነችው ማሙጁ ከተማ ውስጥ አንድ ሆስፒታል ተደምድሟል።
አሪያንቶ በሚል በአንድ ስም የሚጠራው በማሙጁ ከተማ ከሚገኘው የነፍስ አድን ድርጅት “ሆስፒታሉ ሜዳ ሆኗል፣ ወዳድቋል” ብሏል።
በሆስፒታሉ ፍርስራሽ ሥር ተይዘው የቀሩ ህሙማን እና የሆስፒታል ሠራተኞች ስላሉ እነሱን ለመድረስ እየሞከርን ነው ሲሉ በቁጥር የተወሰነ መረጃ ሳይሰጡ ገልጸዋል። ነብስ አድን ሠራተኞቹ በቤታቸው በደረሰ ፍርስራሽ ስር ለተያዙት ስምንት ሰዎች ቤተሰብ ለመድረስ ጥረት እያደረጉ መሆኑንም አክሏል።
በዚህው ዕለት በኢንዶኔዥያ ምዕራብ ሱላዌሲ ግዛት ማሙጁ ከተማ የደረሰውን የመሬት መንቀጥቀጥን ተከትሎ የተበላሸ መኪና እና ሕንፃዎች መታየቱንም ሬውተርስ ዘግቧል።
አንድ አባት ተስፋ ሳይቆርጥ ሲያለቅስ ከቤቱ ፍርስራሽ በታች የተቀበሩት ልጆችን ለማዳን “እዚያ ያሉ ልጆቼ በውስጥ ተይዘዋል፤ እባክህ እርዳኝ” ሲል በፍርሐት እያለቀሰ፤ ከሰዎች ዕርዳታ ሲጠይቅ የሚያሳይ አንድ ቪድዮም እንዳለ ተገልጿል፡፡
በማሙጁ አውራጃ ቢያንስ 62 ቤቶች፣ የህዝብ ጤና ጣቢያ እና አንድ የወታደራዊ ጽህፈት ቤት ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፤ የመሬት መንሸራተትም በሦስት ቦታዎች መነሳቱን እና ማሙጁን ወደ ማጀኔ ወረዳ የሚያገናኘውን ዋና መንገድ ማዘጋቱን የአደጋው ኤጀንሲ ቃል አቀባይ ራዲያ ጃቲ ተናግረዋል።
ሐሙስ ዕለት በዚያው ወረዳ መጠኑ አምስት ነጥብ አምስት የሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ በርካቶች ላይ ጉዳት አድርሷል።
የፓስፊክ ‹የእሳት ቀለበት› እየተባለ የሚጠራው፣ ከፍተኛ የቴክኒክ እንቅስቃሴ ያለው ህዝብ የሆነችው ኢንዶኔዥያ በየጊዜው በመሬት መንቀጥቀጥ ስትመታ ትታያለች። እ.ኤ.አ በ2018 በ7 ነጥብ 5 ኩኣድ መጠን ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ ተከትሎም በፓሉ፣ ሱሉዌሲ ከ4 ሺህ 300 በላይ ሰዎች ሞተዋል ወይም ጠፍተዋል።
እ.ኤ.አ. ታኅሣሥ 26 ቀን 2004 (እ.ኤ.አ.) በሱማትራ የባሕር ዳርቻ ላይ የ9 ነጥብ አንድ ኩኣድ መጠን ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ በመከሰቱ በመላው ኢንዶኔዥያ 170 ሺህ የሚሆኑትን ጨምሮ በጠቅላላው የባህር ዳርቻው ቀጠና 220 ሺህ ሰዎችን የገደለ ሱናሚ ተቀስቅሷል።
አዲስ ዘመን ጥር 10/2013