ሞገስ ተስፋ
እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ትምህርትስ እንዴት ነው? መቼም ኮሮናን እየተከላከላችሁ ትምህርታችሁን በአግባቡ እየተማራችሁ ውጤታማ እንደምትሆኑ አንጠራጠርም። ዛሬ ይዘንላችሁ የቀረብነው ትምህርቱን በአግባቡ እየተማረ ውጤታማ እየሆነ ያለ እንዲሁም በ2012 ዓ.ም የስምንተኛ ክፍል ፈተኛ ወስዶ 95 ካስመዘገበ ጎበዝ ተማሪ ጋር ላስተዋውቃችሁ ነው።
ተማሪ ዲሜጥሮስ ዘሪሁን ይባላል። ዕድሜው 13 ሲሆን የሚማረው ምስካየ ኅዙናን መድሃኒዓለም ገዳም የመጀመሪያ፣ መለስተኛና ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። ዲሜጥሮስ ወደ ዘጠነኛ ክፍል ለመዘዋወር የወሰደው የስምንተኛ ከፍል ፈተኛ 95 ፐርሰንት በማምጣት ከፍተኛ የሆነ ውጤት አስመዝግቧል። መቼም ይህን ውጤት ለማስመዝገብ እንዴት ቢያጠና ነው? ትሉ ይሆናል። ተማሪ ዲሜጥሮስ እንደነገረን አንድ ተማሪ የሚፈልገውን ውጤት ለማስመዝገብ ትምህርቱን በአግባቡ መከታተል እና የተማረውን ትምህርት በእየለቱ በማጥናት ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ የጥናት ፕሮግራም አውጥቶ እንደሚያጠና፣ እንዲሁም በየጊዜው የተማረውን ትምህርት ከቤቱ ከተመለሰ በኋላ በማጥናቱ ለውጤታማነቱ እንደረዳው ነግሮናል።
ተማሪ ዲሜጥሮስ እንደሚለው የዘጠነኛ ክፍል የትምህርት አይነቱም ሆነ ይዘቱ ሰፋ እያለ ስለሚመጣ በትጋት እያጠና ነው። በአሁኑ ወቅት በኮሮና ምክንያት አንድ ቀን ትምህርት አንድ ቀን እረፍት እየሆኑ ስለሚማሩ በእረፍት ቀኑ የተማረውን ትምህርት ለማጥናት ምቹ እንደሆነለት ይናገራል።
ተማሪ ዲሜጥሮስ የስፔስ ሳይንስና የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በሚያዘጋጁት ጥናት እና ምርምር የሚሳተፍ ሲሆን በሚያዘጋጁት ስልጠናም ተሳታፊ በመሆን በስፔስ ሳይንስ ዕውቅና ተሰጥቶታል። ተማሪዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ትምህርታቸውን ፕሮግራም በማውጣት በሚገባ ማጥናት አለባቸው ሲል ይገልፃል።
ዲሜጥሮስ ከጥናት ሲመለስ ስዕል መሳል ይወዳል። ለዚህም ማሳያው በአለፈው ዓመት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የእርግብ ስዕል በመሳል ስጦታ አበርክቶላቸዋል። ተማሪዎች ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ያላቸውን ተሰጥኦ በተግባር በመለማመድ ስኬት ስለሚያበቃቸው ካጠኑ በኋላ እረፍት ሲያደርጉ ልክ እንደ መዝናኛ ተጨማሪ ተሰጥኦዋቸውን መጠቀም መቻል እንዳለባቸው ዲሜጥሮስ ሀሳቡን ያካፍላል።
ልጆች ከተማሪ ዲሜጥሮስ ጥሩ ልምድ እንዳገኛችሁ ተስፋ እናደርጋለን። እናንተም ጠንክራችሁ በማንበብ ልክ እንደ ዲሜጥሮስ ጎበዝ በመሆን ለራዕያችሁ ስኬት ጠንክራችሁ እንደምታነቡ ተስፋ እናደርጋለን። ሰ ላም።
አዲስ ዘመን ጥር 9/2013