ምህረት ሞገስ
ጎረቤታሞች ናቸው። አብሮ መብላት እና መጠጣት፤ ገንዘብ መበደር እና መመለስን ጨምሮ በጎረቤታሞች መካከል የሚኖሩ መስተጋብሮች ሁሉ በእማሆይ ገብረእየሱስ እና በአቶ ዘውዱ መርሻ መካከልም አለ።
በብዙ ኢትዮጵያውያን መካከል እንደተለመደው ሁሉ እነርሱም ጥብቅ ጉርብትናቸው በቀናት ብቻ ሳይሆን በየሰዓቱ እንዲገናኙ አስችሏቸዋል።
ጠዋት እና ማታ እንደምን አደርሽ እንደምን አደርክ፤ ደህና እደሪ ደህና እደር መባባል ብቻ ሳይሆን፤ አብሮ መብላት እና መጠጣትን ጨምሮ በችግር ጊዜ ገንዘብ መበዳደር ላይ ደርሰዋል።
የሁለቱንም የቅርብ ግንኙነት ወዳጆቻቸው ያውቃሉ። ጊዜ ጊዜን ሲተካ መቀራረቡ ገንዘብ ከመበዳደር አልፎ፤ አቶ ዘውዱ ለእማሆይ የገንዘብ ስጦታ እስከመስጠት ደረሱ።
የሁለቱም ዘመዶችም ሆኑ ሌሎች ጎረቤቶች በሁለቱ መካከል ያለው ግንኙነት ወደ ፍቅር አድጎ አንሶላ እስከ መጋፈፍ ይደርሳል ተብሎ ቢገመትም በግላጭ የታየ ነገር አልነበረም። ነገር ግን እማሆይ በመካከላቸው የነበረው ግንኙነት አንሶላ እስከመጋፈፍ ዘልቋል ማለት ጀመሩ።
እናም ግንኙነቱ እንደማሆይ ገለፃ፤ እውነት ነበርና እማሆይ ይፀንሳሉ። የእማሆይ ሆድ ገፍቶ መታየት ጀመረ። ከአቶ ዘውዱ መፀነሳቸውን እርሳቸው ሲነናገሩ፤ የአካባቢው ነዋሪ ደግሞ ማርገዛቸውን አረጋገጠ። የተረገዘ ጊዜ ጠብቆ መወለዱ አይቀርምና እማሆይ ገብረእየሱስ በሰላም ወንድ ልጅ ተገላገሉ።
እማሆይ እንደተናገሩት፤ ልጃቸውን የወለዱት ከአቶ ዘውዱ ነው። ነገር ግን አቶ ዘውዱ ‹‹ምን ሲደረግ አሉ›› በፍፁም እርሳቸው የልጁ አባት አለመሆናቸውን ተናገሩ። እማሆይ ግን ልጃቸውን ሱራፌል ብለው ሲያበቁ የአባቱን ስም ዘውዱ አሉት።
አቶ ዘውዱ፤ ሱራፌል በስማቸውም ቢጠራም የአባትነት እንክብካቤ ለማድረግ ፈቃደኛ አልሆኑም። ‹‹በፍፁም ልጁ የእኔ አይደለም›› ብለው ተከራከሩ።
እናት እማሆይ ልጅ ለእናቷ መክፈል ያለባትን መስዋእትነት እየከፈሉ ሲያሳድጉ ከአጋር ወይም ከልጅ አባት ማግኘት ያለባቸውን ድጋፍ አቶ ዘውዱ ነፈጓቸው። በዚህ ጊዜ በሰሜን ጎንደር ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ መሰረቱ። አቶ ዘውዱ ተጠርተው ሲጠየቁ የሰጡት ምላሽ ‹‹በፍፁም ልጁ የእኔ አይደለም›› የሚል ነበር።
ፍርድ ቤቱ እማሆይ የሰው ምስክር እንዲያቀርቡ በማዘዙ ፤ በምስክር በሁለቱ መካከል ቅርብ ግንኙነት እንደነበር እና በኋላም ልጁ እንደተወለደ ተገለፀ። በእርግጥ አንሶላ ሲጋፈፉ ያየ ምስክር ማቅረብ ይከብዳል።
መስካሪዎቹ ያረጋገጡት በሰዎቹ መካከል ግንኙነት መኖሩን እና ጉርብትናቸውም ጥብቅ እንደነበር ብቻ የሚያመላክት ነበር።
አቶ ዘውዱም በራሳቸው በኩል ምስክር ቢያቀርቡም መስካሪዎቹ ግንኙነት እንደነበራቸው ከመግለፅ ውጪ፤ የፍቅር ግንኙነት ወይም አንሶላ እስከመጋፈፍ የሚያደርስ ግንኙነት በመካከላቸው የለም ብለው ሙሉ ለሙሉ መመስከር ባለመቻላቸው፤ ያንንም ለማረጋገጥ የሚያዳግት በመሆኑ የከፍተኛው ፍርድ ቤት የግራ ቀኝ ክርክሩን ካዳመጠ በኋላ፤ አቶ ዘውዱ የልጁ አባት ነው በማለት ወስኗል።
ነገር ግን እዚህ ላይ አቶ ዘውዱ ከዛ በፊት ‹‹ልጁ የእኔ ከሆነ በዘረመል ምርመራ ይረጋገጥልኝ›› የሚል ጥያቄ ቢያቀርቡም፤ ፍርድ ቤቱ በቂ የሰው ምስክር በመገኘቱ፤ የዘረ መል ምርመራ አያስፈልግም በሚል ‹‹ አቶ ዘውዱ የልጁ አባት ነው›› በማለት ውሳኔ አሳለፈ።
አቶ ዘውዱ ግን በውሳኔው ቅር በመሰኘት ለአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ጠየቁ። የአቶ ዘውዱን ጥያቄ የተቀበለው ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደግሞ የአቶ ዘውዱ አባትነት በማስረጃ አልተረጋገጠም በማለት የከፍተኛው ፍርድ ቤትን ውሳኔ ሽሮታል። በዚህ ጊዜ እናት እማሆይ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ውሳኔ ሲሰጥ ተገኝተው አልተከራከሩም።
ልጃቸውን በማሳደግ ተጠምደው፤ የልጁን አባትነት አረጋግጫለሁ ተወስኖልኛል ብለው ተቀመጡ። ነገር ግን አቶ ዘውዱ አባት ቢባሉም ድጋፍ ካለማድረግ አልፈው ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉዳዩን በይግባኝ ማቅረባቸውን ቆይተው እማሆይ ሰሙ።
ይግባኝ ሰሚ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉዳዩን በሚያይበት ጊዜ አቶ ዘውዱ በሀሰት እማሆይ በአካባቢው የሉም በማለታቸው በሌሉበት ማስወሰናቸውን እንዲሁም አቶ ዘውዱ በከፍተኛው ፍርድ ቤት የዘረመል ምርመራ እንዲደረግ ሲጠይቁ፤ እማሆይም የተስማሙ ቢሆንም ጥያቄው መታለፉን እና ይግባኝ ሰሚውም ይህንን ሳያጣራ ውሳኔውን መሻሩ ያበሳጫቸዋል።
ቆይተው እናት እማሆይ ለክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ ቢያቀርቡም፤ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ቅሬታዎትን አላቀረቡም በማለት ይቃወማቸዋል። በጠቅላይ ፍርድ ቤት የተፈፀመ የህግ ስህተት የለም በማለት አቤቱታቸውን ውድቅ ያደርግባቸዋል።
እማሆይ ልጃቸውን ያለአባት ማሳደጋቸውን ሲቀጥሉ፤ አልብሰው አጉርሰው የአቅማቸውን ያህል ከመንከባከብ ባሻገር ልጁ አባቱን የማወቅ መብት እንዳለው በማመን ከሰበር አልፎ እንዲቀጥል እና ልጃቸውም የአባቱ ማንነት እንዲረጋገጥ በድጋሚ ጥረት ማድረግ ይጀምራሉ።
እማሆይ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ የሰጠው ውሳኔ ትክክል አይደለም። የህግ ስህተት ተፈፅሞብኛል በማለት ጉዳዩን ይዘው ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀርባሉ። ቅሬታቸው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉዳዩን በይግባኝ በሚያይበት ጊዜ አቶ ዘውዱ በሃሰት እማሆይ ‹‹በአካባቢው የለችም›› በማለት፤ ‹‹እኔ በሌለሁበት ጉዳዩ እንዲታይ አድርጎ አስወስኖብኛል።›› ይላሉ።
እማሆይ፤ አቶ ዘውዱ በከፍተኛው ፍርድ ቤት መልስ ሲሰጡ የዘረመል ( DNA) ምርመራ እንዲደረግ ሲያመለክቱ፤ እማሆይም ቢስማሙም ፍርድ ቤቱ ያለአግባብ ጥያቄውን ማለፉን፤ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤትም ይህንኑ ሳያረጋገጥ የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔን መሻሩን እንዲሁም የተሰጠው ውሳኔ ‹‹in the best interest of the child›› የህፃኑን መሰረታዊ መብትና ጥቅም የሚለውን ዓለም ዓቀፋዊ መርህ የሚቃረንና ሕፃኑ ወላጆቹን የማወቅና ከእነርሱ እንክብካቤ የማግኘት መብት በህገመንግስቱ አንቀፅ 36(1)ሐ እና (2) የተመለከተውን የሚፃረር መሆኑን ጠቅሰው ጥያቄ ያቀርባሉ።
በዝርዝር ለፌዴሬሽን ምክር ቤትም ሲያስረዱ፤ ‹‹ አገባሻለሁ ብሎኝ በነበረን ግንኙነት ህፃን ሱራፌል ስለተወለደ የልጁ አባትነት ይታወቅልኝ›› ስል፤ አቶ ዘውዱ በበኩሉ ይህንን ክዷል በማለት ጉዳዩን ገልፀዋል።
ነገር ግን አቶ ዘውዱ ሙሉ ለሙሉ ከመካድ ይልቅ፤ ‹‹ እማሆይ ከወለደች በኋላ በቅንነት አንድ ሺህ ብር ሰጥቼያት የእኔ እና የልጁ ደም ተወስዶ የዘረመል ምርመራ ይካሄድልኝ ›› ብለው እንደነበር እና ለሁለቱም ፍርድ ቤቶች ጥያቄ ማቅረባቸው ታውቋል።
በመጀመሪያ ጉዳዩን የተመለከተው የአማራ ክልል የሰሜን ጎንደር ዞን ከፍተኛው ፍርድ ቤት በእማሆይ በኩል የቀረበው የሰው ምስክር በቂ ነው በማለት የዘረመል ምርመራውን ሳይዝ አቶ ዘውዱ የልጁ አባት ነው ብሎ ወስኗል።
የይግባኝ ሰሚው ጠቅላይ ፍርድ ቤት የከፍተኛ ደረጃ ፍርድ ቤት በበኩሉ ‹‹የቀረበው ማስረጃ በቂ አይደለም›› ብሎ ውሳኔውን ሙሉ በሙሉ ውድቅ በማድረግ የቀረበውንም የዘረመል ምርመራ እንዲያደርግ ትዕዛዝ ሳይሰጥ ቀርቷል።
ሆኖም ይህ የህፃኑን ወላጁን የማወቅ መብትን የገፈፈ በመሆኑ፤ እማሆይ የህግ ስህተት ተፈፅሟል እና ምክር ቤቱ ጉዳዩን ይየው ሲሉ ጠይቀዋል። ምክር ቤቱም በህገመንግስት ትርጉም እና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጉዳዩን መርምሮ የውሳኔ ሃሳብ እንዲያቀርብ የመራው ሲሆን፤ ኮሚቴውም ጉዳዩን በዝርዝር አይቶ ያቀረበው ውሳኔ በምክር ቤቱ በሙሉ ድምፅ ፀድቋል።
ውሳኔ
የህፃናት ጉዳይን በተመለከተ በህገመንግስቱ አንቀፅ 36 ድንጋጌዎች መሰረት ፍርድ ቤቶችም ሆኑ ሌሎች የመንግስት አካላት ህፃናትን የሚመለከቱ እርምጃዎች በሚወሰዱበት ጊዜ የህፃናትን ደህንነት በቀደምትነት መታሰብ እንዳለበት በአስገዳጅ ሁኔታ ተመልክቶ እያለ የክልሉ የጠቅላይ ፍርድ ቤት አቶ ዘውዱ የህፃኑ አባት አይደለም ብሎ ሲወስን እና የአመልካቹን አቤቱታ በገደብ ምክንያት ውድቅ ማድረጉ የሕፃኑን ህገመንግስታዊ መብት የሚጥስ እና የህፃኑን መሰረታዊ መብት እና ጥቅም የሚነካ እና የሚጎዳ ሆኖ ተገኝቷል።
በመሆኑም በሕፃን ሱራፌል ጉዳይ ላይ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተሰጠ ውሳኔ በሕመንግስት አንቀፅ 36(1) /ሐ/ እና (2) የተደነገገውን ሕፃናት ወላጆቻቸውን የማወቅና ከእነርሱም እንክብካቤ የማግኘት መብት አላቸው የሚለውን የሚቃረን ስለሆነ በህገመንግስቱ አንቀፅ (9) ድንጋጌ መሠረት የሰበር ሰሚው ፍርድ ቤት ውሳኔ ተፈፃሚነት ሊኖረው አይገባም በማለት በሙሉ ድምፅ ወስኗል።
አዲስ ዘመን ጥር 01/2013