ግርማ መንግሥቴ
እንደምን አላችሁ ልጆች፣ ሰላም ናችሁ? ባለፈው ሳምንት ስለ አንዲት ጌርተር ስለምትባል ጎበዝ ስዊድናዊ ወጣት አላማ፣ ተግባር፣ ዓለም አቀፍ እውቅና፣ ዝናና አስተዋፅኦ ነግሬያችሁ ነበር። አስታወሳችሁ? በጣም ጥሩ። ጌርተርን እንደ ወደዳችኋትና እናንተም እንደ እሷ ለመሆን ከአሁን ጀምሮ እንደምትጥሩ ተስፋ አደርጋለሁ። አዎ እኔ ለዛ ብዬ ነው የዚህችን ጎበዝ ወጣት ልጅ ተግባር ላስተዋወቅችሁ የፈለኩትና ተሳክቶልኛል ማለት ነው።
ዛሬ ደግሞ ይዥላችሁ የመጣሁት አንድ በጣም ታዋቂና ከልጅነቱ ጀምሮ ባደረገው ከፍተኛ ጥረትና የቤተሰቦቹ እገዛ ከፍተኛ ደረጃ ስለደረሰ ዓለም አቀፍ ሀብታም ሰው ነው። ይህ ሰው አሜሪካዊ ሲሆን ተወልዶ ያደገው እዛው አሜሪካ ሲአትል ነው።
ይህ ሰው ቢል ጌት ይባላል። ዛሬ በዓለም ላይ ከቁጥር አንድ ሀብታሞች ተርታ የሚሰለፍ ሲሆን አጠቃላይ ሀብቱም 121.5 ቢሊዮን ዶላር ነው።
ጌት የራሱ የሆነና “Microsoft Corporation” የሚባል ኩባንያ ያለው ሲሆን ይህ ኩባንያውም በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣም ታዋቂና በከፍተኛ ደረጃ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ አቅም አፍላቂ ነው።
ጌት በዚህ ሁሉ ሀብቱና ንብረቱ በፍፁም አይኮራም። ምን ግዜም ትሁት ነው። የተለያዩ የበጎ አድራጎት ተቋማትን በማቋቋም የተቸገሩ አገራትን ከፍተኛ መጠን ያለው ዶላር ወጪ በማድረግ ይረዳል። ለምሳሌ በሱና ባለቤቱ ስም “Bill & Melinda Gates Foundation” በሚል ባቋቋመው ግብረ ሰናይ ድርጅት አማካኝነት ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ በመመደብ በማደግ ላይ ያሉ አገራትን ይደግፋል።
ኦክቶበር 28፣ 1955 ከታዋቂ ጠበቃ አባቱ ዊሊያም ኤች.ጌትስ እና በተለያዩ ተቋማት አመራር ውስጥ በቦርድ አባልነት ስታገለግል ከነበረችው ከእናቱ ሜሪ ማክስዌል ጌትስ የተወለደው ቢል ጌትስ ህይወቱን ሙሉ ለለውጥ፣ እድገትና ብልፅግና ሲጥር የኖረ ሲሆን አሁንም ይህንኑ ጥረቱን ሳያቆም በተለያዩ አገራት በመዘዋወር የተለያዩ ተቋማትን እየገነባ ሲሆን ልዩ ልዩ ድጋፎችንም በማድረግ ላይ ይገኛል።
ጌትስ ከተለያዩ መንግስታትና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተለያዩ ሽልማቶችን ያገኘ ሲሆን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም የክብር ዶክተሬት ዲግሪውን ተቀብሏል።
ለቤተሰቦቹ አራተኛ ልጅ የሆነው ጌትስ የቤተሰቦቹ ፍላጎት ጌትስ የህግ ትምህርት እንዲከታተልና በዛች አገር ላይ ለሚደረገው የፍትህ ስርአት የማስፈን ስራ ላይ አስተዋፅኦ እንዲያደርግ ነበር። ነገር ግን ጌትስ ህግ የሚባለውን ነገር አልወደደውምና በአስራ ሶስት ዓመቱ “Lakeside prep school” ተመዘገበ። ለመጀመሪያ ጊዜም ስለሶፍትዌር ፕሮግራም በፅህፈት ማሽን ጽሑፍ የፃፈውም በዚሁ ዓመትና ትምህርት ቤት ነው። በቃ፤ ዝንባሌውም ሆነ ተግባሩ ወደ እዚሁ እያደላ መምህራኖቹም እየተረዱለት መጡ።
ሁኔታዎችንም እያመቻቹለት በስራው ውጤታማ እንዲሆን አደረጉት። እንዲህ እንዲህ እያለ ዛሬ የደረሰበት ደረጃ ላይ ለመድረስ በቃ እላችኋለሁ።
አዲስ ዘመን ጥር 9/2013